እሳቸው…
አባ ፋጂ አባቦር መልካም ገበሬ ናቸው። በሚኖሩበት የጅማ ‹‹ቡልቡል›› ቀበሌ ጉልበታቸው አያመርተው፣ እጃቸው አያፍሰው ምርት የለም። ጤፍና በቆሎ፣ በርበሬና ቡና፣ ሙዝና አቮካዶ የልፋታቸው ሲሳይ ናቸው። እሳቸው ዓመቱን ሙሉ የሚደክሙ ብርቱ ሰው መሆናቸውን ሁሉም ያውቃል። አባ ፋጂ ከትዳር አጋራቸው ሰባት ልጆችን ወልደዋል። ከልጆቻቸው መሀል በሞት ያጧቸውን ቢያስቡም በፈጣሪ ሥራ ገብተው አያውቁም። ‹‹ያሉትን ይባርክልኝ›› ብለው በምስጋና እየኖሩ ነው።
ሰባተኛው ልጅ…
አያንሺ ለአባፋጂ የመጨረሻና ሰባተኛ ልጅ ሆኖ ይቆጠራል። ዓይኑ ጎላ ያለ መልኩ ደማቅ ጥቁር ነው። ቀልጣፋና ሩጫ ወዳድ በመሆኑ ከእኩዮቹ ሲዘል ሲጫወት ይውላል። እንደ ልጅነቱ ነፃነቱን የሚጋፋው ጊዜውን የሚቀማው የለም። እንዳሻው ይሆን ዘንድ ተፈቅዶለታል። አሁን ልጁ አምስት ዓመት ሆኖታል። እሱን መሰል እኩዮቹን ሲያገኝ እንደለመደው ዘሎ ተጫውቶ ይገባል።
አንድ ቀን አያንሺ ሲዘል ሲጫወት ውሎ ከቤት ደረሰ። ገጽታው እንደቀድሞው አይደለም። ቅዝዝ እንዳለ ክፍት ብሎታል። እናት አባት ሁኔታውን ቢያዩ ደነገጡ። ልጃቸው ሳቅ ፈገግታው ከፊቱ የለም። ሆዱን ታቅፎ የሚያቃስተውን ታዳጊ እየዳሰሱ ምክንያቱን ጠየቁ።
አያንሺ ውሎው ከወንድሙ ጋር ነበር። ዕለቱን የነበሩበት ዝላይ ሁለቱንም አሰደስቷል። በጨዋታ መሀል አያንሺ ድንገት መውደቁን ያስታውሳል። አወዳደቁ ከባድ ነበርና ፈጥኖ አልተነሳም። ደረቱን ሰቅዞ የያዘው ሕመም አላላውስ ብሎ ትንፋሽ አሳጥቶታል። ምግብ ለመቅመስም ሆነ ጥቂት ለማውራት አልቻለም። እንደተጨነቀ፣ እንዳለቀሰ ምሽቱን ገፋ።
ሁኔታውን ያስተዋሉ ብዙዎች ‹‹ይበጃል›› ስለእሱ ይበጃል ያሉትን ሃሳብ አመጡ። ልጁ ሕመሙ ሳይገፋበት በባህል መድኃኒት እንዲታይ ተመከረ። እናት ከተባለው ቦታ አድርሰው መድኃኒቱን ሞከሩለት። መፍትሔ አልተገኘም። ሕፃኑ ሆዱ እያበጠ፣ ውስጡ እየተጨነቀ ሰነበተ።
አያንሺ እግሮቹ እንዳሻቸው አይራመዱም። ክብደቱ በእጅጉ ቀንሷል። መንገድ ከጀመረ ችሎ መራመድ ይሳነዋል። እሱን አንስተው የሚሸከሙት በሰውነቱ መክሳት ይሳቀቃሉ። በልብስ ተሸፍኖ የሚውለው ሕፃን ደህና ቢመስልም አቅም እያጣ፣ ውስጡ እየደከመ ነው።
ከቀናት በአንዱ ወላጅ እናቱ አያንሺን ይዘው ጤና ጣቢያ ደረሱ። አዳሩ ጥሩ ባለመሆኑ ሲጨነቁ አርፍደዋል። ትንሹ ልጅ ከዚህ ቀድሞ እንዲህ አልሆነም። ቢወድቅ ይነሳል፣ ቢታመም ይድናል፣ የጤና ጣቢያው ባለሙያዎች ልጁን በወጉ አስተኝተው በጥልቅ መረመሩት። ሕመሙ በሚሰማው ቦታ የቆሰለና የደማ ነገር የለም። ጨነቃቸው።
ጥቂት ቆይቶ ወደ ጅማ ሪፈራል ሆስፒታል ሊጻፍለት ግድ ሆነ። እናት አሁንም ልጁን ይዘው ከሐኪም ፊት ቀረቡ። ችግሩ መወደቁ ብቻ መሆኑን አስረድተውም መፍትሔን ጠበቁ። የሆስፒታሉ ሐኪሞች ከቀድሞው በተሻለ ምርመራቸውን ቀጠሉ። አያንሺ ለተከታታይ ሁለት ወራት አልጋ ይዞ ታከመ።
ቆይታው ሲጠናቀቅ ሐኪሞች እሱን ከበው ዳግም መከሩ። የአሁኑ ምክራቸው ከቀድሞው የተለየ ይመስላል። አሁን የሐኪሞቹ ቡድን ታዳጊው ወደ አዲስ አበባ እንዲሄድ ወስኗል። ይህን ትዕዛዝ የተቀበሉት ቤተሰቦች ትንሹን ልጅ ከተባለው ሰፍራ ለመውሰድ ዓይናቸውን አላሹም።
አዲስ አበባ…
አዲስ አበባ ለአባት አባ ፋጂ ሩቅና አዲስ ነው። ከዚህ ቀድሞ ወደዚህ ቦታ ያመጣቸው አንዳች ምክንያት አልነበረም።‹‹ለሀገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ›› የሆኑት ፋጂ መድረሻቸው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሆነ። በእጃቸው ያለው ታዳጊ ዛሬም ታሟል። ራሱን ችሎ ለመራመድ፣ ምግብ አላምጦ ለመዋጥ እያቃተው ነው።
አያንሺ ስፍራው እንደገባ ፈጥኖ አልጋ አላገኘም። ኮሪደሩ ላይ በተገኘው ማረፊያ ተኝቶ ቀናትን ሊጠብቅ ግድ አለው። ጉሉኮስ እየወሰደ ጥቂት የዘለቀው ታዳጊ መኝታው ሲገኝለት መደበኛ ሕክምናውን ቀጠለ።
የምርመራው ውጤት
ውሎ አድሮ አባ ፋጂ የልጃቸው ሕመም የደም ካንሰር መሆኑ ተነገራቸው። እሳቸው ከዚህ ቀድሞ ስለዚህ ሕመም የሰሙት ነገር አልነበረም። እሱን መሰል ልጆች በሕመም ሲሰቃዩ ግን ችግሩ ከፍ ያለ መሆኑ ገባቸው። አባት ስለ አያንሺ ብዙ ሲያስቡ ቆይተዋል። በትምህርቱ ልቆ፣ ከፍ ያለ ደረጃ እንዲገኝ ይመኛሉ። በወጉ ቁርዓን ቀርቶ ሃይማኖቱን እንዲያከብር ይሻሉ።
አባት እውነቱን ካወቁ በኋላ ድንጋጤና ሀዘን ዋጣቸው። ሕክምናው ጊዜ የሚፈልግ ዓመታትን የሚጠይቅ መሆኑ ሲነገራቸው ደግሞ የትንሹ ልጃቸውን ሕይወት ለመታደግ ተዘጋጁ። የሕመሙን መላቅና የሚያስፈልገውን ወጪ ባወቁ ግዜ ሁሉን የመሸፈን አቅሙ እንደሌላቸው ተናገሩ። ደግነቱ ሕክምናውን በሀገር ውስጥ ማካሄድ ይቻላል ተባሉ ። የመድኃኒቱ ዋጋ ቢበዛም ከልጃቸው ሕይወት የሚበልጥ አልሆነባቸውም።
አያንሺ ክፍሉን ቀይሮ ሕክምናውን መከታተል ጀመረ። የኬሞው ሕክምና ከአቅሙ በላይ ነበር። ገና ሲጀምረው ውስጡ ይዳከማል፣ ምግብ ይጠላል፣ ጸጉሩ እየረገፈ ገጽታው ይገረጣል። ከጀርባ አጥንቱ የሚወሰደው ናሙና ለትንሹ ልጅ እጅግ የከፋ ስቃይ ነበረው።
ትንሹ አያንሺ ዕድሜው ከፍ ሲል ያቋረጠውን ትምህርት መቀጠል ይፈልጋል። እንደ እኩዮቹ ደብተር ይዞ ትምህርት ቤት መመላለስ፣ ፊደል መቁጠር፣ በመዝሙር መዝናናት ምኞቱ ነበር። ይህ እንዳይሆን አሁን ከአልጋ ውሏል። በየቀኑ የሚወሰደው ሕክምና አቅሙን እየፈተነው ነው። አዛውንት አባቱ ዛሬም ከጎኑ ናቸው። እሱን ለማሳከም ብዙ ዋጋ እየከፈሉ፣ በርከት ያለ ገንዘብ እያወጡ ነው።
ዛሬም ትንሹ ልጅ ሕክምናውን ቀጥሏል። የመዳን ተስፋ ስለተሰጠው ቤተሰቡ በጎ እያሰበ ነው። አባት ወራት በፈጀው ቆይታ ከዕለት ሥራቸው ርቀዋል። ጠንካራው ገበሬ ዛሬ ከእርሻቸው አይውሉም። ከገጠር አዲስ አበባ መመላለሱ ቢርቅም ከብዷቸው ግን አያውቅም። ሁሉን ስለእሱ ይችሉታል፣ይወጡታል።
የአባት ተስፋ…
አባ ፋጂ ከዚህ ቀድሞ ልጆችን ቀብረዋል። ዛሬ ግን የዓይናቸውን ማረፊያ ትንሹን አያንሺን ማጣት አይፈልጉም። የቻሉትን እያደረጉ ፈጣሪን ይማጸናሉ። ብዙ የደከሙለት ልጅ አሁን ዓይኑን እየገለጠ ነው። ያሳለፈው ስቃይና መከራ በቀላሉ አይወሳም። በርካታ የጭንቅ ቀናት ጥቂት የማይባሉ የሕመም ሌሊቶችን ገፍቷል። አባት ስቃዩን ሲጋሩ፣ ችግሩን ሲካፈሉ ከርመዋል። አሁን ያዩበት ተስፋ ግን የነገ ህልማቸውን ዕውን የሚያደርግ ነው።
አያንሺ ከሕመሙ አገግሞ ቀጣዩን ሕክምና ለመከታተል ማረፊያ ያስፈልገዋል። ለመድኃኒቱ መግዣ በየጊዜው የሚስፈልግ ገንዘብ ቀላል አይደለም። ከሆስፒታል ወጥቶ ቤት ለመከራየት የዕለት ወጪ ለመሸፈን አቅም ይጠይቃል። አባ ፋጂ ‹‹አለንህ›› የሚል ወዳጅ ዘመድ ከጎናቸው የለም።
አሁን ትንሹ አያንሺ ሰባት ሊሞላው ነው። ይህ ጊዜ ክፉና ደጉን የሚለይበት፣ ቁምነገር ማሰብ የሚጀምርበት ነው። ሁሌም የሚያስበው የትምህርት ጉዳይ ዛሬም ከውስጡ አልጠፋም። እሱ ተምሮ ሲጨርሰ ዶክተር መሆን ይፈልጋል፣ ሐኪም መሆኑ የታመሙ ወገኖችን አክሞ ለማዳን ያግዘዋል።
አያንሺ ሆስፒታል በቆየባቸው ጊዚያት የሐኪሞችን ዋጋ አስተውሏል። ሙያው የታመመ የሚድንበት፣ ተስፋ የቆረጠ ውስጡ የሚለመልምበት ስለመሆኑ በራሱ የጤና ለውጥ እያረጋገጠ ነው። አንድ ቀን እሱም ማዳመጫውን በጆሮ ሰክቶ፣ ነጭ ካፖርቱን ደርቦ ጥቁሩን ጨለማ እንደሚገፍ ተስፋ አለው። ትንሹ አያንሺ ግን ዛሬም ከአልጋው እንደተኛ ነው። ነገን አላሚው ሕፃን ፍጹም ተስፋ አይቆርጥም። እንደሚድን ያውቃልና ዕቅዱ ሰፊ፣ ዓላማው ታላቅ ሆኗል።
የጸሎቱ መልሰ…
አሁን አባትና ልጅ ከሆስፒታል የሚወጡበት ጊዜ ደርሷል። ለእንግዳው ሰው፣ ታማሚ ልጅ ለያዘው አባት እንዲህ መሆኑ ይከብዳል። ሁሌም ግን አባት ፋጂ ወደፈጣሪያቸው ይጮሀሉ እንደማይጥላቸው ያወቃሉና ተስፋ ቆርጠው አያውቁም። አንድ ቀን ችግራቸውን ቀርበው ያዋይዋቸው ልበ መልካሞች ለጥያቄያቸው መፍትሔ አላጡም። በዚህ መሰሉ ችግር የሚመላለሱ፣ ግራ ገብቷቸው ማረፊያ ያጡ እንግዶች የሚያርፉበትን አንድ ስፍራ ጠቆሟቸው።
አባት ብቻቸውን አይደሉም። ገና በወጉ ያላገገመ ትንሽ ልጅ አብሯቸው አለ። የሰሙትን ሁሉ ተጠራጠሩ። እንዴት ሲሉም ከራሳቸው ሞገቱ። ይህ ስጋት ግን ከእሳቸው አላለፈም። እንዲሄዱ የተጠቆሙበት ቦታ እሳቸውና አያንሺን የመሰሉ የካንሰር ሕሙማን ሕፃናት እንደቤታቸው የሚያርፉበት ዕልፍኝ ነበር።
አባ ፋጂና ትንሹ አያንሺ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወጥተው ወደ ማቲዎስ ወንዱ የካንሰር አሶሴሽን ግቢ አመሩ። ስፍራው ሲደርሱ የጠበቃቸው አቀባበል የሰጉበትን ችግር ሁሉ አስወገደ። በዚህ ቦታ አያንሺን መሰል ሕፃናት የካንሰር ሕሙማን አርፈው ይስተናገዳሉ።
ማንኛውም እንግዳ ይህ ማዕከል ቤቱ ነው። የምግብ፣ የመኝታ የአምቡላንስና የትራንስፖርት አገልግሎት ባሻው ጊዜ ጥያቄው ሁሉ ይሟላለታል። ለመድሃኒት መግዣ እጃቸው ያጠረ ወላጆች ይህ ድርጅት የቀን መከታቸው ነው። ከተለያዩ ክልሎች መጥተው ሕክምና የሚከታተሉና በቂ ማረፊያ የሌላቸው ወላጆችና ልጆቻቸው በዚህ ቦታ አርፈው ሕክምናቸውን ይከታተላሉ። በሐኪም ቀጠሯቸው ቀን ስፍራው አድርሶ የሚመልሳቸው መኪና ሁሌም ዝግጁ ሆኖ ይጠብቃቸዋል።
ይህ ቤት እስከ ዛሬ በርካታ እንግዶችን ተቀብሎ አስተናግዷል። በዚህ ስፍራ ዕንባቸው የታበሰ፣ ችግራቸው የተወገደ በርካቶች በምስጋና ይመላለሱበታል። አያንሺና አባቱ በዚህ ቤት ማረፍ የጀመሩት ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ነበር። አያንሺ ከእሱ ጋር የነበሩ እኩያ ጓደኞቹ በጊዜ ቆይታ በሞት እንደተለዩት ያስታውሳል። ይህን ሲያስብ በእሱ ሕይወት መቀጠል ፈጣሪውን እያመሰገነ ነው። አሁን እሱና አባቱ በዚህ ቤት ከቤተሰብ በላይ ናቸው። በዚህ ስፍራ ከችግር አምልጠዋል፣ የክረምቱን ጎርፍ፣ የበጋውን ሀሩር አሳልፈዋል።
ዛሬ አያንሺ የአስራ አንድ ዓመት ታዳጊ ነው። ተከታታይ የሕክምና ቀጠሮ ባለው ጊዜ ከአባቱ ጋር ከጅማ አዲስ አበባ ይመላለሳል። ከሆስፒታል መልስ አረፍ የሚለው ደግሞ በዚህ ማዕከል ነው። ትናንት በክፉ የሚያስታውሰው አስጨናቂ የሕመም ጊዜ በሕክምናው ክትትል መፍትሔ አግኝቷል።
ታዳጊው ጤናው በተመለሰ ጊዜ ትምህርቱን አልዘነጋም። ጓደኞቹ ጥቂት ቢቀድሙትም ትምህርት ቤት ገብቶ ሶስተኛ ክፍል ደርሷል። ዛሬም ዶክተር የመሆን ህልሙ አልደበዘዘም። ሕመምተኞችን አክሞ የማዳን፣ ብዙሃንን የመጥቀም ህልሙ ዕውን እንደሆነ ቀጥሏል።
የአያንሺ እህት ወንድሞች ስለእሱ ያላቸው እይታ ይለያል። ሁሌም ትንሹ ወንድማቸው በጤና ቆሞ ማየትን ይሻሉ። በትምህርቱ የበረታ በሃይማኖቱ የጠነከረ እንዲሆንም ከጎኑ ናቸው።
ትናንትናን በትውስታ …
አያንሺ ሲናገር አፉ እንደ ሕፃን ይጣፍጣል፣ የዋህነቱም ከገጽታው ይነበባል። ሮጦ ያልጠገበው ልጅነቱ በሕመም ፈተና ቢያዝም በየምክንያቱ ሰበብ ፈልጎ አይከፋም። ሁሌም ካገኘው ጋር ተግባቢ ነው። ከዓመታት በፊት የነበረውን ስቃይ ዛሬ በትውስታ የሚያነሱት አባት ፋጂ በተለይ በኬሞ መውሰድ ጊዜ የነበረበትን የከፋ ስቃይ አይዘነጉም።
የዛኔ ከቤተሰቡ በቅርብ የተገኙት ብቸኛው ሰው እሳቸው ነበሩ። ያለ ምግብና ውሃ ሕመምን ማስተናገድ ለትንሹ ልጅ የከፋ ስቃይ ነበር። የሰውነቱ መክሳት፣ የእጆቹ መላላጥ፣ የአካሉ መጎሳቆልና አቅም ማጣት ማንነታቸውን ፈትኖ ከጭንቀት ጥሏቸው እንደነበር ሲያስታውሱ ዛሬ የሕልም ያህል ይታያቸዋል።
ዛሬን …
አሁን አያንሺ ፍጹም ደስተኛ ነው። አዲስ አበባ ደርሶ በተመለሰ ቁጥር የሚያስበው ስለትምህርቱ ሆኗል። ከልጅነቱ በውስጠቱ የሰረጸው ጽኑ ዓላማ በፈተናዎች እንደማይረታ ለራሱ ነግሮታል።
አባት ፋጂ ስለልጃቸው ሕክምና ገንዛቤ ወስደዋል። መድኃኒቱ ቢቋረጥ፣ ሕክምናው ቢዘገይ የሚመጣውን አደጋ አሳምረው ያውቁታል። እሳቸው ስልጃቸው የከፈሉት ዋጋ አይቆጫቸውም። እንደውም ለሌሎች ወላጆች ምሳሌ ሆነው በር ካቶችን አስ ተምረዋል።
አሁን አያንሺ እያደገ ነው። ትናንት ያለፈበት የጤና ችግር በእሱ መዘናጋት እንዳይመለስ ሕክምናው ላይ ጥሩ የሚባል አስቤ አለው። ከጅማ አዲስ አበባ ሲመላለስ በምክንያት መሆኑን ያወቃል። ነገ ስለአባቱ ታላቅነት ቆሞ የሚመሰክረው እሱ በጤናወ መቆም ሲችል መሆኑ አይጠፋውም። እናም አያንሺ ብርታት መለያው ሆኗል። የዛሬን ጨለማ አንግቶ ነገን በድል ለመሻገር ከራሱ ጋር በጽናት ይታገላል። አያንሺ ትንሹ፣ ብርቱው ብላቴና።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም