በኢትዮጵያ ጥቂት የማይባሉ ሴቶች በልዩ ልዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ምክንያት ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት ሲያገኙ አይታይም። በተለይ በሚገጥማቸው የገንዘብ እጥረት ምክንያት የጤና መታወክ ሲገጥማቸው ለመታከም ይቸገራሉ። በወሊድ ወቅት ደግሞ ተገቢውን የሕክምና ክትትል አግኝተው ለመውለድ ችግር ይገጥማቸዋል። ይህን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት ታዲያ ሴቶች በገንዘብ እጥረት ምክንያት የሕክምና አገልግሎት ሳያገኙ እንዳይቀሩ የሚያስችል ‹‹ሔዋን›› የተሰኘ የሴቶች ጤና ድጋፍ በጎ አድራጎት ድርጅት ተመስርቶ ከሰሞኑ ስራውን በይፋ ጀምሯል።
ፕሮፌሰር እድልአየሁ በቀለ ‹‹ሔዋን›› በተሰኘው የሴቶች ጤና ድጋፍ በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና የቦርድ አባል ናቸው። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ደግሞ የስነተዋልዶ ጤናና መብት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ይሰራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሎም በአዲስ አበባ ከተማ አንጋፋ ከሚባሉ የሕክምና ተቋማት ውስጥ አንዱ ነው። ሆስፒታሉ ከምስረታው ጀምሮ ገቢያቸው አነስተኛ ለሆኑ ዜጎች የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። የሕክምና አገልግሎቱን እያሰፋ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የተለያዩ ሕክምና አገልግሎቶችን ከሰባ አምስት ዓመታት በላይ እየሰጠ ይገኛል።
በዚህ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ሆስፒታሉ በርከት ያሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ያሉባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎችን እያገዘ ነው። በተለይ ሴቶች ካለባቸው ማኅበራዊ ተፀእኖ አኳያና በሕክምና ሂደት የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ከነዚህ ውስጥም መድሃኒቶችን ለመግዛት መቸገር፣ ተመላልሰው ሕክምና የሚያስፈልጋቸው እናቶች የማደሪያ፣ ትራንስፖርትና ምግብ ወጪ መቸገር፣ የወለዱ እናቶች ጨቅላ ሕፃናቶቻውን የማሞቂያ ክፍል ገብተው ሲታከሙ እነሱ የሚቆዩበት ቦታ ማጣትና መሰል ችግሮች ይጠቀሳሉ።
በነዚህ ችግሮች ምክንያት የሕክምና መቆራረጥና ከሕክምና መቆራረጥ ጋር የተያያዙ የከፉ ጉዳቶች ሲጋጥማቸው ይታያል። ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ ከቅርብ ግዜ ጀምሮ በሆስፒታሉ ኮሌጅ በሚገኘው የማህፀንና ፅንስ ሕክምና ክፍል ባሉ ሃኪሞችና የጤና ባለሞያዎች ከደሞዛቸው ተቆራጭ በማድረግና ጥቂት በጎ አድራጊ ግለሰቦችን በማስተባበር ለሴቶች የተለያዩ የሕክምና አገልግሎት ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።
ይሁንና በኢትዮጵያ የሚታየው የኢኮኖሚ ችግር እየሰፋ በመሄዱና የሴቶች ታካሚዎች ቁጥርም ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ በመምጣቱ ብሎም ሴቶች የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት እየገጠሟቸው ያለው የገንዘብ እጥረት ከቀን ወደ ቀን ከፍ እያለ በመምጣቱ በዚህ መልኩ መቀጠሉ አዋጭ ሆኖ አልተገኘም። ከዚህ አንፃር የተጀመረውን መልካም ስራ በስፋትና በዘላቂነት ለማስቀጠል እንደ በጎ አድራጎት ድርጅት መቋቋምና በዚህ መልኩ መቀጠል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ይህንኑ በመገንዘብ የተለያዩ ሕጋዊ ፍቃድ የማግኘትና የመመዝገብ ስራዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል። ለዚህም ስራ ከሆስታሉ የፅንስና ማህፀን ሕክምና ክፍል ኃላፊዎች ጀምሮ መምህራን፣ ሃኪሞች፣ አዋላጅ ነርሶች፣ የኮሌጁ አስተዳደርና ተማሪዎች ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል። ሴቶች ወደ ሆስፒታሉ ሲመጡ የሚደርሱባቸውን ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ለመቀነስ ይረዳ ዘንድ ‹‹ሔዋን›› የተሰኘ የሴቶች ጤና ድጋፍ በጎ አድራጎት ድርጅት ተመስርቶ በይፋ ስራውን ጀምሯል፤ የገቢ ማስሳቢያ ፕሮግራምም አካሂዷል። አርቲስት የትናየት ታምራትን ደግሞ የድርጅቱ የክብር አምባሳደር አድርጎ ሾሟል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የፅንስና ማህፀን ስፔሻሊስትና ሔዋን በተሰኘው የሴቶች ጤና ድጋፍ በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ወንድሙ ጉዱ በበኩላቸው እንደሚገልፁት ድርጅቱን ለመመስረት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት በእለት ተእለት ስራዎች የሕክምና ወጪያቸውን መሸፈን የማይችሉ ሴቶች በብዛት መታየታቸው ነው። ከዚህ በመነሳት ሴቶቹ ችግሩን ይዘው ሲመጡ መከላከልና መፍታት የሚቻል በመሆኑ የሕክምና ወጪያቸውን መሸፈን የማይችሉት እዛው በተወሰነ መልኩ በበጎ ፍቃደኝነት የመርዳትና ወደ ማኅረሰቡ በመውረድ ችግሮቹን የማቃለል ስራ ተሰርቷል። በዚህም መልኩ ነው ስራው የተጀመረው።
ወደ ማኅበረሰቡ ተወርዶ የሚሰራው ስራ ሴቶችን በትምህርትና በኢኮኖሚ የማብቃት፣ የጤና መረጃዎችን መስጠት፣ ቅድመ ካንሰር ልየታ ምርመራዎችን ማድረግ፣ የሴቶች ጤና ላይ የፖሊሲ ማእቀፍን እንዲጎለብት ማገዝና ጥናትና ምርምር ላይ በመመርኮዝ የሴቶችን ጤና ማበልፀግን ያካትታል። ስለዚህ ስራው ሲጀመር የሕክምና ወጪ የሚያንሳቸውን ሴቶች መርዳት ቢሆንም አሁን ላይ ስራው አድጎ የሴቶችን ጤና ወደ ማበልፀግ ስራ አድጓል። ስለዚህ አሁን ላይ በዋናነት የሚሰራው ስራ የሴቶችን ጤና ማበልፀግ ነው።
ለሴቶቹ እርዳታ እየተደረገ ያለው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ሕክምና ክፍል ነው። የእርዳታ ስራው ከተጀመረ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በነዚህ ሁለት ዓመታት ግዜ ውስጥ በሕክምና ክፍሉ ሀኪሞች፣ መመህራን፣ ተማሪዎችና ሌሎች በጎ ፍቃደኛ ግለሰቦች አማካኝነት 80 የሚደርሱ እናቶች ድጋፍ አግኝተዋል። እስከ 150 ሺ የሚጠጋ ገንዘብም ለነዚህ እናቶች ሕክምና ወጪ ሆኗል።
ዋና ስራ አስኪያጁ እንደሚያስረዱት ሆስፒታሉ የሚፈልገውን የሕክምና አገልግሎት ሰጥቶ ጨርሻለሁ ማለት ይችላል። ነገር ግን በእለት ተዕለት የሚታየው የሴቶች የሕክምና ወጪ ችግር ይህን በጎ እርዳታ ለማከናወን አስገድዷል። በሴቶች በኩል የሚታየው የሕክምና ወጪ የመሸፈን ችግር ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መጥቷል። ይህም ችግር በተለያዩ ምክንያቶች የመጣ ነው። አንደኛው ምክንያት የሴቶች የኢኮኖሚ እቅም ማነስ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የኢኮኖሚ ሁኔታው ቢሻሻል በዛው መጠን የሕክምና ወጪ በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ነው። ዛሬ ላይ የላብራቶሪ፣ አልትራሳውንድ፣ የሲቲ ስካንና ኤም አር አይ፣ ለየት ያሉ የደም ምርመራዎች ወጪዎች ከፍ ብለዋል።
በተመሳሳይ የመድሃኒት ዋጋም የዛኑ ያህል እየጨመረ መምጣት በተለይ ደግሞ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑ የመድሃኒት አይነቶች ከታካሚዎች የመግዛት አቅም በላይ መሆን ለችግሩ መስፋት አይነተኛ ሚና ተጫውተዋል። በጥናት በተደገፈ መረጃ መሰረት ደግሞ ለታካሚዎች ከሚታዘዙ አራት አምስት መድሃኒቶች ውስጥ አራቱ ከታካሚው የመግዛት አቅም በላይ መሆንም የሴት ታካሚዎችን ችግር አባብሶታል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሴቶች ሁለንተናዊ ጤና ሲባል በርካታ ነገሮችን ያካትታል። ሴቶች ገና በታዳጊነት የእድሜ ክልል ውስጥ በትምህርት ቤት እያሉ ግልፅ የሆነ የፆታ ልዩነት ይታያል። ትንሽ ከፍ ሲል ደግሞ ያለ እድሜ ጋብቻ ችግሮች ይታያሉ። ይህም በራሱ በሴቶች የሚያደርሰው የራሱ የሆነ ጫና አለው። በኢትዮጵያ በአብዛኛው የቤተሰብ ገቢ አመንጪ ወንዶች እንደመሆናቸው ሴቶች የኢኮኖሚ ጥገኛ ስለሚሆኑ ይህም በሴቶች ላይ የሚያደርሰው የሥነ ልቦናና ማኅበራዊ ተፅእኖ ይኖረዋል።
እነዚህና መሰል ነገሮች በሴቶች ላይ የጤና ጫና ይፈጥራሉ። ዋነኛ መነሻውም ይኸው ነው። ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ ሴት በመሆናቸው ምክንያት ከወንድ የተለዩ የሕክምና ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። የማኅፀን በር ጫፍና የጡት ካንሰር ለሴቶች የተለዩ በሽታዎች ናቸው። ስለዚህ ማኅበረሰቡ ጋር ያለው ችግር፣ ሴቶች በተፈጥሮ ያላቸው ስነ ሕይወታዊ አፈጣጠርና የሴቶችን ጤና ከማበልፀግ አንፃር ፖሊሲውን ላይ በደምብ አለመሰራቱ የሴቶች ጤና ላይ ሁለንተናዊ ጫና ይፈጥራል። ይህ ደግሞ የብዙ ነገሮች ውጤት ነው።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶች ጤና ቡድን መሪ ወይዘሮ ዘምዘም መሃመድ እንደሚናገሩት እናቶች በተለያዩ የኢኮኖሚ ችግሮች ምክንያት የሚገጥማቸውን የሕክምናና አገልግሎት መጓደል ለመቅረፍ በርካታ ስራዎች መሰራት አለባቸው። በተለይ ደግሞ አሁን ከሚታየው ድህነት አኳያ ሁሉንም ነገር በመንግስት ብቻ መሸፈን ስለሚያዳግት አቅም መፍጠርና ሴቶችን ማገዝ ያስፈልጋል።
ወደ 48 ነጥብ 9 የሚጠጉና በገጠር የሚኖሩ ሴቶች በተለያዩ ምክንያቶች ለሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ባለመሆናቸው እንደዚህ አይነቱ የበጎ አድራጎት ድርጅት መቋቋም ወሳኝ ነው። ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚገኙ ሴቶች ተደራሽ መደረግ አለበት። ከሁሉ በፊት ግን ሴቶችን በሁለንተናዊ መልኩ ማብቃት ያስፈልጋል። ልክ እንደ ጳውሎስ ሆስፒታል ሁሉ በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዲህ አይነቱን ግንዛቤ መፍጠር ከተቻለ ወደጤና ተቋማት የሚመጡ ሴቶች እና ሕፃናት በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሕይወታቸው እንዳይጠፋ መታደግ ይቻላል።
ሔዋን የሴቶች ጤና ድጋፍ በጎ አድራጎት ድርጅትም በዚህ ስራው ብቻ ይገደባል ተብሎ አይታሰብም። ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎችም ተመሳሳይ ስራዎችን ያከናውናሉ ተብሎ ይጠበቃል። በየትኛውም ደረጃ ላይ ያለ ሰው በሕይወቱ ሊኖረው የሚገባው ትልቁ ሃብቱ ጤናው እስከሆነና ሁሉንም ሴከተር አስከሚነካ ድረስ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ዘርፈ ብዙ ምላሽ ይፈልጋል።
ሴቶች ልጆች ትምህርት ቤት እንዲቆዩ የትምህርት ሚኒስቴር ድርሻ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ድርሻ ነው። ሴቶች በትምህርት ቤት በቆዩ ቁጥር ደግሞ በአካልም፤ በአእምሮም እየበቁ ይሄዳሉ። ውሳኔ ሰጪም ይሆናሉ። ለዚህ ታዲያ ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ወንዶችም ትምህርት ቤት ላይ እንዲቆዩ መሰራት አለበት። ምክንያቱም ሴቶች ለተለያዩ በሽታዎች ሲጋለጡ ወንዶች ሴቶችን መደገፍ ስላለባቸው ነው።
ከዚህ አንፃር ሔዋን ወደ ጳውሎስ ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎችም የጤና ጠቋማት ለሚሄዱ ሴቶች እንደማስተማሪያ ሆኖ ያገለግላል። በተመሳሳይ የጤና ባለሞያዎችም አክብሮት፣ ሩህሩህነትና ታጋሽነት የተሟላበት አገልግሎት እንዲሰጡ መሰራት አለበት። ስለዚህ በቀጣይ ለሔዋን የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም