ስለኢሬቻ የተጻፉ የተለያዩ ጽሑፎች እንደሚያመለክቱት፤ ኢሬቻ ማለት ማምለክ እና ማመስገን ማለት ነው። ‹‹ይሄን ስላደረግህልኝ፣ ከክረምት ወደ በጋ (ብራ) ስላሸጋገርከኝ አመሠግናለሁ›› እየተባለ ፈጣሪ የሚመሰገንበት ነው። ኢሬቻ ሠፊ አገልግሎቶች አሉት። መነሻውም በጣም የራቀ ነው። ሠው ማምለክ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የመጣ ነው። ኢሬቻ (እርጥብ ሣር) ይዘው ነው ፈጣሪያቸውን የሚለማመኑት። ኢሬቻ በእርጥብ ሣር ይወከላል። ለጋብቻ ጥያቄ ኢሬቻ እርጥብ ሣር አገልግል ውስጥ ተጨምሮ ነው የሚላከው። እንግዲህ እነዚህን ነገሮች በምናይበት ጊዜ ኢሬቻ ሃይማኖታዊ ዳራ ያለው መሆኑን እንገነዘባለን። ድሮ ሠዎች መልዕክተኛ ሲልኩ እርጥብ ሣር ቆርጠው በመስጠት፣ “አደራህን በፈጣሪ ስም ይህን መልዕክት አድርስልኝ” ብለው ይልኩታል። እንግዲህ ቃል በቃል ሲገለፅ፤ ኢሬቻ ሣር ወይም የተመረጡ ዛፎች ቅጠል ማለት ነው።
ኢሬቻ በዓመት ሁለት ጊዜ ነው የሚደረገው። የመጀመሪያው ከነሐሴ መጨረሻ ጀምሮ እስከ ጥቅምት መጨረሻ ይካሄዳል፤ ሁለተኛው ደግሞ በበልግ ወራቶች ግንቦትና ሠኔ ውስጥ የሚደረግ ነው። ሁለተኛው ግን አሁን እየተረሣና እየተዳከመ ነው ያለው።
ኢሬቻ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው። ለምሣሌ ጥምቀት ሃይማኖታዊ በዓልነው እንጂ ሃይማኖት አይደለም። ኢሬቻም እንዲሁ ነው።
የሃይማኖቱ ስም ዋቄፈና ነው። የእምነቱ ተከታይ ዋቄፈታ ነው የሚባለው። ከዋቄፈና ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ ኢሬቻ ነው፤ ሌሎችም ብዙ በአላት አሉ። ሌላው ከዚህ ሃይማኖታዊ በዓል ጋር በልማድ አብሮ ተቀላቅሎ የሚከወን ነገር አለ። ለምሣሌ ቡና ማፍላት፣ ዛፍ ቅቤ መቀባት፣ ስለት ማግባት፣ ሽቶ ውሃ ውስጥ መወርወር የመሣሠሉ አሉ። እነዚህ ልማዶች ናቸው እንጂ የሃይማኖቱ መርሆች የሚያዛቸው አይደሉም። ሃይማኖቱ በጭራሽ እነዚህን ነገሮች አይፈቅድም። የኦሮሞ ህዝብ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታይ ነው። በክርስትናውም በእስልምናውም ሃይማኖት ውስጥ ያሉ አሉ።
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባሳተመው በራሪ ወረቀት ላይ ተከታዩን መረጃ እናገኛለን። ኢሬቻ ማለት ጥንታዊ የአባይ ሸለቆና መሰል የኦሮሞ ህዝቦች ዘንድ ፈጣሪ(ዋቃን) ለማመስገን የሚደረግ ሥነ ሥርዓት ነው። በዓሉ የበለጠ የሚታየው በአተገባበር(ክዋኔ) ነው። በዚህ ክዋኔ ውስጥ የዋቄፈና የሃይማኖት ተቋም የእምነቱ መሪዎች(ቃሉዎች) ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። የኢሬቻ ስነ ሥርዓት የትና እንዴት መከበር እንዳለበትም የሚወሰነው በቃሉዎች ነው።
ኢሬቻ በሁለት ቦታና ወቅት ይከበራል። አንደኛው በተራራ ላይ የሚከበር ኢሬቻ ሲሆን ሁለተኛው በጅረትና ሐይቆች ዙሪያ የሚከበር ሥርዓት ነው።
በተራራ ላይ የሚፈጸመው ኢሬቻ(ሬቻ ቱሉ) የሚከናወነው በተራራ ላይ ሲሆን የበጋ ወራቶች አልፈው የበልግ ወቅት ሲገባ የሚከበር ነው። የሚከበረውም በበጋ ወቅት የነበረውን የፀሐይ ሙቀትና የውሃ እጥረት አስመልክቶ ዝናብ እንዲዝንብ ፈጣሪን ለመለመን ነው። ቦታውም የደመና ርጥበት የሚታይበት ተራራማ ቦታ ላይ ይሆናል። በቦታው ላይ ሆነውም ለዋቃ ምስጋና ያቀርባሉ።
ሁለተኛው በጅረቶችና ሐይቆች የሚደረገው ነው። ይህኛው በክረምት ወር ማብቂያ እና በብራ ወራት መግቢያ መስከረም ወር አጋማሽ አካባቢ የሚደረግ ነው። አተገባበሩም በሐይቅ ዙሪያ የሚተገበር ነው። በክረምት ወቅት ተዘግተው የሚቆዩ መደበኛ ችሎቶች የሚከፈቱበትም ስለሆነ ‹‹የችሎት መክፈቻ›› ተብሎም ይጠራል። ወቅቱ የአበባና የብራ ወቅት ስለሆነም ለዋቃ ዝማሬ የሚቀርብበት ነው። በውሃ ዳር የሚሆነውም ውሃ የዋቃ ስጦታ ስለሆነ ነው።
በደጋ እና ወይና ደጋ አካባቢ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከብቶቻቸውን ወደ ሆራ ወይም ጨዋማ ውሃ የሚያሰማሩበት ወቅትም ነው። ኢሬቻ በውስጡ ባህልንና ፍልስፍናን ያቀፈ ነው። ትውልድና የመኖር ምስጢርን ያቀፈ ስለሆነ ተፈጥሮም ይታይበታል። የእፅዋትን፣ የእንስሳትን ተዋልዶና የትውልድ መተካካትን ከዋቃ ጋር የሚያዛምዱበት ነው።
ኢሬቻ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ነው። ከዚህ በፊት በቢሾፍቱ ይከበር የነበረ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ደግሞ ከ150 ዓመታት በኋላ በአዲስ አበባ ይከበራል። በእንዲህ አይነት የኦሮሞን ባህል በሚያሳዩ በዓላት ላይ የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ይንጸባረቃል። የኦሮሞን የባህል አልባሳት ዲዛይን የምትሰራው ዲዛይነር ብርቱካን ጂማ እንደምትለው፤ አልባሳቱ አሁን ላይ ዘመናዊ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው። ዘመናዊ ሲሆኑ ግን ባህላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ነው። የሚሰራውም የኦሮሞ ህዝብ በሚወደውና በመረጠው የቀለም አይነት ነው። በእንዲህ አይነት በዓላት ላይ በመደበኛው የተለመዱት የባህል ልብሶች አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የባህል ልብሶች በዘመናዊ መንገድ ተሰርተውም ይለበሳል።
ብርቱካን እንደምትለው፤ የባህል አልባሳቱ ዘመናዊ ሲደረጉ ባህላዊ ይዘታቸውን በማጥፋት አይደለም። ከጥራት፣ ከውበትና ከቅልጥፍና አንጻር ነው የሚዘምነው። በየክልሉ ባህላዊ አለባበስ አለ፤ ያንን በነበረበት ብቻ ይለበስ ቢባል በአሁኑ ጊዜ የማይመች ይኖራል። ሌላው ማህበረሰብም እንዲለብሰው ተደርጎ ነው በዘመነ መንገድ የሚሰራው። ለምሳሌ በአርሲ አካባቢ በድሮው ጊዜ ቅቤ እየተነከረ የሚለበስ ቀሚስ ነበር። ያንን በነበረበት እንዲቀጥል ቢደረግ አይሆንም። አሁን ቅቤው እንኳን ተገኝቶ ልብሱ ቢነከር የሚለብሰው አይኖርም። እነዚህ ነገሮች ናቸው እየተጠኑ ዘመኑን በሚመጥን መንገድ የሚሰራው።
ብርቱካን በመጀመሪያ በሥዕል ሰርታ ነው የምታሳያቸው። ዲዛይኑንም ሆነ የቀለም አይነቱን በሚፈልጉት መንገድ ከሆነ በኋላ ትሰራላቸዋለች። የኦሮሞን ባህል ይገልጻል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ የታመነበት ይሰራል።
ለእንዲህ አይነት ጥበባዊ ሥራዎች ከመንግስት በኩል የሚደረገው ድጋፍ ደካማ እንደሆነ ነው ዲዛይነር ብርቱካን የምትናገረው። በፊት ከነበረው የተወሰነ መሻሻል ቢኖርም፤ ባህላችን ነው፣ የራሳችን ነው የሚለው ስሜት ግን የተቀዛቀዘ ነው። መንግስት ተገቢውን ድጋፍ ቢያደርግ በእንዲህ አይነት ጥበባዊ ሥራዎች ላይ የሚሰሩ ብዙ ወጣቶች ናቸው ያሉ። ሀሳብ ከማፍለቅ ጀምሮ ብዙ አዳዲስና ዘመናዊ ሥራዎችን የሚሰሩ ዲዛይነሮች አሉ። ህብረተሰቡ የሚፈልገው ደግ ጥራት ያለውና ዘመኑን በሚመጥን መንገድ የተሰራ የባህል ልብስ ነው።
እንደ ዲዛይነር ብርቱካን ገለጻ፤ በአሁኑ ጊዜ በማህበረሰቡ ውስጥ የባህል ልብስ ፍላጎት እየጨመረ ነው፤ ዳሩ ግን በጥራት የባህል ልብሱ በሚፈለገው ጥራት እየተሰራ አይደለም። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ሰዎች እየገዙ እየለበሱት ነው። በጥራት ቢሰራ ደግሞ ከዚህም በላይ ተፈላጊነቱ ይጨምር ነበር ማለት ነው። በተለይም በበዓላትና በአንዳንድ ሁነታዊ ዝግጅቶች የሚለበሰው የባህል ልብስ ነው።
የባህል ልብሱ የቀለም አይነት ትውፊታዊ ትርጓሜ ያለውና የተለመደ ቢሆንም አሁን አሁን የፖለቲካዊ ትርጓሜ በመስጠት የባንዲራ ቀለም እንደሚደረግም ዲዛይነር ብርቱካን ታዝባለች። ይሄም ትውፊታዊው የባህል ልብስ ከፖለቲካ ጋር እንዲቀላቀል አድርጎታል። በዚህ ሁኔታ ደግሞ ዲዛይነሮች ገበያ ላይ የሚፈለገውን ታሳቢ በማድረግ ይሰራሉ።
‹‹ሲመርሰን›› የተባለ ድረ ገጽ እንዳስነበበው፤ በኢሬቻ ጊዜ የሚደረገው “ምስጋና” (Galata) ማብዛት እና ደስታን ማብሰር ነው። በዚህኛው በዓል ዘፈንና ጭፈራ ይደረጋል።
በበዓሉ የዋቃ ስም ይለመናል። ለዋቃ መስዋእት ይቀርባል። ለመስዋእት የሚታረደው ጥቁር በሬ አሊያም ጥቁር ፍየል ነው። ይህም በጣም መሰረታዊ ነገር መሆኑ ይነገራል። በበሬው ቆዳ ላይ ቀይ ወይንም ነጭ ነጥብ በጭራሽ መኖር የለበትም። የበሬው ገላ ከጭረትና ከእከክ የነጻ መሆን አለበት። በተጨማሪም በሬው በደንብ የበላና የደለበ ሊሆን ይገባል።
አንዳንድ ሰዎች “የበሬው ቆዳ ጥቁር መሆን አለበት” የሚለውን አስተርዮ እንደ ባዕድ አምልኮ እንደሚያዩት ይታወቃል። ነገሩ ግን እንዲያ አይደለም። የበሬው ቆዳ ጥቁር መሆኑ የሚፈለገው በዋቄፈንና እምነት መሰረት “ሰዎችን የፈጠረውና በሰዎች የሚመለከው አምላክ ጥቁር ነው” ተብሎ ስለሚታመን ነው። ይህም “አምላክ በመልኩ ጥቁር ነው” ማለት ሳይሆን “ዋቃ በስራው እንጂ በአካሉም ሆነ በሚስጢሩ ለሰው ልጅ በጭራሽ አይታወቅም” ለማለት ነው።
ኦሮሞዎች ዋቃን ሲለማመኑት እንዲህ የሚሉት።
Yaa Waaqa (አንተ አምላክ ሆይ)
Jabaa hundaa olii (ከሁሉም በላይ ጥንካሬ ያለህ)
Tolchaa bobbaa fi galii (ወጥቶ መግባቱንም የሚያሳምረው)
Guraacha garaa garbaa (ጥቁሩ እና ሆደ ሰፊው)
Tokicha maqaa dhibbaa (በመቶ ስም የሚጠራው አንድዬ)
ይህ የጥቁር ነገር ከተነሳ ዘንዳ በኦሮሞ ባህል መሰረት ጥቁር በሬ ከፍተኛ ዋጋ ያለው መሆኑ ይነገራል። የቢሾፍቱና የገላን አካባቢ የኦሮሞ አርሶ አደር ሁለት ነጭ በሬዎች የሚገዙበትን ዋጋ ለአንዱ ጥቁር በሬ ብቻ ሊያወጣ ይችላል።
የኢሬቻ እና የደራራ በዓላት በጥንቱ ዘመን ከኦሮሞ ህዝብ በተጨማሪ የምስራቅ ኩሻዊያን (Eastern Cushitic People) በሚባሉት የቤጃ፣ የሳሆ እና የሶማሊ ህዝቦችም ይከበሩ እንደነበረ ይነገራል። እነዚህ ህዝቦች ቀደም ብለው የእስልምናን እምነት በመቀበላቸው በዓላቱን ማክበሩን ትተውታል። ይሁንና እንደነርሱ የኩሻዊ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነው የአፋር ህዝብ እስከ ቅርብ ዘመን ድረስ የኢሬቻን በዓል ያከብር እንደነበረ ልዩ ልዩ ጥናቶች ያስረዳሉ።
ሁለቱ በዓላት የሚከበሩባቸውን ወቅቶች፣ የየበዓላቱን ዓላማ እና በዓላቱ የሚከሩባቸውን አውዶች ያጠኑ ምሁራን በዓላቱ በጥንት ግብጻዊያንም ይከበሩ እንደነበረ አረጋግጠዋል። ይሁንና ተመራማሪዎቹ “የበዓላቱ ምንጭ ጥንታዊት ግብጽ ነች ወይንስ ከግብጽ በታች የሚኖሩት የኩሽ (ኑቢያ) ህዝቦች?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ተቸግረዋል። ጥያቄውን አስቸጋሪ ያደረገው የግብጻዊያኑ እምነት ብዝሃ አማልክት (Polytheism) የተቀላቀለበት መሆኑ ነው። ኩሻዊያኑ ግን “ዋቃ”፣ “ዋቅ፣ “ዋቆ” እያሉ በተቀራራቢ ቃላት ከሚጠሩት አንድ አምላክ በስተቀር ሌሎች አማልክት የሏቸውም። በዚህ ረገድ የሚደረገው ጥናት ሲጠናቀቅ ውጤቱ የሚታወቅ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 24/2012
ዋለልኝ አየለ