በሌማት ትሩፋት ከ10 ቢሊዮን ሊትር በላይ ወተት ተመርቷል

-ዘንድሮ ከ12 ቢሊዮን ሊትር በላይ ወተት ለማምረት ታቅዷል

አዲስ አበባ፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ከ10 ቢሊዮን ሊትር በላይ ወተት ከላምና ከግመል መመረቱን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። በ2017 በጀት ዓመትም ከ12 ቢሊዮን ሊትር በላይ ወተት ለማምረት መታቀዱን ተናግሯል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና የዓሣ ሀብት ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ ጽጌረዳ ፍቃዱ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በ2016 በጀት ዓመት በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ከ10 ቢሊዮን ሊትር በላይ ወተት ከላምና ከግመል ተመርቷል።

በ2015 በጀት ዓመት በመጀመሪያው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር አምስት ነጥብ 6 ቢሊዮን ሊትር ወተት ከላም እንዲሁም አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ሊትር ወተት ከግመል መመረቱን አውስተው፤ በ2016 በጀት ዓመት ከ10 ቢሊዮን ሊትር በላይ ወተት ተመርቷል ብለዋል።

“በ2014 በጀት ዓመት በዓመት ለአንድ ሰው 60 ሊትር ወተት ይቀርብ ነበር፤ በ2016 በጀት ዓመት በሌማት ትሩፋት ሥራ ለአንድ ሰው በዓመት 80 ሊትር ወተት ማቅረብ ተችሏል” ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በ2018 በጀት ዓመት በቀን የአንድ ሰው የወተት አቅርቦት 110 ሊትር ለማድረስ እየተሠራ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ከላም 11 ነጥብ 6 ቢሊዮን ሊትር፤ ከግመል አንድ ነጥብ 6 ቢሊዮን ሊትር በአጠቃላይ ከ12 ቢሊዮን ሊትር በላይ የወተት ምርት ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ እቅዱን ለማሳካት እንስሳትን የማዳቀል፤ መኖን በስፋት የማልማት፤ ወጣቶችን በዘርፉ የማሠማራት፤ የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በ2018 በጀት ዓመትም የሀገሪቱን የወተት ምርት ከ16 ቢሊዮን ሊትር በላይ ለማድረስ ከወዲሁ ታቅዶ እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ጽጌረዳ አያይዘውም ከሌማት ትሩፋት በፊት በዓመት የአንድ ሰው የዓሣ አቅርቦት ዜሮ ነጥብ 5 ኪሎ ግራም ነበር፤ በ2016 በጀት ዓመት አንድ ነጥብ 2 ኪሎ ግራም ደርሷል ብለዋል።

የዓሣ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ባለው የሌማት ትሩፋት በ2016 በጀት ዓመት 138 ሺህ ቶን ተመርቷል፤ በ2017 በጀት ዓመት 260 ሺህ ቶን የዓሣ ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

በ2018 በጀት ዓመት በዓመት የአንድ ሰውን የዓሣ ምርት አቅርቦት ሦስት ነጥብ 36 ኪሎ ግራም ለማድረስና 391 ሺህ ቶን የዓሳ ምርት ለማምረት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተጠናቀቀው ዓመት ስድስት ነጥብ 2 ቢሊዮን እንቁላል ተመርቷል፤ በ2017ና 18 በጀት ዓመት 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን እንቁላል ለማምረት እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በ2018 በጀት ዓመት በዓመት የአንድ ሰው የዕንቁላል አቅርቦት 100 ለማድረስ እየተሠራ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

2016 በጀት ዓመት 207 ሺህ ቶን ማር የማምረት ሥራ ተከናውኗል ያሉት ወይዘሮ ጽጌረዳ፤ በተያዘው በጀት ዓመትና በቀጣይ ዓመት 473 ሺህ ቶን ማር ለማምረት እንደሚሠራም አመላክተዋል።

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You