ሶስቱን ባልንጀሮች ከያሉበት አሰባስቦ ያገናኛቸው ‹‹እንጀራ›› ይሉት ምክንያት ነው።በአንድ አካባቢ ሲኖሩ በቀንስራ ከሚያገኙት ገቢ የሚጠበቅባቸውን የቤት ኪራይ ይከፍላሉ።ሰፈሩ ለእነሱ አቅም የሚመጥን መሆኑ ደግሞ ሌሎች እነሱን መሰሎችን ጭምር አበራክቷል።
ሀይሌ ዳጣ ትውልዱ ከወላይታ አካባቢ ነው ።ዕድሜው ሲደርስ እንደ እኩዮቹ ደብተር ይዞ ትምህርት ቤት ለመሄድ ዕድሉን አላጣም።ቤተሰቡ በችግር የተፈተነ ቢሆንም ለእሱ ጉሮሮ ቁራሽ ፣ለአካሉም ተገን ልብሰን አላጣም።ወላጆቹ ከእነሱ ጥቅም የእሱን ፍላጎት አስቀድመው እንደ አቅማቸው ሊያኖሩት ሞክረዋል።
ዕድሜው ከፍ ማለት ሲጀምር ግን የወላጆቹም ችግር የዛኑ ያህል ይጨምር ያዘ።የቤተሰቡ ቁጥር ሲሰፋ ከትናንት በባሰ እጅ አጠራቸው ።ይህኔ ሀይሉ በሃሳብ ናወዘ።ትምህርቱን ገፍቶ ስምንተኛ ክፍል ቢደርስም ከዚህ በላይ ለመጓዝ የሚያስችል አቅም እንደማይኖረው ገምቶ ልቡን ባሻገር ላከው።
ሀይሌ እሱን መሰል የመንደሩ ልጆች ከሀገር ርቀው ከተማ መኖራቸውን ያውቃል።ከራርመው ሲመለሱም ወዘናቸው ተለይቶ፣አለባበሳቸው አምሮና ኪሳቸው ጭምር ዳብሮ ነው።ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ራቅ ብለው መሄዳቸውና በሥራ መሰማራታቸው መሆኑ አልጠፋውም።
የትምህርቱ ጉዳይ እንዳልሰመረ በገባው ጊዜ እሱም ካለበት ሆኖ የእነሱን ሕይወት ቃኘና ኑሯቸውን ተመኘው።ከሚሰማውና ከሚያውቀው እውነት ተነስቶም ከአንድ ውሳኔ ላይ ደረሰ።ውሳኔው ርቆ በመሄድ ሃሳብ ሲታጠርም ጓዙን ይዞ ለመንገድ ተዘጋጀ።
መንገደኛው ተማሪ መንገዱን ወደ አዲስ አበባ ሲያደርግ የትምህርቱን ጉዳይ ረሳና ስለነገው ገንዘብ መቁጠር ብቻ አሰበ።አገሩ ሲመለስ ስለሚኖረው ለውጥና ስለሚያገኘው ሀብት ንብረት አልሞም ውስጡን በሀሴት መላው።ይህኔ ደብተርና እስክሪብቶውን ጥሎ ለአዲስ ለውጥ መዘጋጀቱ ትክክል ነው ብሎ አሰበ።
አዲስ አበባ ሲደርስ የመጀመሪያውን ኑሮ ‹‹ ሁካታ ›› ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ አደረገ።የሁካታ ሰፈር መገኛ በተለምዶ ‹‹ደሴ በር›› ከተባለ አካባቢ ነው።የሁካታ መንደር ከየስፍራው የመጡና ሀይሌን የመሰሉ በርካቶች ይኖሩበታል።አብዛኞቹ በቀንስራ ውሎ የሚደክሙ ናቸው።ጥቂት የማይባሉትም በተመሳሳይ ሥራ ሲተጉ ከሚውሉት መሀል ይመደባሉ ።
ከእነዚህ የቀን ሰራተኞች መሀል አብዛኞቹ እርስ በርስ ይግባባሉ።የበርካቶቹ ማንነት ራቅ ከሚል ስፍራ የሚቀዳ በመሆኑ ስሜታቸው ተቀራርቦ ጨዋታቸው ይመሳ ሰላል። ሁሉም ቀን በስራ ሲደክሙ ውለው ምሽቱን ወደ ሁካታ ሰፈር ያመራሉ።እረፍት በሆኑ ጊዜም የሚያቀራርባቸውን ምክንያት አያጡም።
መንግስቱ ቶጋ ለሀይሌ የአገሩ ልጅ ነው።በትውልድ ቀዬው ሳለ እሱም እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምሯል።በትምህርቱ እምብዛም እንዳልገፋ ባወቀ ጊዜ ራሱን ለማሳደር ብዙ ሞክሯል።በቻለው ሁሉ ሮጦ እንዳሰበው የልቡ ባልሞላ ጊዜ ግን እንደሌሎች ወጣ ብሎ ገንዘብ ለመያዝ አሰበ።
የገንዘቡን ጉዳይ ሲያስብ በጉልበቱ ማደር ግድ እንደሆነ ገባው።በትምህርቱ አልገፋምና ቀድሞ የሚያገኘው ስራ ይህ ብቻ እንደሚሆን ያውቃል።መተሀራ ስኳር ፋብሪካ ሲቀጠር የልፋቱን ያህል አላጣም።በቀንስራ ውሎ የሚከፈለውን እየቆጠረም ወራትን በተስፋ ተሻገረ።
ውሎ ሲያድር ደግሞ ልቡ አርቆ ማሰብ ጀመረ።ከፋብሪካው ቢወጣ የተሻለ ገቢ እንደሚኖረውም ገመተ።በጉልበት ሥራው ጥሩ ልምድ እንደያዘ ሲገባው ከዚህ የከበደ ሥራ እንደማያቅተው ተማምኖ ከፋብሪካው ለመውጣት ወሰነ።
መንግሥቱ ከነበረበት ለመራቅ ሲወስን የመጀመሪያ ምርጫው አዲስ አበባ ሆነች።በአዲስ አበባ በርካቶች ህይወታቸውን እንደቀየሩ ሰምቷል።ከዚህም አልፎ የቅርብ ጓደኞቹና ዘመዶቹ በከተማዋ ስለመኖራቸው ያውቃል።እነሱም ቢሆኑ ከእሱ የተሻለ ህይወት አላቸው።ይህን ሁሉ አመዛዝኖ በውሳኔው ሲጸና ካለበት ስፍራ ርቆ ከመውጣት ሌላ ምርጫን አላስቀመጠም።
መንግሥቱ አዲስ አበባ እንደገባ ያገሩ ልጆች ተቀበሉት። እነሱን መስሎ ውሎ ለመግባት አልተቸገረም።የቀን ሥራ ላይ ተሰማርቶ ገንዘብ መያዝ ሲጀምር ራሱን ችሎ ቤት ተከራየ።ይህ አጋጣሚም ከትዳር አጋሩ አገናኘው። ሁለቱ ጎጆ ቀልሰው ህይወትን ሲመሩ ልጆችን አፈሩ።በቤት ኪራይ ቤተሰብን አስተዳድሮ ልጆች ማስተማሩ ለእነሱ ቀላል አልነበረም። በዕለት ገቢ የጓዳን ቀዳዳ መሸፈን ቢከብዳቸውም በመረዳዳት ተደጋግፈው ዓመታትን ዘለቁ።
አስራት ጋጋም ከትውልድ ቀዬው የወጣበት ምክንያት እንጀራን ፍለጋ ነው።አገሩ ሳለ በትምህርቱ እስከ አስረኛ ክፍል ዘልቋል።ወደ ቀጣዩ ክፍል ከማለፉ በፊት ግን ልቡ ቀድሞ የሰነቀውን ሃሳብ አቀበለው።እሱም እንደ ባልንጀሮቹ አዲስ አበባ ዘልቆ በሥራ ቢሰማራ የተሻለ እንደሚሆን አመነበት።
አስራት ካራ ከተባለ አካባቢ ቤት ተከራይቶ ኑሮን መግፋት ጀመረ።የቀንሥራው ገቢ ጉልበት ቢያስከፍለውም ለኪሱ ገንዘብ አላሳጣውም።በእረፍት ቀኑ ያገሩን ልጆች እያገኘና አብረውት ካሉት ጋርም እየቀረበ የከተማን ህይወት ተላመደ።
አስራት መንግሥቱንና ሀይሌን ካገኘ ወዲህ የሁካታን መንደር ማዘውተር ጀምሯል።እሱና ሌሎችም በዚህ ስፍራ በተገናኙ ጊዜ ጨዋታቸው ሁሉ ይደምቃል። ሁሌም የአገር ቤት ትዝታቸውን እየመዘዙ የቤተሰቦቻቸውን ናፍቆት ይወጣሉ።የትናንቱን እያወጉ ስለነገው ያልማሉ።
የሁካታ ሰፈር ነዋሪዎችን በአንድ አውሎ በጋራ የሚያማሻቸው የዘንባባ ጠጅ ቤት በየቀኑ ብዙዎችን ያስተናግዳል።ጠጅ ቤቱ ከጠጪዎች በዘለለ የሌሎችንም እንጀራ ከፍቷል።ቆሎ ይዘው የሚሸጡ፣ልብስ በክንዳቸው የሚያዞሩ፣የፈጣሪን ስም ጠርተው የዕለት እንጀራቸውን የሚለምኑ ሁሉ ለጉሮሯቸው የሚሆን አያጡም።
በዚህ ስፍራ ዝምታን ተላብሰው የሚገቡ በርካቶች እንደነበሩ ሆነው አይመለሱም።በጨዋታ ሰበብ የሚጀምሩ ትን ወግ ወደ ነገር ቀይረው ለጠብ የሚጋበዙበት አጋጣሚ ይሰፋል። አን ዳንዱ ከብርሌው ጠጅ ሲደጋግም የሰላ ንግግር ይቀናዋል።ይህኔ ጠጪው ሁሉ እንዲሰማውና ትኩረት እንዲስብ የማያደርገው የለም።
አንዳንዱ ደግሞ በዝምታ ገብቶ በዝምታ መውጣትን የለመደ ነው።እንዲህ ዓይነቱ ደንበኛ የተቀዳለትን ጨልጦ ሌላ ሲያስጨምርም የተለየ ባህሪይ አይታይበትም።ቀዝቃዛ ውሃን በቁሙ እንደጨለጠ ሁሉ ያለምንም መንገዳገድ ቀጥ ብሎ ከቤቱ ይደርሳል።
ከሁሉም የጠጅ ቤቱ ደንበኞች አሰልቺ ባህሪይ የሚታይባቸው ትንሽ ፉት ሲሉ ለጠብ የሚጋበዙት ጠጪዎች ናቸው።እንዲህ አይነቶቹ ነገር ለመጫር ምክንያታቸው የበዛ ነው።የቀደመውን ከአሁኑ እያነሱ በቀላሉ ጭቅጭቅ ይፈጥ ራሉ። አንዳንዴም ዝምተኞች የሚባሉት ጠጪዎች ያጅቧቸውና ጠቡን አጋግለው ከጣራ በላይ ያደርሱታል።
ብዙውን ጊዜ ምግብ ሳይበሉ ጠጅ የሚያዘወትሩ ጠጪዎች አቅማቸው የደከመ ነው።ጥቂት ፉት ብለው ከመውጣታቸው በስካር ናውዘው በየመንገዱ ይወድቃሉ። ሁሌም ፣ከቱቦው፣ ከአስፓልቱ ዳርና ከሜዳው ዳርቻ መታየትም ልምዳቸው ነው።በማግስቱ ግን ራሳቸውን አበርትተው ከጠጅ ቤቱ ለመታደም የሚቀድማቸው የለም።
በዘንባባ ጠጅ ቤት ጋባዥና ተጋባዡ የበረከተ ነው።ዛሬን የጋበዘ ነገን ይጋብዛል።ትናንት ለአንድ ብርሌ ብቻ የከፈለ ዛሬን ደግሞ በርካቶችን ሊጋብዝ ይችላል።የሁካታው ሰፈር ጠጅ ቤት በየቀኑ በደንበኞቹ ታጅቦ መልከ ብዙ ባህሪይን ሲያስተናግድ ይውላል።
ሶስቱ ያገር ልጆች አልፎ አልፎ ከዘንባባ ጠጅ ቤት ጎራ ይላሉ።አንድ ሁለት ባሉ ጊዜም ጨዋታቸው ይደራል።ቆይታቸውን በጠጅ አዋዝተው ሲለያዩም በሞቅታ ስሜት እንደተዋጡ ነው።
ታህሳስ 14 ቀን 2005 ዓ.ም
በዚህ ቀን የሁካታው ሰፈር የዘንባባ ጠጅ ቤት ደንበኞች እንደተለመደው በቦታቸው ተገኝተዋል። ጠጅ ቀጂው ለጠየቁት ጠጪዎች ሁሉ እየቀዳ የጎደሉ ብርሌዎችን በዓይኑ ይፈልጋል።በርካቶቹ በሞቅታ ወስጥ ስለመሆናቸው ገጽታቸው ይመሰክራል።ጥቂት የማይባሉትም ጎናቸው ካለው ጋር ውሉ የማይለይ ጨዋታ ይዘዋል።ባለአረንጓዴው ቀለም አግዳሚ በጠጅ ፍሳሽ ተዘረክርኮ በንቦች አጀብ ተከቧል።
በዕለቱ ከሶስቱ ያገር ልጆች ሁለቱ ሲገባበዙ ቆይተዋል።በጠጅ ቤቱ ሀይሌ የተባለው ባልንጀራቸው አለመታደሙ ቅር ቢላቸው በእጅ ስልኩ ደወሉለት።ሀይሌ ጥሪያቸውን አክብሮ በስፍራው ሲደርስ ጠጅ ቤቱ በሁካታ ውስጥ ነበር።
አሁን ሶስት ሆነው ብርሌያቸውን አንስተዋል። አስቀድመው መጠጡን የጀመሩት ሁለቱ ተጨማሪ አስቀድተው ጓደኛቸውን መጋበዝ ይዘዋል ።በግብዣቸው መሀል ከአንድ ጠጪ ጋር የጀመሩትን ጭቅጭቅ ተመልሰውበታል።የጨዋታቸው አዝማሚያ ያላማረው ሀይሌ ንዝንዛቸውን እንዲያቆሙ ሊመክራቸው ሞከረ።
ደነቀ የሚባለው ጠጪ በስካር መንፈስ ሆኖ ያሻውን እየተናገረ ነው።ለንግግሩ ከአጸፋ በላይ የሚመልሱለት ባልንጀሮች ደግሞ መተጋገዝ ጀምረዋል። ይህን ያስተዋለው ደነቀ በንዴት ግሎ ምላሽ ይሆናል ያለውን ሁሉ እየሰነዘረ ቆየ።አለመግባባቱ ብሶ መሰዳደቡ ሲቀጥልም ሀይሌ ደነቀን ለመማታት ከወንበሩ ተነሳ።
ሁኔታቸውን ያዩ ሊገላግሏቸው ከመሀል ገቡ። ሁለቱም ወደ ቦታቸው ሲመለሱ ግን ደነቀ የሁሉንም ሰሜት የሚነካ ስድብ ከአንደበቱ ተደመጠ።ይህኔ የሶስቱም ገጽታ በተለየ ንዴት ተለወጠ።የእናትን ስም ተጠርቶ ባልተገባ ስድብ መለወሱም እጅጉን አበሳጫቸው።
ከቆይታ በኋላ ሶስቱ ባልንጀሮች ደነቀን የሚያዩበት ዓይን የከፋ ሆነ።ንግግሩ ውስጣቸው ገብቶ ንዴት ቢይዛቸው በርቀት የጎሪጥ እያዩ መውጫውን ናፈቁ።ደነቀ በእጁ የቀረውን የመጨረሻውን ብርሌ ጨልጦ ከጠጅ ቤቱ ወጣ።ይህን ያዩ ባልንጀሮችም ርቆ ሳይሄድ ዱላቸውን ይዘው በቅርበት ተከተሉት።
ደነቀ በሞቅታ እየተንገላወደ መንገዱን ቀጠለ።ጨለማ ቢሆንም የሚሄድበትን አቅጣጫ አልሳተም።መንግስቱ ከሌሎች ቀድሞ የያዘውን ኮብል ስቶን አናቱ ላይ አሳረፈበት።ወዲያው በጀርባው ሲዘረር ከነበረበት ለመራቅ በሩጫ ፈጥኖ አመለጠ።
ጥቂት ቆይቶ አስራት ከስፍራው ደረሰ ።የደነቀን ከመሬት መዘረር እንዳየም በእጁ የያዘውን ድንጋይ በማጅራቱ ላይ ጥሎበት ወደመጣበት ተፈተለከ። አፍታ ሳይቆይ ሀይሌ ደነቀ ወድቆ በደም ከተነከረበት ስፍራ ላይ ቆመ ።እሱም በጠጅ ቤቱ የነበረውን ሁኔታ አስታውሶ በድንጋይ አናቱ ላይ ደገመውና ወደቤቱ ገሰገሰ።
የፖሊስ ምርመራ
ደነቀ በደም ተነክሮ በወደቀበት ስፍራ ሰዎች ሲደርሱ ምሽቱ ገፍቶ ነበር።ህይወቱ መትረፉን ያወቁ ጥቂቶች እየተጣደፉ ከአንድ ከፍተኛ ክሊኒክ አደረሱት።በወቅቱ የነበሩ የህክምና ባለሙያዎች የተጎጂውን ሁኔታ አስተውለው ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሆስፒታል መላክ እንዳለበት ወሰኑ።ይህ እንደታወቀ ወደ ቅዱስ ያሬድ ሆስፒታል ይዘውት የሄዱት ሰዎች ገና ከበሩ እንዳደረሱት ህይወቱ ስለማለፉ አረጋገጡ።
ፖሊስ የደነቀ ህይወት ማለፉን ካወቀ በኋላ ወንጀሉ ከተፈጸመበት ስፍራ ተገኝቶ መረጃዎችን ሰበሰበ።ስለ ሁኔታው ያግዙኛል ያላቸውን ማስረጃዎች ለይቶም ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ አሰሳውን ቀጠለ።በረዳት ሳጂን አማረ ቢራራ የቡድን መሪነት በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 412/ 05 ፋይል የተጀመረው ምርመራ ውሎ ሳያድር ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አዋላቸው።
ከሶስቱ መሀል መንግስቱና አስራት ደነቀን በየተራ በድንጋይ እንደመቱት በዕምነት ክህደት ቃላቸው አረጋገጡ።ሀይሌ ፈጽሞ በድርጊቱ እንደሌለበት አስመስሎ ለመካድ ሞከረ።የዓይን እማኞች ግን ድርጊቱን ሲፈጽም ስለማየታቸው ምለውና ተገዝተው ተናገሩ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 24/2012
መልካምስራ አፈወርቅ