አቶ አለማየሁ ኃይሌ ይባላሉ። በኦሮሞ ባህል ማዕከል የታሪክና ባህል መምሪያ ዳይሬክተር ናቸው። በኦሮሞ ህዝብ ታሪክ ላይ ያተኮሩ መጽሐፎች አሏቸው። እንዲሁም በባህል ዙሪያ ተመራማሪ ናቸው። በዛሬው ዕትማችን በኦሮሞ እና በኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ ዙሪያ ብዙ አጫውተውናል።በተለይም ደግሞ በዛሬው ዕለት የሚከበረውን የእሬቻ በዓል፣ የገዳ ሥርዓት በተመለከተ ሰፊ ሃሳብ ሰጥተውናል።እነዚህንና ሌሎች የታሪክ መሠረቶችን መነሻ አድርገው ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ አድርገዋል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- ከአንባቢያን ጋር ይተዋወቁ እስኪ?
አቶ አለማየሁ፡- አቶ አለማየሁ ኃይሌ እባላለሁ። በአዲስ አበባ ቅርብ ርቀት በምትገኘው አዲስ ዓለም በ1965 ዓ.ም ነው የተወለዱኩት። አዲስ ዓለም እስከ ዘጠነኛ ክፍል ድረስ ተምሬያለሁ። ከዚያም አስፋወሰን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማርኩኝ። ከዚያም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ በዲፕሎማ 1974 ዓ.ም ተመርቄያለሁ።
በመቀጠል በ1975 ዓ.ም ወደ ኤርትራ አሰብ አቅንቼ ሰሊና በሚባል የጨው ኢንዱስትሪ ውስጥ በቴክኒሺያንነት ለሦስት ዓመት ተኩል ሠርቻለሁ። ከዚያ ወደ አዲስ አበባ ተመልሼ ለአንድ አመት በጉለሌ ሳሙና ፋብሪካ ሠርቻለሁ። በመቀጠልም ኢትዮ ፎም የሚባል ፕላስቲክና ስፖንጅ ፋብሪካ ተቀጥሬ ነበር። በመሃል ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪዬን ጀምሬ የነበረ ቢሆንም በመሃል ለትምህርት ወደ ራሺያ አቀናሁ። ከዚያም ማስተርሴን ተመርቄ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ መጣሁ።
አዲስ ዘመን፡- እዚህ ዲፕሎማ ከሆነ ማስተርስ እንዴት ተማሩ፤ የትምህርት ዘርፉንስ ለምን ቀየሩ?
አቶ አለማየሁ፡- ወደራሺያ ያቀናሁት በ1980 ዓ.ም ነበር። ራሺያ የቆየሁት ስድስት ዓመት ነው። በዚያም ማስተርሴን ይዣለሁ። በራሺያ ሦስት ዓመት ከተማርክ በኋላ ስትቀጥል እንደ ማስተርስ ነው፤ እዚያ ዲግሪ የለም። በ1986 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ። ቀደም ብዬ ስሠራበት የነበረው ሥራ መቀየር የፈለኩት የጤና እክል ስላጋጠመኝና በፋብሪካው አካባቢ መቀጠሉ ለጤናዬ ጥሩ እንዳልሆነ በሐኪሞች ስለተነገረኝ ለመቀየር ተገደድኩ። ስለዚህ በራሺያ ማስተርሴን የተማርኩት ‹‹ሶሾ ፖለቲካል ሂስትሪ›› ነው። ከዚያም ለአንድ ዓመት ያለሥራ ተቀምጬ ነበር። ቀደም ሲል የተማርኩት ትምህርት አሁን ከተማርኩት በጣም የራቀና ዘርፉም የማይገናኝ ነው። ውጭ ተምረው ዘርፍ ከቀየሩ በኋላ የመጀመሪያ ቅጥር የፈፀሙት የት ነበር?
አቶ አለማየሁ፡- ከአንድ ዓመት በኋላ በወቅቱ አጠራር በኦሮሚያ ባህልና ስፖርት ቢሮ ተቀጥሬ ወደ ኢሉባቡር አመራሁ። ሁለት ዓመት ከሠራሁ በኋላ የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ ላይ ያተኮረ ጥናት ፕሮጀክት ተቀረፀ። በ1989 ዓ.ም ከኦሮሚያ ዞኖች 12 ባለሙያዎች ተሰባሰብን። ከአጥኚዎቹ ውስጥ አንዱ እኔ ነበርኩ። ከዚያም ጥናቱን ጀመርን። በጥናታችን በርካታ መረጃዎችን አጋላብጠናል። መረጃዎች ሚዛናዊ እንዲሆኑ እና ታሪኩ እውነታ ላይ የተመሰረተ እንዲሆንም በከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት የተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የታሪክ አጥኚዎቹ የትምህርት ዝግጅትና ስብጥር ምን ይመስል ነበር?
አቶ አለማየሁ፡- የታሪክና አንትሮፖ ሎጂ ተማሪዎች ነበሩ። አስተባባሪ ዶክተ ሮችም ነበሩ። የቋንቋ ሰዎችም ነበሩ። በዚህም በተለያዩ ሙያ የተሳተፉ ሰዎች ነበሩ። ሥራውን ስንጀምር የአጭር እና የረጅም ጊዜ ፕላን አዘጋጀን። በቅድሚያ የህዝብ ጥያቄ የነበረው የኦሮሞ ህዝብ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ የሚነገረውን ነገር ማጣራትና እውነተኛውን ነገር ማስቀመጥ ነበር።
የታሪክ ቅርሶችን፣ መልክዓ ምድሮችን እና ሌሎች ቅርሳቅርሶችን ማሟላት በሚለው የዘመናዊ ሳይንሳዊ ዘዴ ተከትለን የጎደለን ማሟላት ነበር ዓላማችን። በዚህም በመላው የኦሮሚያ ዞኖች፣ አማራ፣ ትግራይ እና ደቡብ ብሄርና ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ተዘዋውረን አጥንተናል። በወቅቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጥናቱን ገብተን እንዳናካሄድ በቀጥታ ከለከሉን።
በብዛት ኦሮሞ እዚያ ስላለ ወደ ክልሉ ሊጠቃለል ነው የሚል እሳቤ ሊኖር ስለሚችልም ይሆናል የከለከሉን። አማራ ክልል አልከለከሉንም። በተለይ ወሎ የጁ ድረስ ሄደናል። ሌላው ቀርቶ ባህርዳር ድረስ ሄጄ ያጠናሁት እኔ ነኝ። ትግራይ በከፊል ፈቅደዋል። በአንዳንድ ወረዳዎች ግን ከልክለዋል። ሌላው ደግሞ የሚዘጋጁት ሰዎች ጉዳዩን የማያውቁና እኛ ካጠናነው ታሪክ በተቃራኒ የሆነ መረጃ ይሰጡን ነበር። ለጥናቱ የማይሆኑ ሽማግሌዎችም ይዘጋጁልን ነበር።
በወቅቱ መረጃው በካሴት ነበር የሚሰበሰበው። በካሴት የተሰበሰበውን ወደ ፅሁፍ እንቀይረው ነበር። ከዚያም በየሦስት ወሩ እንገመግመው ነበር። ያንን ደግሞ ‹‹ኦርጋናይዝ›› የሚያደርግ አካል ነበር። በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናቶች ኢንስቲትዩት በጣም ይረዳን ነበር። ከ100 ዓመት በፊት የተመዘገቡ ታሪኮች ተሰድረው ይገኙ የነበረው እዚያ ነው። በርካታ የኢትዮጵያ ነገስታት በዘመናቸው የገጠማቸውን እያንዳንዱን ገድል ይጽፉ ነበር፤ ይህን ገድል እናነብ ነበር። በተለይም ነገስታት ከኦሮሞ ህዝብ የገጠማቸውን ፍልሚያ ይፅፋሉ። ብዙ ጊዜ ፍልሚያቸውም ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ነበር። የአመፀባቸውንና ከማን እንደተዋጉ ይፅፋሉ።
በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ በጎንደር፣ በኤርትራ ባህረ ነጋሽ እና በአክሱም አካባቢም የነበሩ የታሪክ ክስተቶችን አጥንተናል። ለምሳሌ በአክሱም አካባቢ ‹‹ኦና ነገስት፤ ኦነ ንጉስ›› ይላል። በአንትሮፖሎጂ ትንታኔ መሰረት ቋንቋውንም እናጠናለን። በዚያ አካባቢ ቋንቋው ይነገራል ወይ ብለን እንመረምራለን። እዚያ ያለው ትርጉምና እዚህ ያለውን ትርጉም መርምረናል ተመሳሳይ ትርጉም ያለው ብዙ ነበር።
መቀሌ አካባቢ ሄደናል። ለምሳሌ መቀሌን የሚመግበው ትልቁ ውሃ ኢላላ ይባላል። ኢላላ የሚባል ተራራም አለ። ውሃው የሚመነጨው ከዚሁ ተራራ ነው። ይህን ስያሜ እንዴት አገኘ ብለን እናጠናለን። እነ ዋጅራትን እናጠናለን። እነ ‹‹ኢንጣሎ››ን እናጠናለን። ለምሳሌ ኢንጣሎ ፈንታሎ የከረዩ ጎሳ ከጥንት ጀምሮ በአካባቢው መኖሩን ያሳያል።
ታሪካዊ መረጃዎች አሉ። ለምሳሌ በአክሱም ሙዚየሞች ውስጥ ያሉትን ከኦሮሞ የመሥዋዕት ማቅረቢያ እቃዎች ጋር ያለው እነርሱ አካባቢ በሌላ መልክና ጉዳይ ሲተነትኑት ታየዋለህ። እዚህ ደግሞ ‹‹ኡሬጋ›› ይባላል። በየጁ፣ ወሎና ራያ አካባቢ ያለው በአብዛኛው ከኦሮሞ ጋር ተመሳሳይ ነው። የሚያከብሯቸው በዓላት ሆኑ የሚጠቀሙባቸው እቃዎች ብሎም ቋንቋቸው ተመሳሳይ ነው። የመርሳ አባ ጌትዬ መንግሥት እንዴት እንደተመሰረተና ወደ ጎንደር አካባቢ እንዴትም እንደሄዱ ታሪክ ያስረዳል።
አዲስ ዘመን፡- 12 ሆናችሁ ባደረ ጋችሁት ጥናት የኦሮሞ ህዝብ ወደ ኢትዮጵያ የተስፋፋውበ16ኛ ክፍለ ዘመን ነው የሚለውን ታሪክ በምን ደመደማችሁ?
አቶ አለማየሁ፡– መጨረሻ ያገኘነው በርካታ የተዛቡ ታሪኮች መኖራቸውን ነው የተረዳነው። ኦሮሞ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ ገባ የሚለው
ትልቅ ውሸት ነው። ምክንያቱም ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ኦሮሞ በነገስታትነት መልክ በዚህ አገር ውስጥ ተሳትፎ ነበረው። ከክርስቶስ ልደት በፊት አፄ ፈንታሌ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ የሚል በአክሱም አካባቢ ነግሶ በመጨረሻም ስልጣኑን ለልጁ አፄ ጭላሎ ማስረከቡ በቅርቡ በኢትዮጵውያን ጥናት ተረጋግጧል። ይህ መጽሐፈ ነገስቶች ውስጥ ይገኛል። ስለዚህ ኦሮሞ ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ተሳትፎ ያለው ህዝብ ነው።
አዲ ዘመን፡- እንግዲህ እንዲህ የአንድ ዘር ሐረግ ከሆኑ ለምን ይህ ሁሉ መከፋፈል መጣ ብለው ያስባሉ?
አቶ አለማየሁ፡- እዚህ አገር ውስጥ ከእስልምና እና ክርስትና አምነት መስፋፋት ጋር የተሠራው ትልቅ ነገር ነው። ሦስቱም ትልልቅ ሃይማኖቶች የገቡት ከውጭ ነው። ከክርስቶስ ልደት 1000 ዓመት በፊት የይሁዲ ሃይማኖት ገባ። ቀዳማዊ ሚኒልክ የኩሽን ሃይማኖት አውድሞ የኦሪትን እምነት ተቀበለ የአባቱ የሰለሞን ነው ብሎ። ከ1000 ዓመት በኋላ ኢዛና መጥቶ ክርስትናን ተቀብሎ በአካባቢ የቀረችውን የኩሽ እምነት አጥፍቶ ከለቻውን በአንበሳ እና በመስቀል ተካቸው።
የይሁዲንም እምነት አጠፋው። በእነዚህ ሃይማኖቶች ሁለቱን ህዝቦች መከፋፈል ጀመሩ። ለምሳሌ ኦሮሞ ዘንድ መጥተው አንድ ዋቃ ነው የምናምነው ይሏቸዋል። ሙስሊሞችም መጥተው በአንድ አምላክ አሏህ ነው የምናምነው ብለው ነገሯቸው። ስለዚህ ቀድሞ የደረሰ የእምነቱ ተከታይ ያደርግሃል ማለት ነው።
ከዚያ በህዝቡ ዘንድ መከፋፈልና እርስ በእርስ መፈራረጅ ተጀመረ። ወደ ስድብና አንዱ ሌላውን ማጥላላት ተሸጋገረ። ስለዚህ በታሪክ አንዱ ሌላውን ማጥቃት ጀመረ። በዚህ አገር ሃብት ስላለ በርካቶች መቀራመትና ፍልሚያዎች ነበሩ። በ16ኛው ክፍለ ዘመን የሸዋው ኃይል ገኖ ሌላውን አጥቅቶ ሌላውን አወደመ። በአሁኑ ወቅት አንዳንድ አካባቢዎች የታሪክ ምስክር ሆነው ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡- በእምነቶች መካከል ያለው ሽኩቻ አልፈን አሁን ባለው ሥርዓት ውስጥ ገብተናል። ታዲያ በዚህ ሁሉ መከፋፈል ውስጥ ኢትዮጵያ እንዴት ቀጠለች?
አቶ አለማየሁ፡- ሁሉም ዕድገት ነው። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተደረጉ ፍልሚያዎች ዕድገት ናቸው። ለምሳሌ በምንም ዓይነት ድሮ ሸዋ ጎንደር አገሬ ነው ብሎ አያውቅም ካልተማረከ በቀር። ጎጃሞች ንጉስ ተክለሃይማኖት ኢምባቦ ላይ ተማርከው ነው በብዛት ወደ አዲስ አበባ የመጡት። ግን በሂደት በጋብቻ እና በትምህርት ሰዎች ይገናኙ ነበር። ገዢዎቹ አይገናኙም ግን ህዝብ አብሮ ነው ያለው። በገዳ ሥርዓት ውስጥ ሌሎች ህዝቦችም አሉ። በባህላቸው ውስጥ ኦሮሞ ውስጥ የሚፈፀም ባህል ሌላ ቦታ ሲፈፀም ታያለህ።
ባሪያ ንግድ ተብሎ ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላ ሥፍራ ይሄዳሉ። በዚህ ሂደት ሁሉ ሰዎች ይገናኛሉ። በተለይም በንጉስ ሚኒሊክ እና ጎበና ዳጬ የተፈፀሙ የማዋሃድ ሥራዎች ትልቅ ለውጥ አምጥቷል በዚህ አገር ትልቅ ‹‹ሪቮሊሽን›› ነው። ምንም እንኳን ሰዎች ባያከብሩትም ተደርጓል፤ አንድነት ተፈጥሯል በሚኒሊክ እና ጎበና ዳጬ።
ለምሳሌ በየጁዎች አንድ ወቅት ትልቅ ነገር ተደርጓል። የጁ በቀጥታ ጎንደርን ተቆጣጠረ። የየጁ ኦሮሞዎች የራሳቸው ሃይማኖት ጥለው ከክርስቲያኖች ጋር ተዋህደዋል። ኤርትራ፣ ትግራይና ከፊል ጎንደርን ይዛ የነበረችው ኢትዮጵያ የጁና ወሎን አጠቃለለ፤ እየሰፋም ሄደ። በመቀጠል አጼ ቴዎድሮስ የራሳቸውን ድርሻ ሞከሩ ብዙም አልተሳካላቸውም። ከአፄ ቴዎድሮስ እስር ቤት የወጣውም አፄ ሚኒሊክ መጣና በሰፊው ሠርተዋል።
አዲስ ዘመን፡- ነገስታት እንጂ ህዝቡ አብሮ የኖረ በቦታ፣ ጊዜ ያልተነጣጠለ ማህበራዊ ሕይወት የተሰናሰለ ነው ብለዋል። ታዲያ አሁን በሚስተዋሉ ችግሮች ህዝቡን ይለያየዋል ብለው ያስባሉ?
አቶ አለማየሁ፡- በፍፁም ሊደረግ አይችልም። ለምሳሌ እኔ ኦሮሞ ነኝ። ስለኦሮሞ መብት ልናገር እችላለሁ። ይህ ማለት ግን አማራውን፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ሱማሌን ትግሬውን ወይንም ሌላውን ብሄር እጠላለሁ ማለት አይደለም። ግን ‹‹ናሽናሊዝም›› የሚያዝበት ወግና መንገድ አለው።
እነዚህን ህዝቦች የምወድበት ምክንያት አለኝ። ግን አንድ ማወቅ ያለብን ነገር አለ። የየግላችን ቤት አለን። በቤትህ ማዘዝ እችላለሁ፤ አንተም ትችላለህ፤ የግል ቤት አለን። ግን የጋራ ከተማ አለን አዲስ አበባ ማለት ነው። ልክ እንደዚሁ አገር የጋራ መሆኗን መዘንጋት የለብንም፡፡ መለያየትም አይቻልም። አይደለም ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካ የጋራ ናት እያልን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ምናልባት አሁን በአገራችን የምናስተውላቸው ጉዳዮችና ክስተቶች አያስፈሩም?
አቶ አለማየሁ፡– ይህን ተው ይቀራል! ይህ ሥርዓት ያጣ ናሽናሊዝም ነው። ልጓም ያስፈልገዋል የምለው ይህንን ነው።
ከናሽናሊዝም ወደ ናሽናል ቾቨኒዚም እንዳይቀየር መጠንቀቅ ይገባል። ቀኝ አክራሪዎች በኢትዮጵያ ውስጥ አምና ካቻምና በፊት ከሰሜን አካባቢ በመጡ ሰዎች ታይቷል። በፖለቲካ በኢኮኖሚ በሁሉም ነገር መታየት ጀመረ። በዚህ በደጅህ አዛዥ ነኝ ማለት ተጀመረ። በሁሉም ነገር ብቃት አለኝ ተባለ።
ይህ ደግሞ አይቻልም ተባለ። በነገራችን ላይ አማራ እና ኦሮሞ በዚህ አገር ፖለቲካ ላይ ወሳኝ ናቸው። ፍልሚያው የኢኮኖሚና ፖለቲካ ሴክተሮች ማለዘብ እንጂ ያልሆነ ፉክክር ውስጥ መግባት የለባቸውም። ናሽናሊዝም የሚያስፈልገው ለትምህርት መስፋፋት፣ ለኢኮኖሚና፣ ለእግር ኳስ ቡድን ጨዋታ እንጂ ናሽናሊዝም ሌላ ገጽታ ካለው አደጋ ነው። ሂትለር ምርጥ ዘሮች እኛ ነን ብሎ ሌሎች አውሮፓውያን ዕድገት አልጨረሱም ብሎ ሲነሳ ነው ፍልሚያ የተጀመረው። ዮጎዝላቢያ መፈረካከስ የገጠማት እና ስድስት ቦታ የተፈረካከሰችው ከዚሁ የተነሳ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ባህልና ሃይማኖት ተደበላልቆ ብዙ ነገሮች ፉክክር መልክ እየያዙ ነው፤ ታዲያ ይህ ፉክክር ለኢትዮጵያ አደጋ አያመጣም?
አቶ አለማየሁ፡– ይህ ወግ መያዝ አለበት። ለምሳሌ ኦሮሞ የራሱ የገዳ ሥርዓት ነበረው። አንተም ኑር ሌላውም መኖሩን እወቅ ነው የሚለው። ሌሎችን የማጥፋት ፍላጎት የለውም። አካሄዱም ዴሞክራሲያዊ ነው። ሌላው ቀርቶ በጎሳው ውስጥ የራሱ አካሄድና ስርዓት አለው። ወደ ሥልጣን ለመምጣት በ21 ዓመት ሂደት ማለፍ አለበት።
በገዳ ውስጥ እንኳን ንግግር አዋቂ፤ በህብረተሰቡ ተቀባይነት ካለህ፣ መልካም ስነምግባርና በቂ ሃብት ሲኖረው ነው ስልጣን የሚይዘው። ገዳ ኮትኩቶ ነው የሚያሳድገው። በመሰረቱ ወደ ገዳ እንመለሳለን ማለት ሠላማዊ የሆነ የፖለቲካ የሥልጣን ሽግግር መጣን ማለት ነው። በዓለም ላይ ስልጣን በምርቃት ተቀብሎ በምርቃት ከስምንት ዓመት በኋላ ስልጣን የሚያስረክበው ገዳ ብቻ ነው። ይህን የመሰለ ሠላማዊ የስልጣን ሽግግር አለ። በአካባቢያችን ሁላችንም አንድ የሚያደርገን ባህል አዳብረን የግጭት ምንጮችን ማድረቅ ነው።
ጥሩ እሴቶችን ወደ መድረክ ማምጣት ያስፈልጋል። ለዚህ ኢንዱስትሪያሊስትና ካፒታሊስት ማህበረሰብ የሚመጥን አስተሳሰብና አሠራር መተግበር ያስፈልጋል። ከአሁን በኋላ የገዳ ሥርዓቱንም የሚመራው የተማረ ሰው መሆን አለበት። የአገር ውስጥ ሊህቃን እና ፖለቲከኞችም ለአገር በሚበጅ ነገር ላይ መመካከር ይጠበቅባቸዋል። የአንድ ጎሳ ወይንም ብሄር የበላይነት እንዳይነግስ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
ከዚህ በዘለለ ደግሞ ራቁቱን የሚኖረውን ሰው ዘንድ ቀረብ ብሎ መሥራት ይገባል። ለምሳሌ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ራቁት ያሉት ዜጎች ሁሌ በዓለም ካሜራ እይታ ውስጥ የሚገቡትን ሄዶ ማልበስ፣ ማገዝና መንከባከብ ይገባል። ካልሆነ በታሪክ ያስጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን የሚስተዋለው ፉክክርስ የኢትዮጵያን ህዝብ በሙሉ ያቀፈ ነው?
አቶ አለማየሁ፡– አላቀፈም። የአብዛ ኛው የኢትዮጵያ ህዝብ እውቀትና ግንዛቤ ያላገናዘበ ነው። ለምሳሌ በአዲስ አበባ ላይ ያለውን እውቀት ማገናዘብ አልፈለጉም። ለምሳሌ ንጉስ ሚኒሊክ ወደ አዲስ አበባ መጥተው እንጦጦ ላይ ሰፈሩ። ከዚያ በአካባቢው ያሉትን አስተዳዳሪዎች አሳም ነው አብረው መኖር ጀመሩ።
አዲስ አበባና አካባቢዋ የ145 ዓመት ታሪክ ነው ያላት። በዚህ አካባቢ የነበሩ ሰዎች ነበሩ። ታዲያ አሁን ያለውን ክርክር ስናይ ትክክለኛ መረጃ ላይ ያለመመስረትና ከእውነት መሸሽ ነው። ከዚህ በዘለለ ቀደም ሲል ነዋሪዎች ነበሩ። ግን ህዝብ አልነበረም ጫካ ነው ብሎ መከራከር አግባብ አይደለም። 140 ዓመት ቅርብ ጊዜ ነው። ስለዚህ እውነታውን መካድ አያስፈልግም። እኔ በፖለቲከኛ እይታ አትፈርጀኝ ግን ታሪክ መደበቅና ሁኔታው መረሳት የለበትም። ከተማዋ እንደዚህ አላደገችም ነበር።
እኔ የተማርኩት ኤካ አካባቢ ነው። ከፍተኛ 16 ነበር የከተማዋ ዳር። አሁን ተስፋፍቷል። እዚህ አካባቢ ነዋሪ ኦሮሞ ነበር። ሚኒሊክ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በፊት የነበሩ ጎሳዎች ኦሮሞዎች ነበሩ። ይህን በታሪክ ውስጥ የሆነ ክስተት መዘንጋት የለበትም። ከተማው ሲስፋፋ ሁሉም እየመጣ እያደገ መጣ። ግን ቀድሞ ኦሮሞዎች መኖራቸውን መካድ አይገባም፤ እውቅና መስጠት ነውር የለውም። በነገራችን ላይ በአሜሪካ ውስጥ ሬድ ኢንዲያን እየተፈለጉ ክብር እየተሰጣቸው ነው። በአውስትራሊያ ውስጥ አቦርጂነየስ እየተፈለጉ ይቅርታ እየተጠየቁ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይቅርታ መጠየቅ ቢያስፈልግ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለተፈጠረው የታሪክ ዝንፈት ኃላፊነት ወስዶ ይቅርታ የሚጠይቀው ማነው?
አቶ አለማየሁ፡- የፊውዳል መሪዎች ካሉ ይጠየቁ። አሁን ያለው መንግስት በራሱ ጊዜ ለተፈጠሩ ችግሮች ይቅርታ ይጠይቅ። ያለፈው መንግስትማ አልፏል። ይቅርታ መጠየቅ ወንጀል አይደለም። የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም አለበት፤ እያደረገም ነው፤ ማድረግም አለበት። ይህ መብት ነው። ባህልና ማንነቱ እንዳይነካ መጠየቅ አግባብ ነው። በመሰረቱ የምከራከረው ለኦሮሞ ብቻ አይደለም።
በጎጃም ሆነ ጎንደር ወይንም መቐለ የህዝብ ጥቅምና ህልውናቸው ይከበር ነው የምለው። የማወራው የፖለቲካ ጥላቻ አይደለም። አርሶ አደሮች ባለጊዜዎች አፈናቅለውን እኛ ለጥበቃ ዳርገውናል ነው የሚሉት። ይህን በሚገባ ማገናዘብና መብት ማክበር ግዴታ ነው። ኢትዮጵያ የጋራ ሃብት ናት። ግን ደግሞ ያለንን ሃብት በቅጡና በመከባበር መጠቀም ይገባናል። በተለይ ደግሞ አማራ እና ኦሮሞን ለማጋጨት የሚደረገው ጥረት ዋጋ የለውም። በሥጋ ሆነ በደም አንድ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የኦሮሞ ህዝብን ታሪክ ስናነሳ የገዳ ሥርዓትንና ኢሬቻን ማንሳት ግድ ይለናል። በዚህ ላይስ ምን ይላሉ?
አቶ አለማየሁ፡- ገዳ ማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ሥረዓቶችን ያቀፈ ነው። በአውሮፓ ዘመናዊ መንግስታት ሲመሰረቱ የመሰረቷቸው ተቋማት ቀደም ብሎ በገዳ ውስጥ አለ። ገዳ የራሱ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ መዋቅር አለው። ጨፌ አለው። ከዚያ ቀጥሎ አባ ሙዳ ወይንም የቃሉ ተቋም አለ። አባቦኩ ወይንም አባታዊ አስተዳደር ማለት ነው። ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ጋር የሚስተካከል ስልጣን ያለው ማለት ነው።
ከዚያም ሥራ አስፈፃሚ አካል አባ ገዳ አለ። በእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሌሎች ዘርፎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ በሃይማኖት መሪዎች የሚመራው አንዱ ኢሬቻ ነው። አያንቱም አለ። ግን እያከበርን ያለው ኢሬቻ ብቻ ነው። በቃሉ ኢንስቲትዩት ውስጥ ኢሬቻ ማለት የምስጋናን ቀን በጋራ ማክበር ማለት ነው። ኢሬቻ በየዘመኑ እየተለወጠ እና እየተሻሻለ ነው። እኔም ልጅ ሆኜ በየሠፈራችን እናካሂድ ነበር። በቀጣይም እየተሻሻለ የሚመጣ በዓል እንደሚሆን አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ኢሬቻ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሄካድ በዓል ነው። ከዚህ የተለየ ገጽዎችና ያልተነገሩ ታሪኮች ይኖሩ ይሆን?
አቶ አለማየሁ፡- በኦሮሞ ህጎች ውስጥ ሁሌ ነዋሪ ህጎች አሉት። እነርሱም የእግዚአብሄር፣ የምድር፣ የአባት፣ የእናት፣ የቱሉና የመልካ ህጎች ናቸው። እነዚህ የማይቀየሩ ህጎች ናቸው። በዚህ ውስጥ ደግሞ በርካታ ትንንሽ ህጎች ይገኛሉ። ምድር የተፈጠርክባት ስለሆነ በላይዋ በልተህ የምትቀበርበት ስለሆነ ተንከባከባት ነው የሚለው የምድር ህግ። እናትና አባት ወልደው ስለሚሳድጉ እነርሱን ማክበር እንደሚገባ ነው ሕጉ የሚደነግገው።
ምድር ክብር ናት ውሃ አለባት። እግዚአቤሄር ውሃን የፈጠረው ለፍጥረታት ሁሉ ነው። መልካ ሁሌም የተከበረ ነው። ቱሉ ማለት ደግሞ ተራራ ነው። ተራራ ጫፍ ላይ ሁሌም ዝናብና እርጥበት አለ። በተራራ ጫፍ ላይ መላዕክቶች የሰፈሩበት መልካም መንፈስ ያለበት ነው። ለዚህም ኢሬቻ እንዲከናወንበት ይደረጋል። ከተራራዎች በታች ደግሞ ምንጭ አለ። ስለዚህ ምስጋና ፀሎት ይደረጋል።
ተራራዎች ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆኑ ለዓለም ታላላቅ ሃይማኖቶች መነሻ ቦታ ናቸው። በእስልምና ብትሄድ ቢላል አራፋት ተራራ ላይ ወጥቶ ነው መጨረሻ አዋጅ ያወጀው። ሙሴም ከተራራ ላይ ሆኖ ነው አስርቱን ትዕዛዛት ይዞ መጥቶ ለወገኖቹ የሰጠው። እየሱስ ክርስቶስም ከሃዋርያት መጨረሻ ስንብት ፀሎት ያካሄደው በተራራ ላይ ነበር። በኦሮሞ ባህል ተራራዎች የተከበሩ ናቸው። ስለዚህ ከኦሮሞ ጋር ብቻ ሳይሆን ከዓለም ህዝብ ጋር ያለውን ትስስር ማሳወቅ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ብቻ ነው?
አቶ አለማየሁ፡- ኢረቴቻ ሁሉንም የዓለም ሃይማኖቶች ሁሉ ያቅፋል። ምስጋና የማያቀርቡ የዓለም ሃይማኖቶች የሉም። ሁሉም ሄደው ምስጋና ቢያቀርቡ ኦሮሞ ያቅፋቸዋል። የኦሮሞ ቄሶች እየመጡ ለምለም ሳር ይዘው ፈጣሪን ይለምናሉ። እስላሙም ‹‹አሏህ›› የሚሉት እኛ ‹‹ዋቃ›› የምንለው ነው። ልዩነቱ ዶክትሪን ነው። ኢሬቻ ወደፊትም የዓለም የምስጋና ቀን መሆን ያለበት ነው።
ገዳ ስርዓት በተለያዩ ቦታዎች ወድቆ ነበር። አሁን ኢሬቻ ጎትቶ አንስቶት በዓለም ዘንድ አሳወቀው። የዓለም ህዝብም ይህማ ጥሩ ነው ሲል ተቀበለው። ገዳ ደግሞ በሂደት በውስጡ ብዙ ነገሮችን ያሳውቃል። ከጥንት ኢምግሬሽን በፊት ‹‹ኮሎ ጋሉ›› በሚል በገዳ ሥርዓት ይተገበራል። ጉዲፈቻም ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ለሺ ዘመናት በሚገባ ያደገና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሰዎች ኢሬቻ ሃይማኖታዊ ይዘት አለው ይላሉ እውነት ነውን?
አቶ አለማየሁ፡- ትክክል ናቸው። ምክንያቱም ገዳ ባህልና ሥርዓት ነው። ባህሉ ሁሉንም ይዟል። ሃይማኖት እኮ ትንሽ ነገር ናት። ኢሬቻ በገዳ ስርዓት ውስጥ ያለ አንድ ነገር ነው። ባህል እጅግ በጣም ሰፊ ነው። ሃይማኖቶች ሁል ጊዜ የባህል ውጤት ናቸው። ሃይማኖት የሚሆነው የምታመሰግነው አምላክ ነው። ከምትለብሰው ልብስ፣ ከምትመገበው ምግብ፣ የማልቀስ፣ ዘፈን ዘይቤን ጨምሮ ሁሉም ባህል ነው።
ኢሬቻም ባህል ነው። ወንዝ ወርደን፣ ቄጠማ ይዘን፣ ተራራ ወጥን ስንሄድ ባህል ነው። ፈጣሪ ዘንድ ሲደርስ ነው ሃይማኖት የሚሆነው። ክርስቲያኑ ቤተክርስቲያን ሰርቶ የሚያወድሰው የሚዘምረው ባህል ይሆንና ወደ ፈጣሪ ሲመጣ ሃይማኖት ይሆናል። በባህል ውስጥ ያለ የሃይማኖት ይዘት አለ። ሁሌም ባህል የበላይ ነው። ግን ሃይማኖት በባህል ውስጥ ነው። ነገር ግን በባህል ውስጥ ሆኖ ሃይማኖት ባህሉን ይለውጠዋል። ስለዚህ ኢሬቻ የምስጋና ቀን ነው። ኢሬቻ ኦሮሞ ከሌሎች ጋር ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት አቃፊ በዓል ነው።
አዲስ ዘመን፡- የዓለም ህዝብ እንዲያከብር የሚገባ ከሆነ ትኩረት እንዲያገኝ ምን መደረግ አለበት?
አቶ አለማየሁ፡- በዚህ ዘመን ቱሪዝም ትልቅ የኢኮኖሚ ምሰሶ ነው። ለምሳሌ ከመስቀል ጀምሮ በርካታ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት ወቅት ነው። በመሆኑም መንግስት፣ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩበት ይገባል። የበዓሉ ታዳሚዎችም ለበዓሉ በሚመጥን መንገድ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።
ከዚህ ዘመን እሳቤ እና አረዳድ ጋር የማይመጥኑ ተግባራትን ማከናወን የለባቸውም። ይህ በዓል በጋራ ምስጋና የሚቀርብበት እንጂ ግለሰባዊ ፍላጎቶችና አምልኮት የሚካሄድበት ባለመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። በኢሬቻ ውስጥ ያለውን እሴት አገራዊና ዓለም አቀፋዊ እሴት እንዲሆንም መረባረብ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 24/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር