ወርሀ መስከረም ትልልቅ ብሔራዊና ህዝባዊ በዓላት የሚከበሩበት ወር ነው። በወሩ መባቻ ከሚከበረው የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ የአዲስ ዓመት በዓል ባለፈ፤ በሀድያ ብሔር ሆዴ መስቀላ፤ በወላይታ ጊፋታ፤ የአዲስ ዓመተ ማብሰሪያ፤ እንዲሁም የመስማማት፤ የአንድነት የእርቅና የምስጋና በዓል የሆነው ኢሬቻ ይከበሩበታል። ከዚህ በተጨማሪም፤ ሀይማኖታዊ መሰረትና ባህላዊ ይዘት ያለው የመስቀል በዓልም የሚከበረው እንዲሁ በመስከረም ወር ነው።
እነዚህ ሁሉ በዓላት ከሌሎች ለየት የሚያደርጋቸው ደግሞ ከቤት ውጭ ወይም በአደባባይ መከበራቸው ነው። አሁንም ከቤት ውጭ መከበራቸው ብቻ ሳይሆን፤ የብዙዎች፤ ምናልባትም የሚሊዮኖች የጋራ በዓላት መሆናቸውና የተለያዩ ባህላዊ እሴቶች የሚንጸባረቁባቸው መሆኑ ጭምር ለየት ያደርጋቸዋል።
እናም በጥቂቱ በአስራዎችና በመቶ ሺዎች ተሰባስበው፤ ሲበዙ ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝ|ቦች በአደባባይ ወጥተው የሚያከብሯቸውና ስሜታቸውንና ምኞታቸውን የሚገልጹባቸው በዓላት ናቸው።
የአገራችን ህዝቦች እንደየአካባቢያቸውና አግባባቸው በበዓላቱ ለአንድም ቀን ይሁን ለቀናት በአደባባይ ተሰባስበው ክብረ በዓላቱ ላይ የሚደምቁባቸውን አልባሳትና መዋቢያዎች ተጎናጽፈው፤ ስርዓትና ምግባር አክብረው የመዐልት ክንዋኔዎችን በቀን በጸሐይ፤ የምሽት ክንዋኔዎችን ደግሞ በጨረቃና በመብራት ደምቀው ሲያከብሯቸው ለተመለከተ እውነትም ኢትዮጵያ የበርካታ መንፈሳዊ ሀብቶች ባለቤት እና የብዙ ጸጋዎች መገለጫ እንደሆነች መመስከር ይችላል።
በተለይ፤ በኢትዮጵያ በወረሀ መስከረም ይሁን በሌሎች ወራት በአደባባይ የሚከበሩ ብሔራዊና ህዝባዊ በዓላት ለበርካታ ዘመናት ሲከወኑ ሌላው መገለጫቸው ያለአንዳች ሁከትና ብጥብጥ በመሆኑ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም ወደ ቤቱ የሚመለስባቸው ናቸው። እናም፤ የኢትዮጵያውያን በበዓላት፤ የፍቅር፤ የአብሮነት የሀገራዊና የህብረ ብሔራዊ ስሜት መገለጫዎች በመሆናቸው ከህጻን እስከ አዋቂ፤ ከጎበዝ እስከ አቅመ ደካማ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በአብሮነት የሚከውኗቸው መገለጫም መድመቂያም ሀብቶች ናቸው።
ይሁን እንጂ፤ ከጥቂተ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው አለመረጋጋት በነዚህ ክብረበዓላትና በርካታ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው አውዶች ላይም መታየትና መከሰት ጀምረዋል። በመሆኑም፤ አንዳንድ ጊዜ የአደባባይ ክብረ በዓላት ስጋት እያንዣበበባቸው፤ በዓል አክባሪው በፍርሀትና በውጥረት ውሎ የሚመለስባቸው ሲሆኑ ተስተውለዋል።
እርግጥ ነው፤ ብሔራዊ፤ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ክብረ በዓላት ሲከበሩ ከሁሉም በላይ የህዝቡን ደህንነትና ጸጥታ የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ የተሰጣቸው የጸጥታ ኃይሎች ይመደባሉ። ይሁን እንጂ፤ ትልቁ ኃላፊነት የሚወቀድቀው ደግሞ በራሱ በዓሉን ለማክበር በወጣው ታዳሚ ትከሻ ላይ መሆኑ አይጠረጠርም። እናም፤ ህዝቡ የራሱን ደህንነትና የአካባቢውን ጸጥታ በራሱ ያከብራል፤ ያስከብራልም።
በዚህ ረገድ በያዝነው ሳምንት መገባደጃ ላይ የኢሬቻ ዓመታዊ ክብረ በዓል በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል በሆራ አርሰዴ ቢሾፍቱ እንደሚከበር ይታወቃል። ኢሬቻ የምስጋና ቀን ወይም በዓል ነው። በክረምቱ መግባትና በወንዙ መሙላት ሳይገናኙ የከረሙ ዘመድ አዝማድ፤ በወንዙ መጉደልና በውሀው መቀነስ ደግሞ በህይወት ቆይተው በአይነ ስጋ ሲገናኙ ለፈጣሪያቸው “እንኳን ለዚህ አበቃኸን” ሲሉ ምስጋናቸውን የሚያቀርቡበት በመሆኑም በዓሉ ፍቅር የሚገለጽበትና የሚሰበክበት፤ አብሮነት የሚጎላበትና አንድነት የሚደምቅበት፤ ሚሊዮኖች ዘር ቀለም ሳይለዩ፤ ጾታና እድሜ ሳይቆጥሩ በጋራ የሚሳተፉበት ነው።
በተለይ፤ የዘንድሮው የኢሬቻ ክብረ በዓል በሁለት የተለያዩ ቦታዎች በተከታታይ ቀናት የመከበሩን ያህል አፈጻጸሙን በተመለከተ ቀደም ሲል የተቋቋመው አስተባባሪ አስፈላጊውን ዝግጅት ስለማድረጉ ገልጿል። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በሚከበረው በዓል ላይ እስከ ስድስት ሚሊዮን ህዝብ እንደሚሳተፍ ይጠበቃል። ዋናው ጉዳይ ይህ ሁሉ ህዝብ በሰላም ወጥቶና የወጣበትን በዓል በፍቅርና በአብሮነት እክብሮ በሰላም ወደ ቤቱ እንዲመለስ የማድረጉ ነገር ነው። በማግስቱ በሆራ ቢሾፍቱ የሚከበረውም በዓል ተመሳሳይ ሁኔታ ይጠበቃል።
በመሆኑም፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው፤ አገራዊና መንግስታዊ ኃላፊነት ያለባቸው የፖሊስ፤ የመከላከያና የደህንነት አካላት ለዚህ ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ ተገልጿል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የአባገዳ ፎሌ ወጣቶች ለዚሁ ተብሎ ተመልምለውና አስፈላጊውን ስልጠና ወስደው በማስተባበር፤ በመደገፍና ስርዓት በማስከበር አገልግሎት ለመስጠት እንደተዘጋጁ ታውቋል። እንዲህ ዓይነቱ የተደራጀና የጉዳዩን ባለቤት በቀጥታ ያሳተፈ የጸጥታና የደህንነት ማስከበር ተግባር የሚደገፍና ይበል የሚሰኝ ነው።
አዎን ወጣቶችና በዚህ መልኩ ተመልምለው ኃላፊነት የሚሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ግዴታን የመወጣት ከፍተኛ ትጋት አላቸው። እነርሱ የሚሰሩት በአብዛኛው የማግባባት የማማከርና አገልግሎት የመስጠት ተግባር በመሆኑ በመሰሎቻቸውም ሆነ በአጠቃላይ በታዳሚው የመደመጥ አቅማቸው ከፍተኛ ነውና ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው። እናም በህዝቡ መሀል ሆነው ከሚሰጡት ሰብዓዊና ማህበራዊ አገልግሎት በተጨማሪ አፍራሽ ተልዕኮ ይዘው እንዲህ ዓይነቱን የህዝበ ደስታና አንድነት ለማወክ የሚንቀሳቀሱ እኩይ ኃይሎች ከተገኙ በቀላሉ ለማጋለጥና ለሕግ አስከባሪዎች አሳልፎ ለመስጠት ዓይነተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል።
ከሁሉም በላይ ግን በዓሉ የህዝብ በዓል ነውና በበዓሉ የሚሳተፈው ከአገራችን ብሔር ብሔረሰቡችና ህዝቦች የተውጣጣ፤ ከዓለም ማህበረሰብ የተገኘ፤ ከከተማም ከገጠርም ነቅሎ የወጣው ህዝብ የሚሰባሰብበት በመሆኑ ህብረተሰቡ የራሱን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ይኖርበታል።
በዚህም ህዝቡ በእያንዳንዱ እርምጃና እንቅስቃሴው የሚያጋጥሙትን የተለዩ አዝማሚያዎች በአጽንዖት በመከታተልና ለጽጥታ ኃይሎች መረጃ በመስጠት የራሱን ደህንነት ይጠብቅ። በተናጠልም ይሁን በጋራ የተለየ እንቅስቃሴ የሚያሳዩና የሚያጠራጥሩ አካላት ሲያጋጥሙ ደግሞ በአቅራቢያው ላሉ የጸጥታ አካላት በማሳወቅና ለሕግ አሳልፎ በመስጠት የራሱን በዓልና ደህንነት ራሱ የመጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል እንላለን!
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2012