ሰላም የሁሉ ነገር ዋስትና ነው። ሰርቶ የመለወጥ፣ ወልዶ የማሳደግ፣ ወጥቶ የመግባት፣ ዘርቶ የማፍራት በአጠቃላይ በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ተግባር ውስጥ ከምንተነፍሰው አየር ያልተናነሰ ዋጋ አለው። ሰላም ከሌለ ነገ የለም። ስለነገ ማሰብም ማቀድም የሚቻለው በሰላም ውስጥ ነው። ስለ ሰላም አስፈላጊነት በዚህች በተወሰነች ገፅ ዘርዝሮ መጨረስ ፈፅሞ የማይቻል ቢሆንም እንደ ሀገር ግን መግባባት የሚገባን ጉዳይ ለመሆኑ ደግሞ ጉንጭ ማልፋት አይቻልም፤ አይገባምም።
ሰላም ለሁሉም ፍላጎታችን መሳካት መሠረት ነው። ያለ ሰላም ዕቅዶቻችንንም አገራዊ ራዕያችንንም ከግብ ለማድረስ አንችልም። ሰላም ማጣት የሚያስከፍለው ዋጋ እንደዋዛ አይታይም። የሰላም እጦት ሕይወትና ንብረትን በማሳጣት ብቻ የሚወሰን አለመሆኑን እያየን፤ በህሊናችንም እያብሰለሰልነው እንገኛለን። በመሆኑም ሰላም ያጣ ሕዝብና አገር ማንነቱንና ክብሩን እንደሚያጣ የአለም ተሞክሮ በግልፅ እያሳየን ነው። የውርደት ማቅ እንደሚያለብስ፣ ለተመጽዋችነትና ለእንግልት እንደሚዳርግ የእኛም የኋላ ታሪክ ምስክር ነው።
ለሰላም ሳንካ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመነጋገርና በመደማመጥ መፍትሔ ከማግኘት ይልቅ በበሬ ወለደ ወሬዎች ሳቢያ ዜጎችም ሆኑ ኢትዮጵያም እንደ ሀገር እየተፈተነች ነው። ለግጭትና ለጭቅጭቅ በማያበቁ አጀንዳዎች አንዱ ሌላው ላይ ጦር እንዲያነሳ የሚደረግበት ነውረኛ ጊዜ ላይ መድረሳችን ደግሞ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን አጥፊም ጭምር ነው።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደምናየው የግጭቶች ምንጭ ተብለው የሚጠቀሱ ጉዳዮች ውሀ የሚቋጥሩ አለመሆናቸው ደግሞ ግርምት ያጭራል። አንገትንም ያስደፋል። እንደ ሕዝብ፣ እንደ አገር እንዲህ ያለውን ክፋትና ነውር ከየት ተማርነው? የሚያሰኙ ጸያፍ ድርጊቶች በየመንደራችን እና ቤታችን ሳይቀር እያየን ነው። ነገን የማያስመኙ፣ ተስፋን የሚያሳጡ ክፋቶች የዕለት ዜና እወጃ ሊሆኑ ደግሞ አይገባም። ሊቆሙ ይገባል።
አንዱ በሌላው ወገኑ ላይ እንዲነሳበት ጥቂት ክፉ ጠንሳሾች የሚያራግቡት ወሬ ለኢትዮጵያችን አደጋ እየሆነ ነው። ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› እንደሚለው ተረቱ በወሬ የሚነዳው ቤት ይቁጠረው። ምክንያታዊነት ጠፍቶ አይናችን የተጋረደ እስኪመስለን ድረስ በማህበራዊ ሚዲያ ተፈጥረው እኛን ሊያጫርሱ ባልተገባ ነበር። ለእነዚህ ጉዳዮች እጅ ከመንሳት ይልቅ ወግድ! ልንል ይገባናል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ጊዜው አሁን ነው።
መልካም አጋጣሚዎችን በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ እኔ ብቻ ከሚል እሳቤ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› እንዳለችው እንስሳ በየቦታው በተቧድኖ የሚደረጉ ግርግሮች ሰላምን በማወክ ለውድቅት እያንደረደሩን ነው። ጨዋነትን በመቃረን የራስ ፍላጎትን ለመጫንና ለማስተግበር ማሴር እየተበራከተ ነው።
አንዱ ሌላውን ችሎና ተጋግዞ፣ ያለችውን ተቃምሶ ይኖር የነበረውን የኅብረተሰብ ክፍል፣ ያለፍላጎቱ በመጎትጎትና በማስገደድ ጭምር የሚፈጸም ጥቃት እየባሰበት ሲመጣ እያየንም እየሰማንም ነው። ግን ደግሞ አንድ ሆነን አልታገልነውም። ዳር ሆኖ እሳት መሞቅ አይቻልም፤ እሳቱ የማይነካው የለምና።
በግጭት ያተረፉ አሉ ብሎ መደምደምም አይቻልም። የግጭት ነጋዴዎች ግን ለልጆቻችን ነገን ለሚያስናፍቁን እንቦቅቅላዎቻችን፣ ለወጣቶችና ጎረምሶቻችን፣ ለቅርሶቻችንና ለመከበሪያ ማንነታችን ቦታ የሌላቸው በሰው ቁስል እንጨት የሚሰዱ፣ በሰው ሲቃ የሚንደላቀቁ የደም ከበርቴዎች እንደሆኑ ብንገነዘብ የሚያጣላን ችግር ምንኛ ባነሰና በጠፋ ነበር።
ተወደደም ተጠላ በለውጥ መንገድ ላይ በኩራት ለመራመድ የኢትዮጵያችን ሰላሟ መጠበቁ ግድ ነው። ጥያቄ አለኝ፣ ችግር ደርሶብኛል ተጎድቻለሁ የሚለው አካል ሁሉ ለሚያነሳው ጉዳይ ምላሽ መስጠት የሚጠበቅበት አካል ኃላፊነቱን በሐቅና በአግባቡ በመመለስ ከግርግርና ካለመተማመን የፀዳ ማኅበረሰብ በመፍጠር ችግሮችን የመፍታት አቅም ማዳበር አለበት። ለዚህ መተባበርና መነሳት የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዳየነው የአገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት አባቶች አባገዳዎች ያበረከቱዋቸው አስተዋጽኦ እንደ ምሳሌ የሚወሰድና ሽማግሌ አያሳጣን ብለን እስከማወደስ የደረስንባቸውን የመረጋጋት ሥራ ሠርተዋል።
ነገር ግን ካለው ችግር አንፃር አሁንም በየባህሉና በየሃይማኖቱ አንቱ የተባሉ ሽማግሌዎች ተግባር የተገኘው መረጋጋት በአግባቡ መጠቀም ካልቻልንና በሰበብ አስባቡ ለግጭትና ለልዩነት በር የሚከፍቱ አጀንዳዎችን ይዞ በመምጣት አንፃራዊውን ሰላም መልሶ የሚበርዝ ከሆነ የሽምግልና ትርጉሙ አልገባንም ማለት ነው። ደግሞም እዚህም እዚያ ለሚከሰቱ ግጭቶች ሁሉ ሽማግሌዎችን እያፈላለጉ መዝለቅ አይቻልም። ዜጎች ራሳቸውን መግራት፣ እንዴት ተባብሮ መኖር እንደሚገባን በማሰብ ካልተራመድን አገርን በጋራ ለማራመድ ይቸግራል።
ስለሰላም በተግባር የሚያስተምር ጠፋ እንዴ? የሰላምን አስፈላጊነት ለመረዳት ከእልቂታችን መማር አይጠበቅብንም። እንደሞኝ ከራሳችን ሳይሆን ከሌሎች ለመማር የሚያበቁ በርካታ እልቂቶችን በአይናችን አይተናል። እያየንም ነው። ስለዚህም የሰላም መምህራን ሊበራከቱልን ይገባል። በልጆቻችን ዘንድ ስለፍቅርና አንድነት፣ መልካምነትና መተሳሰብን በማስረጽ የነገ ሕይወታቸው እንዲያበራ በማድረግ በኩል ወላጆች፣ ጎረቤትና ሰፈር አድባሩ አለሁ ይመለከተኛል ሊል ይገባዋል። ጊዜውም አሁን! ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2012