እኛ ኢትዮጵውያን ጨዋነታችንን፣ ሰው አክባሪነታችንን፣ ጀግንነታችንን ዓለም የሚያደንቅልን መልካም ዕሴቶቻችን ናቸው። ሃቀኝነታችን፣ እንግዳ ተቀባይነታችንና በአብሮነት ላይ የተመሰረተ ማህበራዊ ኑሯችንን ጨምሮ የሌሎችም በርካታ ጠቃሚ ባህሎች ባለቤቶች መሆናችንም የሚያስከብሩንና የሚያኮሩን ናቸው።
በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን በተደጋጋሚ ከምንተ ችባቸውና ከምንታማባቸው ነገሮች መካከል ደካማ የንባብ ባህላችን ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል። ሃሜት ብቻም ሳይሆን በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረገ አንድ ጥናት የንባብ ባህላችን በእጅጉ ደካማ መሆኑን አመላክቷል። ዋና ከተሞቻቸውን እንደ ማሳያ በመውሰድ የዓለም ሃገራትን የንባብ ባህል የገመገመው ጥናት እንደ ጃፓንና ጀርመን የመሳሰሉትን አገራት በማንበብ ባህላቸው ከፍተኛ ደረጃ መድረሳቸውን የጠቆመ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ያለው የንባብ ባህል ግን በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን አመላክቷል።
የዓለም ሃገራት ዋና ዋና ከተሞችን የንባብ ባህል “ከፍተኛ”፣ “መካከለኛ” እና “ዝቅተኛ” በሚል በሦስት ምድብ ውስጥ በቅደም ተከተል ስማቸውን በደረጃ ያስቀመጠው ጥናቱ የእኛዋን አዲስ አበባ ግን ዝቅተኛም ቢሆን ከነጭራሹ ደረጃ ውስጥ ሳያስገባት “የማታነብ ከተማ” በማለት ተሳልቆባት አልፏል። የንባብ ባህላችንን በሚመለከት ሃቁ ቢመረንም ለእኛም ልካችንን ነግሮናል። የማያነብ ህዝብ ደግሞ የብልጽግና ትንሳኤው ሩቅ ነውና ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ የንባብ ባህላችንን ለማሻሻል እንደ ዜጋ እያንዳንዳችን የበኩላችንን መወጣት ይጠበቅብናል። የዛሬው ዕይታዬ በዚሁ ዙሪያ የሚያጠነጥን ይሆናል።
ንባብ የለም፣ ትምህርት የለም፣ ዕውቀት የለም
ንባብ በመዝገበ ቃላት ትርጉሙ ከአራቱ መሰረታዊ የቋንቋ ክህሎቶች አንዱ በሚል ሊገለጽ ይችላል። ነገር ግን ንባብ ክህሎት ብቻ አይደለም። ንባብ በመደበኛው የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ዋነኛው መሳሪያ ከመሆኑም በላይ ራስን ለማሻሻልና ህይወትን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ዕውቀቶች የሚቀሰሙበት ወሳኝ ክህሎት ነው። በመሆኑም የእያንዳንዱ ግለሰብ የእለት ተዕለት ልምድ ከልምድም በላይ ባህል ሊሆን ይገባዋል። እንደ ማንኛውም ክህሎት ንባብም በአንድ ጀምበር የሚገኝ ሳይሆን ቀስ በቀስ የሚዳብርና ደረጃ በደረጃ በጊዜ ሂደት የሚገነባ ነው።
በዚህ ረገድ የንባብ ባህልን ለማስፋፋትና ለማሳደግ የማህበረሰብ መሰረት ከሆኑት ከቤተሰብና ከልጆች ሊጀመር ይገባል። የማህበረሰቡን የንባብ ባህል ለማጎልበት በዋነኝነት መጭው ትውልድ ላይ ትኩረት ተደርጎ በህጻናት ላይ ሊሰራ ይገባል። ለዚህም የንባብ ባህልን በማህበረሰቡ ውስጥ ለማዳበር እንደ ሃገር በርካታ ሥራዎችን መስራት ያስፈልጋል። ንባብ ተመራማሪ ዜጋ ለመፍጠር ዋነኛው መሰረት ነው። የሀገር ባህልና ታሪክ የሚጻፈውና ወደ ቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፈው በመጽሃፍትና በንባብ አማካኝነት ነው። ይህን ንባብ ለሃገር ዕድገት የሚያበረክተውን ከፍተኛ ፋይዳ በመረዳት ወላጆች ልጆቻቸውን ከንባብ ለማቆራኘት የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ መክፈል ይጠበቅባቸዋል። የንባብ ባህልን ማሳደግ ላይ የተሰሩ ልዩ ልዩ ጥናቶች የሚያመላክቱትም ይህንኑ ነው። ወላጆች የሁሉም ነገር መሰረቶች በመሆናቸው የንባብ ባህልም መወረስ ያለበት ከወላጆች መሆኑን በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ።
በሌላ በኩል የንባብ ባህልን ለማጎልበት አንባቢ ብቻ ሳይሆን የሚነበቡ ነገሮችም ሊኖሩ የግድ ይላል። “የንባብ ባህልን ለመፍጠር ትክክለኛው ቦታ ህጻናት ናቸው” የሚሉት በዚህ ጉዳይ ላይ ለጸሃፊው አስተያየታቸውን እንዲያካፍሉ የተጠየቁት የ “ና ህትመትና ፊልም ፕሮዳክሽን” ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም “ማስተዋል” ና “ፖንደር” በሚሉ ርዕሶች በአማርኛና በእንግሊዝኛ በየሳምንቱ የሚታተሙ ሁለት የህጻናት ጋዜጦችን በማሳተም ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ አርማችን አንበሳ ናቸው። “ብዙ ጊዜ የማንበብ ባህላችን አነስተኛ ነው እየተባለ ይወራል፤ ግን ደግሞ የሚነበብ ነገር ማቅረቡ ላይም ችግሮች አሉ” የሚሉት የህጻናት ጋዜጣ አሳታሚው፤ በተቻለ መጠን በአቅርቦቱ አካባቢ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ይናገራሉ።
በቂ ነው ባይባልም በመጽሃፍት በኩል የህጻናት የተረት መጽሃፍቶችን በማቅረብ ረገድ አበረታች ሁኔታዎች መኖራቸውን የሚያመላክቱት የህጻናት ጋዜጣ አሳታሚው፤ መጽሃፍት በርከት ያሉ ገጾችን የያዙ በመሆናቸውና የንባብ ልምድ ደግሞ ደረጃ በደረጃ የሚዳብር በመሆኑ ሕጻናቱ በቀላሉ አጠር ያሉ ጽሁፎችን በጋዜጣ ማንበብ እየተለማመዱ እንዲሄዱ በሚል ወደዚህ ሥራ መግባታቸውን ያመላክታሉ።
ማንበብ፣ ማሰብንና ማሰላሰልንም እንደሚጨምር የሚያመላክቱት አቶ አርማችን ለዚህም ልጆች ካነበቡ በኋላ ያነበቡትን ነገር ምን ያህል መገንዘብ እንደሚችሉ ራሳቸውን የሚፈትኑባቸው የግንዛቤ ጥያቄዎችና ሽልማቶች የሚሰጡባቸው አምዶች ሊኖሩ ይገባል። ማንበብና መጻፍ ተያያዥ ክህሎቶች በመሆናቸውም ንባብ ብቻ ሳይሆን የልጆችን የመጻፍ ክህሎትም ለማዳበር ልጆች ራሳቸው የሚጽፉባቸው ቦታዎችም እንዲሁ ያስፈልጋሉ። ‹‹ ለልጆች የንባብ ባህል መዳበር ስንልም ምቹ ሁኔታን እየፈጠርን ነው›› ይላሉ።
“የንባብ ባህልን ለማዳበር ትክክለኛው ቦታ ህጻናት ናቸው” የሚሉት በህጻናት ጋዜጣ ህትመት ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ አርማችን ይሁን እንጂ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ችግር መኖሩን ይጠቁማሉ። በተለይም የህጻናት ጋዜጣ በአገሪቱ የለም በሚባልበት ደረጃ መኖሩን አመላክተው ሥራው ያልተለመደ በመሆኑ ገበያ ላይም ያን ያህል ተጠቃሚ ባለመኖሩ እንዲሁም ወረቀትና የህትመት ዋጋ ውድ በመሆኑ በዘርፉ ለሚሰማሩ አካላት ፈታኝ መሆኑን ያመላክታሉ። “የእውነት የንባብ ባህልን ማሳደግ ካስፈለገ መንግስትም ዘርፉን ሊደግፈው ይገባል፤ ሥራውም እንደ ንግድ ሳይሆን እንደ ማህበራዊ ኃላፊነት ታይቶ ሊሰራ ይገባዋል” የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ። እውነት ነው “ከልብ ካዘኑ እንባ አይገድም” እንደሚባለው አንባቢ የለም እያሉ በሃሜት ላይ ብቻ ከመጠመድ የሚነበብ ነገር እንዲኖር መስራትም ከመንግስት የሚጠበቅ ነው።
የንባብ ባህልን ለማሻሻል መቅደም የሚገባው ባህል
በነገራችን ላይ የንባብ ባህል ዝም ብሎ የሚመጣ ነገር አይደለም። ጀርመናውያን በአንድ ወቅት “በመጸዳጃ ቤቶቻችን የምናነበው ነገር ይቀመጥልን” በማለት ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው መንግስታቸውን መጠየቃቸውን ታሪክ ይነግረናል። ሆኖም ታሪክ የእኛዎቹ ጥራዝ ነጠቆች እንደሚሉት ፋይዳ የሌለው ባዶ ተረት ተረት አይደለምና፤ ሰዎች በተግባር ለትውልድ ያስተላለፉት ሰርቶ ማሳያ ቅርስ ነውና እኛም ከዚህ ታሪክ የምንማረው ትልቅ ቁም ነገር አለ። ይህም ጀርመናውያኑ እንዲህ ዓይነቱን ድንቅ የንባብ ባህል እንዴት አዳበሩት፣ እኛስ የንባብ ባህላችንን ለማሻሻልና እነርሱ የደረሱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ነው።
ጀርመናውያኑ መጸዳጃ ቤት ውስጥም ሆነው ማንበብ ይፈልጋሉ ማለት እጅግ የሚደነቅ ከፍተኛ የሆነ የንባብ ባህል አላቸው ማለት ነው። ለመሆኑ ጀርመናውያኑን መጸዳጃ ቤት ውስጥ ሳይቀር እንዲያነቡ ያነሳሳቸው ምክንያት ምንድ ነው? እንዲህ ዓይነቱን አንባቢነትስ “የንባብ ባህል” የሚለው ብቻ ይገልጸዋልን? ደካማውን የንባብ ባህላችን ለማሻሻል እነዚህን መሰረታዊ ጥያቄዎች መመርመርና መመለስ ይገባል። ምክንያቱም የንባብ ባህላችን ለማሻሻል ትልቁ ሚስጥር ያለው በእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ ነውና። የዳበረ የንባብ ባህልን ለመፍጠር በቅድሚያ “የንባብ ፍቅር” ሊኖረን ይገባል። አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር፤ እንደ ሃገር የዳበረ የንባብ ባህል ባለቤት ለመሆን መፍትሄውም ይኸው ነው-መጽሃፍትን ማፍቀር፣ ንባብን ማፍቀር!
ምክንያቱም አንድን ነገር ሳንፈልገው፣ ሳንወደው እንዴት እንዲኖረን እናደርገዋለን? እናም በምንፈልገው ነገር ላይ ጥሩ ችሎታ እንዲኖረን ከፈለግን ከሁሉም በፊት ለዚያ ነገር ፍቅር ሊኖረን ይገባል። ከላይ የተገለጸው የጀርመናውያኑ ሁኔታም የሚያሳየን ይህንኑ ነው። እነርሱ አይደለምና በመደበኛው ጊዜያቸው በዚያች የደቂቃ የመጸዳጃ ቤት ቆይታቸውም የሚነበብ ነገር ማጣት አይፈልጉም። ለምን ቢሉ ንባብን ያፈቅሯታልና! ከማንበብ ፍቅር ይዟቸዋልና! ይህም የንባብ ፍቅራቸው በከፍተኛ ደረጃ የዳበረና የበለጸገ የንባብ ባህልን ፈጠረላቸው።
የእኛም አገር ችግር የንባብ ባህል አለማደግ ሳይሆን የንባብ ፍቅር አለማደግ ይመስለኛል። ለመሆኑ ማንበብ እንወዳለን? ስንቶቻችን ነን ለመደበኛ ትምህርት ወይም የሆነ አስገዳጅ ነገር ተፈጥሮብን ካልሆነ በስተቀር ለንባብ ፍላጎትና ፍቅሩ ኖሮን የምናነበው? ማንበብን የምንስለውስ እንዴት ነው? እንደ አንድ አስጨናቂ ሥራ ወይስ እንደ አዝናኝ የአዕምሮ ምግብ? መልሱን ለእያንዳንዳችን ልተወው። ከዚሁ ከንባብ ፍቅር ጋር በተያያዘ አንድ ወዳጄ የነገረኝን ቀልድ የምትመስል ዕውነት ነግሬያችሁ ወደ ቀጣዩ ክፍል ልለፍ። “ልጆች ያስቀመጥከውን ብር እያነሱ ካስቸገሩህ መጽሃፍ ውስጥ ደብቀው፣ ሌባ ይወስድብኛል የሚል ስጋት ካለህም ይህ ዘዴ ግሩም መፍትሄ ይሆንልሃል”። አይገርምም? በእኛ አገር መጽሃፍት የሚፈለጉና የሚፈቀሩ ሳይሆኑ የሚያስፈሩና የሚያስጠሉ ናቸው ማለት ነው? ታዲያ እውነት መጽሃፍትን እየፈራናቸውና እየጠላናቸው፤ እንዲህ እየሰለቸናቸው ከሆነ እንዴት ነው የንባብ ባህላችን የሚያድገው?
ስለ ንባብ ፍቅር ከምንጩ
ለማንኛውም ከዚህ አመለካከታችን ተላቅቀን እንደ ሌሎቹ የዳበረ የንባብ ባህል ለመገንባት ያግዘን ዘንድ የዳበረ የንባብ ባህል ምንጭ ስለሆነው የንባብና የመጽሃፍት ፍቅር የዓለማችን ታላላቅ ሰዎች ያሉትን በራሳቸው አንደበት ላቅርብላችሁ። ውሃን ከጥሩ ቢጠጡት፣ ነገርን ከሥሩ ቢሰሙት መልካም ነውና! ስለ ማንበብ ጥቅም እኛ ከምንናገር ንባብን አፍቅረው በተግባር ከኖሩት ከእነርሱ ከራሳቸው ብንሰማ እንለወጥበታለንና እነሆ።
ሎርድ ማክዋሌ፣ ብሪታኒያዊ ታሪክ ጸሃፊ፣ ሃያሲና ፖለቲከኛ “ሁልጊዜም ትንሿን ልጄን ስለማስደሰቴ ሐሴት ይሰማኛል-እርሷ መጽሃፍትን የመውደዷን ያህል ደግሞ የሚያስደስተኝ ምንም ነገር የለም። ምክንያቱም እንደ እኔ እድሜዋ ሲገፋ መጽሃፍት ከየትኛውም ኬክ፣ አሻንጉሊትና ከማንኛውም ጨዋታና ትዕይንት ሁሉ የተሻሉ መሆናቸውን ትገነዘባለች። ማንም እስከ ዛሬ ከኖሩት ነገስታት ሁሉ ታላቁ እንዲሁም ባለ ቤተ መንግስትና ባለ አትክልት ሥፍራ ቢያደርገኝ፣ የተመረጠ የእራት ግብዣ ከወይን መጠጥ ጋር የሚቀርብልኝ፣ ንጉሥ ሊያደርገኝ ቢፈልግ እንኳ መጽሃፍትን የማነብበት ዕድል ከሌለኝ ንጉሥ መሆንን ነፍሴ አትቀበለውም። ማንበብን የማያፈቅር ንጉስ ከመሆን ከበርካታ መጽሃፍቴ ጋር በአንዲት ትንሽ ክፍል ብታጎር እመርጣለሁ። ”
ጀምስ ዊሊስ ‹‹የመጽሃፍት ፍቅር በየዕለቱና በየሰዓቱ ገደብ የለሽ የሆነ በማንም ጥገኛ ያልሆነ አግባብነት ያለውን የፍስሃ ምንጭ ይከፍትልናል። እናም ከቀኑ የተወሰኑ ሰዓቶቹን በክፍሉ ውስጥ ሆኖ በመጽሃፍት ውስጥ ከሚኖሩ ከበሬታን የሚያላብሱ ታላላቅ ሰዎች ጋር ከማያሳልፍ ሰው ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ዋጋ ያለውን አንዳች ነገር ተስፋ ማድረግ አያስፈልገንም። ”
ሪቻርድ ዲ በሪ “መጽሃፍት ያለ በትርና ያለ አለንጋ፣ ያለ ቁጣና ያለ ስድብ፣ ያለ ገንዘብና ለሙገሳ የሚያስተምሩንና የሚያነጹን ጌጦች ናቸው። ቤተ መጽሃፍት ከሃብት ሁሉ ይበልጥ ውድ የሆነ ነገር ነው፤ የምንመኘው ማንኛውም ነገር ከእርሱ ጋር ይነጻጸር ዘንድ ብቁ አይደለም። ማንም ራሱን ቀናኢ የዕውነት፣ የደስታ፣ የጥበብ፣ የሳይንስ ወይም የዕምነት ተከታይ አድርጎ የሚቆጥር ከሆነ የግድ ራሱን የመጽሃፍት አፍቃሪ ማድረግ ይኖርበታል። ”
ዶክተር ጀምስ ስኖውደን፣ እውቅ ደራሲና መምህር “መጽሃፍት ውድ ዋጋ ያላቸውን ንብረቶችንና የዓለማችን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሃብቶች፤ የሃሳብ ጭነቶችን የተሸከሙ ጀልባዎች ናቸው። ከሚኖሩህ ነገሮች ሁሉ የተወሰኑ ጥሩ መጽሃፍት ይኑሩህ። አንብባቸው፣ አሰላስልባቸው፣ ያላቸውን ወደ ነፍስህ እስኪያንጠበጥቡልህና ጠቢብ፣ ባለፀጋና ብርቱ እስኪያደርጉህ ድረስ ወደ ልብህ አስጠግተህ እቀፋቸው››
እነዚህን እንደ አብነት አነሳን እንጂ በተለያዩ መስኮች የዓለማችንን ስልጣኔ ከፊት ሆነው በፊታውራሪነት የመሩ ሁሉም ታላላቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ስብዕናዎች ለመጻህፍት ያላቸውን ልዩ ፍቅር የነበራቸው ናቸው። በአንድ ወቅት መላ አውሮፓን ጠቅሎ ከገዛው ታላቁ ንጉስ ናፖሊዎን ቦናፖርት፣ ከአንድ ሺ በላይ ፈጠራዎችን እስካበረከተው ቁንጮ ሳይንቲስት ቶማስ ኤዲሰን፤ ከባለቅኔው ሼክስፒር እስከ ፈላስፋው ሶረን ኪርክ ጋርድ ሁሉም ስለመጻህፍት ያልተቀኘ የለም።
“የታላቅ አገር መሰረቱ የሕዝብ አንድነት ነው” በሚል ፍልስፍናቸው የሚታወቁትና በግለኝነት አስተሳሰብ በዘቀጡ ዘመነ መሳፍንታውያን ተከፋፍላ የተዳከመችውን ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ አንድነቷ የመለሳት፤ ለታላቅነቷ ታላቅ ራዕይን ይዘው ህይወታቸውን እስከ መስጠት ድረስ የታገሉላት፣ የጀግንነትና የታላቅ ስብዕና ምልክት የሆኑት ኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሠት አፄ ቴዎድሮስም ለመጽሃፍ ልዩ ፍቅር ነበራቸው። በዚህም ንጉሡ በህይወት ዘመናቸው ልዩ ልዩ ዕውቀትና ጥበብ የያዙ እስከ አንድ ሺ የሚደርሱ መጽሃፍትን በመቅደላ ጊዜያዊ ቤተ መንግስታቸው ሰብስበው እንደነበር የአገር ውስጥና የውጭ የታሪክ ምሁራን ጽፈዋል።
የዛሬውን ትዝብቴን አሜሪካዊው ደራሲ፣ አርታዒና ተዋናይ ሮበርት ኤች. ዴቪስ የማተሚያ ቤቶችን ተግባርና ምርቶቻቸውን አስመልክቶ በተናገረው ላጠቃልል። “ከእናት ምድር የተወለድኩ ማተሚያ ድርጅት ነኝ። ልቤ አረብ ብረት፣ ክንዴ ብረት፣ ጣቶቼ ነሐስ ናቸው። የዓለምን ቅኔ እቀኛለሁ፣ የታሪክን ትረካ እተርካለሁ፣ የዘመናትን ሁሉ ኦርኬስትራ እጫወታለሁ። የዛሬ ድምጽ የነገ መልዕክት ነኝ። በታሪክ ሸማ ውስጥ የመፃዒን ፈትል እሸምናለሁ። የሰላምንና የጦርነትን ትረካ እንደ አንድ እነግራለሁ። የሰውን የልብ ትርታ በግለት ወይም በርህራሄ እንዲሸነፍ አደርገዋለሁ። የመንግስታትን የደም ንዝረት እጨምራለሁ፤ ጀግኖችን የጀግንነትን ጀብድ እንዲፈጽሙ፣ ወታደሮችን ለተሰለፉለት ዓላማ ህይወታቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ አደርጋለሁ። በእኩለ ሌሊት ከማሽን ጋር ሲታገል የሚለፋውንና የዛለውን ባተሌ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲያተኩር ያለ ፍርሃትም የዘላለምን ተስፋ መፅናናት እየፈለገ ከፊቱ ወደ ተንጣለለው መፃዒ እንዲያነጣጥር አደርገዋለሁ።
እኔ ስናገር ሚሊዮኖች ድምጼን ይሰማሉ…ሁሉም ይገነዘቡኛል…በየሰዓቱ ሐሴታቸውንና ኀዘናቸውን እዘምራለሁ። ብርሃን፣ ዕውቀትና ኃይል ነኝ። አዕምሮ በቁስ ላይ ያለውን የበላይነትና አሸናፊነት አንጸባርቃለሁ። የሰው ዘር ስኬታማ ክንውኖች ሁሉ መዝገብ እኔ ነኝ። በንጋት፣ በቀትር፣ በምሽትም መዝጊያ ሰዓታት፣ በጎስቋላ ደብዛዛ ኩራዝም ይሁን በተንጣለለ የባለፀጋ ውብ ሳሎን፤ የእኔ የዘር ሐረግ – ልጆቼና የልጅ ልጆቼ ሁሉ ወደ እናንተ ይደርሳሉ። እኔ የዓለም የፍስሐ ሳቅና የኀዘን እንባ ነኝ። ሁሉም ነገር ወደ ማይሰራ ብናኝ እስኪመለስ ድረስ ፈፅሞ አልሞትም። እኔ ማተሚያ ድርጅት ነኝ። ”
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2012
ይበል ካሳ