የአዲስ አበባ መንገዶችና ከተማዋን አቋርጠው የሚፈሱ ወንዞች ቀን ሊወጣላቸው የመጨረሻው ደረጃ ላይ የደረሱ ይመስላሉ። በከተማዋ ጎዳናዎች የሚመላለስ ወጪና ወራጅ፤ በወንዞቹ አቅራቢያ የሚዘዋወር ሁሉ ፊቱን ሳያቀጭም፣ አፍንጫውን ሳይሸፍን ማለፍ አይሆንለትም።
ይህ ሁሉ ካለምክንያት አይደለም። ለከተማዋ ውበት የሚያስብና የሚጨነቅ ከማግኘት ይልቅ በእጁ ላይ የቀረውን አገልግሎቱ ያለቀ አንዳች ነገር ባገኘው ቦታ እየጣለ፣ በአደባባይ እየተፀዳዳ፣ ቆሻሻ ፍሳሹን በመተላለፊ መንገድ እየደፋ በገዛ እጁ በሽታን የሚጠራ ማየት የተለመደ በመሆኑ እንጂ። በዚህ የተነሳ ማንም ከማንም ሳይለይ ለአስጸያፊው ተግባር የየድርሻውን አበርክቷል ማለት ይቻላል።
የከተማዋ መቆሸሽ የሚቆረቁራቸው አንዳንድ ቀና ዜጎች ታዲያ ይህንን አስጸያፊ ተግባር በመኮነን በግልም ይሁን በመንግሥት ደረጃ ቅስቀሳ በማድረግ ለጽዳት ቢነሳሱም አንዱ ሲያጸዳ ሌላው እያቆሸሸ ጅምሩ መክኖ ወደነበረበት ተመልሶ ማየት የተለመደ ሆኖ ቆይቷል።
ለበርካታ ዓመታት የታለመው ከተማዋን ጽዱና አረንጓዴ፣ የአፍሪካ መዲናነቷን የምታስመሰክር፣ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች የሚጎርፉባት፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ ሆና የማየት ህልም ዛሬ ላይ ሊሳካ የጉዞ እርምጃውን አንድ ብሏል። ባለፈው ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አጠናክረው የቀጠሉት አርዓያ በመሆን በዘመቻ ወጥቶ ከማጽዳት ተግባር ጎን ለጎን የወንዞች ዳርቻን የማልማት ሥራ ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት በቁርጠኛነት ከፍጻሜ ለማድረስ የሚያስችለው ሥራ በይፋ መጀመሩ በርግጥም አዲስ አበባ እንደ ስሟ የሚገባትን ደረጃ ልታገኝ በመሆኑ ያስደስታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ግንቦት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት በታላቁ ቤተ መንግስት በተካሄደው የእራት ግብዣ ላይ ‹‹የሁሉም ተሳትፎ ከታከለበትና ዜጎች ባሉበት ጠንክረው መስራት ከቻሉ በአጭር ጊዜ አዲስ አበባን ጤናማና ለኑሮ ተመራጭ ከተማ ማድረግ ይቻላል። አዲስ አበባ የነበራትን ነፋሻ አየር፣ ጽዱነትና ለኑሮ ምቹነት ካጣች ዓመታትን አስቆጥራለች። ወደነበረችበት ጥሩ ገፅታዋ የመመለሻው ጊዜ ያለፈ ቢሆንም አሁንም አልረፈደም ››ሲሉ የተናገሩትን እውን ሆኖ ለማየት ከመንግሥት ብቻ የሚጠበቅ መሆን የለበትም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ‹‹ የታላቂቱ አፍሪካ ዋና ከተማና የብዙ ታሪካችን ማማ ለሆነችው ለአዲስ አበባ አደይ አበባዋንና ነፋሻ አየሯን የመመለስ ኃላፊነት ያለበት የአሁኑ ትውልድ ነው ›› በማለት አሁን ያለው ትውልድ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ለመጪው ትውልድ የተሻለች አዲስ አበባን ገንብቶ አሻራ ለማስቀመጥ ወቅቱ አሁን መሆኑን መግለጻቸው ከተማዋን የማስዋቡ ጅማሬ አሁን መሆኑን ለማመልከት ነው።
ከተማን የማስዋብ ታሪካዊ ልማት ላይ በመሳተፍ ሁሉም የበኩሉን መወጣቱ ለሀገርና ለወገን የሚበጅ ተግባር መሆኑን በማወቅ የዚህ ዘመን ትውልድ ቀደምት አባቶች ያወረሱትን ታሪክ በመረከብ ራሱ በወንዞቹ ዳርቻ እንዲዝናና፣ በዛፎቹ ሥር ሆኖ ተፈጥሮን እንዲያደንቅ፣ ይገነባሉ ተብለው በተወጠኑት ቤተ መጻሕፍት ውስጥ እውቀትን መገብየት እንዲችል በመልካም አሳቢነት ሙሉ እገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2012