ንጉስ ሚካኤል የልጃቸውን መሻር ሰምተው የጦር ሰራዊታቸውን በአዋጅ አስከትተው ወደ ሸዋ መገስገሳቸውን ሴራ ጠንሳሾች የነበሩት መኳንት፣ ሹማምንትና ሚኒስትሮች ሰምተው የምልጃ ደብዳቤ የጻፉላቸው ከ102 ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት (መስከረም 24 ቀን 1909 ዓ.ም) ነበር።
አጼ ምኒልክ ዙፋናቸውን ያወረሱትን ልጅ ኢያሱን ለመሻር መኳንንቱ፣ ሹማምንቱና ሚኒስትሮቹ መክረው ሲያበቁ በዋናነት ያቀረቡበት ክስ መናፍቅነት ነበርና የአድማው መሪ እጨጌው ወልደጊዮርጊስ ነበሩ። አድመኞቹ የሚሰባሰቡት በእጨጌው ቤት ሲሆን፤ ሌላው አቀናባሪ ፊትአውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ነበሩ። የልጅ ኢያሱ ዕጣ አሳዛኝነት ይበልጥ የሚታየው ደግሞ ያቀረባቸውና የሸለማቸው ሁሉ በጭንቅ ጊዜ ሲከዱት ነው። ከነዚህም መካከል ሊጋባ በየነ ወንድምአገኘሁ፣ በጅሮንድ ይገዙ በሀብቴ፣ የኢያሱን እህት ወይዘሮ ስህንን እስከማግባት የደረሱትና በኢያሱ ዘመን ከፍተኛውን ስልጣን የያዙት ቢትወደድ ኃይለጊዮርጊስና የኢያሱ አማካሪ የነበሩት ምሁር ተክለሃዋርያት ተክለማሪያም ይገኙበታል።
ኢያሱን ለማውገዝ ያልቸኮሉት አቡነ ማቲዮስ ብቻ ነበሩ። አድመኞቹ ለኢያሱ ከገቡለት ቃለ መሃላ እንዲፈቷቸው ሲጠይቋቸው እንቢ ብለው ነበር። በኋላ ግን የእጨጌው ግፊት ስለበዛባቸው አድመኞቹን ከግዝት ፈቷቸው። ከዚያ በኋላ በዕለተ መስቀል ኢያሱ ከስልጣን እንዲወርድ ተወስኖ የምኒሊክ ልጅ ዘውዲቱ ዙፋኑን ሲወርሱ ደጃች ተፈሪ መኮንን አልጋ ወራሽ ተባሉ። ልጅ ኢያሱ ከስልጣን መውረዳቸውን እንደሰሙ ከነበሩበት ከጅግጅጋ ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግሱ መኤሶ ላይ 15 ሺ የሸዋ ጦር ጠብቆአቸው ጦርነት ገጥመው ተሸንፈው ወደ አፋር በርሃ ሸሹ።
ንጉስ ሚካኤል ልጅዎ ምክራችንን አልሰማ ስላሉ ሽረናቸው ንግስት ዘውዲቱን አንግሰን ልዑል ራስ መኮንንን አልጋወራሽና ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴ አድርገናል የሚል የስልክ መልዕክት ስለተላለፈላቸው፣ “ልጄን እኔ መክሬና ተቆጥቼ እመልሰዋለሁ እንጂ አያቱ አጼ ምኒልክ የሰጡትን አልጋ ሲወስዱበት ዝም ብዬ አላይም” ብለው የጦር ሰራዊታቸውን በአዋጅ አስከትተው ወደ ሸዋ መገስገሳቸው ሲሰማ መኳንንቱ፣ ሹማምንቱና ሚኒስትሮቹም በአንድነት ሆነው ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ደብዳቤ ጽፈው ላኩላቸው።
ይድረስ ከንጉሥ ሚካኤል። ዘስልጣኑ ጽሑፍ ዲበ መትከፍቱ ንጉሠ ጽዮን።
ልጅዎ ልጅ ኢያሱ አልጋ ወራሽ ከሆኑ ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ የሚሰሩት ስራ ሁሉ የልጅ ስራ እንደሆነ ንጉሡም ያውቁታል። እኛም መክረን ተቆጥተን እናሳድጋለን ብለን ብናስብ ባንድ ስፍራ የማይቀመጡ ስለሆነብን ጊዜ አላገኘንም። አንዳንድ ጊዜም እያገኘን ብንመክራቸው አልተቀበሉንም። እኛም ምናልባት ከነገ ሣልስት የመንግስታቸውን ጥቅም፤ የራሳቸውን ማእረግና ክብር እያወቁ ይህን የልጅነት ስራቸውን ይተውት ይሆናል በማለት ሰውነታቸው እንዳይሳቀቅ ታግሰን ብንጠብቃቸው የልጅነት ስራ መስራታቸው አልበቃ አላቸው። … ይህንንም ሁሉ ታግሰን ሁላችንም ባንድነት ሆነን ሊቀ ጳጳሱንና እጨጌውን ጨምረን ለማናቸውም ቢሆን ለእንቁጣጣሽ (ላዲሱ አመት) ወደ አዲስ አበባ ይምጡ ብለን ደብዳቤ ጽፈን ብንልክላቸውም ሳይመጡ ቀሩ። ይህንም ሁሉ ለንጉሥ መጻፋችን ዐጼ ምኒልክን እኛንም ሁሉ እንዲወዱ እናውቃለንና አሳብዎ ከአሳባችን ሳይለይ በአንድነት እንድንቆም እንጂ በተለየ ንጉሥ እንዲቀየሙና ልጅ ኢያሱ እንዲጎዱ ብለን ያደረግነው አይደለም።
መስከረም 24 ቀን 1909 ዓ.ም
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ስለ ልጅ ኢያሱ መሻር ሲገልጹ “እንደታሰበው ለአዲስ አበባው ውሳኔ ዋናው ተቃውሞ የመጣው ከኢያሱ ሳይሆን ከአባቱ ከንጉሥ ሚካኤል ሆነ። ንጉሥ ሚካኤል “የጠፋ ልጄን አፋልጉኝ” ብለው 80 ሺ ጦር እየመሩ በሸዋ ላይ ዘመቱ። በሸዋ በኩልም ቁጥሩ 120 ሺ የሚደርስ ጦር ከቶ ነበር። የመጀመሪያው ውጊያ ቶራ መስክ ላይ በጥቅምት ሰባት ቀን 1909 ተደርጎ የወሎ ጦር ሲያሸንፍ የሸዋው መሪ ራስ ልዑል ሰገድ አጥናፍ ሰገድም ውጊያው ላይ ወደቁ። ይህ የመጀመሪያው ድልና የሸዋው ጦር ዋና ስትራቴጂስት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ የሽንገላ ቃላትና ገጸበረከት ንጉስ ሚካኤልን አዘናግቷቸው ከአድዋ ጦርነት በኋላ ብዙ ደም የፈሰሰበት ከፍተኛ ውጊያ ሰገሌ ላይ ጥቅምት 17 ሲደረግ የሸዋ ጦር የከበባ ስልት ተጠቅሞ የወሎን ጦር ባላሰበበት በደጀኑ ሲያጠቃው ተበተነ። ንጉስ ሚካኤልም ተማረኩ። የስልጣን ዝውውሩም በደም ታነጸ” ይላሉ።
ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ “ህይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ከንጉስ ሚካኤል ጋር ስላደረጉት ጦርነት ተከታዩን አስፍረዋል።
“ንጉስ ሚካኤል መስከረም 24 ቀን የጻፍንላቸው ደብዳቤ ከደረሳቸው በኋላ ምንም ቢሆን አልመለስም ብለው ወደፊት መገስገሳቸውን መልዕክተኞቻችን በስልክ ስላስታወቁን ለጊዜው በአዲስ አበባ የተገኘውን የጦር ሰራዊት በራስ ልዑል ሰገድ አበጋዝነት አድርገን አስቀድመን ሰደናቸው ነበርና ቶራ መስክ ከሚባለው ከሸዋ አውራጃ ሲደርሱ፤ ከንጉሥ ሚካኤል የጦር ሰራዊት ጋር በድንገት ተገጣጥመው በጥቅምት ሰባት ቀን ማክሰኞ ራስ ልዑል ሰገድ፣ ደጃች ተሰማ ገዝሙ፣ ሊቀ መኳስ አበበ አጥናፍ ሰገድ፣ ፊታውራሪ ዘውዴ ጎበና፣ አሳላፊ አቤ፣ ቀኛዝማች ድልነሣው፣ አሳላፊ ድልነሤ፣ አቶ ሸዋዬና ሌሎችም የጦር አለቆች በጦርነቱ ውስጥ መሞታቸውን በስልክ ሰማን።
ከዚያም በፊት የጦር ሚኒስትራችን ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ በጥቅምት ሦስት ቀን ከአዲስ አበባ ተነስተው ተጉዘው ኮረማሽ ሲደርሱ፤ በኮረማሽ ካለው የጦር መሳሪያ ለየወታደሩ ሲያካፍሉ እንዲሰነብቱ አድርገን ነበርና እኛ በጥቅምት ዘጠኝ ቀን ተነሳን። ከየአውራጃውም የሚመጣው የጦር ሰራዊት እንደተቻለ በግስጋሴ እንዲደርስ ለሰራዊቱ አዋጅ አሳወጅን።
ይህንንም አዋጅ ካስነገርን በኋላ ወደፊት ገሰገስን። ነግር ግን የኢትዮጵያ ሰው እርስ በእርሱ ደም መፋሰስ የሚያሳዝን ስለሆነ፤ ከደብረ ሊባኖስና ከዝቋላ ገዳማት ከየአድባራቱም ሁሉ መነኮሳትና መምህራን እየተመረጡ መጥተው መስቀል እየያዙ ንጉስ ሚካኤል ጦርነት ሳያደርጉ ወደ ወሎ እንዲመለሱ እንዲለምኗቸው አደረግሁ። ንጉሥ ሚካኤል ግን እንኳን ሊመለሱና ለማስታረቅ የተላኩትን መነኮሳት እየያዙ አሰሩዋቸው የሚል የስልክ ቃል ስለመጣልን ለመዋጋት ቁርጥ አሳብ ማድረጋቸው የታወቀና የተገለጠ መሆኑን ተረዳነው።
በጥቅምት 15 ቀን ከኮረማሽ ተነስተን ተጉዘን ነበርና በጥቅምት 16 ቀን ሰገሌ በሚባለው በጠራ ወረዳ ሜዳ የእኛና የንጉስ ሚካኤል ሰፈር ግንባር ለግንባር ተያይቶ አደረ። በጥቅምት 17 ቀን ዓርብ ከሌሊቱ በ ሰባት ሰዓት ጀምረው የጦር አለቆቻቸውን በቀኝና በግራ አሰልፈው እርሳቸው መሃል ሆነው መጥተው ጧት ሲነጋ ቃፊር ሆነው ባደሩት በመድፈኞቻችን ላይ አደጋ ጥለው ተኩስ ጀመሩ። ከዚህም በኋላ የጦር ሚኒስትራችን ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ በግንባር፣ ራስ ካሳ በንጉሥ ሚካኤል ጀርባ፣ የቀሩት ራሶችና ደጃዝማቾች በቀኝና በግራ እንዲሰለፉ አድርገን እኛ ለጦር ሰራዊቱ ሁሉ ደጀን ሆነን ተጋጠምናቸው።
ከጧቱም ጀምሮ አምስት ሰዓት ያህል እንደ ተዋጋን የሸዋ ጦር ሰራዊት ፍየል እንዳየ ነብር፣ ላም እንዳየ አንበሳ እየዘለለ ጎራዴውን እየመዘዘ እጅ ለእጅ ተያይዞ በሰልፉ ውስጥ በገባ ጊዜ ንጉሥ ሚካኤል ድል ሆነው ተማረኩ። ከሰራዊታቸውም የሞተው ሞቶ፤ የተማረከው ተማርኮ የተረፈው እየሸሸ ወደ ወሎ ተመለሰ።
ልጅ ኢያሱም በአዳል መሬት ዞረው ለጦርነቱ ለመድረስ ሲገሰግሱ አንኮበር በደረሱ ጊዜ ንጉስ ሚካኤል ድል መሆናቸውን ሰምተው ወደ ኃላቸው ተመልሰው በአዳል መሬት ዞረው ወደ ወሎ መሬት ገቡ። ንጉሥ ሚካኤል ግን ምንም ተማረኩ ቢባል ለስሙ ያህል ነው እንጂ ማናቸውም የውርደት ነገር እንዳያገኛቸው ለክብራቸው የሚገባውን ሁሉ አድርገንላቸው ነበር። ለሌሎቹም ምርኮኞች ከወሎ ጋር ሌላ ጠብ እንደሌለን ሁላችንም ያንዲት እናት ተወላጆች መሆናችንን እያስረዳን ከተለቀቁ በኋላ በአዋጅ ወደ አገራቸው ወደ ወሎ እንዲመለሱ አደረግን። የድሉንም ነገር በስልክ ወደ አዲስ አበባ ስላስታወቅን ከንግስት ዘውዲቱ ጀምሮ የከተማው ህዝብ በሙሉ ታላቅ ደስታ አደረገ። ወደ አዲስ አበባም በተመለስን ጊዜ በጥቅምት 23 ቀን ኃሙስ ግርማዊት ንግስት ዘውዲቱ በጃን ሜዳ በትልቁ አጅባር ድንኳን ሆነው የከተማው ህዝብ ሁሉ ተሰብስቦ በእልልታና በደስታ ተቀበሉኝ። ”
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2012
የትናየት ፈሩ