እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ስለ ዋስትና
በዕለት ተዕለት መስተጋብራችን ውስጥ አንዳችን ካንዳችን ገንዘብ ጠያቂ፤ ሌላኛችን ደግሞ ባለዕዳ የምንሆንባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው። ባለዕዳ (Debtor) የሚባለው አንድ ነገር የመፈጸም ግዴታ ያለበት ሰው ሲሆን፤ ባለገንዘብ (Creditor) የሆነው ወገን ደግሞ አንድ ነገር እንዲፈጸምለት ባለዕዳውን የመጠየቅ መብት ያለው አካል ነው። በዚህ የመብት ጠያቂነትና የባለግዴታ ግንኙነት ውስጥ ታዲያ “ዋስ” ሆኖ በመካከላችን የሚገኝ ሰው አይጠፋም።
በባለመብቱና በባለዕዳው መካከል የዚህ ሰው መገኘት ደግሞ የሁለቱ ግንኙነት ውጤት እንዲያገኝ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል። የጊዜና የሁኔታዎች ጉዳይ ነው እንጂ በመስተጋብሮቻችን ውስጥ እያንዳንዳችን ባለመብቱንም፣ ባለዕዳውንም አልያም ዋሱንም ልንሆን እንችላለን። ለዚህ ነው በተለይም ዋስ የምንሆን ከሆነ የግንዛቤ ስንቅ እንድንቋጥር በማሰብ ይህንን ጽሁፍ ያሰናዳነው። (ጽሁፉ ለባለገንዘብና ለባለዕዳም በተመሳሳይ ጠቃሚ ነው)
እርግጥ ነው በውልም ሆነ ከውል ውጭ በሚመነጭ ግንኙነት ከባለዕዳው ገንዘብ የሚጠይቁ ባለመብቶች ሁሉ ዓይነተኛ መያዣቸው የባለዕዳው ንብረት ነው። ባለገንዘቦች ከባለዕዳው ላይ የሚጠይቁትን ማናቸውንም መብት በፍርድ ካረጋገጡ በኋላ አፈጻጸሙን ደግሞ በንብረቱ ላይ የመጠየቅ መብት አላቸው። ለዚህም ነው በሕጋችን “ሊያዝበት አይገባም ተብሎ በህግ ከተደነገገው በስተቀር የባለዕዳው ንብረት ለግዴታው አፈጻጸም ማረጋገጫ (መያዣ) ነው” ተብሎ በግልጽ የተቀመጠው።
ታዲያ የባለዕዳው ንብረት ለባለገንዘቡ ሁነኛ መያዣው ከሆነ የዋስ አስፈላጊነቱ ምኑ ላይ ነው ሊባል ይችላል። ነገር ግን ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ አይሆኑም። የባለዕዳው ንብረት መያዣ ስለሚሆንልኝ ግዴታውን ባልተወጣ ጊዜ የምፈልገውን ነገር በንብረቱ ላይ አስፈጽማለሁ በሚል ተደላድሎ እንደማይተኛ ግልጽ ነው። ከባለዕዳው ገንዘብ ያላቸው ሰዎች በርካታ ሆነው ንብረቱ ደግሞ እዚህ ግባ የማይባል ከሆነ፤ ኪሳራ ቢያጋጥመው እንዲሁም ንብረቱን ለሌላ ቢያስተላልፈው አልያም በክፉ ልቡና ቢያሸሸው ይህን ጊዜ ባለገንዘቡ ሜዳ ላይ ይቀራል።
ለዚህ ነው ብልህ ባለገንዘብ “አውቅሃለሁ አንተ ታማኝ ነህ፤ ንብረትም አለህ፤ እንደምትመልስልኝ አምናለሁ፤ ያ ባይሆን እንኳን ንብረትህ መያዣዬ ነው፤ ግን ዛሬ ነገ ስላልሆነ ገንዘቤን እንደምትመልስልኝ ዋስ ጥራልኝ” የሚለው። ባለዕዳውም ከተስማማ በሁለቱ ግንኙነት መካከል ሌላ ሰው ዋስ ሆኖ ብቅ ይላል ማለት ነው። ይህም ከላይ ከተገለጸው በባለዕዳው ንብረት ላይ መብትን ማስከበር ከሚለው በተጨማሪ ሕግ ለባለገንዘቡ የሚሰጠው የመብት ማረጋገጫ ነው።
ዋስትና ከዕዳ ማረጋገጫ ውሎች ውስጥ አንዱ ነው። የመያዣ ውል፣ የወለድ አግድ ውል እና የአደራ ውል ሌሎቹ የዕዳ ማረጋገጫ ውል ዓይነቶች ናቸው። የመያዣ ውል የባለዕዳውን ወይም የሌላውን ሰው ንብረት በመድህንነት መያዣ የሚደረግበት ሲሆን፤ የወለድ አግድ ውል የሚባለው ደግሞ አንድ ባለገንዘብ ባለዕዳው ግዴታውን እስከሚወጣበት ጊዜ ድረስ የማይንቀሳቀስ ንብረቱን በመያዣነት ተቀብሎ ሲገለገልበት የሚቆይበት ነው።
የአደራ ውል የሚባለው ባለአደራው በውሉ መሰረት ሊከፈለው የሚገባው ገንዘብ ካለ ገንዘቡን እስከሚሰጠው ድረስ በአደራ የያዘውን ንብረት በእጁ ይዞ የሚያቆይበት ውል ነው። ዋስትና ከሆነ ደግሞ ከንብረት ጋር በተያያዘ በመያዣነት ከሚያገለግሉት ከእነዚህ ውሎች በተለየ መልኩ የባለዕዳው የመክፈል ችሎታና ብቃት የሚረጋገጠው “እኔ አለሁለት፤ እዋሰዋለሁ” በሚለው በራሱ በዋሱ ነው።
የዋስትናን መሰረት ከሚደነግገው የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 1920 ላይ እንደምናነበው ለግዴታው አፈጻጸም ዋስ የሚሆን ሰው ባለዕዳው ግዴታውን ያልፈጸመ እንደሆነ ለባለገንዘቡ ይህንን ግዴታ ሊፈጽም ይገደዳል። ሕጉ የዋስትናን መሰረተ ሀሳብ በዚህ መልኩ ከማስቀመጥ ውጭ ዋስትና ምንድን ነው የሚለውን ትርጓሜ አልሰጠውም። ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ የኢትዮጵያ የውል ሕግ መሰረተ ሀሳቦች በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚያብራሩት ዋስትና ማለት ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ባደረጉት ውል ወይም በእነርሱ መካከል ባለ የባለገንዘብነትና የባለዕዳነት ግንኙነት ውስጥ ከእነርሱ ውጭ የሆነ ሶስተኛ ሰው ባለዕዳው ዕዳውን በሙሉ ወይም በከፊል ያልከፈለ እንደሆነ ወይም ግዴታውን በአግባቡ ያልተወጣ እንደሆነ እኔ በእርሱ ስፍራ ሆኜ ገንዘቡን እከፍላለሁ ወይም ግዴታውን እወጣለሁ በማለት ለባለገንዘቡ ማረጋገጫ የሚሰጥበት ነው።
ብዙውን ጊዜ ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ ዋስትናን ከመድን ውሎች እና ከመድን ማረጋገጫዎች ጋር ማቀላቀል የተለመደ ነው። ሶስቱም በህግ የተለያየ አንድምታ ነው ያላቸው። የመድን ውል (Indemnity Contracts) አንድ ሰው ሌላ ሰው ለሚደርስበት ጉዳት ወይም በሌላ ሰው ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት አስቀድሞ በገባው ግዴታ ልክ አላፊ የሚሆንበት የውል ዓይነት ነው። የኢንሹራንስ ውሎች ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ናቸው። የመድን ሰጭው አላፊነት ቀጥተኛ ነው። “እኔ የምጠየቀው መድን ተቀባዩ የጉዳቱን ካሳ ራሱ ካልከፈለ ወይም መክፈል ካልቻለ ነው” የሚል መከራከሪያ ከመድን ሰጭው በኩል ሊቀርብ አይችልም።
የጉድለት ማረጋገጫ (Warranty) በሚባለው ውል ደግሞ አረጋጋጬ የሚገባው ግዴታ የውሉ ጉዳይ የሆነው ነገር በውሉ ላይ እንደተመለከተው ስለመሆኑ ነው። የጉድለት ማረጋገጫ ብዙውን ጊዜ የሚሰጠው በሽያጭ ውል ነው። የተሸጠው ነገር ባለቤት ራሱ ስለመሆኑ፤ የተሸጠው ነገር ግድፈት የሌለበት ስለመሆኑ ወዘተ… ሻጩ ማረጋገጫ የመስጠት ኃላፊነት አለበት። ይህ ግዴታ የሻጩ የራሱ ግዴታ በመሆኑ በተለምዶ አነጋገር ይህ ግዴታ ዋስትና እየተባለ የሚጠራ ቢሆንም በውጤቱ ግን ከመደበኛው የዋስትና ውል መሰረታዊ የሆነ ልዩ ባህርይ እንዳለው ልብ ይሏል።
የዋስትና ማረጋገጫ አስቀድሞ ለታወቀ ግዴታ (እንደ ብድር ያለ) ወይም ወደፊት ሊደርስ ይችላል ተብሎ ለሚገመት ግዴታ (ለተቀጣሪ የመንግስት ሰራተኛ) አልያም ከአንድ ሁኔታ መድረስና አለመድረስ ጋር በተያያዘ ለሚመጣ ግዴታ ሊሰጥ ይችላል። በዚህ ጽሁፍ እየቃኘን ያለነው ከውል ወይም ከውል ውጭ በሆነ የፍትሐብሔር ግዴታ ላይ ስለሚኖር የዋስትና ጉዳይ ነው እንጂ በወንጀል ጉዳይም ዋስትና ይሰጣል።
ይሁንና በወንጀል ጉዳይ የሚገባው ዋስትና የተጠርጣሪውን (የተከሳሹን) የወንጀል ኃላፊነት ለመቀበል ሳይሆን (የወንጀል አላፊነት ግላዊ በመሆኑና ወደሌላ ሰው ስለማይተላለፍ) ተከሳሹን በተፈለገበት አልያም በተቀጠረበት ጊዜ ሁሉ ለፍትህ አካላት ለማቅረብ ነው። በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የገንዘብ መቀጫ እንዲከፍል የተወሰነበት ተከሳሽ ቅጣቱን ወዲያውኑ በማይከፍልበት ጊዜ ፍርድ ቤት በሚያስቀምጥለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ለመክፈል የሚችል መሆኑ እንዲረጋገጥም ዋስትና ሊቀርብ ይችላል።
የዋስትና ባህርያት
ዋስትና እሱን ከመሰሉት የግዴታ ማረጋገጫዎችም ሆነ ከአጠቃላይ ከሌሎች ውሎች የሚለይበት የራሱ የሆኑ ባህርያት አሉት። ከፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 1920 እንደምንገነዘበው በዋስትና ውስጥ ዋስ፣ ዋና ባለዕዳ እና ባለገንዘቡ የተሰኙ ሶስት ወገኖች አሉ። ሁለት ዓይነት ግዴታዎችም አሉ – ባለገንዘቡ ከዋናው ባለዕዳ የሚጠይቀው (ባለዕዳው ለባለገንዘቡ የሚወጣው ግዴታ) እና ዋሱ ለባለእዳው ግዴታ አፈጻጸም የሚሰጠው የማረጋገጫ ግዴታዎች ናቸው። በባለገንዘቡና በባለዕዳው መካከል ያለው ግዴታ ዋና ዕዳ ወይም ዐቢይ ግዴታ (Principal Obligation) ሲባል፤ ዋሱ ለባለገንዘቡ የሚሰጠው የግዴታ ማረጋገጫ ደግሞ የዋስትና ግዴታ (Suretyship) ይሰኛል።
ከዚህ የምንረዳው የዋስትና ግዴታ የሚኖረው በዚህ ዋስትና የሚረጋገጥ ዕዳ ሲኖር መሆኑን ነው። እናም ከሁለቱ ግዴታዎች ቀዳሚው ዐብይ ግዴታው ነው። የዋስትና ግዴታ ደግሞ የዐብይ ግዴታን መኖር ተከትሎ የሚመጣ ስለሆነ ተቀጽላ (ደባል) ግዴታ (Accessory Obligation) ነው። ከሕጉ ቁጥር 1926 እንደምንገነዘበውም ዋናው ዕዳ በማናቸውም ምክንያት ቀሪ የሆነ እንደሆነ (ለምሳሌ ባለዕዳው ግዴታውን ከተወጣ፤ ባለገንዘቡ ዕዳውን ከሰረዘለት፤ ዋናው ዕዳ ሕጋዊ ውጤት ካጣ፤ ከተተካ፣ ከተቻቻለ ወይም በይርጋ ቀሪ ከሆነ ወዘተ…) ዋሱ ከግዴታው ነጻ ይሆናል ወይም ዋስትናው ይወርድለታል። ስለዚህ የመጀመሪያው የዋስትና ባህርይ የዋናው እዳ ደባል ግዴታ መሆኑ ነው ማለት ነው።
የዋናው ግዴታ በማናቸውም ሁኔታ መቅረት ዋስትናውን ቀሪ ያደርገዋል ቢባልም ቅሉ፤ ዋሱ ተጠያቂ ሊሆን የሚችልበት ውስን ምክንያት እንዳለ ልብ ይሏል። ይኸውም ፈራሽ በሆነ ግዴታ ላይ የተመሰረተ ዋስትና ሲሆን ነው። አንድ ባለዕዳ በመገደድ፣ በመሳሳት፣ በተንኮል ወይም ሕጋዊ ችሎታ ሳይኖረው (ሕጻን፣ ዕብድ፣ ወይም የተከለከለ ሰው) ውል ቢያደረግ ውሉ ፈራሽ ይሆናል። ነገር ግን ዋሱ ይህ ባለዕዳ ውለታ ያደረገው በመሳሳት፣ በተንኮል፣ በመገደድ ወይም ችሎታ ሳይኖረው መሆኑን እያወቀ ዋስ ከሆነ ዋናው ግዴታ ፈራሽ ቢሆንም የዋስትና ግዴታው ግን ይጸናበታል። ባለገንዘቡም እሱን መክሰሱ አይቀሬ ነው። ባለዕዳው የፈቃድ ወይም የችሎታ ጉድለት የነበረበት መሆኑን ሳያውቅ ዋስ ሆኖት ከሆነ ግን “ነገሩን ባለማወቄ የዋስትና ግዴታ ውስጥ ስለገባሁ ዋስትናው ፈራሽ ይሁንልኝ” ብሎ መከራከር ይችላል።
ሌላው የዋስትና ባህርይ በችሮታ ላይ የተመሰረተ ግዴታ መሆኑ ነው። ዋሱ ለባለዕዳው በመዋሱ የሚያገኘው የተለየ ጥቅም ወይም ወሮታ በሕግ አልተቀመጠም። ዋስትና በአብዛኛው ከባለዕዳው ጋር ባለ መቀራረብና ወዳጅነት ላይ የተመሰረተ እንጂ ዋሱ ያገኛል ተብሎ ታሳቢ በሚደረግ ጥቅም ላይ የተመሰረተ አይደለም። ለዚህ ነው ዋስትና በችሮታ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት የተሰኘው። ሕጋችንም “ባለዕዳው ሳይጠየቅ ወይም ሳያውቅ እንኳ ቢሆን ለሱ ዋስ ለመሆን ይቻላል” በማለት ዋሱ ጥቅም አገኛለሁ ባይ ሳይሆን ወዶ-ገብ መሆኑን ይገልጻል።
ዋስ ለመሆን ያሰበ ሰው ታዲያ እንዲሁ በጭፍን ዘሎ ወደ ካቴናው መግባት ሳይሆን ከወዳጅነትና ከዝምድናም ባሻገር እንደ ብድር ያለ የቁርጥ ዕዳ ከሆነ የባለዕዳውን የመክፈል አቅም፤ አንድን ሥራ ሰርቶ የማስረከብ ግዴታ ከሆነ የቀደመ የሥራ ብቃቱን፣ ትጋቱንና ጥራቱን ማወቅ አለበት። ግዴታው አንድን ነገር ከማድረግ ለመቆጠብ ከሆነም ዋናው ባለዕዳ ዕምነት የሚጣልበትና ቃሉን ጠባቂ ሰው መሆኑን በቅጡ ማወቅ ያስፈልጋል። እነዚህ የዋሱ ትጋቶች ታዲያ ህጉን ከማወቅ ባልተናነሰ መልኩ ዋሱን ኋላ ላይ ከሚመጣ ከባድ ኪሳራ እንደሚያድኑት ግልጽ ነው።
ሶስተኛው የዋስትና ባህርይ በጽሁፍ መደረግ ያለበት መሆኑ ነው። እርግጥ ነው ተዋዋዮች የውላቸውን ፎርም የመወሰን ሙሉ ነጻነት ስላላቸው በቃልም ሆነ በጽሁፍ መዋዋል ይችላሉ። ነገር ግን ዋስትናን በተመለከተ ሕጉ በልዩ ሁኔታ በጽሁፍ እንዲደረግ ስለሚያዝ በዚሁ አግባብ መፈጸም አለበት። እናም ዋስትና አለ የሚል ተከራካሪ ዋስትና መኖሩን የማስረዳት ሸክም ያለበት ሲሆን፤ የጽሁፍ ማስረጃውንም ማቅረብ ይጠበቅበታል። ከዚህ ውጭ ግን ውሉ ጠፍቷል፣ ተቀዷል ወይም ተሰርቋል ብሎ፤ ግን በአግባቡ ማስረዳት ካልቻለ ዋስትናን በምስክር ወይም በህሊና ግምት አረጋግጣለሁ ማለት የዋህነት መሆኑን ነው ከህጉ ቁጥር 1922 እና 2003 ጣምራ ንባብ የምንረዳው ነው።
የዋስትና ግዴታ ወሰን ያለው መሆኑ አራተኛው የዋስትና ባህርይ ነው። ዋስትና ባለዕዳው ሊከፍለው ከሚገባው ነገር በላይ ወይም የበለጠ ከባድ ወጪን በሚያመጣ ሁኔታ ሊደረግ አይገባም። ይህ ማለት ዋስትና በዋና ግዴታው ልክ የተወሰነ ነው ማለት ነው። ዋናው ባለዕዳ ሊከፍለው የሚገባውን እንጂ የማይገባውን ዋሱ አይጠየቅም። የዋስትና ውሉ ከዚህ በተቃራኒው ዋሱን ከዋናው እዳ በበለጠ እዳ ውስጥ የከተተው ከሆነ ግን የዋሱ ግዴታ በዋናው ግዴታ መጠን ልክ ይቀነስለታል። “ዋስትናዬን አክብዶብኛልና ዋስትናው ፈራሽ ይሁንልኝ” የሚል ክርክር ማንሳት ግን አይፈቀድም።
ባለገንዘቡ ዋሱን ሳያስፈቅድ የዕዳ መክፈያ ጊዜውን ለባለዕዳው አራዝሞለት ከሆነ ዋሱ ነጻ እንደሚሆን ደግሞ ማወቅ ብልህነት ነው። በተራዘመው ጊዜ ውስጥ የባለዕዳው የመክፈል አቅም ቢዳከም፣ ንብረቱን ቢያሸሽ፣ ቢወረስበት ወይም ቢያስተላልፍ በችሮታው ምክንያት ግዴታ ውስጥ የገባውን ዋስ ስለሚጎዳው ነው ህጉ ይህንን መላ ያስቀመጠለት። እዚህ ላይ አንድ መሰረታዊ ቁም ነገር ጨብጦ ማለፍ ያስፈልጋል። ዕዳው ወለድ የሚታሰብበት ከሆነ ወይም ባለዕዳው ዕዳውን በተቀመጠው ጊዜ ካልከፈለ ከዚያ በኋላ ላለው ጊዜ ባለገንዘቡ ወለድ የሚጠይቅ ከሆነ ዋሱ ለወለዱም የተዋሰ ለመሆኑ ሕጋዊ ግምት ይወሰዳል። ከዚህ በተጨማሪም ዋሱ በቂ ማስጠንቀቂያ ደርሶት ለባለገንዘቡ ዕዳውን እንደባለዕዳው ሆኖ ባለመክፈሉ ምክንያት ክስ ቢቀርብበት የዳኝነት ወጪውንም ይከፍላል። ስለሆነም እነዚህ ምክንያቶች የዋሱን ግዴታዎች ከዋናው ዕዳ የበለጠ ያደርጉታል።
አምስተኛው የዋስትና ባህርይ የዕዳው (የግዴታው) ልክ በግልጽ በዋስትና ውሉ ላይ መቀመጥ የሚገባው መሆኑ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ዋስትናው ፈራሽ ነው። ከላይ እንደጠቀስነው አንድ ሰው ዋስ የሚሆነው በችሮታ እንጂ ዋስ በመሆኑ ምክንያት በምላሹ ጥቅም ወይም ወሮታ አገኛለሁ ብሎ አይደለም። ይህ ሰው ታዲያ ሌሎች ሁለት ሰዎች ባደረጉት የጥቅም ግንኙነት ውጤታማ የመሆን ጉዞ ውስጥ በፈቃዱ እጁን ሲያስገባ ከተዋሰለት ሰውም ሆነ ከሌሎች ውጫዊ ምክንያቶች ወደፊት ሊመጡ የሚችሉ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ሁሉ በትከሻው ተሸክሞ ነው።
ስለዚህ ህግ ይህንን ሰው ካልተጠበቁ ሁኔታዎች የሚከላከልበት አንዱ ጋሻ በዋስትና የሚገደድበት የዕዳው ልክ በውሉ ላይ እንዲቀመጥ ግዴታ በመጣል ነው። የገንዘብ ብድር ሲሆን ዋሱ በሙሉ ወይም በከፊል የሚገደድ ከሆነ የገንዘቡ ልክ በግልጽ መቀመጥ አለበት። ሥራ ለሚቀጠር የመንግስት ሰራተኛ ዋስትና ለሚገባ ሰው እስከ ምንያክል ገንዘብ ድረስ ዋስ ስለመሆኑ በግልጽ በዋስትና ውሉ ላይ ሊሰፍር ይገባል።
አርሲ ነጌሌ አካባቢ የሚኖር አንድ ሰው የ20ሺ ብር ኢጣሊያ ሰራሽ የእህል ሚዛን ለጓደኛው ያከራያል። ሌላ ወዳጃቸው ደግሞ ተከራዩ ሚዛኑን ካልመለሰ ተመሳሳዩን ሚዛን በዓይነት ለመተካት ዋስትና ይገባል። ዋናው ባለዕዳ ሚዛኑን ሊመልስ ባለመቻሉ ባለገንዘቡ በዋሱ ላይ ክስ መስርቶ ከወረዳው ፍርድ ቤት ጀምረው እስከ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ድረስ ተከራክረዋል። በፍጻሜውም ሰበር ችሎቱ ዋሱ ግዴታ የገባበትን የሀላፊነት መጠን በዓይነት እንጂ ልኩ ምን ያክል እንደሆነ በገንዘብ ስላልተገለጸ ዋስትናው ፈራሽ ነው ሲል ዋሱን በነጻ አሰናብቶታል። ከዚህ የምንረዳው ታዲያ የዋስትና ግዴታው መጠን በግልጽ በዋስትና ውሉ ላይ መቀመጥ አለበት የሚለው የህጉ አነጋገር በገንዘብ መቀመጥ ይገባዋል በሚል አስገዳጅ ትርጉም በሰበር ችሎቱ የተሰጠው መሆኑን ነው።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2012
(ከገብረክርስቶስ)