የወቅቱ የአዲስ አበባ መልክ ዝንጉርጉር ነው። ዳር ዳሩን ያሉት ሠፈሮቿ ማዲያት ለብሰው በመጎሳቆል የስልጣኔ ያለህ እያሉ ይጮኻሉ። ሥልጣኔው እንኳን ቀርቶብን መሠረታዊ የመብራትና የውሃ አቅርቦት ባገኘን እያሉ የአዲስ አበባ ዳር ሀገር ሠፈሮች ሲነጫነጩ የመሃል አዲስ አበባዎቹም ኸረ ጩኸታችንን አትቀሙን ቢያንስ እናንተ ሠፈር የወንዝ ውሃ እንኳን አይጠፋም እያሉ ይበሻሸቃሉ። ቦሌዎችም ሳይቀሩ “እሳት ካየው ምን ለየው” እያሉ በመብገን “ስም ብቻ እንጂ የተረፈን እኛንም ከእናንተ ብሰናል” በማለት ሲተርቱ ማድመጥ በእጅጉ ቀልብን ይስባል። አንዳንዶች ዘባቾችማ በ1886 ዓ.ም ሰባት ሺህ ማርያ ቴሬዛ ብር የወጣበትንና በሲውዘርላንዱ ተወላጅ በአልፍሬድ ኢልግ ከእንጦጦ ተራራ ላይ ተስቦ ቤተ መንግሥት የደረሰውን የቧንቧ ውሃ የዕድሜ ታሪክ በማስታወስ እንዴት በ125 ዓመት ልንሻሻል አልቻልንም በሚል ቁጭት “ወይ ነዶ!” ሲሉ ይቆጫሉ። መላው አዲስ አበቤ የውሃ ጥም ሲያሳርራቸው የሚከተለውን ጥንታዊ ግጥም ላለመስማት ጆሯቸውን ከደፈኑ ሰንብተዋል። እውነት አላቸው “ውሃ የጠማው አፍ አይዘፍንም!” ይባል የለ።
“አዲስ አበባ ላይ አየነ ታሪክ፣
ውሃ ሲሰግድለት ላጤ ምኒልክ።
እንግዲህ አባ ዳኘው ምን ጥበብ ታመጣ፤
ውሃ በመዘውር ወዳየር ሲወጣ።
እዩት በእኛ ጊዜ እንዲህ ያለ መጥቷል፣
ደግሞ ጥቂት ቢቆይ ከፈረንጅ ይበልጣል።
ውሃ በመዘውር ወደ ላይ ሲወጣ፣
የቆሸሸው ታጥቦ የጠማው ሲጠጣ፣
ከምኒልክ ወዲያ ምንድር ንጉሥ ይምጣ።
የአዲስ አበባን ዝንጉርጉር መልክ ከሚያሳጡት ምክንያቶች አንዱ የመሃል ሕንጻዎቿ በቻይና መስታወት ተገጥግጠው ዓይን ሲያጥበረብሩ የዳር ዳር ሠፈሮች ደግሞ ያለቀሱበት ዓይናቸው ሞጭሙጮ የዝንብ መናሃሪያ ሆኗል። ለእዚህም ነው አንዳንድ ተረበኞች “አዲስ አበባ ውስጥ ኢትዮጵያ አለች፤ ኢትዮጵያም ውስጥ አዲስ አበባ አለች” እያሉ የሚያፌዙት። ነዋሪዎቿን በክረምትም ሳይቀር ውሃ ለማጠጣት ለተሳናት አዲስ አበባም “ቪቫ!” በማለት “ያደንቋታል። ”
የቪቫ አድናቆታችንን እንቀጥል። ኮንትሮባንድ ያዋረዳቸው ርካሽ ሸቀጦች የአዲስ አበባን ጎዳናዎች ስለወረሩ መንገደኞች የሚረማመዱት እንደ በዓል ስጥ የተዘረሩትን ውራጅ ትርኪምርኪዎች እንደ ፌቆ እየዘለሉ ነው። አዲስ አበባ የሚሊዮኖች እናት መሆኗን ለማረጋገጥ ስታትስቲክስ ማቀነባበሪያ ተቋምን ቤት ለቤት እየዞርክ ቁጠር ከማለት ይልቅ ነጋ ጠባ በውራጅ አልባሳቱ ዙሪያ የሚራኮቱትንና ለትራንስፖርት የሚሰለፉትን የሰው ጉንዳን ዜጎቿን ቢቆጥሩ በቀላሉ ስንት ሚሊዮን እንደሆንን ለማወቅ አይገድም።
ስለ ኑሯችንም ቪቫ! ከዕለት ወደ ዕለት እንደ ሮኬት የሚወነጨፈው የገበያዋ ምህዳር ለሸመታ አቅም ያጡ ዜጎችን ጦም ውሎ ማሳደር ከጀመረ ውሎ አድሯል። የዕለት እንጀራ ብርቅ እስከ መሆን ከደረሰባቸው የዓለም የዲፕሎማቲክ ከተሞች መካከል አዲስ አበባዬን የሚቀድም ከተማ አይገኝም። ነዋሪዎቿን ወደ ዳር ለመገፍተር የዘየደችው ብልሃት የመጠለያዎቿን ኪራይ በማናር የአግላይነት ሚናዋን አጠናክራ በመጫወት ላይ መሆኗስ ምስጢር ነው። “ደሃ ዳር ዳሩን፤ ባለጠጋ መሃሉን” የሚለውን ፍልስፍና ለየዋሆቹ የሀገራችን ከተሞች እስከ ማስተማር የደረሰችው ይህቺው ጉደኛ ሸገርም አይደለች።
በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ ከሚንፈላሰሱት የዘመኑ ምጡቅ የቴክኖሎጂ ሥሪት መኺናዎች ጎን ለጎን የሚንኮራኮሩት የጃጁ አውቶሞቢሎች እንኳንስ ለሚያሽከረክሯቸው ባለቤቶቻቸው ቀርቶ አምራቾቹ ራሳቸው ሳይቀሩ መቼ እንደፈበረኳቸው ቢጠየቁ ሊመልሱ ያለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን “የዓለም አቀፉ የአውቶሞቢሎች መብት ተከራካሪ ተቋም” ራሱ ጎስቋሎቹን መኺኖች ወክሎ ለመብታቸው ፍርድ ቤት ቢገትራት አዲስ አበባ መረታቷ አይቀርም። ዕድሜ ለሱማሌ ተራዎቹ “የእጅ ጠቢባን” ይሁን እንጂ ከተዘነጣጠሉና ከተዘነጠሉ ቢጤዎቻቸው እስትንፋስ ባይዘሩላቸው ኖሮ የአዲስ አበቤ መኪኖች በመላ ወደ ሙታን መቃብር ወርደው ሦስት ሰባታቸው በወጣ ነበር።
አዲስ አበባ ከተማ የዓለም አቻ ከተሞችን የምትመራው በርካታ ሪከርዶችን በማስመዝገብ ነው። የመጀመሪያ ሪከርዷ በሰልፍ አንደኛ መሆኗ ነው። ጉዳይ ለማስፈጸም የቀበሌ ሰልፍ፣ ፍትሕ ለማግኘት የፍርድ ቤት ሰልፍ፣ ሃይገርና ሸገር አውቶቡሶችን ለመሳፈር ረጂም ሰልፍ፣ የዕለት ዳቦ ለመግዛት ሰልፍ፣ ወሬ ለማዳመቅ ሰልፍ፣ ያልተጠቀሙበትን የመብራትና የውሃ ቢል ለመክፈል ሰልፍ፣ በየሆስፒታሉ በሽተኛ ለመጠየቅ ሰልፍ፣ ወደ ቀብር ለመሄድ ሰልፍ፣ ከቀብር መልስ በሟቹ ቤት ንፍሮና ጠበል ጠዲቅ ለመቅመስ ሰልፍ። ከወታደራዊ ካምፖች ባልተናነሰ ሁኔታ የዜጎች ሰልፍ ዕለት በዕለት የሚስተዋለው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መሆኑን ለማሳመን መሃላ አያስፈልግም። ቪቫ! ለሰልፈኞች መናሃሪያ ለሸገር!
አንዳንድ ወዳጆቼ የኢሚግሬሽንንና የአሜሪካ ኤምባሲን ሠልፍ እንዳልዘነጋ መክረውኛል። እሺ ብዬ የወዳጆቼን አስተያየት እንዳልቀበል ወርሃዊ ግብራቸውን ከፍለው ከገቢዎች በትር ለመገላገል ፀሐይ የሚያንቃቃቸው ሰልፈኞችን የመሳሰሉት ሌሎች ጉዳዮችም እየታወሱኝ የሰልፋችን አበዛዙ ናላዬን ያዞረዋል። አዲስ አበባ የበርካታ የሩጫ ብራንዶች “ልዕልት” መሆኗንም ባልጠቅስ ደግ አይሆንም። “ታላቅ” የሚል ስያሜ የሚሰጣቸው “የቲ ሸርት” ሩጫዎች በሳምንቱ ማብቂያ ላይ ሳይካሄዱ መዋላቸውን እርግጠኛ አይደለሁም። ትራንስፖርት ለመያዝ የሚደረገው የዜጎቿ የፊጋ ግብግብ እንኳ ደረጃው ከሩጫም ከፍ ስለሚል ስም እስከሚወጣለት ድረስ ደረጃ ለመስጠት መጠንቀቅ ይኖርብናል። ሌላኛው የሩጫ ዓይነት ደንብ አስከባሪዎችና የጎዳና ላይ ነጋዴዎች የሚወዳደሩበትና አሸናፊው በቆመጥ፣ ተሸናፊው በእንባ የሚጠናቀቅበት ትርዒት ነው። የሁለቱ ግብ ግብ ጥንታዊያን ሮማዊያን የሰውን ልጆች ከዱር አራዊት ጋር የሚያታግሉበትን ትርዒትን ያስታውሰኛል። ቪቫ በሩጫ ስሟ ለገነነው ከተማችን።
የ130 ዓመቷ አዲስ አበባ መጃጃቷ ይሁን መሞላቀቋ በማይለይበት ሁኔታ ሲያሻት ወይዘሪት፣ ሲብስባት እማሆይ እየተባለች ስትጠራ ግራ ታጋባናለች። ከኒውዮርክና ከጄኔቫ ከተሞች ቀጥላ ሦስተኛዋ ለእንግዶች የተመቸች የዲፕሎማቲክ ከተማ መሆኗን ለእንግዶቿ ስታስተዋውቅ እኛ ለመዲናችን ቻርተር ተገዢ የሆንን ዜጎቿ “አቤት ውሸት” እያልን ጥርሳችን እንዳይታይ በእጃችን ሸፍነን ስንገለፍጥ እንኳ ይሉኝታ ይዟት እንደማፈር አያደርጋትም። ብራቮ ፊኒፊኔያችን!
እንደ ሰናፍጭ እርሻ በአንድ ቦታ ችምችም ብለው የበቀሉት ሆቴሎቿ በዋጋ ውድነት ራሳቸውን ፑሉቶ ፕላኔት ላይ ሰቅለው “አራት አምስት” በሚሉ የተንሸዋረሩ የከዋክብዋት ደረጃ “እኛ እኮ” እያሉ መመጻደቃቸውን የምንሰማው ጓዳ ጎድጓዳችንን ለመጎብኘት ከሚመጡ የቱሪስት እንግዶች ነው። ይብላኝ ሸገርን ብለው ለሚመጡ እንግዶች እንጂ እኛ ባለሀገሮቹማ በጓዳዋ ውስጥ ሰጋቱራ ከጄሶ ተመጣጥኖ የምንሸምተው የዕለት እንጀራ እስከ ዛሬ አልነጠፈብንም። “እውር አሞራ መቀለብ የማይሳነው አምላክ” በቸርነቱ እያኖረን ነው። እርግጥ ነው አንዳንድ መሠረታዊ ሸቀጦችን በሙዚየም ካልሆነ በስተቀር በቀላሉ ከገበያ እንደማናገኛቸው ከተረዳን ሰንብተናል። ለምሳሌ ነጭ ሽንኩርት፣ ምስርና ቅንጬን የመሳሰሉትን ዱሮ በዕለት ምግብነት ዘንድሮ ለላንቲካ እየተፈለጉ ነው። ቅቤና ማርም የተረፈን ስማቸው እንጂ ባህሪያቸውን ከለወጡ ሰነባብቷል። “ተወዳጇን አዲስ አበባ ተዳፍረን ባንሳደብም” ዘመኑን ግን እንደፈለገን ስንወቅጥና ስናበሻቅጥ ብንውል ዲሞክራሲ ያጎናጸፈን መንግሥትም ሆነ እስትንፋስ የለገሰን ፈጣሪ ላይቆጡን ቃል ገብተውልናል። እኛ ብሶተኞች ዘመኑን ላለመኮነን ብናንገራግርም ዘመኑ ራሱን በራሱ መታዘቡ አይቀርም።
የአዲስ አበባ ውሪ ሕጻናት መጫዎቻ ሜዳቸው በሙሉ “ለትንግርታዊ ልማት” ስለተነጠቀባቸው መጫወቻ ሜዳ በማጣት የፊጥኝ ታስረው ቤት ውስጥ የሚውሉት በታሰረው እጃቸው የቴሌቪዥን ሪሞት እንደጨበጡ ነው። ለድሃ ልጆች “ቃና” ለነምንትስ ቅልጥጤዎች ደግሞ ዲ.ኤስ.ቲቪ ፊታቸው ስለሚገሸርላቸው ምን ተዳቸው። “ልጅነት ተመልሶ አይመጣም” ተረት ተለውጦ “ልጅነት ጅልነት”ን አግንነንላቸዋል። የምን ሀገር! የምን ዜግነት! የምን ብሔራዊ ኩራት ልናወርሳቸው ! የምን አብሮ ማደግ! ለስኬትሽ ክብር ቪቫ አዲስ አበባ!
ተናጣቂ የበዛባት ይህቺ ጉደኛ ከተማችን በእርጅና ስሟ አዲስ አበባ፣ በልጃገረድ ስሟ ወ/ት ፊንፊኔ በፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት ከዓለም ከተሞች ብትወዳደር አሸናፊነቷ የሚረጋገጠው ያለማንም ተቀናቃኝ ነው። በየዕለቱ እንደ ጅብ ጥላ የሚፈለፈሉት “ግራ ገብ የፖለቲካ ቡድኖቿም” እንኳንስ ለእኛ ለተራ ዜጎቿ ለምርጫ ኮሚሽን አለቃቸውም ሳይቀር ዓይነታቸውና ብዛታቸው ግራ አጋብቶታል። ምናልባትም “ዲሞክራሲ” የሚል ቃል በብዛት ከሚነገርባቸው አቻ የዓለም ዲሞክራቲክ ከተሞች መካከል አዲስ አበባችን በረጅም ርቀት ሳትመራ አትቀርም። “የምላስ አደሮቹ” አክቲቪስቶች ቁጥርማ ከተደመረ “የጊነስ ሪከርድ ቡክ” አዘጋጆች የሐምሌውን “የችግኝ ተከላ” ውጤት ወደኋላ አስቀርተው በአንደኛነት ሳይመዘግቧት አይቀሩም። ለዲሞክራቲክ ብቃትሽ ቪቫ ሸገር!
እንደ ቅዱስ መጽሐፉ “የዮናስ የጥላ ዛፍ” በአንድ ጀንበር ተደርድረው የሚበቅሉት የአዲስ አበባ ሊፍት አልባ የኮንዶሚኒዬም ተራሮች ኤሎሄ እያሉ ለሚማጠኑት የከተማዋ ነዋሪዎች በአግባቡ መዳረስ ተስኗቸው የተስፋ ምንጭ ከመሆን ይልቅ ለተስፈኛ ጠባቂዎቿ የእንባ ምንጭ መሆናቸውን ወ/ት ፊንፊኔ የተረዳችው አይመስልም።
በአንፃሩ አዲስ አበባ ራሷን ያለ ስስት እንደ ፋሲካ ዳቦ እየገመሰች በሪል ስቴት ስም የመበልፀጊያ ጎዳናውን ያመላከተቻቸው አብዛኞቹ ባለሀብቶች በቤት ባለቤትነት ተስፋ ሱባዔ እስከመያዝ ለደረሱት ደንበኞቻቸው እየሰጡ ያለው ተስፋ ውሃ እንደማይቋጥር እየታወቀ ከተማችን የመረጠችው ዝምታን ነው። ያልገነቡትን አፓርትመንት ብቻ ሳይሆን ቢቻል ዓየሩንም እስከመሸጥ የማይሰቀጥጣቸው የአዲስ አበባ ቤት አልሚዎች በእንባ በሰበሰቡት ገንዘብ አሜሪካና አውሮፓ እየተዝናኑ ሲንፈላሰሱ አዲስ አበባ አታውቅም አትሰማም ማለት አይቻልም። አካሏን ገምሳ በሰጠቻቸው ጋሻ መሬቶች ላይ ያልገነቡትን ሸጠው በዛቁት ሀብት ዱባይና አቡዳቢ ላይ ለራሳቸው ቪላና “ሰመር ሃውስ” የሚገነቡ ባለሃብቶችንም አፍርታ ዓለምን አስደንቃለች። ይህቺው አዲስ አበባ። በዓለም ላይ በርካታ “የሪል ስቴት አጥፊና አልሚዎችን” በብቷ አቅፋ በመያዝም ተወዳዳሪ የላትም። ቪቫ አዲስ ለደግነትሽ!
የእንባችንን ሣግ ገታ አድርገን ጥቂት የሳቅ እፎይታ እንድርግ!
እውነት እውነት እንመስክር ብንል የአዲስ አበባው ቁንጮ ሰውዬ ቅንና ገር ባህርይ እንዳላቸው እኛ የከተማዋ ዜጎች የተገነዘብነው የመዲናዋን ቁልፍ የተረከቡ ዕለት ያደረጉትን ንግግር ካዳመጥንበት ዕለት ጀምሮ ነው። በርግጥም የከተማዋና የከተሜው አለቃችን የሥራ ሰው መሆናቸውን በአጭር ጊዜ የወንበር ቆይታቸው ማንነታቸውን አስመስክረዋልና ከልባችን፤ ቪቫ ከንቲባችን!
የአዲስ አበባ ከተማ የወንዝ ዳር ልማት ፕሮዤ በእርግጥም በእርሳቸው ዘመን የሚጠናቀቅ ከሆነ ከላይኛው ጠቅላይ ሰውዬአችን ጋር ታሪክ በመንታነት የሚዘክራቸው ነፍስና ሥጋቸው ከተጣመረው “ከቴዎድሮስና ከገብርዬ” ጋር እያመሳሰለ ስለመሆኑ ጥርጥር አይገባንም። የእምነት ደሃ በመሆን ይህ እውነታ የማይዋጥለት ሰው እንኳ ቢኖር “ስድቡ” ሳይሆን የተቃዋሚነት ዲሞክራሲያዊ መብቱ ሊከበርለት ይገባል። የዐድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታ እውነት ሆኖ በተግባር የሚረጋገጥ ከሆነማ የከተማችን አለቃ ስማቸው ሲታወስ የሚኖረው ከምኒልክ ጎን ተጽፎ ስለመሆኑ ጥርጥር አይገባንም። እኒህን ተወዳጅ የከተማችንን የሥራ ሰው የእምዬ ምኒልክን ስምና ተግባር ከሚያንቋሽሹ ወገኖች ክፉ ምላስ ፈጣሪያቸው ይጠብቃቸው፤ ጸሎታችን ነው። የከንቲባችንን በጎነት እየተረክን ቪቫ በማለት ለምንፎክረው ለእኛም ከዘባቾች አንደበት አምላክ ይታደገን።
ሰሞኑን በበጎ ፈቃደኞች ትብብር ያከናወኗቸው ሰፋፊ ሥራዎችም የከተማችንን ቁንጮ ሰውዬ በእጅጉ እያስመሰገናቸው እንደሆነ ብዙ ምስክር መጥራት ይቻላል። ትምህርት ቤቶችን አሳድሰው፣ ለተማሪዎች ዩኒፎርምና መማሪያ ደብተር በነጻ አድለው፣ መምህራኑን በቴክኖሎጂ አስታጥቀው፣ ለበርካታ የኩላሊት ህሙማን ነጻ ህክምና ፈቅደው፣ በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ተማሪዎች ቁርስና ምሳ ለማዘጋጀት ወስነው፣ ሆ! ሆ! ህሊናችንን ካልዋሸን በስተቀር እምዬ ምኒልክም ሆኑ አባባ ጃንሆይ አልፎ አልፎ ግብር ሲያገቡ ካልሆነ በስተቀር ጭቡ ነው ይህንን ይህንንስ አልተገበሩ። እርግጥ ነው ምኒልክ ልጆቻቸውን ውጭ ሀገራት ልከው አስተምረዋል፣ አባባ ጃንሆይም በየትምህርት ቤቱ እየተገኙ ሹራብና ቁምጣ ለተማሪዎች ይሸልሙ እንደነበር ታሪክ ያጫውተናል፣ ብርቱኳንና ሙዝም ለየበዓሉ ማደላቸውን ከህያዋን ከምስክሮች አንደበት እየሰማን ነው። በጥንቱ ምርቃት “ከንቲባችን ሆይ ሺህ ዓመት ይንገሡ!” እንዳንል ዘመነ ዲሞክራሲ ያለመፍቀዱ ብቻ ሳይሆን ለተረበኞች ምላስ እንዳንጋለጥም በመስጋት ጭምር ነው።
እኒህ የከተማችን ሰውዬና የላይኛው ጠቅላዩ የሀገሪቱ አለቃ እየተመካከሩ የሚሠሩት ስራ በእጅጉ “ክፉ ዓይን” እንዳያያቸው እንቱፍቱፍ ሊባልላቸው እንደሚገባ በዕድሜ ታላቅነቴ ትዕዛዝ አውጥቼያለሁ፤ “አሹ ጎፍቶሊ ኬኛ!”። ከላይ በምጸት ሽርደዳ ሕይወትን ለማቅለል ሲባል ብቻ “ቪቫ!” እያልን ሣግ እየተናነቀን ብሶት የዘረገፍንበትን ችግሮቻችንን ፈተው “ስለት የሚሰምር” ከሆነማ አዲስ አበቤ የአበባ ጉንጉን አንገታቸው ላይ ለማጥለቅ መሽቀዳደሙ አይቀሬ ነው። እስከዚያው ግን በቀልድ ሳይሆን የምራችንን ቪቫ አዲስ አበባ! ከንቲባችን እስከ ዛሬ ላከናወኗቸው መልካም ስኬቶችም ብራቮ ሸገር!። ግርሻ ሆነውብን መፍትሔ ላጣንባቸው ለመዲናችን አንገብጋቢ ችግሮች ደግሞ አደራ! አደራ! አደራ! ብልሃት ይበጅላቸው መደምደሚያችን ነው። ሰላም ለኢትዮጵያዊያንና ለአፍሪካዊያን ሁሉ ከተማ ለሸገር !!!
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2012
(በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)