የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እና የግብጹ ፕሬዚዳንት ፊልድ ማርሻል አብዱልፈታህ አልሲሲ ሰሞኑን በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በተካሄደው 74ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ መድረክ ላይ የዓለምን ሕዝብ ቀልብ የሳበ ዲፕሎማሲያዊ ሙግቶችን አድርገዋል፡፡
የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ የመሠረት ድንጋዩ ከተጣለ ስምንት ዓመታት ያለፈውን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገው ድርድር ያሰቡትን ውጤት ያለማግኘታቸው በክፍለ አህጉሩ መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ማስጠንቀቂያ አዘል ንግግር አድርገዋል፡፡
«ያለ በቂ ጥናት ተጀምሯል» ሲሉ የወነጀሉትን የአባይ ግድብን ኢትዮጵያ ስትጀምረው አገራቸው እንዳልተቀየመች፣ ላለፉት አራት ዓመታት የግድቡን የውሀ አሞላል እና አስተዳደር በተመለከተ ሲደረግ የነበረው ድርድር የሚፈልጉትን ውጤቶች እንዳላመጣ ተናግረዋል።
ግብጽ በጉዳዩ ላይ በይፋ ማራመድ የጀመረችው ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ትንሽ ሰንበት ያለ ነው። የውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ ሳሜህ ሽኩሪ በካይሮ የአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ በድርድሮቹ ኢትዮጵያ «ግትር» ሆናለች ሲሉ መውቀሳቸውን አል ሞኒተር የተባለው የግብጽ ጋዜጣ ዘግቧል። የግብጽ ውጭ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ሐምዲ ሎዛ በበኩላቸው መቀመጫቸውን በካይሮ ካደረጉ የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮች ጋር በጉዳዩ ላይ ባደረጉት ውይይት “ኢትዮጵያ የሌሎች አገሮችን ጥቅም ችላ በማለት የራሷን አተያይ ብቻ ለመጫን ጥረት እያደረገች ነው” ሲሉ ወቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ መድረክ ላይ በአማርኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግር ለግብጹ ፕሬዚዳንት ንግግር አንጀት አርስ ምላሽ ሰጥተዋል። “ግብጽ በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ከትብብር ውጪ ሌላ አማራጭ የላትም” ነበር ያሉት፡፡
የቀድሞ ስመጥር ዲፕሎማት እና የአሁኗ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፤ የወንዙ አጠቃቀም በዓለም አቀፍ መርሆዎች ብቻ መመራት እንደሚገባው የኢትዮጵያ የጸና አቋም ነው ብለዋል። አያይዘውም የአባይ ወንዝ ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሀብት እንጂ የጥርጣሬ እና የውድድር ምንጭ ሊሆን አይገባም። የአባይን ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ለመጠቀም የተፋሰሱ ሀገራት በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ሲሉ አክለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለግብጽ ያደላል የሚባለውና እ.ኤ.አ. በ1929 በታላቋ ብሪታኒያ የተፈረመው የናይል የውሃ ክፍፍል ስምምነት እንዲቀየር እንደምትፈልግ በተደጋጋሚ አቋሟን መግለጿ የሚታወስ ነው። ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ በአሁን ጊዜ ተቀባይነት ያለው መርህ የእኩል ተጠቃሚነትና ጉዳት ያለማድረስ መርሆዎች ናቸው። በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት የ1929 እና የ1959 ስምምነት ሙሉ በሙሉ ግብጽን እና በከፊል ሱዳንን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ዘጠኙን የተፋሰስ ሀገራት ያገለለ በመሆኑ የአባል ሀገራቱ ስምምነት ሳያገኝ ቀርቷል።
የግብጽ ጥርጣሬ ማገርሸት መነሻ
ግብጻውያን የፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ አስተዳደርን በሙስናና በሀብት ብክነት መክሰስ ከጀመሩ ሰንበት ብለዋል። ከሳምንታት በፊት ግን ይህ ክስ ወደቁጣ ተቀይሮ የታህሪር አደባባይ ከስድስት ዓመታት እፎይታ በኋላ በሚሊየን የሚቆጠሩ ግብጻውያንን ተቃውሞ ለማስተናገድ በቅቷል። አልሲሲ የግብጻውያንን ምድር አንቀጥቅጥ ተቃውሞ ከ1 ሺ 200 በላይ ንጹሀንን የጥይት ራት በማድረግ በኃይል ለመጨፍለቅ ያደረጉት ሙከራ እንደማይሳካ በተረዱ ጊዜ አጀንዳውን ወደአባይ ወንዝ አዞሩት። እነሆም አልሲሲ የአባይን አጀንዳ መዝዘው ሕዝባቸውን መካሪ ሆነው ብቅ አሉ፡፡
“በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት የጀመረችው ሃገራቸው እ.አ.አ. በ2011 የገባችበትን ቀውስ ተከትሎ መሆኑን ‘አህራም ኦንላይን’ ከተባለው የዜና ወኪል ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
”ግብጽ በዚያ ወቅት አለመረጋጋት ውስጥ ባትሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ መገንባት አትጀምርም ነበር” ካሉ በኋላ ”ከ2011 ግርግር ግብጻውያን ብዙ መማር ያለባቸው ነገሮች አሉ። ይህንን ትልቅ ሃገራዊ ስህተት ልንደግመው አይገባም” ሲሉ ምክር ለግሰዋል፡፡
ይህ ንግግር እንዲሁ ለይስሙላ የተነገረ አለመሆኑን ያረጋገጠው መድረክ ደግሞ በ74ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ላይ አልሲሲ በአማልዱኝ ቅላጼ ኢትዮጵያ ላይ ያቀረቡት ክስ ነበር። የክሱ ጭብጥ በአጭሩ ኢትዮጵያ የግብጽን ጥቅም በሚጻረር ሁኔታ የግድብ ግንባታ እያከናወነች ስለመሆኗ እና እስካሁን የተደረጉ ድርድሮች ፍሬ አልባ መሆናቸውን የሚያትት ነበር። ከሳምንት በፊት በካይሮ ሲካሄድ የነበረው ውይይት ያለውጤት መበተኑም የግብጽ ግለኝነት የፈጠረው ችግር ነጸብራቅ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ላለመግባባቱ መነሻ የሆነው ግብፅ ግድቡ በሰባት ዓመታት ውሀ እንዲሞላ ያቀረበችው ምክረ ሐሳብ ነበር።
ኢትዮጵያ ይህን ምክረ ሃሳብ እንደማትቀበል የውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ገልጸዋል። ሚኒስትሩ ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ግብፆች «የህዳሴ ግድብ በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የመልቀቅ ስምምነት እንዲደረስ ይፈልጋሉ። ይኸ ደግሞ ተገቢ አይሆንም። ያንን ያህል ውኃ ወደ ታች የማስተላለፍ ግዴታ ልንስማማ አንችልም» ብለዋል። የአስዋን ግድብ የውኃ መጠን ከ165 ሜትር በታች ከቀነሰ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሀ በመልቀቅ ብቻ እንዲገታ የግብጽ ተደራዳሪዎች ያቀረቡትን ጥያቄ ኢትዮጵያ ውድቅ ማድረጓንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
አልሲሲ ማንናቸው?
ነፍሳቸውን ይማርና፤ ፍርድ ቤት ውስጥ በድንገት ተዝለፍልፈው በመውደቅ ድንገተኛ ሞትን ያስተናገዱት የቀድሞ የግብጽ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ ነሐሴ 12 ቀን 2012 (እ.ኤ.አ.) ጄኔራል አብደል ፈታህ አልሲሲን በመከላከያ ሚኒስትርነትና በጠቅላይ ኤታማዦርነት ሲሾሙ ጦሩን በሕዝባዊ አብዮት ከስልጣን ከተወገዱት ከሆስኒ ሙባረክ ታማኞች የማፅዳት ርምጃ ተደርጎ ነበር። በርግጥ ከአብዛኞቹ የጦር ጄኔራሎች ወጣቱ፣ መስጊድ አዘውታሪው፣ ስለፖለቲካ ብዙም የማያውቁና የማይታወቁትም ጄኔራል የነናስርን ፖለቲካዊ አስተምህሮ ከጦሩ አርቀው ወታደሩን በወታደርነቱ ብቻ እንዲያገለግል የሚቀርፁ፣ በውጤቱም ለጅምሩ ዴሞክራሲዊ ስርዓት ፅናት የሚታትሩ መስለውም ነበር።
መንግስት የሚቆጣጠራቸው መገናኛ ዘዴዎችም «አብዮታዊ አስተሳሰብ ያላቸው የጦር አዛዥ» እያሉ አንቆለጳጵሰዋቸዋል። ከዓለም የ10ኛ ደረጃ የያዘውን ግዙፍ የጦር አዛዥነት ሥልጣንን ድንገት የተረከቡት አልሲሲ ስልጣን በያዙ በሰባተኛው ወር ለጦሩ ያስተላለፉት መልዕክት ግን ሰውዬው የመሰሉትን እንዳልሆኑ፣ የታመኑትን እንደማይጠብቁ፣ ምናልባትም ለፍትሕና ዴሞክራሲ ሥፍራ እንደሌላቸው ጠቋሚ ሆነ። ሲና ከእስራኤል አገዛዝ ነፃ የወጣችበት በዓል ሚያዚያ 28 ቀን 2013 ሲከበር ባደረጉት ንግግር «ግብፃውያንን የሚጎዳ የማንኛው ኃይል እጁ ይቆረጣል» ነበር ያሉት። መልዕክቱ ግብፃውያንን አከራክሮ ሳያበቃ አይናፋሩ ጄኔራል የሾሙ የሸለሟቸውን፣ ያመኑ-ያስጠጓቸውን ከሁሉም በላይ በሕዝብ የተመረጡትን የፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲን የስልጣን ገመድ በጥሰው ጣሉት።
የሐምሌ 3 ቀን 2013 መፈንቅለ መንግስቱ፣ ጅምሩ ዴሞክራሲ መጨናገፉን የሚያረጋግጥ፣ ትልቂቱን፣ የረጅም ታሪክ ባለቤቲቱን አረብ-አፍሪቃዊት ሀገር ከ1952 ጀምሮ ወደነበረችበት ወታደራዊ አገዛዝ እንደሚመልስ የተናገሩ፣ ያስጠነቀቁ፣ ባደባባይ የተቃወሙትም ብዙ ነበሩ። «እዚህ አደባባይ የወጡት ሰዎች የግብፅ የመጀመሪያው ዴሞክራሲ ገና ሲወለድ መጨናገፉን የሚቃወሙ ናቸው። ወታደራዊው መፈንቅለ መንግስት ሕገ-መንግስቱንም የሚፃረር ነው» ብለው ነበር፡፡
የሰማ እንጂ የተቀበላቸው ብዙም የለም። በተለይ የርዕሠ ከተማ ካይሮ ነዋሪዎች ከዓመት በፊት በአብላጫ ድምፅ የመረጧቸው ፕሬዚዳንት ከስልጣን መወገዳቸውን ደግፈው ባደባባይ ቦረቁ። የመፈንቅለ መንግሥቱን መሪና አስተባባሪ የጄኔራል አልሲሲን ፎቶ ግራፍ አንግበው ያደንቁ፣ ያወድሱ፣ ያሞግሷቸው ገቡ።
አልሲሲ ገማል አብድናስርን፣ በጥቂቱ አንዋር አሳዳትን መሆናቸውን አረጋገጡ። የሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበር መሪዎችን፣ አባላትን እና ደጋፊዎችን እያስለቀሙ ወሕኒ ወረወሯቸው። የማሕበሩን መገናኛ ዘዴዎች፣ ፅሕፈት ቤቶች፣ የርዳታ ድርጅቶች፣ ትምሕርት ቤቶችን በሙሉ ዘጉ።
አልሲሲ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲን ሐምሌ መጀመሪያ ላይ ከስልጣን ለማስወገዳቸው የሰጡት ሰበብ ሰኔ ላይ የሙርሲን አገዛዝ ባደባባይ ሰልፍ ለመቃወም የወጣውን ሕዝብ የሙርሲ ደጋፊዎች አጥቅተዋል የሚል ነበር።
ጄኔራሉ የመሩትን መፈንቅለ መንግስት በመቃወም አደባባይ የወጡ በመቶ የሚቆጠሩ ሰልፈኞችን በጅምላ አስረሸኑ። ሺዎችን አሰሩ። የሙስሊም ወንድማማቾችን ጨምሮ የተለያዩ ማሕበራትን፣ ነፃ መገናኛ ዘዴዎችን ዘጉ። መንግስታቸው ሳይፈቅድ የአደባባይ ሰልፍ እንዳይደረግ አገዱም። ለራሳቸው ግን የማርሻልነት ማዕረግ ደረቡ።
የአልሲስን ርምጃ ቀድመው የደገፉት ሕዝባዊው አመፅ እንደ ቤን ዓሊ፣ እንደ ሙባረክ ለዘመናት ከቆዩበት ቤተ-መንግስት አሽቀንጥሮ ይጥለናል ብለው የፈሩት የሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት ኤሚሬቶች ነግስታትና ብጤዎቻቸው ነበሩ።
ሁለቱ ሀገራት የማርሻሉን የአፈና ርምጃ ለማጠናከርም በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወደ ካይሮ ያንቆረቁሩ ገቡ። ሌላ ሀገር የሚደረግ መፈንቅለ መንግስትን ለማውገዝ ሰዓታት የማይፈጅባቸው የዋሽግተንና የብራስልስ ፖለቲከኞችም (ከያኔው የጀርመን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በስተቀር) የአልሲሲን መፈንቅለ መንግስት ባይደግፉት እንኳን በይፋ አላወገዙትም።
አልሲሲ የማርሻል ማዕረጋቸውን አውልቀው በኮት-ከራባት ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ እንኳ ተቺዎቻቸውን እያሳደኑ ማሰር-ማስፈረዱን አላቋረጡም። ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደዘገበው የአልሲሲ መንግስት በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ፖለቲከኛ፣ ጋዜጠኛና የመብት ተሟጋቾችን አስሯል።
የመብት ተሟጋቹ የአልሲሲን አፋኝ፣ ጨቋኝነት በይፋ በሚያወግዙበት ወቅት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በክብር እንግድነት ጋበዟቸው።
መስከረም 2017 – ዋይትሀውስ
«የግብፁ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ዛሬ እዚህ በመምጣታቸው ታላቅ ክብር ተሰምቶኛል። በተለያዩ መስኮች ለረጅም ጊዜ ጠንካራ ሥራ አከናውነናል። ብዙ ውጤትም አግኝተናል። ላደረጉት በሙሉ አመሰግናለሁ። አደንቃለሁም። እኛም የሰራነውን እንደሚያደንቁ አውቃለሁ። ግንኙነቱ በጣም ጥሩ ነው።»
ትራምፕ አልሲሲንና ስራቸውን ሲያደንቁ ቢያንስ 12 የአሜሪካ ዜጎች ግብፅ እስር ቤቶች ውስጥ ይማቅቁ ነበር። አልሲሲ ግብፅን እስከ 2034 ድረስ መግዛት የሚያስችላቸው ሕገ-መንግስት ያስረቅቁ ነበር።
የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እንደራሴዎች (ሴናተሮች) ፕሬዚዳንቱ የግብፁን አምባገነን እንዳያነጋግሩ፣ ካነጋገሩም የአልሲሲን ጭቆና እንዲቃወሙ ይጠይቁ ነበር። ሴናተር ፓትሪክ ሌሒ አንዱ ናቸው።
«አሁን ባለው ፕሬዚዳንት አመራር ግብፅ በጣም አደገኛ ጎዳና እየተከተለች ነው። ፍፁም ጨቋኝ አምባገነን ሥርዓት ነው። »ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሴናተሮቻቸውን ተቃውሞ፣ የመብት ተሟጋቾችን አቤቱታ፣ የፖለቲካ ተንታኞችን ብያኔን ምናልባት ፈጥነው አውቀውት ይሆናል። በይፋ የተናገሩት ግን ባለፈው ነሐሴ ቢያሬትስ-ፈረንሳይ በተሰየመው የቡድን ሰባት ጉባኤ ላይ ነበር። ትራምፕ ከግብፁ መሪ ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ ወደያዙበት ክፍል ሲገቡ «የምወደው አምባገነን የታለ?» ብለው ጠየቁ አሉ እዚያ የነበሩ።
ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው ትራምፕ ያሉትን ሲሉ የግብፁን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጨምሮ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ይሰሙ ነበር። የቀድሞው ማርሻል የሰሙት ግን ቁልምጫውን ነው።
«ፕሬዚዳንት አልሲሲ መጀመሪያ ካገኘኋቸው ጊዜ ጀምሮ በጣም ከምቀራረባቸው ሰዎች አንዱ ናቸው። መጀመሪያ ያወቅኋቸው በምርጫ ዘመቻዬ ወቅት ነው። ፕሬዚዳንት አልሲሲ በጣም አስቸጋሪ በሆነ-ሁኔታ በርካታ አስገራሚ ስራዎችን ሰርተዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ከግብፅ እና ከግብፅ ሕዝብ ጎን እንደቆመች ነው። ትደግፋችኋለች። ክቡር ፕሬዚዳንት ለርስዎ ማለት እምፈልገው ከዩናይትድ ስቴትስና ከኔ ጠንካራ ድጋፍና ወዳጅነት አላችሁ »ነበር ያሉት፡፡
በፕሬዚዳንት ትራምፕ አገላለፅ ዩናይትድ ስቴትስ ከጎኑ የማትለየው የግብፅ ሕዝብ ከስድስት ዓመታት ትዕግስት፣ አፈና፣ መከራ፣ ፍራቻ በኋላ የአልሲሲን አገዛዝ ባደባባይ ተቃወመ። ሰሞኑን በየከተማው አደባባይ የወጣው ሕዝብ ቁጥር የሚሊዮኖችን ሰልፍ ለለመደችው ግብፅ በርግጥ ትንሽ ነው። በመቶ የሚቆጠር። ኢምንቶች ሚሊዮኖች እንደሚሆኑ ግን ከራስዋ ከግብፅ፣ ከ2011ዱ ሰልፍ ሌላ የተሻለ ምሳሌ በርግጥ የለም።
ከካይሮው ታህሪር አደባባይ፣ እስከ ሜድትራንያን ባሕር ጥጓ ከተማ አሌክሳንደሪያ፣ ከቀይ ባሕሯ ዳርቻ ስዊዝ እስከ ዓባይ ዳርቻዋ ማሐላ በየስፍራው የተሰለፈዉ ሕዝብ ያቀነቀናቸው መፈክሮችም የሚደርስበትን ጭቆና፣ ያለበትን ፍራቻ በግልፅ መስካሪ ነው።«ተናገር። አትፍራ። ሲሲ (ከስልጣን) መወገድ አለባቸው።»
የአልሲሲ መንግስት ተቃዋሚ ሰልፈኛን አሸባሪ እያለ ባደባባይ ሲረሽን፤ እያፈሰ ሲያስር፣ ሲያሰቃይ ያየ፣ ሰልፍ እንዳይደረግ በሕግ መታገዱን የሚያውቅ ግብፃዊ መፍራቱ አያስወቅሰውም። የሰልፈኛው ቁጥርም ካነሰባቸው ምክንያቶች አንዱ ፍራቻቸው ነው።
የተቃውሞው መነሻ ፕሬዚዳንቱና የጦር አዛዦቻቸው በሙስና ተዘፍቀዋል መባሉ ነው። ከሐገሩ ተሰድዶ ስፔን የሚኖር አንድ ግብፃዊ እንዳጋለጠው አልሲሲና የጦር አዛዦቻቸው ከመንግስት ካዝና በሚወስዱት ገንዘብ የየግላቸውን ቤተ-መንግስት አከል ቤት እየገነቡ፣ ኑሯቸውን እያቀማጠሉ፣ ዘመድ ወዳጆቻቸውን እያበለፀጉ ነው።
የግብፅ የጦር ጄኔራሎች በሙስና የተዘፈቁ፣ የትላልቅ የንግድ ድርጅቶችና ተቋማት ባለቤቶች መሆናቸው ለግብፅ ሕዝብ በርግጥ እንግዳ አይደለም።
ስፔን የተሰደደው ግብፃዊ በማኀበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ያሰራጨው መልዕክት ግን ግብፃዊው ወትሮም በየቤቱ የሚያብሰለስለውን ሐቅ ባደባባይ ያፈነዳ፣ የሕዝብን የጋራ ብሶት ያጋለጠ በመሆኑ ከ2013 ወዲህ እርስ በርሱ የሚጠራጠረውን ወጣት በጋራ ማቆም፣ በቀላሉ ማሳደም ችሏል።
ፕሬዚዳንት አልሲሲ ሕዝብን ለተቃውሞ ስላሳደመው ሙስና በቀጥታ ያሉት ነገር የለም። ባለፈው ሳምንት ካይሮ ውስጥ ለተሰበሰቡ ወጣቶች ባደረጉት ንግግር ግን ጦር ሠራዊታቸው በሙስና መታማት፣ መተቸት የለበትም በማለት አሳስበዋል። ለግብፅ ጦር በየዓመቱ የአንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያ የምታስታጥቀው ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ናት። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከግብፅ ሕዝብ ጎን እንቆማለን ሲሉም አብነት የተጠቀሱት አፋኝ አምባገነን ገዢ፣ ሙስኛ ጄኔራሎች ለሚያዙት፣ ግብፃውያንን በተለይ ሲናዎችን አንዴ አሸባሪ ሌላ ጊዜ የአሸባሪ ተባባሪ እያለ ለሚገድለው ጦር አሜሪካ የምታስታጥቀውን ጦር መሳሪያ ነው።
«የጦር ኃይላችንን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ከፍተኛ ደረጃ እየገነባን ነው። የተዋጊ ጄቶች ግዢ ትዕዛዝ፣ የመርከቦች ትዕዛዝ፣ የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች ትዕዛዝ፣ የጦር ኃይላችን በጣም እያዘመንን እያደረጀን ነው። በዚህ ባለንበት ወቅት ከምንጊዜውም በላይ የሚያስፈልገን ይኽ ነው።»
የሰሞኑ ተቃውሞ ሰልፈኛ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳያግደው አደባባይ ወጥቶ በወታደሮች ጥይትና አስለቃሽ ጢስ መሀል አልሲሲን በግልጽ “በቃህ” ብለዋቸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት አልሲሲ በወታደሮቻቸው ጉልበት እና በአባይ ወንዝ አጀንዳ ተከልለው የገጠማቸውን ተቃውሞ ለመሻገር ላባቸውን እየዘሩ ነው። ፕሬዚዳንቱ ከመጣባቸው ሕዝባዊ ናዳ በአንዳች ተአምር ይተርፉ ይሆን? በጊዜው የምናየው ነው። (ማጣቀሻዎች፡- የጀርመን ድምጽ፣ ቢቢሲ፣ ሮይተርስና ፋና ናቸው፡፡)
ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2012
(ፍሬው አበበ)