አህመዲን ጀበል በማረሚያ ቤት ቆይታው በጻፈው “ፈርዖን የአምባገነኖች ተምሳሌት” በተሰኘ መጽሐፉ የቀበሮ ስትራቴጂ በሚል ርዕስ የጻፈውን የጎሽና ቀበሮ ታሪክ ለዛሬው ጽሑፌ ማንጸሪያ አድርጌ ተጠቅሜዋለሁ። ታሪኩን ስታነቡ ጎሾች ለተለያዩ ኃይሎች መጠቀሚያ እየሆኑ ያሉትን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፤ ቀበሮዎቹ ደግሞ ጽንፈኛ አክቲቪስቶችን፣ ብጥብጥን አጀንዳቸው ያደረጉ ፖለቲከኞችንና አክራሪ ሃይሎችን እንደሚወክሉ እያሰባችሁ ይሁን።
ጐሽ በጉልበትም ሆነ በአካላዊ ግዝፈቱ ከቀበሮ በአራት እጥፍ ይበልጣል። ሆኖም ከጥንት ጀምሮ ጐሽ በቀበሮ እየታደነ ይበላል። ይህ እንዲሆን ያደረገው ቀበሮው ስኬታማ ስትራቴጂ በመከተሉና ጎሽም ከስህተቱ ለመማር ባለመቻሉ ነው። አንዲት ቀበሮ ለብቻዋ አንድ ጐሽን ለመፋለም አትደፍርም። ቀበሮዎች አቅማቸው ከጐሽ እንደሚያንስ ስለሚያውቁ በተናጠል ጐሽን ለማደን አይነሱም። ከዛ ይልቅ ተሰባስበው ስትራቴጂ ይነድፋሉ። ከዚያም በጉልበትም ሆነ በብዛት ከሚበልጧቸው ጐሾች መካከል አንዱን ለማደን በቡድን ወደ ጐሾቹ መንጋ ይጠጋሉ። ዕቅዳቸው እንዲሳካም በመጀመሪያ ሆን ብለው ጐሾችን ያስደነብራሉ። ጐሾቹም በሚያሳዝን ሁኔታ ከጥንት ጀምሮ በአባቶቻቸው ላይ ሲፈጸም ከነበረው ጥቃት ትምህርት ሳይወስዱ ሁሌም በተመሳሳይ መልኩ ስሜታዊ ምላሽ ይሰጣሉ።
ጐሾች በብዛት ከቀበሮዎች ቢልቁም ተሰብስበው አብረው ከመታየት ውጪ የሚያስተሳስራቸው ጠንካራ አንድነት የላቸውም። በተናጠል እንጂ እንደ ቡድን አያስቡም። ይህ በመሆኑ ቀበሮዎች ሊያጠ ቁዋቸው ሲጠጓቸው እያንዳንዱ ጐሽ በስሜት ራሱን ለማዳን ይበረግጋል። ቀበሮዎች የሚያስደነብሯቸው ከመንጋው ነጥለው ወደ ፈለጉት አቅጣጫ ሊወስዷቸው መሆኑን ጐሾቹ አይረዱም።
ስለዚህ እያንዳንዱ ጐሽ ራሱን የሚከላ ከልበትን ቀንድ ተሸከሞ ተደናብሮ ይሸሻል። በዚህ ጊዜ ቀበሮዎቹ ለመታደን ምቹ በሆነው ጐሽ ላይ ትኩረታቸውን ያደርጋሉ። ኃይላቸውን አቀናጅተውም በመረባረብ ጐሹን በቁጥጥራቸው ሥር ያውሉታል፤ ቀለባቸውም ያደርጉታል። ጎሾቹ ጠላቶቻቸውን ለመመከት አንድ መሆን ሲገባቸው መበታተንን በመምረጣቸው በየተራ የቀበሮዎች እራት ይሆናሉ። እያንዳንዱ ጐሽ መሸሹን እንጂ ዛሬ ማምለጥ ቢችል እንኳ ቀጣይ ባለተራ መሆኑን አይረዳም።
ጐሾቹ በቀንዳቸው ለመጠቀም ሳይሞ ክሩ መሮጣቸው ምን ያህል በስሜት እንደ ሚነዱ ያሳያል። ቀበሮዎች በበኩላቸው በተናጥል ጐሽን ማሸነፍ እንደማይችሉ ተረድተው በጥናት ላይ የተመሰረተ ስልት ነድፈው በጋራ መንቀሳቀሳቸው የሰለ ባቸውን ዳካማ ጎንና ስነልቦና ጠንቅቀው እንደሚያውቁና ምቹ ጊዜ እንደሚጠብቁ ያሳያል። ለዚህ ነው ጥቂት ቀበሮዎች የጐሽ መንጋን በማስበርገግ ወጥመዳቸው ውስጥ የገቡትን በቀላሉ ተከታትለው የሚያድኑት። ጐሾችም በስትራቴጂና በቡድን ስሜት ባለመንቀሳቀሳቸው ብዛታቸውና ጉልበታቸው ምንም ሳይጠቅማቸው በየተራ የቀበሮዎች ቀለብ የሚሆኑት።
ከዚህ የጐሽና የቀበሮ ታሪክ የስትራቴጂን ወሳኝነት እንረዳለን። ትክክለኛ ስትራቴጂ በመቅረጽ በአንድነት ለተግባራዊነቱ የሚንቀ ሳቀሱት ቀበሮዎች በብዛትና በኃይል የሚበል ጣቸውን የጎሽ መንጋ ማሸነፍ ችለዋል። ያለ ስትራቴጂ በተናጠል የሚንቀሳቀሱት ደግሞ የቱንም ያህል ብዛት፣ ኃይል፣ ሀብት፣ ሌላም ነገር ቢኖራቸው እንኳን እንደጐሾቹ መጠቃትና መሸነፍ ዕጣ ፈንታቸው ሆኖ ይቀጥላል።
ታሪኩ እንደሚነግረን ቀበሮዎች ሆን ብለው ጐሾችን አስደንብረው በመበታተን በቁጥር መብዛታቸው ትርጉም እንዲያጣ በማድረጋቸው ጐሾች ቀንዳቸውን ተሸክ መው ለጥቃት ተጋልጠዋል። ደንብረው በፍርሃት ስለተዋጡ በተናጠልም ሆነ በቡድን ኃይላቸውን መጠቀም አልቻሉም። ጎሾች አደጋ ባንዣበበ ቁጥር ሮጦ ለማምለጥ እንጂ ሁኔታውን ለመመርምር ባለመጣመራቸው ካለፈ ታሪካቸው መማር ሳይችሉ ቀርተው በየተራ የጥቃቱ ሰለባ ይሆናሉ።
ቆም ብለው እየሆነ ያለውን ባስተውሎት መመልከት ቢችሉ ኖሮ የቀበሮዎችን ዕቅድና ስትራቴጂ እንዲሁም የራሳቸውን ድክመት ተረድተው ሲሳይ ከመሆን ይድኑ ነበር። ነገር ግን ይህን ማድረግ ባለመቻላቸው ሕይወታቸውን የሚያጡት እንደ ቀድሞ የአብራኮቻቸውን ክፋይ ለመታደግ ሲፋለሙ ሳይሆን ለቀበሮ ዕቅድ መሳካት ነው። እናም ለፍቅር ሲሉ መሰዋታቸውን የሚገልጸው “ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች” የሚለው አኩሪ ብሂል በድክመታቸው ምክንያት “ጎሽ ለቀበሮ ስትል ተወጋች” በሚል አንገት የሚያስደፋ አባባል ተተክቷል።
ጎሾች መጠየቅ መጀመር አለባቸው። ወገኖቻችን እንዴት በቀበሮዎች ወጥመድ ውስጥ ሊወድቁ ቻሉ ? ትናንት የመታን ድንጋይ ለምን ዛሬም መልሶ ይመታናል ? በሆነ ባለሆነው ለምን እንበረግጋለን ? ለምንድን ነው በጥቂት ቀበሮዎች እየተነዳን ወደ ሞት ጎዳና የምንተመው ? መለያየታችን ጠቀመን ወይስ ጎዳን ? በአንድ ቦታ መሰባሰባችን ብቻውን “አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል” አይሆንም ? ከዚህ በኋላስ የሚደገስልንን ሞት ማምለጥ የምንችለው እንዴት ነው ? … እያሉ።
ይሄኔ ከእንቅልፋቸው ይነቃሉ። ቀንዳ ቸውን ስለመጠቀም ያስባሉ። አንድ የመሆንና የመተባበር ጥቅም ይከሰትላቸዋል። በጥቂት ቀበሮዎች አሮጌ ቅኝት ተደናብረው ከመጨፈር ተቆጥበው በአንድነት ጸንተው ይቆማሉ። ስትራቴጂያቸው የተበላ ዕቁብ መሆኑ ሲገባቸው ቀበሮዎችም በጉድጓዳቸው መክረው ሆዳቸውን ለመሙላት ሌላ አማራጭ ይፈልጋሉ። አቅማቸውን ያውቃሉና ደግመው በአንድነት መንፈስ የተጠመቁት ጎሾች አጠገብ ድርሽ አይሉም።
በመንጋነት መቆየትን የመረጡ ጎሾች የመሪያቸውን ድምጽ ለመስማት ጆሯቸውን ይሰጣሉ። እናም እንዲህ ሲባሉ ያዳምጣሉ
“እነርሱ በሰላማዊ ቦታ፣ በድሎት ሥፍራ ተቀምጠው ባለ መጥፎ ጠረን የቃላት ዘመቻቸውን ወደ መማሪያ ግቢዎቻችሁ ይልካሉ። የሐሰት ወሬ፣ የግጭት ቅስቀሳ፣ የብሔር ጥላቻ፣ በየኮሌጆቹ በየማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ይልካሉ። እርስ በእርሳችሁ እንድትጠራጠሩ፣ እንድትከፋፈሉና እንድት በጣበጡ ያደርጋሉ። በመጨረሻም በገዛ እጃችን ወደ ቆፈሩልን ጉድጓድ ሰተት ብለን እንገባለን። እነርሱ ምንም አይሆኑም። በድኻው ልጅ ሕይወትና ሕልም ላይ ግን ይጫወታሉ። ተዋጉ ብለው ከቢጤዎቻቸው ጋር በግፍ በሰበሰቡት ገንዘብ ራት ይገባበዛሉ። ተነሡ ብለው ወደ ምቹ አልጋዎቻቸው ሄደው ይተኛሉ። እናንተ ተሠዉ፣ ሙቱ ብለው ሰብከው ሲጨርሱ እነርሱ ግን እድሜያቸውን ለመቀጠል ልጆቻቸውን ይዘው ለእረፍት ለሽርሽር ይሄዳሉ። ወጣቶች በፍጹም አትሞኙ። ማንኛውም ነገር ከማድረጋችሁ በፊት ወላጆቻችሁን፣ ሀገራችሁንና የነገ ተስፋችሁን አስቡ። እናንተ ግብ ያላቸሁ ወደ አቀዳችሁት ዒላማ የምትገሠግሡ ባለ ሕልሞች ናችሁ። በተቆፈረለት መንገድ ሁሉ የምትፈሱ የትውልድ ኩሬና የመስኖ ውኃ አይደላችሁም።”
መነጣጠላቸውን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው የሚያስተሳስራቸውን ገመድ ጨርሰው በመቆራረጥ ዝርያቸውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የሚቋምጡ ቱሪስት ቀበሮዎችም ምኞታቸው ቅዠት ሆኖ ይቀራል። አንድ በመሆናቸውና በመተባበራቸው ምክንያት ራሳቸውን ከጥቃት ተከላክለው ሰላማዊ ህይወት መምራት ይጀምራሉ። መጪው ጊዜያቸውም ብሩህ ይሆናል።
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2012
የትናየት ፈሩ