አዲስ አበባ፡- አገሪቱ ካላት የሚዳሰሱና
የማይዳሰሱ ሀብቶች አንፃር ብዙዎቹ ቅርሶች በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የትምህርት እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ያልተመዘገቡ
ቢሆንም ቅርሶቹን ለማስመዝገብ የሚደረገውን ያህል ጥረት ደግሞ ከተመዘገበ በኋላ ትኩረት እንደማይሰጠው ተገለጸ::
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝም ቢሮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ከፍተኛ የጥናት እና ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቅርስ ባለሙያ መምህር መክብብ ገብረማርያም በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ከምዝገባ በኋላ መሰራት ያለባቸው ሥራዎች በአግባቡ እንዲሰሩ ኃላፊና ባለሙያ ተመድቧል:: መመሪያና ፖሊሲም ወጥቶ በየሥራ ድርሻው መተግበር ያለባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ተለይተዋል:: ሆኖም በተሰጠው ትኩረት ልክ እየተሰራ አይደለም:: ከግል ተነሳሽነት ባለፈ ትኩረት ሰጥቶ መሰራት ያለባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ለሚመለከተው ሰጥቶ ማሰራትና መሥራትም ላይ ችግር አለ ብለዋል::
እንደ መምህር መክበብ ማብራሪያ፤ አብዛኞቹ በዩኔስኮ ምዝገባ የተደረገላቸው የማይዳሰሱም ሆኑ የሚዳሰሱ ቅርሶች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ፣ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ፣ አገርን ማስተዋወቂያና የባህል ገጽታ መገንቢያ ናቸው:: ነገር ግን ይህንን ተመልክቶ ወደ ጥቅም መቀየር ላይ የግንዛቤ ክፍተት ተፈጥሯል:: ለዚህም ምክንያቱ የሚመለከተው አካል ይህንን በማስረዳቱ ዙሪያ ብዙም አለመሥራቱ ነው:: ሥራዬ ነው ብሎ ያለመስራትም ችግር፣ ሥራው በባህልና ቱሪዝም እንዲሁም የቅርስና ጥበቃ ብቻ አድርጎ ማሰብም ለማስመዝገብ የተደረገውን ያህል ጥረት ከምዝገባ በኋላ እንዳይቀጥል አድርጎታል::
ቅርሶች ከምዝገባ በኋላ መተዋወቅና የገቢ ምንጭ መሆን ያለባቸው ለማህበረሰቡ ነው:: ስለሆነም ከባህልና ቱሪዝም ባሻገር የሆቴል ባለቤቶች፣ የዲፕሎማቶች፣ የአምባሳደሮች፣ የዳያስፖራው እንዲሁም የአገሪቱ መንግሥት መሆን እንዳለበት የሚያነሱት መምህር መክብብ፤ ይህ ምዝገባ ገጽታችንን ያስተካከለ መሆኑን ተገንዝቦ ይበልጥ ሊሰራበትና ራሳችንን ልንሸጥበት እንደሚገባ ገልፀዋል::
የማስተዋወቅ ልምዳችን አናሳ መሆን ችግሩን አባብሶታል የሚሉት መምህር መክብብ፤ ሌሎች አገራት የሌላ ወርሰው የእኛ ነው በማለት ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ይጥራሉ:: ብዙ ገንዘብም ይሰበስቡበታል:: አገሪቱ ላይ ያለው ልምድ ግን ዓለም የሰጠን እውቅና እንኳን በሚገባ ትኩረት ተሰጥቶት ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ አልተቻለም፡፡ ስለሆነም ዛሬ መንቃትና ቢያንስ በዓለም የታወቀውን ቅርስ ተጠቅሞ ራስን ማስተዋወቅና ጥቅም ማግኘት ላይ መረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡
የኃላፊዎች ቸልተኝነት ከምዝገባ በኋላ ቅርሶች እንዳይተዋወቁና ገንዘብ እንዳይሆኑ አድርጓል የሚሉት መምህር መክብብ፤ ካስመዘገብን በኋላ ውጤት ነው ብሎ ማረፍ፣ ዩኔስኮ ይዞታልና ማስጠበቅም፣ ማስተዋወቅም ያለበት እርሱ ነው ብሎ ማሰቡ ላለመሰራቱ መንስኤ እንደሆነ ጠቅሰው ሲመችም ሳይመችም ከምዝገባ በኋላ ያሉ ቅርሶችን ማስተዋወቅ ላይ መሥራት እንደሚያስፈል አስገንዝበዋል፡፡
በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ፋንታ በየነ እንደገለፁት፤ የቅርስ ምዝገባ ጉዳይ በየጊዜው ይሰራበታል፡፡ ልዩ ትኩረትም ተሰጥቶ ከዕለት ወደ ዕለት ተግባራዊ እንዲደረግም የተለያዩ ወጪዎች ወጥቶ ትውውቅ ይፈጠርባቸዋል፡፡ ሆኖም ከምዝገባ በኋላ ግን ይሄ የነበረው ጥረት በነበረበት ልክ ሲቀጥል አይታይም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ የበጀት እጥረትና መንግሥትም ሆነ ማህበረሰቡ ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ የተቀዛቀዘ ነው፡፡
እንደ አቶ ፋንታ ገለፃ፤ ቀደም ባሉት ዓመታት የመስቀል በዓልን ለማክበር የተለያዩ ሲምፖዚዬሞች ተዘጋጅተው ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በመጋበዝ ሰፊ ሥራ ይሰራበት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ለሁለት ዓመት ያህል ሥራው በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጧል፡፡ ይሄ ደግሞ ከምዝገባ በኋላ ትኩረቱ መቀዛቀዙን ያሳያል፡፡
«ቅርሶች ሲመዘገቡ በአክባሪው ዘንድ የሚኖረው ትኩረት ይጨምራል፤ በዩኔስኮ አባል አገራት ሁሉ የሚታወቅበትን ሁኔታም ያመቻቻል፤ የቅርሱን ቀጣይነት ለማረጋገጥም ያስችላል» የሚሉት አቶ ፋንታ፤ ከተመዘገበ በኋላ ግን ሁነቶችን ፈጥሮ በሚገባ እንዲታዩ ማድረግ ላይ ክፍተት እንዳለ ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2012 ዓ.ም
ጽጌረዳ ጫንያለው