የዛሬ መጣጥፌ ርዕስ የግጥም አንጓ ክፋይ ለዛውም ባለሁለት ስንኝ (መንቶ ) ሆኖ አርፎታል። እንግዲህ የውስጥ ምሪት፣ ድምፅ ከሆነ ምን ያደርጉታል። ከመንጋው ተነጥሎ ውስጥን መስማት፣ ማዳመጥ ደግሞ ሕሊናን መከተል ነው። ወደ ማህበረሰብ፣ ወደ ሕዝብ ወደ ሀገር ሲያድግም እንዲህ ውስጥን ከማዳመጥ መነሳት ይበጃል። መደመር ውስጥን መልሶ መላልሶ ማድመጥ ወደ ራስ መመልከት ነው ብዬ አምናለሁ።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርም ይህን እሳቤ ይዘው የመጡት መቼም በአንድ ጀምበር፣ በደራሽ የሀሳብ ብልጭታ አይደለም። እራሳቸውን መልሰው መላልሰው አድምጠው፣ ከቁርበታቸው መክረው፣ የትውልድን የሀገርን የዘመኑን ድምፅ፣ ጥሪ ጭምር ተከትለው እንጂ።
ወደ ዛሬው ርዕሴ ስመለስ ቤት ይመታል። ቤት ይደፋል። ምጣኔ ፣ ምት ፣ ዜማ አለው ። ሙዚቃዊም ነው። ቃላት + ሀረግ + ስንኝ + መንቶ + ሶስቶ + አራቶ + አንጓ + ምት + ዜማ = ሙዚቃ / ስነ ግጥም ። የቃላት ምርጫ word diction የስሌቱ ማዳወሪያ መሆኑ ሳይዘነጋ ። መደመርም እንዲሁ ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መደመርም ሲሉ ወደፊት ያመጡት ሀሳብ የሚበጀውን፣ መልካም መልካሙን በመሰብሰብ፣ በማከማቸት፣ በማካበት ወደፊት ለመገስገስ እምር ብሎ መዝለያ ኃይል ነው።
አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ከደማሙ ሸገር ኤፍ ኤም 102 . 1 መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ተወዳጇ፣ ተደናቂዋ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ጋር ስለ አደረጉት ጭውውት በተለይ ስለ” መደመር “ የሰጡትን ትንታኔ ላጋራችሁ አስቤ ብዕሬን ከወረቀት ሳዋድድ ርዕሴ በድንገት የግጥም ዘለላ ሆኖ ቢያርፈውም ግጥሙን ለእነ ኤፍሬም ስዩም ልተወውና ስለፈጠረብኝ ተምሳሌታዊ ውርርስ ትንሽ ላንሳና የአራዳ ልጆች እንደሚሉት ወደገደለው ወደ ፍሬ ነገሩ እገባለሁ።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዋቢ ያደረጉት የደስታ ተክለወልድም ሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ተቋም ያዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት መደመርን፦ 1.መሰብሰብ 2. ማከማቸት 3.ማካበት ሲል ይበይኑታል። የእንግሊዝኛው ሜሪያም ዌብስተር መዝገበ ቃላት ደግሞ የመደመር አቻ፣ ተቀራራቢ ትርጉም ተደርጎ የሚወሰደውን sinergy ; : the increased effectiveness that results when two or more people or businesses work together
Full Definition
1 : synergism; broadly : combined action or operation
2 : a mutually advantageous conjunction or compatibility of distinct business participants or elements (as resources or efforts)
ብሎ ይበይንና ስረወ ቃሉ ethymology ከላቲኑ synergia, ከግሪኩ synergos , የሚመዘዝ ሲሆን ትርጉሙም በአንድ ላይ መስራት (working together.) መሆኑን በምሳሌ ያትታል። ቃሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው እ አ አ በ1660 መሆኑን ያወሳል። በእርግጥ ቃሉ በንግዱ ዓለም እንዲሁም በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ቤተኛ ነው። ሆኖም ሀገርን ለማሻገር ወይም ፖለቲካዊ እይታ ሆኖ ሲመጣ ግን የመጀመሪያው ይመስለኛል። ለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወሮታውን ይወስዳሉ።
ወደ ርዕሴ ተምሳሌታዊ ትስስር ስመለስ ሸገር የሁሉም ኢትዮጵያውያን ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ንብረት መሰብሰቢያ፣ መከማቺያና ማካበቺያ መሆኗ እና መደመር ደግሞ መሰብሰብ፣ ማከማቸት፣ ማካበት መሆኑ የሁለቱን ስሞች ተምሳሌታዊ ትስስር ያመለክታል ። የ 5 ሚሊዮንና ከዚያ በላይ ዜጎች ባህል መናኸሪያ ፣ የተለያዩ ነገዶች፣ ጎሳዎች በአንድነት በሰላም የሚኖሩበት፣ ዝንቅ melting pot፣ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መገላበጭያ እንዲሁም የሀገሪቱና የአፍሪካ ፖለቲካዊ መዲና መሆኗ የመደመር ተምሳሌትነቷን ያጎላዋል። ሸገር፣ አዲስ አበባ የመደመር ፅንሰ ሀሳብ ለዜጎች፣ ለቀጣናው፣ ለአህጉሩ፣ ለዓለም የታወጀባት፣ የሚታወጅባት ከተማ መሆኗ ተምሳሌታዊነቷን ይበልጥ ያጎላዋል።
ዳሩ ምን ያደርጋል ለዚሁ ጋዜጣ በምሞነጫጭራት መጣጥፍ የተነሳ ጆሮም፣ ዓይንም፣ ቀልብም ነፍጌው የነበረው Arts ቴሌቪዥን በድንገት በስስ ብልቴ Achilles’ hell፣ በድክመቴ በቴዲ አፍሮ ለዛውም በ “ ማር እስከ ጧፍ “ መጣብኝና ቀልቤነም፣ ልቤንም መግዛቱ ሳያንስ ለደቂቃዎች ሀሳቤን ጭልጥ አድርጎ ወሰደው። ከመጣጥፌ አናጠበኝ፣ ለየኝ። ክቡር ሀዲስ አለማየሁ የዘመናትን ታሪክ በአንድ ዘመን ተሻጋሪ ፣ የሀገር ልጨኛ masterpiece በ” ፍቅር እስከ መቃብር “ መፅሐፍ በ፴፬ ምዕራፍ በ፭፻፶፪ ገፅ ቀነብበው ለታዳሚው አደረሱ።
ተአምረኛው ከያኒ ወጋየሁ ንጋቱ በወርቃማ ድምፁ በመተረክ ዳግመኛ የሕይወት እስትንፋስ በአፍንጫው እፍ አለበት። “ ብላቴናው “ ቴዲ ደግሞ በደቂቃዎች ከዘፈን ግጥም ፣ ከዜማ፣ ከሙዚቃ፣ በተንቀሳቃሽ ምስል ክሊፕ አጅቦ ከልቦለዱ አዋደደው። በክብር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ግሩም ድንቅ ምናብ ከገሀዱ ዓለም ተቀድቶ በታሪክ ተዋዝቶ በትልም plot በድርጊቶች ሰንሰለታዊ ሒደት ተቀጣጥለው፣ ተንሰላስለው ፣ በግጭት ፣ በጡዘት ፣ በልቀት ተጋምዶ ፣ በገፀ ባህሪያት ስጋ ለብሶ በመቼት setting ከማንኩሳ እስከ አዲስ አበባ በተለያዩ አንፃሮች ተተርኮ ከእኛ ደርሷል። ልብ ብሎ ላስተዋለው በዚህ ሂደት ሁሉ መደመር አለ።
ወጊሾ በወርቃማ ድምፁ ሲተርከውም ሆነ ከያኒው ቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ሲያደርገው በክሊፕ ሲገላልጠው ያለፈበት ሂደት የመሰብሰብ፣ የማካበት በመጨረሻም የማከማቸት ገጾችን በቅደም ተከተል ማለፉን ልብ ይሏል። ይህ ፈጠራን ጨምሮ እያንዳንዱ የሕይወት ውቅር ሆነ የተፈጥሮ ኡደት በመደመር ሂደት ያለፈ፣ የሚያልፍ መሆኑን ያሳያል። የወቅቶች መፈራረቅም ሆነ የሰው ልጅም ሆነ የእንስሳት አካላት ብልቶች መመጋገብ፣ መንሰላሰል፣ መናበብ፣ መተጋገዝ እንዴት ቆመው ለመሄድ እንደሚያበቃቸው ለአፍታ ያህል ብናሰላስል በዚያ መደመር አለ።
ለዚህ ነው መደመር ለሕይወት የቅርብም ቅርብ ሆኖ የሚሰማኝ። እንደ ጨው መደመር የሌለበት ተፈጥሮአዊ ሂደት የለም ማለት ይቻላል። ፅንሰ ሀሳቡ ሰዋዊም ተፈጥሮአዊም ነው። ለዚህ ይመስለኛል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መደመር ብቸኛው አማራጭም አቋራጭም ነው የሚሉት። ይህን ያሉት እንደ ቀደሙት ገዥዎቻችን በእኔ አውቅልሀለሁ አባዜ ተይዘው አይደለም። ፅንሰ ሀሳቡ የእኛነታችን ሴልፊ ፣ ነፀብራቅ ከመሆን አልፎ አተያዩ ሁሉን አቀፋዊ እና ሁለንተናዊ ስለሆነ እንጂ።
መደመር ብሔር፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ አይዶሎጂ ድንበር ፣ ሀገር ፣ ዜግነት ፣ ወዘተ . የለውም። ስለሁሉም በሁሉም ነው። በሸገር ኤፍ ኤም 102 .1 ሬዲዮ የአዲስ ዓመት መልዕክታቸው ፅንሰ ሀሳቡን ከማብራራት አልፈው በቅርብ መፅሐፍ ሆኖ ለሕዝብ እንደሚደርስ ይፋ አድርገዋል። በተለይ ስለ መደመር የተናገሩትን አለፍ አለፍ ብዬ በተረዳሁት መጠን ነጥቦችን ከማንሳቴ በፊት በአጋጣሚው ስለ ባለውለታችን ሸገር ኤፍ ኤም ያለኝን ምልከታ ማጋራት ፈለግሁ ።
ስለሀገር፣ ስለታሪክ ፣ ስለባለውለታዎች ፣ ስለየሕግ የበላይነት ፣ ስለፍትሕ ፣ ስለዴሞክራሲ ፣ ስለማህበራዊ ህፀፆቻችን ፣ ስለህልማችን ፣ ስለተስፋችን ፣ ስለሕመማችን ፣ ስለሰጋታችን ወዘተ . ትንፍሽ የሚል፣ የሚናገር፣ የሚፅፍ ብርቅ በሆነበት ፣ ሀይ ባይ ጠፍቶ በነበረበት ባለፉት ዓመታት ፤ ሸገር ኤፍ ኤም 102 .1 ገርበብ ባለችው በር በጎን ገብቶ በድፍረት ፣ በመላ ፣ በዕውቀት ፣ በጥበብ ፣ በማስተዋል ሀገርንም ፣ ትውልድንም ለመታደግ በጭፍራነት ሳይሆን በመሪነት ፣ ጅራት ሳይሆን ራስ በመሆን የመጣ የክፉ ቀን መውጫ ሬዲዮ ነው።
ዛሬ የተገረበበችዋ በር ብርግድ ብላ ብትከፈትም ፤ እንደ ሸገር የሚመራን ሚዲያ ግን ገና አልተወለደም ። አድማጭ ፣ ተመልካቹ ፣ አንባቢው የሚመራው ጭራ ፣ ጭፍራ እንጂ ። ሸገር አድማጭ ፣ ተመልካቹ ፣ አንባቢው ኳስ ፣ ሙዚቃ ፣ ድራማ ፣ ዘውጌ’ዊነት ፣ የሴራ ፖለቲካ ወዘተ . ስለወደደ ጠብ እርግፍ ብሎ የሚያስተናግድ እልፍኝ አስከልካይ አይደለም። አጀንዳ ቀርጾ ፣ ሀሳብ አዋጥቶ ፣ ታሪክን አዋዝቶ ፣ ባህልን ወግን ጠብቆ ፣ ውለታን ሳይረሳ ፣ ውሃ ልኩን ሳያዛንፍ ፣ ደርዙን ሳይለቅ ፣ ጠገጉን በመጠበቅ ፣ ጨዋነትን ፣ ትህትናን በማከል አስተምሯል። አሳውቋል። አዝናንቷል። የራሱ ድምፅ፣ አሰላለፍ ያለው ብሔርተኛ Nationalist ወግ አጥባቂ Conservative
ሬዲዮ ነው ። ብሔርተኛ ያልሁት ሀገር ፣ ሕዝብ ወዳድነቱን ለመግለፅ ሲሆን ወግ አጥባቂ ስል የደረብሁለት ደግሞ ለሀገራዊ ወግ፣ ባህልና እሴት ያለውን መታመን እውቅና ለመስጠት ነው። ስለሸገር አንድ ቀን ራሱን አስችዬ ስለምመለስበት ለዛሬ በዚህ ላብቃ ። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ከሸገር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፦
«…ትክክለኛውን መንገድ እስከያዝን ድረስ ፈተናው የሚያቆመን አይሆንም። …በእኔ እምነት ሕዝቡም፣ መንግሥትም በትክክለኛው ከመጓዝ በስተቀር ምርጫ እንደሌለው። ትክክለኛው መንገድ ማለት መስከን ፣ ራስን ማሸነፍ ፣ ራስን መግዛት፣ መሰብሰብ ፣ መደመር በጋራ ሆኖ ትልቅን ሀገር የማሻገር ኃላፊነትን መሸከም ነው ።…» ብለዋል። በተሰናበትነው ዓመት ሀገሪቱም ሆነ ሕዝቡ ያለፉበትን ፈተና መነሻ አድርገው ባብራሩበት በዚህ ምልልስ ምንም ዓይነት ፈተና ቢገጥመንም ትክክለኛውን መንገድ እስከያዝን ድረስ የሚያቆመን ከጉዞአችን የሚገታን የለም በማለት እንዲሁም ትክክለኛው መንገድም መደመርና መደመር ብቻ መሆኑን አስረግጠዋል።
በማስከተልም «…ኢትዮጵያውያን በተደመረ እሳቤ ነገአችንን ማሳመር እንችላለን። መደመር ራሳችንን፣ አካባቢያችንን የምንመለከትበት መነፅር ነው። ከዓለም ጋር ተንሰላስለን የምንኖርበትን መንገድ የምናይበት ነው። እይታ ነጋችንም መንገዳችንም ነው ። የማያ መነፅር የሚነሳው ምንም ነገር በራሱ ሙሉኡ ነው ብሎ አይደለም። ሁሉም ነገር ጎደሎ ነው። የሰው ልጅ ተጓዥ ነው። ጉዞው ወደ ሙላት ነው ። ወደ ሙላት የሚጓዝ ሰው ጎዶለነት አለበት ወይስ የለበትም የሚል ክርክር አያስነሳም ። ሙሉኡ ከሆነ መኖር አያስፈልግም ። ወደ ሙላት የሚደረግ ጉዞ ከተጠናቀቀ መኖር አያስፈልግም ።
የሰው ልጅ የሚሞትለት አላማ ከሌለው የሚኖርበት ምክንያት የለውም ። ወደሙላት የሚደረግ ጉዞ ለብቻ የሚደረግ ጉዞ ስላልሆነ ነው መደመር የሚያስፈልገን። የብቸኝነት ጉድለት በሁሉም ላይ ያለ ቢሆንም በሰው ላይ የጎላ ነው። ለዚህ ነው ተጨማሪ አጋዥ ወገን የመፈለግ ልምምድ ያለው ።…» ብለዋል። የመደመር ፅንሰ ሀሳብ ሰወኛ ፣ ተፈጥሮአዊ እና አብሮነትን፣ ሙላትን የሚለፍፍ መሆኑን ተንትነዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መደመርን ከቀደሙት ፖለቲካዊ አይዲዮሎጂዎች ጋር በማነጻጸርም ምን ያህል ሙሉኡ እንደሆነ አብራርተዋል።
«… የ19ኛው ክፍለ ዘመን አይዲዮሎጂዎች አንዱ ውስንነት ፉክክርን ብቻ አተኩረው ትብብርን ይተዋሉ ። ትብብርን አተኩረው ፉክክርን ይተዋሉ። መደመር ግን የትብብርና ፉክክር አስፈላጊነትና ሚዛን በእጅጉ የሚያምን እሳቤ ነው። ስለዚህ መደመር ዛሬን በመሰብሰብ፣ ትናንትን በማከማቸት ነገን በማካበት አስተሳስሮ የሚሄድ እሳቤ ነው። … “ መደመር በአጭሩ፦
«… ዛሬን በመሰብሰብ ትናንትን በማከማቸት ነገን በማካበት የሚያስተሳስር ነው ። በተቃራኒው አለመደመር መዛነፍን መጨንገፍን ያስከትላል። በመጨረሻም መጠፋፋትን ያመጣል። …» ብለዋል። በእሳቸው ትንታኔ አለመደመር መዛነፍን፣ መጨንገፍን ስለሚያስከትል መጨረሻው ቀውስ ነው። በማያያዝ የመደመርን ሁሉን አቀፍነት፣ ዙሪያ መለስነት የደርግን «መሬት ላራሹን » እና የቀዳማዊ ኢህአዴግን «የብሔር ጥያቄ » በአብነት በማንሳት የነበራቸውን ጉድለቶች በንፅፅር አብራርተዋል።
«…መሬት ለአራሹ መሬት በተወሰኑ ሰዎች ተይዟልና የተገባ አይደለም ብለው የሚያስቡ ሰዎች ተደራጅተው ታግለው መልሰዋል። ለአንድ ጥያቄ የተነሳ ሀሳብ ነው። በኋላም የብሔር ጉዳይ እንደዚሁ ነው። መደመር ግን ችግሮቻችንን ከአንድ ማዕቀፍ አንጻር በማየት የመፍታት ፅንሰ ሀሳብ ነው። …» አፍሪካውያን እህት ወንድሞቻችን ሳይቀሩ በተስፋ የተቀበሉትን የመደመር ፅንሰ ሀሳብ ለማስፋት፣ ለማዝለቅ በቅርቡ መፅሐፋቸው ለንባብ እንደሚበቃ በስፋት እንደሚብራራና እንደሚተነተን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ከዚያስ …! ?
ከዚያማ፦
1ኛ . ዴሞክራሲም ሆነ ካፒታሊዝም አልያም ነፃ ገበያ ወይም ሶሻል አልያም ሊበራል ዴሞክራሲ እንዲሁም ሶሻሊዝም እንደ አይዲዮሎጂ የተጠነሰሱት በግለሰብ፣ በቡድኖች ሀሳብ አፍላቂነት ነው። የሚሊዮኖች የቢሊዮኖች ሀሳብ የሆኑት ተከታታይ የማኸዘብ popularize፣ የማስተዋወቅ፣ የማስፋት፣ የተግባቦት እንዲሁም አስገድዶ የማጥመቅ indoctrination የፕሮፓጋንዳ ሥራዎች በመሰራታቸው ነው። ስለሆነም የመደመር ፅንሰ ሀሳብን የማስተዋወቅ ሥራዎች ዘመኑን በሚዋጁ የተግባቦት አግባቦች ሊከናወኑ ይገባል።
የእነ አፄ ምኒልክ የፀረ ቅኝ ግዛት ትግል፣ የእነ ማህተመ ጋንዲ፣ የእነ ማርቲን ሉተር ኪንግ ሰላማዊ ትግል ፣ የእነ ማንዴላ የፀረ አፓርታይድ እንዲሁም የስቲቭ ቢኮ የጥቁር ንቃተ ሕሊና black consciousnes ንቅናቄ ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ሊያገኝ የቻለው በተጠና የተግባቦት ስትራቴጂ ሊመራ በመቻሉ ነው ። የመደመር ፅንሰ ሀሳብንም ብዙዎች በባለቤትነት ስሜት እንዲይዙት ተግባራዊ እንዲያደርጉት በተጠና የተግባቦት ስልት የመተጋገዙ ነገር ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል።
2ኛ . ልሒቃን፣ ከፍተኛ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪልና የሙያ ማህበራት ፣ የመንግሥትም ሆነ የግል መደበኛም ሆነ ማህበራዊ ሚዲያዎች የመደመር ፅንሰ ሀሳብን በመሔስ፣ በመተቸት ሊያጎለብቱት ይገባል። በፅንሰ ሀሳቡ ዙሪያም ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ሊዘጋጁ ይገባል። ፅንሰ ሀሳቡ ሀገር የሚመራበት ከፍ ሲልም ለሰው ልጆች አማራጭ ሆኖ የቀረበ ስለሆነ ጊዜ ተወስዶ በተጠየቅ፣ በአብርሆትና በአመክንዮ ሊመከርበት ፣ ሊተነተን ፣ ሙግት ሊከፈትበት ፣ ወዘተ . ይገባል ።
3ኛ . እንደ ሶሻሊዝም ወይም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለካድሬ ብቻ ከተተወ የጋን መብራት ሆኖ ስለሚቀር የሕዝቡን የግንዛቤ ደረጃ ከግምት ባስገባ መልኩ ቀለል ባለ አግባብ በሚዘጋጁ የመወያያ ሰነዶች ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ባሳተፈ መልኩ ግልፅ ውይይት ሊካሄድ ይገባል።
4ኛ . ከሁሉም በላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆኑ ገዥው ፓርቲ ወይም መንግሥታቸው ከተለያዩ መድረኮች የሚመጡ ግብረ መልሶችን ሆነ አወንታዊ ወይም አሉታዊ ትችቶች ለማስተናገድ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም በግብዓትነት ለማካተት አበክረው ሊዘጋጁ ይገባል።
ኢትዮጵያ ሀገራችን በልጆቿ ታፍራና ተከብራ
ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን ።
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2012