ለውጥ ከምቾት መውጣትን ይጠይቃል። ሕልምን ማሳካት ከስሜት በላይ መሆንን ይፈልጋል። መጨከን ይጠይቃል። መተኛት እያማረህ ተነስተህ የምታነበው፣ ተነስተህ ስራ የምትሰራው፣ ዝቅ ብለህ ስፖርት የምትሰራው፣ ቀዝቃዛ ሻወር የምትወስደው፣ ማድረግ የሚገባህን ሁሉ የምታደርገው አዕምሯዊ ጥንካሬ ዲስፕሊንና ከስሜት በላይ የመሆን ጥበብ ካለህ ብቻ ነው። እንዴት ነው ታዲያ ይህ ጥበብ ሊኖርህ የሚችለው?
የሠው ልጅ በየቀኑ እንደማደግ ደስታ የሚፈጥርለት ነገር የለም። ማደግ ደግሞ መጨከን ይጠይቃል። የሚያዘናጉህን ሠዎች አትሰማም። ‹‹አትችልም! አርፈህ ቁጭ በል! የትም አትደርስም!›› የሚሉህን ሠዎች ጆሮ አትሰጣቸውም። ለጊዚያዊ ስሜትህ አትንበረከክም። ውስጥህ ፈታ በል፣ ተዝናና፣ ስልክህን አውጥተህ የሚያስቅ ነገር እይ እያለህ አንተ ግን የስሜትህ ባሪያ ስላልሆንክ አታደርገውም። ይህን ማንነት የምትገነባው ታዲያ እንዴት ነው?
አንዳንዴ እኮ ምን ማድረግ እንዳለብህ ታውቃለህ። ምን ብትሰራ ሕይወትህ እንደሚቀየር ታውቃለህ። ግን ወደ ድርጊት መግባት አቅቶሃል። መለወጥ ትፈልጋለህ። መቁረጥ ትፈልጋለህ። ነገር ግን ደግሞ የያዘህ፤ የጎተተህ ነገር አለ። ምንድን ነው ማድረግ ያለብህ? የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲው ምሁር ዶ/ር ፍሬድ ለስኪን አእምሯችን በቀን ውስጥ ከ60 ሺ በላይ ሃሳቦችን ያስባል ይለናል። አብዛኛው ደግሞ ተደጋጋሚ ነው። ግማሹ ስለትናንት ነው። ቁጭት ነው። ብሶት ነው። ‹‹ወይኔ! እንዲህ ባላደርግ ኖሮ፣ አበላሸሁት፣ አጠፋሁ›› እያልን ነው የምናስበው። ግማሹ ደግሞ ስለነገ ነው። ‹‹እንዲህ ቢሆን፣ እንዲህ ባገኝ የሚል›› ምኞት ነው።
ለውጥ የሚጀምረው ደግሞ አሁን ላይ ትኩረት አድርገህ በመወሰን ነው። ከዚህ በፊት የወሰንካቸው ውሳኔዎች ያሰጡህ ደስታ አለ። የአእምሮ ሰላም አለ። እንዳውም ሰዎች መጥተው ‹‹አንተ ጀግና ነህ። እንዲህ በማድረግህ አድንቅሃለው›› ያሉህ ግዜ አለ። ‹‹እህቴ አንቺ በጣም ጎበዝ ነሽ፣ እንዲህ በማድረግሽ ገርሞኛል›› ብለው ያደነቁሽ ወቅት አለ። ያ ወቅት በጣም ቆራጥ ሆነሽ የወሰንሽበት ነው። በዚሁ ቅፅበት ሱስን ለማቆም መወሰን አለብህ። ፈርተህ ያቋረጥከውን ትምህርት ለመቀጠል መወሰን አለብህ። እጀምራለሁ ብለህ እያመነታህ ያለኸውን ያን ስራ ለመጀመር አሁን መወሰን አለብህ።
በትምህርቴ፣ በስራዬ፣ በፍቅር ግንኙነቴ፣ በትዳሬ ወዘተ ‹‹ለውጥ እፈልጋለሁ›› ብለህ ካሰብክ መጀመሪያ መወሰን አለብህ። ከዛ ወደ ተግባር መግባት አለብህ። ግን ‹‹እንዴት አድርጌ ልወስን፤ ሶፋ ላይ ቁጭ ብሎ ቁረጥ! ወስን ማለት ማን ያቅተዋል›› ካላችሁ ልክ ናችሁ። ለዚህ የራሱ መንገድ ያስፈልገዋል። ቀጥሎ የሚዘረዘሩት ነጥቦች ወደ ተግባር እንድትገባ፣ የድርጊት ሰው እንድትሆንና ለውጡን አሁኑኑ እንድትጀምረው ይረዱሃል።
1ኛ.ራስን ማስጨነቅ መለማማድ
ሃሳቡ በጣም ያስገርማል። በሕይወትህ ውስጥ የሚጠቅምህ ነገር ግን አንተ ማድረግ የማትፈልገው ምቾት የሚነሳህን ነገር ጨክነህ ማድረግ ተለማመድ። በቃ! ራስህን ማስጨነቅ ተለማመድ ይላል። ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን የተባለ ደራሲና ፈላስፋ ‹‹ማደግና መለወጥ የምትፈልግ ከሆነ ከማትፈልጋቸው ነገሮች ጋር መጋፈጥን ተለማመድ›› ይለናል። ምቾት ውስጥ ሆነህ ልትለወጥ አትችልም። አንተን የሚያሳድጉህ፣ የሚለውጡህ ነገሮች ያሉት ከምቾትህ ጀርባ ነው። በጠዋት መነሳት ራስን ማስጨነቅ ነው። ከሚጠበቅብህ በላይ መስራት ራስን ማስጨነቅ ነው። ፊልም አጥፍተህ ማንበብ ራስን ማስጨነቅ ነው።
እየመረረህ እንኳን ጨክነህ የምታደርጋቸው ነገሮች ቢያስጨንቁህ እንኳን ሕይወትህን ይቀይሩታል። ቶኒ ሮቢንስ ‹‹ሁል ግዜ በጠዋት ተነስቼ ከሞቀ አልጋዬ ወጥቼ ቀዝቃዛ ሻወር ውስጥ እገባና ውሃው እየወረደብኝ ቁጭ እላለሁ። ያኔ የሆነ ኃይል ውርር ያደርገኛል። ጥንካሬ ይሰማኛል›› ይለናል። ለሕይወትህ ከጠቀመህ ምቾት ቢነሳህ እንኳን ተነስና አድርገው። ከስሜትህ በላይ መሆን ከፈለክ ራስህን ማስጨነቅ ተለማመድ።
2ኛ.መጨረስ የምትፈልግ ከሆነ ጀምር
ሁሉም ሠው የሚገራርም ሃሳብ አለው። ችግሩ ሃሳብ ብቻ ነው። እንደውም ዶ/ር ማይልስ ‹‹ትልቁ የተሰጥኦ ክምችት ያለው የመቃብር ስፍራ ነው። ምክንያቱም አንዳንዱ የሚገርም ሙዚቃውን ሳያቀነቅነው ሞቷል። ሌላው ደግሞ መፅሃፉን ሳይፅፈው አንቀላፍቷል። አንዳንዱ ድንቅ የሆነ የቢዝነስ ሃሳቡን ሳይተገብረው አልፏል›› ይለናል። የባከነ ተሰጥኦ፣ አቅም፣ ጥበብ የተሰበሰበው መቃብር ስፍራ ላይ ነው ይለናል።
አንተ እድሉ አለህ፤ እየተነፈስክ ነው፤ በሕይወት አለህ። መቼ ነው ያሰብከውን ወደ መሬት የምታወርደው? ፀሃፊ መሆን ከፈለክ በየቀኑ ቢያንስ አንድ ገፅ መፃፍ የምትጀምረው መቼ ነው? በትንሹም ቢሆን የምትጀምረው መቼ ነው? ቆይ ጥሩ ቀን ይምጣ ስትል እኮ ፍላጎትህም አብሮ ይቀንሳል። ‹‹የመንገዱ መብራት ሁሉ አረንጓዴ ካልሆነ፤ አውራ ጎዳናው ክፍት ካልሆነ ከቤት አልወጣም›› አትልም እኮ! መቼ ነው የምትጀምረው ? ደግሞ ስትጀምረው በትንሹ ጀምረው።
ስቴቨን ኪንግ በዓለማችን ላይ በጣም የተከበረና የሚደነቅ ደራሲ ነው። መፅሃፎቹ በሚሊዮን ኮፒ ተሽጠዋል። አንድ ጊዜ በጣም ረጅም ልብ ወለድ ፅፎ አስመረቀና አንድ ጋዜጠኛ ጠጋ ብሎ ‹‹በጣም ነው የሚገርመው! እንዴት አድርገህ ነው ይህን የሚያክል ጥራዝ መፅሃፍ ፅፈህ የጨረስከው›› አለው። ስቴቨን ኪግም ‹‹በአንድ ግዜ አንድ ቃል እየፃፍኩ›› ሲል መለሰ። ቀላል ይመስላል ሃሳቡ። ግን መጨረስ የምትፈልግ ከሆነ በትንሹም ቢሆን አሁኑኑ ጀምረው ነው መልዕክቱ። በዚህ ዓለም ስትኖር የምታደርገው ማድረግ የምትችለውን ብቻ ነው። አለበለዚያ አትበጣጠስ። ችግሩ ማድረግ የምትችለውን ነገር ካላደረክ ነው። ስለዚህ መጨረስ የምትፈልግ ከሆነ ጀምረው።
3ኛ.ለመስነፍ አልተፈጠርክም
ከስሜትህ በላይ መሆን ከፈለክ ለመስነፍ እንዳልተፈጠረክ ለራስህ መንገር አለብህ። ወደዚህ ዓለም የመጣህበት ልዩ ዓላማ አለህ። ማርከስ ኦሬለስ የተባለ የሮም ንጉስና ፈላስፋ ‹‹አልጋዬ ውስጥ ተኝቼ ማርፈድ በጣም ደስ የሚል ስሜት ይሰጠኛል። ግን ተኝቼ ለማርፈድ አልተፈጠርኩም። ስለዚህ ዓላማዬን ለመኖር ስል እየደበረኝ ቢሆን እነሳለሁ›› ይላል። ዓላማህን ስታውቅ አትሰንፍም። አታመነታም። ቢርብህ እኮ ወደድክም ጠላህም ትበላለህ። ወደዚህ ዓለም ያለምክንያት አልመጣህም።
ስለዚህ ዓላማህን ለማሳካት ስትል ዋጋ መክፈል አለብህ። ለራስህ ንገረው። ተነስቼ ካላጠናሁ ታዲያ ለምን ተፈጠርኩ? ተነስቼ በደምብ አድርጌ ጥሩ አድርጌ ካልሰራሁ ወደዚህ ዓለም ለምን መጣሁ? ብለህ ለራስህ ንገረው። ለስንፍና እንዳልተፈጠርክ እየደጋገምክ ለራስህ ንገረው። ዓላማ እንዳለህ፤ ፈጣሪ ያለምክንያት ወደዚህ ምድር እንዳላመጣህ ለራስህ ደጋግመህ ንገረው። ያኔ ከስሜትህ በላይ መሆን ትችላለህ። ለስንፍና አልተፈጠርክም ወዳጄ!
4ኛ.ወጥ አቋም ያስፈልግሃል
ብዙ ሰዎችን እናውቃለን። በልባችን ግን ትልቅ ቦታ የምንሰጣቸው ሰዎች በአቋማቸው የሚፀኑ ሰዎችን። በዚህ ዓለም ላይ በአቋም መፅናት፤ ጥረትን አለማቆም ትልቅ የስኬት ምስጢር ነው። ያውም ጥረትን መቀጠል፤ እየጨመሩ መሄድ ደግሞ በጣም ከባድ ነው። አይተህ ከሆነ ስራው ስትጀምረው ያለህ ጉጉት፣ ጥረት አሁን ድረስ አብሮህ ቢቀጥል አንተን የሚያክል የዛ መስሪያ ቤት ቁልፍ ሰው አይኖርም። ትምህርቱን ከመጀመሪያው ጀምሮ ስትጀምረው ያለህ ስሜትና ጥረት እስከመጨረሻው ቢቀጥል አንተን የሚያክል ስቃይ ተማሪ አይኖርም።
ማቆም ቀላል ነው። ሁሌም ግን ለራስህ ያወጣኸውን ደረጃ አስጠብቀህ መቀጠል እሱ ነው ከባዱ። አንድ ደራሲ ‹‹የማይሸነፍ አንድ ሰው አውቃለው እርሱም ተስፋ ቆርጦ ጥረቱን የማያቆም ነው!›› ይላል። አንዳንዴ እንደሞኝ ላመንክበት ነገር ግግም ማለት ጥሩ ነው። የምትፈልገው ነገር ተፈጠረ፤ አልተፈጠረ ስትራቴጂህን እየቀያየርክ ጥረትህን መቀጠል። ወዳጄ! እውነተኛ ለውጥ የምትፈልግ ከሆነ ወጥ አቋም ያስፈልግሃል።
5ኛ. ወደኋላ የሚጎትቱህን ነገሮች መቁረጥ
ለምሳሌ በቆሻሻ ውሃ የተሞላ ብርጭቆ ውስጥ ትንሽዬ ንፁህ ውሃ ጠብ ብታደርግ ምንድን ነው የሚፈጠረው? በርግጠኝነት ያው ቆሻሻ ውሃ ነው። ግን ለምሳሌ ደግሞ በንፁህ ውሃ በተሞላ ብርጭቆ ውስጥ ትንሽ ቆሻሻ ውሃ ጠብ ብታደርግስ ምንድን ነው የሚፈጠረው? አሁንም ቆሻሻ ውሃ ነው የሚፈጠረው። አየህ በትንሹ እንኳን የሚረብሹ ሁኔታዎች ውስጥ ካለህ መለወጥ በጣም ከባድ ነው። ምን አይነት ሰዎች ናቸው በዙሪያህ ያሉት? ምን አይነት ወሬዎችን ነው የምትሰማው? ምን አይነት ነገሮች ናቸው ወደ ውስጥህ የሚገቡት? አሉባልታ ነው? ከንቱ ነገር ነው? ብሶት ነው? ጭንቀት ነው? ምንድን ነው ወደ ውስጥህ የሚገባው?
ትንሿ መርዝ ናት ወንዝ የሚያክል ውሃ የምትበክለው። እንዳትለወጥ፤ ወደ ድርጊት እንዳትገባ ያደረጉህን ነገሮች ለያቸውና ከሕይወትህ ውስጥ ቆርጠህ ጣላቸው። ሁሌም እንደሚባለው የተመረዘ እጅ የሚቆረጠው ባለቤቱ ስለማይፈልገው አይደለም። ነገር ግን ሌሎቹን የሰውነት ክፍሎች ስለሚመርዛቸው ነው፤ ዙሪያህን ፈትሸው። ከምን አይነት ሰዎች ጋር ነው ግዜህን የምታሳልፈው? ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለኸው? የማይጠቅሙህን ሰዎች፣ እንደማትችል የሚነግሩህን ሠዎች፣ መጥፎ ነገር በውስጥህ የሚዘሩትን ሠዎች ከሕይወትህ አውጣቸው። አርቃቸው። ስልካቸውን አታንሳ። አታውራቸው። ግንኙነትህን ቀንስ።
እንዲህ የምታደርገው ስለማትወዳቸው አይደለም። ግን ሕልምህን ቆፍረው እንዳይቀብሩት ነው። ለዛ ነው ለውጥ መጨከን ይጠይቃል፤ ከስሜት በላይ መሆን ይጠይቃል የሚባለው። የማይጠቅሙህን ነገሮች ማስወገድ ተለማመድ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2017 ዓ.ም