የብርዕ እልቅናቸው ሞገስ ይሆንላቸውና በነበራቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣንነት ጎን በሥነ ጽሑፍም የተካኑበት መሆኑ የሚታወቀው ደራሲ ደጃዝማች ግርማቸው ተከለ ሐዋርያት ‹‹አርአያ›› በተሰኘው ልብ ወለድ መጽሐፋቸው ያሰፈሩትን ጠቅሼ በማንደርደሪያነት ወደ አንባብያን ላጉዝና ወደ ይበልታው እንዳመራ ይፈቀድልኝ።
ደራሲ ደጃዝማች ግራማቸው ተክለ ሐዋርያት ገጸ ባሕርይ ያደርጉት ‹‹አርአያ›› ከሀገረ ፈረንሳይ ተመልሶ በመጣበት ወቅት የልጅነት ጓደኛው ከነበረው ከ‹‹ታደሰ›› ጋር ሌሎችንም ወዳጅና ባልንጀሮች ጨማምረው በድሬዳዋ ከተማ ሲዝናኑ በነበረበት ሰዓት ያካሄዱትን ውይይት በአጭሩ እንዲህ እንመለከታለን፡–
ከአውሮፓ ወደ ትውልድ ሀገሩ የገባው አርአያ ከቀረበለት መጠጥ እጅግ መጠን አድርጎ ተጎነጨና ‹‹በቃኝ›› ይላል። ‹‹ምነው አይደጋግሙም እንዴ! ባንድ መለኪያ ብቻ ምነው ተሸነፉ›› ሲሉ አንዱ አዛውንት ‹‹ዓይናቸውን በርበሬ፣ ፊታቸውን ጉበት አስመስለው›› እንግዳውን አርአያን በማፌዝ አኳኋን ይጠይቁታል። አርአያም ‹‹መሸነፍ›› ሲባል መቼም ‹‹መረታትም፣ ድል ጉልበት ማጣት›› መሆኑን ከመረዳት አልታቀበንም! እንዲህም አለ፡– ‹‹እኔስ አልተሸነፍኩም ይልቁንስ ያሸነፍኩት ይመስለኛል! ባሸንፍ እኮ ነው ከልክም በላይ አልጠጣም ለማለት መቻሌ!›› ሲል በከረረ አነጋገር ይመልስላቸዋል። እንዲያ እንዲያ እያሉ ተጫወቱ።
በውኑ የዚህ የመጠን ዘለል ጠጪነት ነገር ከዕለት ዕለት ከዓመት ዓመት እየባሰ እንጂ እየቀነሰ ሊሄድ ያልበቃበት ኩነት ‹‹አሳሳቢ›› መባል ያለበት ጉዳይ ይመስለኛል። አንዳንዱ ጠጪ እንዲያውም ‹‹አትስከር›› ሲሉት የሚያኮርፍ ነው። አንዳንዱ ደግሞ ሲመክሩት የሚያሾፍ አለ። ‹‹ውሃ ሲወስድ አሳስቆ፣ አሳስቆ ከእንጀራ ጋር አናንቆ›› በማለት እንደ ሰካራም እየተለፋደዱ ቃላት ጎትተው ቋንቋ እያወለጋገዱ፣ ጥቂት እየቀለዱ የሚዘፍኑ አንድ ክራር መቺ ‹‹የውሃ ነገር›› ሲነሣ ትዝ ይሉኛል። ወረደም ወጣ የክራረኛው አዘፋፈን ‹‹እንዲያ የቧልት ብቻ ነው›› ብሎ በዚሁ መደምደሚያ የሚቻል አይመስለኝም።
‹‹ምነው?›› ቢሉ ‹‹ውሃ ሲወስድ አሳስቆ፣ ከእንጀራ ጋር አናንቆ›› የተሰኘውን ለማስተባበል የሚችል የለምና! እኔ እንደ አመለካከቱ ቁም ነገር ያዘለ፣ ከቀልድ የዘለለ እንዲያውም ‹‹ትምህርታዊ›› ሊባል የሚበቃ ነው። የእሳቸውን ዜማ ያዳመጠ ሁሉ በአዝናኝነታቸው ሳያሞግሱ አልቀረም። ግና ምን ያደርጋል? ሰካራሙ ከጨዋታ እኩል እየሳቀ ብርሌና መለኪያ እንዳነቀ አለቀ እንጂ!!
የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ባገኘው መድረክ ነገሩ እየተደጋጋመ ትንሽ ማሰልቸቱ ባይቀርም ጉዳዩን እንደ ዋዛ እያልፈውም። በተለይም ብርዕና ወረቀት ለማዛመድ ከተቻለበት ጊዜ አንሥቶ የዚህን የሰካራሞች የስካርን አስከፊ ገጽታ ከማስረዳት የቦዘነበት ጊዜ የለም። ይህም ምክንያት የሌለው አለመሆኑን አንባቢ ይገነዘብልኝ ዘንድ እሻለሁ። በእውነቱ ለመናገር እንደ ሰካራም ሻጩን የሚታደግ ታላቅ ባለ ውለታ የለም ማለት ያስደፍራል። መቼም ሰው አዕምሮ ያለው ሰብዓዊነት ያልጎደለው ፍጡር መሆን ከታመነ ዘንድ ወዳጁን፣ ጓደኛውን፣ ወገንና ጎረቤቱን የማይረዳ የለም። ሁሉም አይባልም እንጂ አቅም በፈቀደ ለረድኤት ወደ ኋላ አይልም። የጠጪ አጋዥ፣ የሰካራም አጋር ግን ከዚህ እጅግ በጣም የተለየ ነው። እርሱ በአረቂ እየተኮማተረ፣ ጉበቱ እያረረ የመሸታ ቤት ባለንብረት ያስከበረ ነው። ‹‹ቁምነገረኛ›› ነው። እርሱ አጥቶ እየገረጣ የከሰረ ነጋዴን ከጉድ የሚያወጣ ባለ ውለታ ነው።
‹‹አይዞሽ የእኔ አንጀት ይረርልሽ፣ የእኔ ጉበት ይለቅልሽ፣ እኔ ልፍረስልሽ›› የሚል ወገን!!! እንዲያውም ይህን መሰል ባለ ውለታ፣ ይህን መሰል አለኝታ፣ ይህን መሰል መከታ ለመሆኑ ከውዴታ ይገኛል? በሥጋ ልደት የተዛመዱት፣ በጋብቻ ጥምረት የተዋሃዱት እንኳን እራሱ እያለቀ፣ እየተቸገረ ወገኑን አይረዳምና!
እኔ ለዚህ ነጥብ መላልሼ አጽንዖት በመለገሴ የነቀፋት ሰው ቢኖር እንዲያውም እስከ ወዲያኛው ያኮረፋት መሆኑ አይጠረጥርም። ነገር ግን እሱም ይነቅፋል፣ እድሜ ልክ ያኮርፋል እንጂ ጉዳዩን እንደ ዋዛ አላልፈውም። በአንድ ጥቂት የዓመታት በሆነ ወቅት አደባባይ የዋለ የፍተሻ ሰነድ እንዳመላከተው በዓለማችን ካሉ ሰዎች ከሁለት ቢሊዮን የማያንሱት የአልኮል መጠጥ ተጠቃሚዎች ናቸው። በጠጪነት ‹‹1›› የተባሉት አውሮፓውያን ሲሆኑ አሜሪካውያን በቁጥር ‹‹2›› መሆናቸው ተመልክተዋል። አፍሪካዊያን በ‹‹3››ኛ ደረጃ መቀመጣቸው በጊዜው ተዘግቧል። ሀገራችን ኢትዮጵያ በክፍለ ዓለሙ ስንተኛ እንደሆነች አልታወቀም።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያችንን በተመለከተ በቅጡ ብንመረምር አንዳንድ አሳዛኝ ሁኔታዎች መገኘታቸውን ለማስተባበል የምንችል አይመስለኝም። ለምሳሌ አንድ ሰው ላም አርብቶ፣ ጥገት አልቦ ወተት ከሚሸጠው ላይ ጠላ ጠምቆ፣ ጠጅ ጥሎና አረቂ አውጥቶ ቢሸጥ በአንድ ጀምበር እጥፍ ድርብ አኃዝ ብር ይቆጥራል፣ ጥሪት ይቋጥራል፣ ይከብራል። በአሁኑ ወቅትማ እንደ ነገሩ መከልከሉ ቢቻልም ፍፁም የመጠጥ ጎጂነት ለሕዝብ በይፋ እንዲሰራጭ መደረጉ አልታወቀም። ከቶውንም እንዲያውም አዲስ የመጠጥ ፋብሪካ ሲቋቋም የምሥራቹ በየጎዳናው እየተለፈፈ መሆኑን እናደም ጣለን።
ዘወትር የሚባል አንድ አባባል አለ። ይኸውም ‹‹ከሁለት ዲግሪ አንድ ግሮሰሪ›› የሚል አሳዛኝ ዘይቤ ነው። በነገራችን ላይ ‹‹ግሮሰሪ›› የተሰኘው ቃል እጅግ የሚደንቅ ታሪክ ያለው ነው። በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አረቂ ቸርቻሪ ሁሉ ‹‹በ…………. ቤት ›› ብሎ የከፈተበት ኩነት ነበረ። በዚህ ቤት ቡና፣ ሻይም የሌለበት! ፍቃድ በገደብ ይሆን ዘንድ ስላደረጉ እና ፍቃድ ፈላጊውን ‹‹ አሻሻጭ‹‹ ብሎ የቆጠራቸውን ሴቶች ጤንነት አስመርምሮ ማስረጃ ማቅረብ ስለነበረበት ወንድ አንስተናጆች የምስክር ወረቀት እንዲያቀርቡ የአስተናጋጅ ሥርዓት ስላወጣ ነገሩን አስጨንቆ ወደ ሌላ ተለወጠና ግሮሰሪ በስንት ምጥ ተወለደ። አንድ ሰው እንዳሉትም በብርቱ ምጥ የተወለደ ነበር። አራዶች አዋላጅ ሳይሆኑ አልቀሩም።
በመሠረቱ ከዚህ በፊት ‹‹ግሮሰሪ›› የሚባል መጠጥ ቤት አልነበረም። እንደ ፈረንጆቹ ሀገር መጠጥም ሌላ የመባል ሸቀጥ እንደ ዛሬ ሱፐር ማርኬት ልዩ ልዩ መባልዕት የሚሸጥ ብቻ ነበር። ያንንም መጠጥ በድፍኑ ብቻ የሚነግድ እንደነበረ ይታወቃል። በዚህ አኳኋን ግን እነ ጮሌ ‹‹ነግዶ አውልቅ›› ወደ ‹‹ግሮሰሪው›› ዞሩና በመጀመሪያ መጠጥ ለማከፋፈል ሌላም ምግብ ነገር ሸቀጣ ሸቀጥ መነገድ ጀመሩ።
በለስላሳ መጠጥና በቢራ ሳጥን ጠጪ እየተቀመጠ እንዲጠጣ ተነገደ። ሕዝብም ያን አግኝቶ እንደ ልቡ መስከር ቻለ። ዘየደ። ቀጥሎም በአጠገቡ ልኳንዳ ቤት አቁሞ ብርንዶ ሊያስቆርጥ ገባ። ውሎ አድሮ ያን ዱለቱን፣ ጥብሱንም ተከተለ። ቀን ቀንን እየተካ ሲሄድ በሙዚቃው አሟሟቂነት ጥቂት ሶፋም ታክሎበት የግሮሰሪ ታሪክ በአዲስ ምዕራፍ ልዩ ትርጓሜ ይዞ ቀጠለ። ‹‹ከሁለት ዲግሪ አንድ ግሮሰሪ›› በማሰኘትም ጠጪን ደለለ። መንግሥትንም ደርግ ሲመጣለት ይበልጡንም ደስ አለውና ሁሉን ሸነገለ።
ወደ መጠጡ ጉዳይ ልመለስና የአልኮል መጠጥ እንዲህ በቀልድ የሚያልፋት አይደለም ። የተመራማሪዎች የፍተሻ ወረቀት እንደሚያስረዳው ሰዎች የአልኮል መጠጥ ሲጎነጩ በቅድሚያ አንድ ወይም ሁለት ብለው መጠጡን ይጠጡታል። ከዚያ ሦስተኛው ሲጀምር መጠጡ ሰዎቹን መጠጣት ይቀጥላል። እንዲያ እንዲያ እያለም ሲሄድ በርከትከት እያለ ስድስት፣ ሰባት እየሆነ ሲራመድ መጠጡ መጠጡን ይበልጡን የሚጠጣው ይሆንና ያ ‹‹ጠጪ›› የተባለው ሰው እንደ በድን እየበደነ ይደነዝዝና ይቀራል። ከዚህ ወዲያ እምብዛም የሚያውቀው ነገር የለም።
በአንድ ወቅት ሰውየው እስከ መንፈቀ ሌሊት ሲጠጣ ቆይቶ ወይም እንደ ተባለው መጠጡ መጠጡን ሲጠጣ በምስክርነት ቆሞ ሲያወራርድ ውድቀት ላይ ደረሰና መሐል አደባባይ ሰውም ዝር ባለበት ጊዜ ተገትሮ እላይ ታቹን እየተመለከተ በነበረው ሰዓት ከሥራ የመጣ አንድ ወዳጁን ድንገት ያገኘዋል። ‹‹ምነው በዚህ አጓጉል ሰዓት በእዚህ ቦታ ብቻህን ምን ትሠራለህ?›› ሲል ይጠይቀዋል። ሰውየውም ‹‹ብዙ ቤቶች በዙሪያዬ እያለፉ ሲሄዱ በማየቴ የእኔም ቤት ድንገት መጥቶ ይወስደኝ እንደሆነ ብዬ እየጠበቅሁ ነው›› ብሎ መለሰለት ይባላል። በማግሥቱ ሲጠይቅ ግን የሰከረው ሰው ካለ ሁኔታው አላወቀም። እርሱ እራሱን አልነበረምና!
የዚህን የመጠጥና የሥካር ነገር ከአንድ አንደ እኔው አረቂ እርሙ ከሆነ ወዳጄ ጋር ስንጨዋወት ነበር። መቼም የአልኮሆል መጠጥ ከተባለ ጎጂነቱን እንጂ ጥቅሙን አወራን ማለት አይቻልምና በሙያ ክሂሎታቸው በተለይ በኪነጥበብ ብልኃታቸው ‹‹አንቱ›› የተባሉ ሰዎች በዚህ አጓጉል ‹‹የውሃ ስንቁነት›› ልማድ የቱን ያል እንደተጎዱ እያነሣን ነገሩን የውይይታችን ርዕሰ ጉዳይ አድርገነው ከቆየን በኋላ በእርሱ አሳሳቢነት ነው እንደገና ልንዳስሰው የፈቀድኩት። እኔ እንኳን ‹‹በዚህ ጉዳይ ደጋግሜ መጻፌን ነግሬው ከዚህ ወዲያ ለመተው ፈልጌ ነበር።›› እንዲህ ስለው እርሱ ግን ‹‹ትምህርት እኮ ዕገሌ ስላልገባው ይቁም አይባልም፣ እስኪገባው መቀጠል አለበት›› ስላለኝ እንደገና ጉዳዩን አነሣሁት።
ካለፈው ሰሞን ጥቂት ቀደም ብሎ የድሮው አሜሪካዊ ዕውቅ የኪነ ጥበብ ሰው ፍራንክ ሲናትራ ሲዘከር ነበር። ያ ሁሉ ጥበብ እያለው ያን መሰል ችሎታ ሳያጣ ጠጪነቱ ግን ሕይወቱን ቅጥ አሳጥቶት እንደነበረ ዘጋብያን አስምረውበታል። ሌላው አሜሩካዊ ዶን ጊብሰንም እንዲህ ዘመነ ሕወቱ ብልሹ ሆኖ ለሕልፈት በቅቷል።
እዚህ በሀገራችን ያየን እንደሆነ እጅግም ከዚህ የተለየ አይመስለኝም። ‹‹ለምን እንዲህ አደረጉ?›› በማለት ሙት ወቃሽ አልባል እንጂ በቁጥር ያላነሱ፣ በኪነ ጥበባት ተግባራቸው እጅግ የተወደሱ፣ የተሞገሱ፣ እንዲያውም በኅብረተሰቡ ‹‹አርአያ‹‹ ሊሆኑ የሚበቁ በተቃራኒው ሆነው ማለፋቸው እጅግ ያሳዝነኛል። እኔ ዕገሌ ዕገሊት ብዬ መጥቀሱን ልተወውና ‹‹ተምሳሌት›› ሲሰኙ የሚበቁ ጠቢባን በአሳዛኝ መልክ አልፈዋል።
የአንድ ነገር ‹‹ተምሳሌት›› መባል እኮ ቀላል ነገር አይደለም። እንዲያው ለመልካም ተምሳሌት ምሳሌ ልስጥና ‹‹አንበሳ የጀግና ተምሳሌት ነው›› ሲባል እንሰማለን። ‹‹ብርሃን የደስታ ተምሳሌት›› መሆኑን እናውቃለን። እናም እነዚህ እንደ ዓይን ብሌን የምንሳሳላቸው፣ እንደ ዕንቁ የምናያቸው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን የደስታ ተምሳሌት ሆነው ዘመነ ሕይወታቸውን ቢጨርሱ ኖሮ ግን ከትናንትና ወዲያ ከትናንት ዛሬም በሕልፈተ ሕይወት የተሰናበቱትን ወገኖች ስናስብ አሟሟታቸው በኃዘን ላይ ኃዘን ተደራርቦ ብዙዎች መጽናናትን እንዳንችል አድርጎናል። ለምሳሌም ታምራት ሞላን እናስበዋለን። እርሱ እራሱ እንዳለው ከሆነ ግን በሌሎቹ እንደታየው አይደለምና ቃሉ ማጽናኛ ሆኖናል።
በአንድ ወቅት ይህ ዕውቅ ዘፋኝ ታምራት ሞላ መሬቱን ገለባ ያደርግለትና በጋዜጠኛ ሲጠየቅ በዘመነ ሕይወቱ አንድ ጠብታ አስካሪ መጠጥ ቀምሶ እንደማያውቅ ነበር በኩራት የተናገረው። እንግዲህ እርሱ ብቻ ሆነ እንጂ ሌሎች ተዋናይም ሆኑ ተዋንያት ወይም ዘፋኞች ወይም ሌሎች የኪነ ጥበባት ‹‹ከዋክብት›› ስለ መጠጥ ሲጠየቁና ሲመልሱ እኔ በበኩሌ አልሰማሁም። ነገሩ ‹‹የታወቀ›› ነውና መጠየቁም፣ ማስጠየቁም ቁም ነገር ያለው ሆኖ ባለመገኘቱ ይመስለኛል ተወት የተደረጉት። ተፈራ ካሳ ግን በቃለ ምልልስ አላዳምጠው እንጂ ‹‹በመጠጥ ደስታ ይገኛል ብላችሁ፣ መጠን አትለፉ ትቃጠላላችሁ›› ያለው ትዝ ይለኛል። እንግዲህ ‹‹በጥቂቱ ጠጡ›› ለማለት ሳይሆን አይቀርም። የቱን ያህል መልካም እንደሆነ አንባቢ ይወቀው።
ሌላው አፍራሽ ግን አለ። ‹‹እልም ነው ጭልጥ ነው እንጂ ጂን አይላመጥም – ጉበት ዘመድ ላይሆን አልለማመጥም›› የሚል ቧልተኛ ሞልቷል። ታዲያ ይህ አያሳዝንም? በአንድ ወቅት አንድ ምሰንቆኛ በዚህ ስንኝ ሲያቧልት ነጋዴው የመቶ ብር ኖት በግንባሩ ላይ ለጥፎለታል። የመጠጥ ነጋዴ እድሜ ልኩን እንዲህ በሰው ሕይወት እንዳላገጠ ኖረ። እንዲህ በጠጭ አሾፈ፣ ጠጪም በራሱ እያላገጠ በወዛ እየዘነፈ ተጠለፈ። ጊዜውን በብኩንነት አሳለፈ፣ በስንፍና ተከፍፎ ረገፈ። ጎበዝ፣ ጎበዙ የአረቂ ሰው እንዲህ ሲታረድ ይስቃል።
‹‹ስንፍናን የዘራ ችግርን አጨደ- ሲታረድ ይስቃል ወዛን የወደደ›› እንዲባል!! ደግሜ እለዋለሁና ተመልካች አንብቦ ልብ ይበለው!! ‹‹ሲታረዱ መሳቅ!!›› እጅግ አሳዛኝ!!! ይህን ርዕስ በየጊዜው የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ባስነበባቸው ጽሑፎች በየመድረኩ ሳይቀርቡ፣ በተናገራቸውም ቦታዎች ሳያስደምጣቸው ቀርቶ አያውቅም። ሰሚ ግን እስካሁን እያነሰ እንጂ እየዳጎሰ መሄዱን መመስከር የሚችል ያለ አይመስለኝም። እስቲ ይህንን የያዝነውን 2012ን ዓ.ም በንፁህ አዕምሮ የምናስብበት ጊዜ ፈጣሪ አምላክ ያደርግልን ዘንድ ጸሎት ማድረግ ይገባናል።
መልካም የመስቀል በዓል ይሁንላችሁ
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2012