የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ 100 የኩላሊት ሕሙማንን የአንድ ዓመት የኩላሊት እጥበት (ዳያሊሲስ) ወጪ የሚሸፍን የገንዘብ ድጋፍ ስለማድረጉ ከሰሞኑ ተሰምቷል። በዚህም መሠረት ህሙማኑ በሐኪም የታዘዘላቸውን የኩላሊት እጥበት መርሐ ግብር ሳይቆራረጥ በሳምንት ሦስት ቀን ለአንድ ዓመት የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
የኩላሊት ህመምተኞቹ ላለፉት በርካታ ጊዜያት በሳምንት የታዘዘላቸውን የሦስት ቀን የኩላሊት እጥበት መርሐ ግብር በገንዘብ እጥረት ምክንያት ማድረግ ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡
የድጋፍ ዜናው የተሰማው ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) እና ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሰሞኑን በጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ህክምና ክፍሎች በመዘዋወር ታካሚዎችን ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡
ድጋፉ በጳውሎስ፣ ዘውዲቱ እና ምኒልክ ሆስፒታል ተኝተው ህክምናቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ 100 የኩላሊት ህሙማን የተደረገ ሲሆን በገንዘብ ሲተመን ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ይደርሳል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የኩላሊት እጥበት ለሚያከናውኑ ህሙማን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያፈላልግ ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ በጉብኝታቸው ወቅት መናገራቸውን ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
***
ይኸን ዜና ስሰማ የተደበላለቀ ስሜት ውስጤ ሰርጓል። የኩላሊት ህመምን ጨምሮ በአጠቃላይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መንሰራፋት በርካታ አምራች ዜጎችን አሳጥቶናል፣ እያሳጣንም ይገኛል፡፡
ግሎባላይዜሽን ዓለምን ወደአንድ ጠባብ መንደርነት እየለወጠ ነው። የከተሜነት ዘመናዊ አኗኗር ተስፋፍቷል። ከአኗኗር ዘይቤ መለወጥ ጋር ተያይዞ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መፈንጫ ሆነናል። ዛሬ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ የስኳር ሕሙማን ሕጻናት በየሆስፒታሉ ደጃፍ ማየት እንግዳነቱ ቀርቷል። እንደ ስኳር፣ ደም ግፊት፣ የአዕምሮ ሕመም፣ ካንሰር፣ አስም፣ ስትሮክ፣ ኩላሊት፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት፣ ሥር የሰደደ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች… የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እየተፈታተኑና እየቀጠፉም ነው፡፡
በድንገት ካጣናቸው እጅግ በርካታ ወገኖቻችን አንዱ ወጣቱ ድምጻዊ ኢዮብ መኮንን መቼም አንረሳውም። ኢዮብ ሮጦ ባልጠገበበት ዕድሜው በድንገት ያጣነው በስትሮክ ሕመም ነበር፡፡
ድምጻዊ እዮብ መኮንን ዘውዴ ከአባቱ ከአቶ መኮንን ዘውዴ ይመኑ እና ከእናቱ ከወ/ሮ አማረች ተፈራ የምሩ ጥቅምት 12 ቀን 1967 ዓ.ም በጭናቅሰን ገብርኤል ጅጅጋ ከተማ ተወለደ።
ለአቅመ አዳም ከደረሰ በኋላ አልበሙን እስካወጣበት 2000 ዓ.ም ድረስ የሌሎች ድምጻውያንን ሥራዎች፣ በዋነኝነት የአሊ ቢራን እና የቦብማርሊን ዘፈኖችን ሲያቀነቅን የቆየ ሲሆን በነዚህ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ውጭ ወደ ዱባይም በመመላለስ በድምጻዊነት ሰርቷል። በጥቅምት 2000 ዓ.ም በአብዛኛው በሬጌ ስልት የተዘጋጀው “እንደቃል” የተሰኘው የመጀመሪያ አልበሙ ከተለቀቀ አጭር ጊዜ በኋላ፣ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን በማትረፍ እስካሁን ድረስ በከፍተኛ መጠን በመደመጥ ላይ ይገኛል። በአዲስ ጣዕም የመጣው “እንደቃል” አልበም በኢትዮጵያ ውስጥ የሬጌ ሙዚቃ ይበልጥ ይወደድ ዘንድ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጥሯል።
ከዚህ አልበሙ በኋላ በሀገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የሙዚቃ ዝግጅቶችን እያቀረበ ቆይቷል። በአዲስ አበባ የተለያዩ የሙዚቃ ቦታዎች ላይም ለረጅም ጊዜያት በቋሚነት የራሱን ዘፈኖች ለአድናቂዎቹ በመድረክ ሲያቀርብ ነበር። ሁለተኛ አልበሙንም በመሥራት ላይ የነበረ ሲሆን በድንገት እስኪታመም ድረስ ሙሉ ትኩረቱ በዚሁ ሥራው ላይ ነበር።
ድምጻዊ እዮብ መኮንን ነሐሴ 7 ቀን 2005 ዓ.ም በድንገተኛ የስትሮክ ህመም መኖሪያ ቤቱ ደጃፍ ላይ የወደቀ ሲሆን፤ ህመሙ ጠንቶ እራሱን ሳያውቅ በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል የህክምና ክትትል ሲደረግለት ቆይቶ በወዳጅ ዘመዶቹ ርብርብ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ናይሮቢ ኬንያ ሄዶ፣ በአጋካን ሆስፒታል ሕይወቱን ለማትረፍ ጥረት ቢደረግም በታመመ በአምስተኛ ቀኑ ነሐሴ 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ምሽት በ38 ዓመቱ ሕይወቱ ማለፉን የምናስታውሰው በታላቅ ሐዘን ነው፡፡
የጤና ሚኒስቴር ሐሳብ
ከጤና ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ በትኩረት ከተሰራ በቀጣይ 15 ዓመታት የ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ሰዎችን ህይወት መታደግ ይቻላል፡፡
የጤና ሚኒስቴር በቅርቡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ የሚመክር ስብሰባ አካሂዷል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማንን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ዶክተር አሚር አማን በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚመዘገበው ሞት ውስጥ 52 በመቶ የሚሆነው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት የሚከሰት መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ የተነሳም ሀገሪቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2017 ላይ በዘርፉ 31 ቢሊየን ብር ስለማጣቷም ጠቅሰዋል፡፡
መንግሥት የዜጎችን ጤና ለማስጠበቅ የተለያዩ የጤና ፖሊስዎችን፣ስትራቴጂዎችን እንዲሁም አዋጆች በሥራ ላይ እንዲውሉ እየሠራ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ ሚኒስቴሩ ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል እና መቆጣጠር በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ የተሰራ የ15 ዓመት የኢንቨስትመንት ጥናታዊ ጽሁፍ ይፋ ተደርጓል።
ጥናቱ በተለይም የልብና የደም ቧንቧ በሽታ፣ ካንሰር፣ የስኳር ህመም እና ሥር የሰደደ የመተንፈሻ አካላት በሽታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ነው የተገለፀው።
ይፋ የተደረገው ጥናት የዜጎችን ህይወት በቀላሉ ለመታደግ በሚቻልበትና በዘርፉ የሚባክነውን የሀብት ብክነት ለማስቀረት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
በቀጣይ የዜጎችን የአመጋገብ ባህል ለማሻሻል ማለትም ከስኳር፣ ጨው፣ አልኮል እና ጫት አጠቃቀም እንዲሁም በሌሎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥና የሕግ ክልከላ ሥራ የሚሠራ መሆኑም ተገልጿል።
በዚህ መሠረትም የጨው፣ ስኳር እና ሌሎችም ለተለያዩ በሽታዎች አጋላጭ የሆኑ የምግብ ዝርዝሮች ላይ ሲደረግ የቆየው ጥናት በአዋጅ ሊታጀብ መሆኑ ተነግሯል።
ዓለም አቀፍ መረጃዎች ምን ይላሉ
በመላው ዓለም በየዓመቱ 41 ሚሊየን የሚሆን ሕዝብ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሕይወቱን እንደሚያጣ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ይህም በመቶኛ ሲሰላ 71 በመቶ ይደርሳል።
ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ከሚሞቱት መካከልም 15 ሚሊየኑ ዕድሜያቸው በ30 እና 69 ዓመት መካከል የሚገኝ ነው። ከተጠቀሰው ላይ 85 በመቶ የሚሆነው ሞት የሚደርሰውም ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባለባቸው አገራት እንደሆነም በቅርቡ ድርጅቱ ይፋ ያደረገው መረጃ ይዘረዝራል።
የካንሰር፣ የልብና ስኳርን የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በገዳይነታቸው ግንባር ቀደም ከሚባሉት በሽታዎች ውስጥ እንደሚመደቡ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። እነዚህ በሽታዎች በዓለም ዙሪያ ከ 36 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በየዓመቱ ለህልፈተ ህይወት እንደሚያበቁ መረጃዎች ያመለክታሉ። ጤነኛ ያልሆነ አመጋገብ፣ የአኗኗር ዘይቤዎች፣ ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል መጠጣት፣ በቂ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ ለእነዚህ በሽታዎች መንስዔ ተደርገው ይጠቀሳሉ።
በዚህም የተነሳ በሽታዎቹ በዓለም ዓቀፍም ይሁን በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ልዩ ትኩረት የሚፈልጉ መሆናቸውን በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሀኪምና የዓለም ዓቀፍ የስኳር ህመምተኞች ፌደሬሽን የአፍሪካ ሪጅን ሊቀመንበር ዶክተር አህመድ ረጃ ተናግረዋል፡፡
በሽታዎቹን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያደርጉት ጥረት የአሳሳቢነታቸውን ያህል እንዳልሆነ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በምህጻሩ WHO በቅርቡ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል። «ክሊኒክ ኮምፔር» የተባለ ለንደን የሚገኝ የጤና ተቋምም፤ ከዓለም ዓቀፉ የጤና ድርጅት WHO፣ ከአሜሪካው ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት CIA እና ከዓለም ዓቀፍ የሳንባ ጤና ድርጅት አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት፤ የዓለም አገራት ከበሽታዎቹ ጋር ተያይዞ ያሉበትን የሥጋት ደረጃ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት ከፍተኛ የጤና ችግር ያለባቸውና የጤና ችግር በሚል በሁለት ምድብ አስር አስር አገሮችን በቀዳሚነት አስቀምጧል።
በመጀመሪያው ምድብ ማለትም ከፍተኛ የጤና ችግር ያለባቸው 10 አገራት የተካተቱ ሲሆን ሲጋራ በማጨስና አልኮል በመጠጣት ቼክንና ስሎቫኪያን የመሳሰሉ በአብዛኛው የምስራቅ አውሮፓ አገራት በዚህ ዝርዝር ተቀምጠዋል። ዩኤስ አሜሪካ ከልክ ባለፈ ውፍረት የተነሳ 35 በመቶ የሚሆኑት ዜጎቿ ጤንነታቸው ሥጋት ላይ ነው በሚል በዚህ ምድብ ውስጥ የተካተተች ብቸኛዋ አውሮፓዊ ያልሆነች አገር ነች።
በሁለተኛው ምድብ ማለትም የጤና ችግር ካለባቸው 10 የዓለም አገራት ዝርዝር ውስጥ አፍጋኒስታንና ኔፓል በዚህ ዝርዝር የተቀመጡ ብቸኛዎቹ የኤዥያ አገራት ሲሆኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኛው የአፍሪካ አገራት የተካተቱበት ነው። ከአገራቱ መካከል ጊኒ፣ ኒጀር፣ ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ ኤርትራ፣ ማላዊ፣ ሶማሊያ እና ሞዛምቢክ ይገኙበታል። ኢትዮጵያ ደግሞ በ10ኛ ደረጃ ተቀምጣለች።
በእነዚህ የአፍሪካ አገራት ከደረጃው ዝርዝር አንፃር ሲታይ ሥጋቱ መለስተኛ ይምሰል እንጂ በተለይ በኢትዮጵያ የካንሰር፣የልብና የስኳር በሽታዎችን የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እየጨመሩ መምጣታቸው ይነገራል። በተለምዶ የሀብታም አገራትና ሰዎች ችግር ተደርገው ይወሰዱ የነበሩት እነዚህ በሽታዎች አሁን መካከለኛ ገቢ ያላቸውንና ድሃ የሚባሉት አገራትና ሰዎችም እያጠቃ መምጣቱ እየተነገረ ነው። ለዚህ ደግሞ ጤነኛ ያልሆነ የአመጋገብና የአኗኗር ዘይቤ የአልኮል መጠጥና የአደንዛዥ ዕፆች አጠቃቀም በድሀ አገራት እየተበራከተ መምጣቱ የበሽታዎቹ ሥጋት እንዲጨምር ማድረ ጉን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ ከከተሞች እድገት ጋር ተያይዞ በከተማ የሚገኙ ወጣቶች በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም ሳይቀር ጫትና ሺሻ እንዲሁም በአልኮል መጠጥ ሱስ መጠመድ እየተለመደ መምጣቱ ይነገ ራል። በሀገሪቱ በቂ የስፖርት ማዘውተሪያና የመዝናኛ ቦታዎች አለመኖርም ችግሩን እንዳባባሰው ይስተዋላል። ጤናማ ያልሆኑ የምግብ ሸቀጣሸቀጦች ለገበያ መቅረብም ሌላው የጤና ሥጋት እየሆነ መምጣቱን ብዙዎች ይገልፃሉ። ዶክተር አህመድ ረጃ እንደሚሉት ችግሩን ለመፍታት የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል።
እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መንግሥታት የዜጎቻቸ ውን የአኗኗር ዘይቤ እንዲሻሻል በማድረግ በበሽታዎቹ ሳቢያ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በርትተው ሊሰሩ ይገባል።
እንደማጠቃለያ
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአመዛኙ ከአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ጋር የተያያዙ ናቸው። በተለይ ያልተመጣጠነ አመጋገብ እና ከአካላዊ እንቅስቃሴ (ስፖርት) መራቅ ለበሽታዎቹ እንደሚያጋልጠን ባለሙያዎች በየጊዜው የሚያስጠነቅቁት ጉዳይ ነው።
እዚህ ላይ አንድ አብነት ላንሳ።በተለምዶ ርዕስ በርዕስ ስንገባበዝ፣ ሠርግ፣ ክርስትና፣ ልደት፣ ጠበል ፀዲቅ… ስንደግስ ከምናቀርባቸው የምግብ ዝርዝሮች ውስጥ እንደ ጥሬ ሥጋ(ቁርጥ) እና ክትፎ የሚቀሩ አይደሉም፡፡ በተቃራኒው የአትክልትና ፍራፍሬ አቅርቦት አነስየሚልበት፣ አንዳንዴም ከእነጭራሹ የማይቀርብበት ሁኔታ በብዛት ያጋጥማል፡፡ ይህ ከአመጋገባችን ልምዳችን ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ነው።ሌላው ቀርቶ የጓደኛ የምሣ ግብዣ እንኳን ከቁርጥና ክትፎ የማይዘልበት ክፉ ልማድ አለን። ጓደኛን ክትፎና ቁርጥ መጋበዝ እንደታላቅ የክብር መገለጫ የምናይ መሆናችን ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች መቀፍቀፊያ ምቹ ጫካ እንዲፈጠር ረድቷል፡፡
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መስፋፋት እንደሀገር ጤናማ እና አምራች ዜጎችን እያሳጣን ነው። እንደቤተሰብና ማህበረሰብ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ልጆቻችን (ሕጻናትና ወጣቶች) ያለአሳዳጊ እያስቀረ፣ ትውልዱን በተስፋ መቁረጥ ራዕይ አልባ እያደረገ ነው።
ሐኪሞች በየዕለቱ አመጋገባችንን እንድናስተካክል ይመክራሉ። (በተለይ ከዕለት የምግብ ገበታችን ስኳርና ጨው መቀነስ፣ አልኮል፣ ጫት፣ ሐሺሽ የመሳሰሉ ቢቻል መራቅ አለበለዚያም መቀነስ፣) መደበኛ ስፖርትን ማዘውተር (በየቀኑ በእግር መጓዝን ጨምሮ)፣ ቢበዛ በዓመት አንድ ጊዜ የተሟላ የጤና ምርመራ በማድረግ ጤንነታችንን እንድንከታተል ሐኪሞቻችን ደጋግመው ይመክራሉ፡፡
እንደሰማነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ100 ሰዎች የአንድ ዓመት የኩላሊት እጥበት (ዲያሊሲስ) ማድረግ የሚያስችል ድጋፍ አድርጓል። ይህ ለሕሙማኑና ለቤተሰቦቻቸው ትልቅ ትርጉም ያለው በጎ እርምጃ ነው። ግን ድጋፉ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሲመዘን ኢምንት ነው። አስተዳደሩም ሆነ የፌደራል መንግሥት ከመሰል የዕለት የእሳት ማጥፋት እርምጃ ይልቅ ዘላቂ መፍትሔ ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ይጠበቃል።
የፌደራልና የክልል መንግሥታት የኩላሊት እና መሰል ተላላፊ በሽታዎች በቀላሉና በአስተኛ ወጪ ሕክምና የሚሰጥባቸው ሆስፒታሎችና የጤና ማዕከላት በማስፋፋት፣ በቁሳቁስ በመደገፍ፣ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ሥራዎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ቢንቀሳቀሱ አምራች ዜጎችን በዘላቂነት ለመታደግ ያስችላቸዋል፡፡
(ማጣቀሻዎች፡- የዓለም የጤና ድርጅት ድረገጽ፣ ጤና ሚኒስቴር፣ የጀርመን ድምጽ፣ ፋና፣ ሪፖርተር…)
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2012