. በህግ ማስከበር ሂደቱም ህዝቡ ከጎናችን ሊቆም ያስፈልጋል
. ኦነግም ሰላማዊነቱን በተግባር ማረጋገጥ ይኖርበታል
አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ተባብሶ የቀጠለውን ችግር ከመፍታት አኳያ የክልሉ መንግሥት ማንኛውንም ዕርምጃ በመውሰድ በክልሉ የህግ ማስከበር ሥራ እንደሚያከናውን ገለጸ፡፡ በሂደቱም የክልሉ ህዝብ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም የተጠየቀ ሲሆን፤ ኦነግም አሁን ያለው የትጥቅ እንቅስቃሴ ለሰላም ያለውን አቋም ጥያቄ ውስጥ የሚከት እንደመሆኑ ሰላማዊነቱን በተግባር ማረጋገጥ እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡
የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ዓለሙ ስሜ፣ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በለውጥ ሂደቱ ጉልህ ድርሻ የነበራቸውን አካባቢዎች በተለይም የኦሮሚያ ክልልን የግጭት ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ ይህ ሂደትም በተለይ በክልሉ ምዕራባዊ አካባቢዎች ላይ የዜጎችን ህልውና አደጋ ላይ ጥሏል፡፡ የሕይወት መጥፋት፣ ንብረት መውደምና ሌሎችም ሕገ ወጥ ተግባራትን አበራክቷል፡፡ በመሆኑም የክልሉ መንግሥትም ሆነ ክልሉን የሚመራው ፓርቲ በማንኛውም መልኩ የሕግ የበላይነትን ማስከበር እንደሚገባ ወስኖ ወደተግባር ገብቷል፡፡ የክልሉ ህዝብም ይሄን ተገንዝቦ ድጋፉን ሊያደርግ ይገባል፡፡ ኦነግም ሰላማዊነቱን በተግባር ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
ዶክተር ዓለሙ እንዳሉት፤ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝቦች በስርዓቱ ላይ የሚታየውን ችግር በመቃወም የተለያየ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ውስጥ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጉልህ ድርሻ ያለው ቢሆንም፤ የዚህ ትግል እንብርትና ማዕከል የሆነውና ትልቅ መስዋዕትነትም የከፈለው የኦሮሞ ህዝብ በተለይም የኦሮሞ ወጣት ወይም ቄሮ ለለውጡ ትልቅ አስተዋጽዖ ያደረገ ኃይል ነው፡፡ እንደ ድርጅትም ክልሉን የሚመራው ድርጅት ኦዴፓ ለውጡን እውን ለማድረግ ከሌሎች እህት ድርጅቶችና የለውጥ ኃይሎች ጋር ከባድ መስዋዕትነት በመክፈል ዛሬ የተደረሰበት ላይ ተደርሷል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ለውጥ ጥቅማቸውን የነካባቸው ኃይሎች አሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች እንደፈለጋቸው የሰዎችን ሰብዓዊ መብት እየረገጡ፤ ሰዎችን እያሰቃዩ፤ ጥፍር እየነቀሉና ሌሎች ኢሰብዓዊ የሆኑ ሰይጣናዊ ድርጊት በሰው ልጅ ላይ ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው፡፡ የአገሪቱን አንጡራ ሀብትም ሲዘርፉ የቆዩ ናቸው፡፡ ለውጡን ተከትሎም እነዚህ ኃይሎች ለሠሩት ወንጀል መንግሥት ተጠያቂ እያደረጋቸውና ለህግ እያቀረባቸው ይገኛል፡፡ ስለዚህ ይሄ ያሰጋቸው ኃይሎች የለውጡ መጠናከር የእነርሱን ተጠያቂነት የሚያጠናክር መሆኑን ስለሚያውቁ ይሄንን ለውጥ ለመቀልበስ ካልሆነም ለማዳከም የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ለዚህም የዘረፉትን የአገር ሀብት በመርጨትና ፀረ ሰላም ኃይሎችን በማስታጠቅ ሰላምን በማወክና ሽብር በመፍጠር ይሄንኑ ተግባራቸውን ከሚደግፏቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እየሠሩ ነው፡፡
በተለይም ኦሮሚያ የለውጡ ማዕከል ከመሆኗ አንጻር፤ አሁንም ለውጡን በማራመድ ትልቅ ሚና ያለው ከመሆኑ አኳያና ህዝቡም የዚሁ አካል እንደመሆኑ፤ እነዚህ ኃይሎች ትኩረታቸውን በኦሮሚያ እና በሌሎችም ለለውጡ አስተዋጽዖ ባላቸው ትልልቅ ክልሎችም ሆኑ አመራሮች ላይ ማድረጋቸው ግልጽ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የለውጡ አካል የሆኑ አመራሮችን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር፤ ህዝቡንም በለውጡ ላይ እምነት እንዲያጣ ለማድረግ ቀን ከሌሊት እየተሠራ ነው፡፡ በዚህም በተለይም በክልሉ ምዕራባዊ አካባቢ የዜጎች ሕይወት እየጠፋ፣ አመራሩም ዋጋ እየከፈለና ሕይወቱ እያለፈ፣ ፖሊስ ጣቢያ እየተሰበረ መሳሪያ እየተዘረፈ፣ ባንክ እየተዘረፈ፣ የዜጎች በነፃነት ወጥቶ የመግባትና የመንቀሳቃስ መብት ተገድቦ፣ ዜጎች በፍርሐት ተሸብበውና የመንግሥት አገልግሎትም ተቋርጦ፣ ልጆች ከትምህርት ተለያየተው፣ እስከአሁን ታግሰናል፡፡ ለምን ከተባለም፣ ለሰላም ሲባል ነው፡፡ የአንድ አገር ልጆች መገዳደል የለብንምና በድርድር ይሄን ችግር እንፍታው ብለን ስድስት ወር ህዝብም፣ የመንግሥት መዋቅሩም ሆነ ሥርዓቱ ዋጋ እየከፈለ ታግሰናል፡፡
አሁን ግን ህዝቡም ተማሯል፤ ህዝቡ የህግ የበላይነት ይከበር በማለት መንግሥትን እየጠየቀ ነው፤ መንግሥት የለም ወይ የሚባልበት ደረጃም ስለደረሰ፤ የክልሉ መንግሥትና ክልሉን የሚመራው ፓርቲ ከዚህ በኋላ ሕገ ወጥነትንና ስርዓት አልበኝነትን የምንታገስበት ሁኔታ የለም፡፡ በሕግ ማንኛውንም ዕርምጃ ወስደን ሕግና ስርዓት የማስከበር ሥራ መጀመር እንዳለበት አቋም ወስደን እየተንቀሳቀስን ነው ያለነው፡፡ ይሄም ሆኖ ግን አሁንም የሰላም በራችን አልተዘጋም፡፡ ምክንያቱም ሁላችንንም የምንጠቅመው በተለይም አገሩንና ህዝቡን የሚወድ ዜጋ የሚጠቅመው ህዝቦች ያለምንም መሸማቀቅ በሰላም ወጥተው የሚገቡባት አገርን ስንፈጥር፤ በጋራ ያለመጠፋፋት ከተንኮልና ሸር ፖለቲካ ወጥተን ለሰላማዊ ፖለቲካ በጋራ ስንሰለፍ ነው አገርም ሆነ እኛ የምንጠቀመው፡፡
ሙሉ ለሙሉ ጥቅም የቀረባቸውና ትናንት አገሪቱን ሲዘርፉ ብሎም ኢሰብዓዊ ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩ አካላትም ቢሆኑ ለጊዜው ለህግ መቅረብን እንደ ጥፋት ዓይተው የሚያደርጉት ጥፋት አይጠቅማቸውም፡፡ በመሆኑም ህዝቡ ቀደም ሲል ለለውጥ ታግሎ ለውጥ እንዳመጣና ከለውጥ ኃይሉ ጎን እንደቆመ ሁሉ፤ ለወራት በደል ሲደርስ የታገስነው ኃይል አጥተን ወይም ዕርምጃ መውሰድ አቅቶን ሳይሆን ለሰላም ቅድሚያ በመስጠታችን መሆኑን አውቆ አሁንም ህግን ለማስከበር በምናደርገው ጥረት ከጎናችን ሊቆም ይገባል ነው ያሉት ዶክተር ዓለሙ፡፡
በቅርቡ ኦነግ የሰጠውን መግለጫ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ድክተር ዓለሙ በሰጡት ምለሽ እንደተናገሩት፤ ከኦነግ በተለይም በአቶ ዳዉድ ኢብሳ ከሚመራው ኦነግ የሚጠበቀው መግለጫ ማውጣት አይደለም፡፡ የሚጠበቀው እውነተኛ የሰላም ታጋይ መሆን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለተ ሹመታቸው እንደ መንግሥት ያቀረቡት ጥሪ ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት መገዳደል፣ መጠላለፍና መጠፋፋት ይቅር በማለት፤ ሁሉም በሰላም፣ በእኩልነትና በነፃነት ተንቀሳቅሶ የሚሠራባት አገር እንፍጠር የሚል ነበር፡፡ ከዚህ ጥሪ ባለፈም በተለያየ ምክንያት በአሸባሪነት ተፈርጀው፣ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸውና በሌላም ምክንያት ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ሕግ የሚከለክላቸው ሳይቀሩ ምህረትና ይቅርታ ተደርጎላቸው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወደአገሩ ገብቶ በእኩልነት የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡ ለኦነግም ይሄው ዕድል ተፈጥሯል፡፡
ዶክተር አለሙ እንደገለጹት ኦነግ፣ በአንድ በኩል በሰላም ለመታገል አሥመራ ያለውን 1ሺ300 ወታደሩን በሰላም ትጥቅ አስፈትቶ አስገብቶ እያለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የታጠቀ ኃይል በምዕራብ ኦሮሚያ በኩል ማንቀሳቀስ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ጥርጣሬ ውስጥ ያስገባዋል፡፡ በሰላምና ዴሞክራሲያዊ መንገድ የአገሪቱን ህግና ሕገ መንግሥት አክብረን እንታገላለን ማለት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በሰላም እንንቀሳቀሳለን ብሎ በትጥቅ መንቀሳቀስ ሕገ ወጥ ነው፡፡ ምክንያቱም በሰላም መንቀሳቀስ ማለት ከትጥቅ ውጪ ያለ እንቅስቃሴ ነው፡፡
ስለዚህ ልክ ሌሎች በክልል እንዲሁም በአገር ደረጃ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ሰላማዊ መንገድን መርጠው ትጥቅ በመፍታት እንዳደረጉት ሁሉ ኦነግም ይሄንኑ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም በትጥቅ ተደራጅቶ ሲታገል የነበረው ኦነግ ብቻ ሳይሆን፤ የአርበኞች ግንቦት ሰባትና ሌሎችም ድርጅቶች ነበሩ፡፡ እናም እነርሱ እንዳደረጉት ሁሉ እርሱም ቁርጠኛ ሆኖ ሙሉ ኃይሉን ወደሰላም ማስገባት ይጠበቅበታል፡፡ ለራሱም ሆነ ለኦሮሞ ህዝብና ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅመውም ከመግለጫ ባሻገር በተግባር ይሄን ቁርጠኝነት ማሳየት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2011
ወንድወሰን ሽመልስ