‹‹የመስቀል ወፍ›› የሚለው ቃል ፈሊጣዊ ትርጉም አለው፡፡ ቃሉ የሚዘወተረው ገጠር አካባቢ ነው፡፡ የመስቀል ወፍ ማለትም ጠፍቶ ቆይቶ አንድ ጊዜ ብቻ ብቅ የሚል ማለት ነው። የተባለበት ምክንያትም በራሷ በመስቀል ወፍ ባህሪ ነው፡፡
የመስቀል ወፍ የምትባለው የወፍ አይነት የምትታየው ከመስቀል ሰሞን ጀምሮ ነው፡፡ በክረምት ወቅት አትታይም። እንኳን በክረምት ወቅት የበጋውን ወቅት ራሱ ሙሉውን አትታይም፡፡ ቆይታዋ የጸደይና የመኸር ወቅት ላይ ብቻ ነው፡፡ የት እንደምትሄድ ባይታወቅም ከታህሳስና ጥር ወራት በኋላ አትታይም፡፡ በዚች ወፍ ላይ የተሰራ ጥናትም ስላልተገኘ ምክንያቷን ማወቅ አልተቻለም፡፡
በልምድ ከምናየው ግን ስለወፏ ባህሪ ማውራት እንችላለን፡፡
በመኸር ወቅት የምትታየው ጤፍ የሚወቃበት(የሚመረትበት)አውድማ አካባቢ ነው፡፡ ከጤፍ መጠን በላይ የሆነ የእህል አይነት አትመገብም፡፡
ሌላው ባህሪዋ ከሌሎች ወፎች ጋር ተቀላቅላ አትታይም፡፡ ብቻዋን ነው አውድማ ውስጥ እና በአውድማ ዙሪያ ባሉ ዛፎች ላይ የምትታየው፡፡ ምናልባት አውድማ ውስጥ ለጤፍ ለቀማ ስለሚገቡ ሌሎች ወፎች አብረዋት ይሆናሉ እንጂ እሷ አትቀላቀልም፡፡አልፎ አልፎ ግን ራሳቸው የመስቀል ወፎች ሁለትና ሦስት ሆነው ይታያሉ፡፡ እንደ ሌሎች የወፍ አይነቶች ግን ብዛት የላቸውም፡፡
የመስቀል ወፍ ትክክለኛ ምስሏን ኢንተርኔት ላይ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ በስዕላዊ አገላለጽ ለመናገር ያህል፤ ጥቁር ሆና በደረቷ ላይ ነጭ ነገር አላት፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ጥቁር ብቻ ናት፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ቀይ የመስቀል ወፍም አለች፡፡
ስለመስቀል ወፍ ሌላም የሚወራ ነገር አለ፡፡ የመኸር ወቅት የወፎች መራቢያ ስለሆነ የተቃራኒ ፆታን ለመሳብ ይቺ የመስቀል ወፍ የምትባለዋ ቀለሟን ስለምትቀይር ነው እንጂ ከየትም የመጣች አይደለችም፤ የነበረችው ወፍ ናት ቀለሟን የምትቀይር የሚባል ነገር አለ፡፡
ስለመስቀል ወፍ የተሰራ ጥናት ባናገኝም ገጣሚ መንግሥቱ ለማ ‹‹ማን ያውቃል›› በሚለው ግጥሙ የአደይ አበባና የመስቀል ወፍን የመስከረም ቀጠሮ ይነግረናል፡፡የአደይ አበባም እንደ መስቀል ወፍ የሚታየው በመስከረም ወር ብቻ ነው፡፡የቱንም ያህል መስኖ ዳር ይሁን፣ ዓመቱን ሙሉ ዝናብ ይጣል አደይ አበባ ከመስከረም ወር ውጭ አይታይም፡ ፡ አደይ አበባን የሚያበቅለው የውሃ ማግኘት ሳይሆን ከመስከረም ወር ጋር ቃልኪዳን ያለው ይመስላል፡፡ ለዚህም ነው ባለቅኔው ‹‹ማን ያውቃል ቀጠሮ እንዳላቸው›› ሲል የተናገረው፡፡
የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ፣
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ፣
ማን ያውቃል………?
መንግሥቱ ለማ
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2012