የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለን ነው። አንድ አፈንጋጭ ጓደኛችን ነበር፡፡ አፈን ጋጭ ያልኩበት ምክንያት ብዙዎቻችን የተስማማንባቸውን ነገሮች የሚጥስ ሀሳብ ስለሚያመጣ ነው፡፡ አለ አይደል አንዳንዴ በጋራ የምንስማማባቸው ነገሮች? አለ አይደል የሆነ የማንደፍራቸው ነገሮች? እነዚያን ነገሮች ደፍሮ ይናገር ነበር፡፡
የሆነ ‹‹አሳይመንት›› ተሰጠን፡፡ የተሰጠን ሥራም በግቢው ውስጥ አስገራሚ ሕይወት ያላቸውን ሰዎች ወይም አስተማሪ የሆነ ሕይወት ያላቸውን ፈልጎ በቃለ መጠይቅ የሕይወት ታሪካቸውን ማቅረብ ነው። ዕቅዱ ተሰጥቶን ሌላ ቀን ያገኘናቸውን ሰዎች ይሆናሉ አይሆኑም የሚለውን ለመምህራችን እያቀረብን ነው። አንደኛው ቡድን ያቀረበው በግቢው ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ከአትክልተኝነት ጀምሮ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ሲያገለግሉ የቆዩ ሽማግሌ ነው፡፡ የተመረጡበት ምክንያትም ለበርካታ ዓመታት አገልግለው በከፍተኛ ድህነት ውስጥ እየኖሩ መሆኑ ነው፡፡ ይሆናል አይሆንም በሚለው ላይ ተወያዩበት ተባልን፡፡
የሁላችንም ሀሳብ ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህን ያህል ዓመት ዩኒቨርሲቲውን ያገለገሉ ሰውየ እንዲህ መቸገር የለባቸውም፤ ዩኒቨርሲቲው ቤትም ሊሰጣቸው ይገባል አልን፡፡
ይህኔ ይህ አፈንጋጭ ነው ያልኳችሁ ልጅ እጁን አወጣና አስተያየት መስጠት ጀመረ። ‹‹የእኝህን ሰውየ የሕይወት ታሪክ ስትሰሩ የቁጠባ ባህላቸውንም ጠይቋቸው፤ ይህኔ እልም ያሉ ሰካራም ቢሆኑስ? ገንዘባቸውን ያባከኑት በመጠጥና በሌሎች አልባሌ ነገሮች ቢሆንስ? ዩኒቨርሲቲው እኮ እንደማንኛውም ሠራተኛ ይሆናል የከፈላቸው፤ እና እርሳቸው አባካኝ የሆኑ እንደሆነ ዩኒቨርሲቲው ምን ያድርግ?›› አለ። በወቅቱ ብንስቅም እየቆየ ሲሄድ ግን ‹‹እውነቱን እኮ ነው›› ማለትም ጀመርን፡፡
ሽማግሌውን ታታሪ ሠራተኛ እና የግቢው ከፍተኛ ባለውለታ ያደረግናቸው ስለተቸገሩ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ብዙ ጊዜ ልብ ብላችሁ ከሆነ በምቾት ውስጥ ያለ ሰው ምንም ያህል ለተቋምና ለአገር ውለታ ቢውል ተመስጋኝነቱ ትንሽ ነው፡፡ ተመችቶት የሚኖር ሰው የሚሰደበውና የሚወቀሰው ይበልጣል።
በአንፃሩ ተቸግሮና ተጎሳቁሎ የሚኖር ደግሞ ሰነፍ ቢሆን እንኳን ተመስጋኝ ነው። ነገሩን ካየነው ግን የሥራ ትጋት ስለተቸገሩ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሀብት ያላቸው ሰዎች ከህዝብ አጭበርብረው ነው ያገኙት የሚል እሳቤ ስላለ ነው፡፡
እንግዲህ ይሄ ነገር ሲነሳ ቀዳሚዎቹ የመንግሥት ባለሥልጣናት ናቸው፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት የባለሥልጣናቱን የሀብት መጠን መዝግቤ ለህዝብ አሳውቃለሁ ሲል ነበር፡፡ ለነገሩ ባለሥልጣናቱም ፈቃደኛ አይደሉም የሚባል ነገር አለ፡፡
ቆይ ይሄ ነገር ግን ደግ ነው? (ለባለሥልጣን ወገንክ በሉኝ ደግሞ) እርግጥ ነው ሌባ ባለሥልጣናት አሉ፤ ግን ሀብታም የሆነ ሁሉ የግድ በሙስና ነው እንዴ? ራሳቸው የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ምን ሲሰሩ ነበር? ‹‹ከአንድ ብር ተነስቶ መኪና የገዛ፣ ከምንድንትስ ተነስቶ ምንድንትስ የሆነ…›› እያሉ ሲሰሩ አልነበር? ሰው ከአንድ ብር ተነስቶ ሚሊየነር(ቢሊየነርም ቢሆን) መሆን እንደሚችል እየታወቀ፤ በወር ምናምን ሺህ ብር የሚያገኝ ሰው ሀብታም ቢሆን ታዲያ ምን ይገርማል? ወይስ የመንግሥት ባለሥልጣን ቆጥቦም ቢሆን ሀብታም መሆን የለበትም? የህዝብ አገልጋይነቱ የሚረጋገጠው የግድ ድሃ ከሆነ ነው?
ይሄ ነገር መግቢያ ላይ የገለጽኩት አይነት ገጠመኝ ነው፡፡ አንዳንድ ሰው የቱንም ያህል ገንዘብ ቢያገኝ አባካኝ አለ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ገንዘቡን በትክክል ሥራ ላይ የሚያውል አለ። ለምሳሌ አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ገና ተራ ሠራተኛ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ የሚያገኛትን ደሞዝ አጠራቅሞ ትንሽ ሥራ ጀመረ እንበል፡፡ የሥራ መደቡ እያደገ ሲሄድ ደሞዙም ይጨምራል፡፡ ያንንም እያጠራቀመ የጀመረውን ሥራ በልጆቹ በኩል እያሰፋው ሊሄድ ይችላል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ከፍተኛ ካፒታል አንቀሳቃሽ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ይሄ ሰውየ ሀብታም ቢሆን ምን ችግር አለው? ይሄ ሰውየ ለህዝብ የሚጠቅም ካምፓኒ አቋቁሞ የሥራ ዕድል ቢፈጥር ነው ወይስ የሚበላውና የሚለብሰው አጥቶ በየቦታው ‹‹እየየ!›› ቢል ነው? እንዲያውም ሁሉም ሀብታም ሆነው የሥራ ዕድል ቢፈጥሩ ይሻል ነበር፡፡
እዚሁ ላይ አንድ ነገር ልብ ይባልልኝ። እያወራሁ ያለሁት ስለሌባ ባለሥልጣናት አይደለም፡፡ ሲጀመር የሌባ ባለሥልጣን ገንዘብ ለቁም ነገር ስለማይውል የሥራ ዕድልም አይፈጥርም፡፡ እንዲህ አይነት ባለሥልጣናት መኖራቸው አይካድም። የእነዚህ ባለሥልጣናት ገንዘብ ግን ጉድጓድ ውስጥ ተቀብሮ የውስኪ መራጫ ነው እንጂ የሥራ ማስኬጃ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ከህዝብ አጭበርብረው ሕንፃ የገነቡም ይኖራሉ፡፡ መንግሥት እነዚያን ነው መቆጣጠር መቻል ያለበት፡፡ ያንን መቆጣጠር ሲያቅተው ነው ‹‹የሀብት መጠን ምዝገባ›› የሚል?
የሆነው ሆኖ ግን ይሄ የሀብት መጠን ምዝገባው ሙስናን ያስቀር ይሆን? ወይስ መጠኑን ብቻ አውቆ መተው ነው? ቆይ ግን ባለሥልጣናቱ ሲጠየቁ ‹‹ሰርቄ ነው ያገኘሁት›› ይሉ ይሆን? ይህን ካላሉ ታዲያ ከየት እንዳመጡት በምን ይታወቃል? ከአንድ ብር ተነስቼ ነው ሀብታም የሆንኩ ቢሉስ? ወይስ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የመጡበትን አካሄድ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ይኖር ይሆን? እንግዲህ እንዴት እንደሚሆን እናያለን፡፡
ለነገሩ የሀብት ምዝገባው አሁን ላይ ተረስቷል አይደል? ማለቴ አንድ ሰሞን ተወርቶ አሁን ላይ ዝም ተብሏል፡፡ ይሄንንም ወደፊት እናያለን፡፡
መንግሥት ነገሩን ከልብ ካሰበበት መጀመሪያውኑ እንዳይዘርፉ ማድረግ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የሀብት መጠን ማስመዝገቡ ላይ ባለሥልጣናቱ ፈቃደኛ አልሆኑም የተባለው ነገር ግን ምንን ያመለክታል? እውነትም ሰርቀው ነው ያገኙት ማለት ነው? ታዲያ ለምን ያገኙበትን መንገድ አይናገሩም?
የመንግሥት ባለሥልጣን የግድ ድሃ መሆን አለበት አይባልም፡፡ ዳሩ ግን ነጋዴ ከሆነም ችግር ነው፡፡ ያ ማለት የተጣለበትን ኃላፊነት አይወጣም። ትኩረት የሚሰጠው ለግል ቢዝነሱ ነው።
ለምሳሌ መምህር ሆነው ሱቅና ሌሎች የንግድ ሥራዎች ያላቸው አሉ፡፡ እነዚህ መምህራን በተደጋጋሚ ክፍለ ጊዜ ይቀጣሉ። ይሄ ትውልድን መግደል ነው። በሌሎች የኃላፊነት ሥራዎችም እንደዚሁ ነው፡፡ የግል ቢዝነሱን የሚሠራ ሰው ኃላፊነቱን በሚገባ አይወጣም፤ ያ ማለት የተሰጠው ኃላፊነት የሚፈልገውን ዓላማ አያሳካም ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ከታየ የመንግሥት ባለሥልጣን ሀብታም መሆን የለበትም ማለት ነው፡፡
ለማንኛውም መንግሥት የባለሥልጣ ናቱን የሀብት መጠን ሲያሳውቅ እንዴት እንዳገኙት ጨምሮ ይሁን! በጥሩ የሥራ ፈጠራ ዘዴ ከሆነ እንዲያውም ሊሸለሙ ይገባል፡፡ የህዝብ ሀብት ዘርፈው ከሆነም ሊቀጡ ይገባል፡፡ ዳግመኛ እንዲህ አይነት ነገር እንዳይፈጠር የሚያደርግ አሠራርም ይኑረው!
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2012
ዋለልኝ አየለ