ለለውጥ አወንታዊ አስተሳሰብ እንዴት መገንባት ይቻላል?

ሕይወትህን በአዲስ አቅጣጫ ለመለወጥ ትፈልግ ይሆናል፤ አሁን ካለህበት በተሻለ ጠንካራ የመሆን ህልም ይኖርሃል፤ የበለጠ ደስተኛ፣ የበለጠ ስኬታማ የመሆን ፍላጎት ለማሳካት ግን ምን ማድረግ እንዳለብህ ላታውቅ ትችላለህ። ይህንን ለማሳካት አስማተኛ መሆን አይጠበቅብህም። ስኬት በዕድልም አይገኝም፤ ሚስጥሩ የእለት ተእለት ባህሪህን ማሻሻል፣ አዳዲስ አዎንታዊ ልማዶችን መማር ላይ ነው ያለው። ጥናቶች በየቀኑ የምታደርጋቸው ትናንሽ ነገሮች አስተሳሰብህን እና የስኬት መንገድህን እንደሚቀርፁ ይናገራሉ። ይህ በተለይ ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች እጅግ ጠቃሚ ነው። ለስኬት ያለህ ፍላጎት፣ የምታወጣው ጉልበት እና ህልምህ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ አሉታዊ ሃሳቦች ወደ ኋላ ሊመልሱህ ይችላሉ። ያንን ግን መቀየር ትችላለህ። አወንታዊ ልማዶችን መገንባት አዎንታዊ አስተሳሰብን ለማዳበር ይረዳል። ዘላቂ ለውጥም የሚመጣው በዚህ መንገድ ነው። ለዚህ ነው ዛሬ በ‹‹መጋቢ አዕምሮ›› አምዳችን ላይ ‹‹ለለውጥ እንዴት አዎንታዊ አስተሳሰብ መገንባት ይቻላል›› በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ትኩረት ለማድረግ የወደድነው።

ከዚህ የሚከተሉት ሃሳቦች አዎንታዊ አስተሳሰብን ለማዳበር የሚረዱ መንገዶችን ይጠቁሙናል። ለመሆኑ አዎንታዊ ልማዶች የምንላቸው ምንድን ናቸው? ዓለም አቀፍ ጥናቶችስ ስለእነዚህ ልምዶች ምን ይመክሩናል። የአሜሪካን የሳይኮሎጂ ማህበር (APA) ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፣ አዎንታዊ ልማዶች በሚከተሉት መንገዶች ሊገለፁና ልናዳብራቸው የምንችላቸው ናቸው።

በሕይወታችን ውስጥ በእያንዳንዱ ጥረታችን ውስጥ ልምድ ልናደርጋቸው ከሚገቡት መካከል የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ አንዱ አንደሆነ ጥናቱ ይጠቁማል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጡንቻዎቻችንን ብቻ ለማዳበር የሚጠቅም አይደለም። ይልቁኑ ለአዕምሯችን ንቁ መሆን ሁነኛ መፍትሄና መድሃኒት ነው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በምናደርግበት ሰዓት አንጎላችን ‹‹ኢንዶርፊን›› የተባሉ ኬሚካሎችን ይለቃል። እነዚህ የበለጠ ደስተኛ እንድንሆን እና የጭንቀት ስሜት እንዳይሰማን ያደርጉናል። ከዚህም በተጨማሪ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በተሻለ ሁኔታ ለመተኛት እና የበለጠ ለማሰብ ይረዳል። ታዲያ እነዚህን አዎንታዊ ስሜቶች ለማግኘት ስፖርት መሥራት ልምድ ልናደርግ ይገባል። ይሁን እንጂ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የግዴታ ብዙ ብር ከፍሎ ጂም መግባት አያስፈልግም። ለምሳሌ ከሥራ መልስ በፍጥነት መራመድ፣ በምንወደው ሙዚቃ በእረፍት ሰዓት መደነስ፣ ከጓደኞች ጋር እግር ኳስ መጫወት፣ በቤት ውስጥ ቤተሰቦቻችንን የቤት ውስጥ ሥራዎች ማገዝ በቂ ሊሆን ይችላል።

ይህንን እንቅስቃሴ ለመጀመርና በእለት ተእለት ሕይወታችን ውስጥ ልምድ ለማድረግ ቀስ በቀስ በትንሹ መጀመር እንችላለን። አካላዊ እንቅስቃሴ በየእለቱ ለማድረግ ቢያንስ በቀን አምስት ደቂቃ በጣም ጥሩ ጅምር ነው። ይህንን ልማድ ቀስ በቀስ መገንባት ይቻላል። በተለያዩ ሀገራት በተካሄዱና ብዙ ሰዎችን ባሳተፉ ግዙፍ ጥናቶች ላይ እንደተመለከተው፣ አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለአዕምሮ ጤና እና ድብርትን ለመከላከል ከሚረዱት ምርጥ ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው። በተለይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ምን ያክል ችሎታ እንዳለን እና በተለይ በራሳችን ላይ ያለን እምነት እንዲጎለብት ይረዳል።

የማሰብ ቸሎታን መለማመድ

በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ከሚያስፈልጉ አዎንታዊ ልማዶች ውስጥ ሌላው ወሳኙ ጉዳይ የማሰብ ችሎታን መለማመድ መሆኑን ጥናቱ ይጠቁማል። ይህ ማለት በቀላሉ ለአሁኑ ሕይወታችን ሙሉ ትኩረት መስጠት ማለት ነው። ስላለፈው ነገር አለመጨነቅ ግን ስለወደፊቱ አጽንዖት አለመስጠት አይደለም። ይልቁኑ “አሁንን” በጥልቅ ማሰላሰልና ማስተዋል አዕምሮን ያረጋጋል፤ አሉታዊ ሃሳቦችን ይቀንሳል። ይህንን አዎንታዊ ልማት እንዴት መለማመድ አንደሚቻል ጥናታዊ ውጤቶች ይመክራሉ። በመጀመሪያ የማሰብ ችሎታን ለማዳበር ለአንድ ደቂቃ ያህል በፀጥታ ለመቀመጥ መሞከር አንዱ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሌሎች የሚረብሹ ሃሳቦችን ወደ ጎን በመተው በውስጣችን ላይ ትኩረት አድርገን ማሰላሰል ይኖርብናል። ይህንን በምናደርግበት ወቅት አዕምሯችን እየተቅበዘበዘ ሊያስቸግረን ይችላል። ያ የተለመደ ነው! ነገር ግን ራሳችንን እያረጋጋን እና ወደ ውስጣችን ብቻ እያሰላሰልን መቆየት ይኖርብናል። ይህንን ልማድ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በምናደርግበት እና በእግር በምንጓዝበት ልምምዱን ማድረግ እንችላለን። ለምሳሌ እግሮቻችን በመሬት ላይ ሲራመዱ ማስተዋል አንዱ ዘዴ ሊሆን ይችላል። ሌላው የማሰብና ወደ ውስጥ የማሰላሰል አዎንታዊ ልማድን በምንመገብበት ጊዜ ማድረግ አንችላለን።

ወደ ውስጥ ማሰብ የማሰላሰል አቅማችንን ያዳብራል። ከውጪው ዓለም ጋር ተነጥለን ውስጣችንን ማዳመጥ እንድንችል ያግዘናል። አብዝተን በሕይወታችን ውስጥ ትናንት ሰለሆነው ነገር ከማሰብ ይልቅ አሁን በጥንካሬ ማድረግ ስለምንፈልገው ነገር ማሰላሰል ስንችል ከውጥረት መላቀቅ እንችላለን። እንደ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በመሰሉ ትላልቅ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በማሰላሰላችን ውስጥ ባለፈው ነገር ላለመረበሽ እና ወደ ውስጣችን በትኩረት ለማሰብ ጥንቃቄ ማድረግ ከጭንቀት ጋር የተያያዘውን የአንጎል ክፍል እንዲቀንስ እና ከትኩረት እና ከመረጋጋት ጋር የተያያዙ ክፍሎችን እንዲያድግ ይረዳል። በተለይ ሃሳቦችን እንደ ሃሳቦች ብቻ ሳይሆን እንደ እውነታ እንድንመለከት ይረዳናል። ይህም ለውሳኔዎቻችን እና በራሳችን ላይ ለሚኖረን መተማመን ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።

አዳዲስ ነገሮች መማር

አዎንታዊ ከሆኑ የሕይወት ልምዶች ውስጥ አንዱ በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን መማር ነው። ይህንን ልምድ በአንድ ጊዜ ልናዳብረው አንችልም። ከላይ በተደጋጋሚ ለመግለፅ አንደሞከርነው አወንታዊ ልምዶችን ቀስ በቀስ ነው ማዳበር የሚኖርብን። ለምሳሌ አንድ የማናውቀውና በሕይወታችን ውስጥ አዲስ ነገር የሚጨምርልንን ልማድ በትንሹ ማድረግ ልንጀምር እንችላለን። ለምሳሌ ስለ አንድ አስደሳች ነገር የአንድ መጽሐፍ አንድ ገጽ ማንበብ ሊሆን ይችላል፤ በኢንተርኔት ላይ አጭር ትምህርታዊ ቪዲዮ መመልከትም ሊሆን ይችላል። በሌላ መልኩ እኛ የማናውቀውን አሊያም ሌሎች የሚችሉትን ክህሎት (ሥራ) እንዴት እንደሚሠራ መጠየቅ አዲስ ነገር ለመማር ከሚረዱ መንገዶች ውስጥ አንዱ ነው። በየቀኑ አንድ አዲስ ቃል በእንግሊዝኛ (ወይም ሌላ ቋንቋ ሊሆን ይችላል) ለመናገር መሞከር ልምዳችንን ያዳብርልናል። ይህንን የሕይወት ልምድ በየእለቱ ማድረግ ስንችል አንጎላችን “ማደግ እችላለሁ፣ መሻሻል እችላለሁ” የሚለውን አምነት እያዳበረ ይመጣል። ይህም በራስ መተማመናችንን ይገነባል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት በመደበኛነት አዳዲስ ነገሮችን የሚማሩ የሚያጋጥማቸውን የሕይወት ፈተናዎችን ለመጋፈጥ የበለጠ የተሻለ እድል አላቸው።

ከመልካም ሰዎች ጋር መዋል

በሕይወታችን ውስጥ ልምድ ልናደርጋቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል። አዎንታዊ አስተሳሰብ ካላቸው ከመልካም ሰዎች ጋር ግንኙነት መፍጠር ነው። ለምሳሌ አብዛኛውን ጊዜ የምናሳልፈው ከሰዎች ጋር ይሆናል። በዚህ ወቅት እኛንና ዓላማችንን የሚደግፉ ጓደኞች መምረጥ ይኖርብናል። አሉታዊ ድርጊቶች ውስጥ ስንገባ ያለመሰልቸት ወደ መስመር የሚመልሱን እና ጠንካራ እንድንሆን አቅጣጫ የሚያሳዩን ጓደኞች ሊኖሩን ይገባል። ለሕይወት ቀና አመለካከት ያላቸው እና ደስተኛ የሆኑ (ፈገግታን የመረጡ) የሚስቁ ጓደኞችን እንምረጥ።

ሁል ጊዜ የሚያደንቁን ብቻ ሳይሆን የሚተቹንና ሃሳባችንን የሚሞግቱ ሰዎችን መጥላት የለብንም። ምክንያቱም በሥራችን ውስጥ የምንፈጥረውን ክፍተት ያሳዩናል። ሌላው የምንሠራውን ሥራ ስኬት ላይ አንድናደርስ የሚያበረታቱን፣ የሚያነሳሱን ሰዎችን በዙሪያችን እናድርግ። እኛም በተመሳሳይ መሰል ጓደኞቻችንን እንርዳ። የደግነት ተግባራት እኛንም ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ያደርጋሉ። ከ80 ዓመታት በላይ የፈጀው ዝነኛው “የሃርቫርድ የአዋቂዎች ልማት ጥናት” ጥሩ ግንኙነት በሕይወት ውስጥ በጣም ጠንካራ የደስታ እና የጤና በረከቶች እንዳሉት አሳይቷል።

ከላይ ከጠቀስናቸው ክህሎቶች በተጨማሪ በርካታ አዎንታዊ ልምዶች አሉ። እነዚህን ልምዶች የተለያዩ መጽሐፍትን በማንበብ እና ትምህርታዊ ሥልጠናዎችን በመውሰድ ልናዳብር እና በሕይወታችን ውስጥ እንደ ቅመም ልንጠቀማቸው እንችላለን። አወንታዊ ልማዶችን መገንባት ዘር እንደ መትከል ነው። ዛሬ ትንሽ የችግኝ ዘር ትተክላለህ፤ በየቀኑ ትንሽ ውሃ ታጠጣዋለህ፤ ከአረም (ከመጥፎ ልምዶች) ትጠብቃለህ፤ ይህን ልማድ ለማድረግ ጊዜ ይወስዳል፤ ትዕግስት ይጠይቃል፤ ነገ ግን ትልቅ ዛፍ ይሆናል። ቀስ በቀስ በእርግጠኝነት ጠንካራ ሥሮች ይኖሩታል፤ ረዥም ቅርንጫፎችን ያበቅላል፤ ጥላ እና ፍሬ ይሰጣል፤ የእኛም አወንታዊ ልማዶች ለአዕምሯችን ልክ አንደ እነዚያ ዘሮች ናቸው። በየቀኑ በትንንሽ ድርጊቶች ልናሳድጋቸው ይገባል።

አንተ በዚህ መልኩ ሕይወትህን መቀየር እንደማትችል ውስጥህ የሚነግርህ ከሆነ በየቦታው ሕይወታቸውን በዚህ መልኩ የቀየሩትን ወጣቶች አስታውስ። በየቀኑ 15 ደቂቃ ብቻ መማር የጀመሩ እጅግ በርካታ ወጣቶች (ተማሪዎች) የትምህርት ውጤታቸውን አሻሽለዋል። ይህንን እውነታ ያልተቀበሉ እና በአሉታዊ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ግን ውጤታማ መሆን አይችሉም። በሚሠሩት ሥራ እና በሚያገኙት ውጤት ምስጋናን የተለማመዱ እና ዓለማቸውን እውን ያደረጉ ሰዎች ሁሌም በተስፋና በደስታ የተሞሉ ናቸው። በመሆኑም በአዎንታዊ ልማዶች የተለወጡ ሰዎችን ምሳሌ አድርገህ አንተም ልክ እንደእነሱ ለመለወጥ መሥራት ይኖርብሃል።

ወጣቶች የወደፊቷ ኢትዮጵያ ተረካቢዎች ናቸው። አንተም የእነዚህ አካል እንደሆንክ ጥርጥር የለውም። የአንተ ክህሎት፣ ማሰላሰል፣ ጉልበትህ እና እውቀትህ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ነው ሁሌም እራስህን በመማር፣ በማሰላሰል፣ በአዎንታዊ እሳቤዎች ሁሉ መገንባትና ማሳደግ የሚኖርብህ።

በአንድ ሌሊት ተነስተህ ዛሬ ሁሉንም ነገር ለመለወጥ አትሞክር። አንድ ትንሽ አዎንታዊ የሆነ ልማድ መምረጥና መጀመር በቂ ሊሆን ይችላል። ምናልባት በየቀኑ ጠዋት ውሃ መጠጣት ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ጭንቀት ሲሰማህ ሶስት ጊዜ በጥልቀት ትንፋሽህን ወደ ውስጥና ወደ ውጪ ማስወጣትና ማስገባት መለማመድ ሊሆን ይችላል። ምናልባት ከመተኛትህ በፊት አንድ ጥሩ ነገር ስለራስህ እና ስለወደፊቱ እቅድህ መፃፍ ሊሆን ይችላል። ቀለል አድርገህ መለማመድ ጀምር። ከቀን ወደ ቀን፣ ደረጃ በደረጃ፣ በልማድ፣ አእምሮህን ትለውጣለህ። ጥንካሬን ትገነባለህ፣ ተስፋ ትገነባለህ፤ የምትኮራበትን ሕይወት ትገነባለህ። የወደፊት ስኬትህ አና ተስፋህ በእጅህ ላይ ነው። ዛሬ መልካም ዘሮችን መትከል ጀምር። ሰላም!!

በዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You