
– አቶ ጉግሳ ደጀኔ የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባና የአስተዳደርና አገልግሎት ክላስተር አስተባባሪ
በኢትዮጵያ ከተሞች እየታየ ያለው ፈጣን የመሰረተ ልማት ግንባታ እንደሀገር ለመድረስ ከታሰበው የብልፅግና ማማ እያንደረደሯት ይገኛሉ። በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ላለፉት ሁለት ዓመታት እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪዶር ልማት ሥራዎች ሀገሪቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከበለፀጉት ሀገራት ተርታ ሊያሰልፋት እንደሚችል ማረጋገጫ እየሆነ ነው።
በአዲስ አበባ የታየውን የለውጥ ጮራ ተከትሎ በርካታ የሀገሪቱ ከተሞች ላይ ከፍተኛ መነቃቃት ተስተውሏል። ያረጁ ቤቶችንና ሕንፃዎችን አፍርሶ ከመገንባት በዘለለ ነዋሪውን ማዕከል ያደረጉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችም ጎን ለጎን መከናወናቸው ለብዙዎች እፎይታን ፈጥሯል።
የሀገሪቱን አጠቃላይ ገፅታ በመሰረታዊነት መለወጥ የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን ጭምር እያከናወኑ ካሉ ከተሞች መካከል ደግሞ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የሸገር ከተማ አንዱ ነው። ከተማው ከተመሰረተ ምንም እንኳን በጣት የሚቆጠሩ ዓመታት ቢሆኑትም አስተዳደሩ የአፍሪካና የኢትዮጵያ መዲና ከሆነችው አዲስ አበባ ጋር የተናበበ፤ የተቀናጀና የተጣጣመ የልማት ተግባራትን ለማከናወን ጥረት እያደረገ ይገኛል። በተለይም የወደፊቱ ስማርት ሲቲ እንዲሆን በማለም ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ተነድፈው ሥራ ተጀምሯል፡፡
በሌላ በኩል ከከተማው ምስረታ እድሜ ጋር በተያያዘ የነዋሪውን ፍላጎት ማዕከል ባደረገ መልኩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ያለመከናወኑ፤የመልካም አስተዳደርና መሰል ችግሮች ይስተዋሉበታል። በእነዚህና በሌሎችም ከሕብረተሰቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመያዝ የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባና የአስተዳደርና አገልግሎት ክላስተር አስተባባሪ የሆኑትን አቶ ጉግሳ ደጀኔ ቢሮ ጎራ ብለናል። ይኸው ከእንግዳችን ጋር ያደረግነው ውይይት እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ሸገር ከተማ ከተመሰረተበት ዓላማ አንፃር አስተዳደሩ ያከናወናቸውን የልማት ሥራዎች ያብራሩልንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ጉግሳ፡- እንደምታስታውሱት ሸገር ከተማ የተመሠረተው 2015 ዓ.ም ሲሆን ከዚያ በፊት ስድስት የሚሆኑ ከተሞች ተበታትነው የነበሩና የራሳቸው አስተዳደር የነበራቸው ነበሩ። እነኚህ ከተሞችና በከተማ ዙሪያ የነበሩት ወደ 41 ቀበሌ ገበሬ ማኅበራት የነበሩ ሲሆን ከተሞቹንና ቀበሌዎቹን በአንድ ላይ በማደራጀት ነው አንድ ትልቅ ከተማ እንዲመሰረት የተደረገው። ከተሞቹ ጎን ለጎን የነበሩ ቢሆንም በመሰረተ ልማት የተሳሰሩ ባለመሆናቸው የቅርብ ሩቅ ሊባሉ የሚችሉ ናቸው።
የክልሉ መንግሥት በተበታተነና ባልተናበበ መንገድ የሚከናወነው የልማት ሥራም የታሰበውን እድገት ማምጣት የማይችል መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት በአንድ ላይ እንዲጣመሩ አድርጓል። በመሰረቱ በዚያ መልኩ መቀጠሉ ከተማው ተወዳዳሪነቱን የሚጎዳ እንጂ የሚጠቅም አይደለም፤ በተጨማሪም ሃብት ለብክነት የሚያጋልጥ ስለሆነ ወደ አንድ መምጣቱ በብዙ መልኩ ጠቃሚ እንደሆነ እሙን ነው።
ይህንን ከተማ ስንመሰርት በዋናነት ለሀገሪቷም፤ ለክልልም የከተሜነት ደረጃችንን ያሻሽላል በሚል ታሳቢ ያደረገ ነው። የሀገራችን ከተሞች በከተሜነት ደረጃና መስፈርት ስንለካ የሚጎላቸው ነገሮች አሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ስናይ ዝቅተኛ የሚባል ነው። በመሆኑም ይህንን ደረጃ ሊያሻሽል በሚያስችል መልኩ ነው ሸገርን ለመመስረት ታሳቢ የተደረገው። በነገራችን ላይ አንድ ከተማ ደረጃውን ጠብቋል የሚባለው ለሰው ኑሮ፣ ሥራ ኢንቨስትመንት፣ ለንግድም ሆነ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ መሆን ሲችል ነው። የከተሞቻችንን ደረጃ ሳንጠብቅ የምንመኘውን ብልፅግና ማምጣት አንችልም።
በዚህ አግባብ እንደ ክልል መንግሥት አቅጣጫ ተቀምጦ በተለይ ሶስት ነገሮችን ማዕከል አድርጎ ነው እንዲሠራ የተደረገው። በመጀመሪያ ደረጃ መሬትን በማዘመን ሥራ መሥራት ያስፈልጋል የሚል ነው። ይህም ሲባል የመሬትን ውጤታማነት የሚጨምርና የበለጠ በመሰረተ ልማቶች የተሳሰሩ ለማድረግ ያለመ ነው። ሁለተኛ መሬት ብቻ ሳይሆን የሰውንም አኗኗር መቀየር ያስፈልጋል። ይህም ሲባል ነዋሪው ራሱ የከተሜነት ባህሪ ሊኖረው ያስፈልጋል።
ይበልጥ የሰለጠነ፣ የከተማ ባኅሪን በአግባቡ የተገነዘበ፣ ሥራ ፈጣሪ የሆነ፣ ሙያ ያለው ማኅበረሰብ መፍጠር ይጠበቃል። በሶስተኛ ደረጃ ከተሜነት የተላበሰ የከተማ አስተዳደር ማደራጀት ያስፈልጋል በሚል ነው። ይህም ሲባል በተለይ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደታችን ሰውን ማዕከል ያደረገ፤ ችግሮችን የሚቀርፍ፤ የተፋጠነና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚችል መዋቅር በተግባር የግድ የሚል ነው።
በተጨማሪም በኤሌክትሮኒክስ፤ በቴክኖሎጂ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደቶችን ማዕከል ባደረገ መልኩ ከተሞቻችን ማስፋትና ማሳደግ ይገባል በሚል እሳቤ ሲሠራ የቆየ ሲሆን እነዚህን ተልዕኮዎች ለማስፈፀምና መሬት ለማውረድ ጥረት ተደርጓል። በዚህ መሰረት በቅድሚያ መሬትን ከተማ የማድረጉ ሂደት በፕላን እንዲመራ ለማድረግ ጥረት የተደረገ ሲሆን፤ በዋናነትም አጠቃላይ ከዚህ በፊት ተበታትኖ የነበረውን ስድስት ከተማ አንድ ማስተር ፕላን የማዘጋጀት ሥራ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ሲከናወን ቆይቷል። እንዲሁም ማስተር ፕላኑን መሬት ለማውረድ የሚረዱት የአካባቢ ፕላን፣ ጎን ለጎን የተለያዩ የሕግ ማሕቀፎችን የማዘጋጀት ሥራ እንዲሠራ ተደርጓል።
ከተዘጋጁ የሕግ ማሕቀፎች መካከልም የሕንፃ ከፍታዎችን አግባብ ሥርዓቶችን የምንመራበት መመሪያዎችና ሰነዶች ተጠቃሽ ናቸው። እንደሚታወቀው ከተማው የሚመራበት ከማስተር ፕላኑ የሚቀዳ ስትራቴጂካል ፕላኖችን ማዘጋጀት ይጠበቃል። ይህንን መሰረት በማድረግ ፊዚካል ሥራዎችን የምንሠራበት ስትራቴጂካል ፕላን ማዘጋጀት ሥራ ሥንሠራ ነበር። እንዲሁም ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ መሰረተ ልማቶችን የመዘርጋትና የመገንባት፤ መሬትን የማዘመን ሥራዎች ተጀምረዋል። በመጀመሪያ ደረጃ ያለውን ጥራቱን የማሻሻል፤ ሁለተኛ አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን መዘርጋት ሥራዎች ሲሠሩ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በእነዚህ ዓመታት ከተሠሩ መሰረተልማቶች መካከል ለአብነት ቢጠቅሱልን?
አቶ ጉግሳ፡– በተለይ ለአዲስ አበባም የትራፊክ መጨናነቅ መፍትሔ ሊሆን ያስችላል ተብሎ የታሰበው 155 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ቀለበት መንገድ ተጠቃሽ ነው። ይህ መንገድ ከተማውን ዙሪያውን የሚያገናኝ 250 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በመጀመሪያው ምዕራፍ ወደ 38 ኪሎ ሜትር የሚሆን መንገድ ግንባታው ተጀምሮ አፈፃፀሙ 20 በመቶ ላይ ደርሷል። በዚሁ 38 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የቀለበት መንገድ ወደ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በከተማ አስተዳደሩ የተበጀተለት ሲሆን በእቅዳችን መሰረት በሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ ነው እየሠራን ያለነው።
አጠቃላይ ግንባታው ከአምስት እስከ አስር ዓመት ባሉት ግዜያት ውስጥ ለማጠናቀቅ ነው የታቀደው። ሆኖም አንዳንድ ቦታዎች ላይ አስቸጋሪ የሆኑ መልካምድር በመኖሩ ካሰብነው ጊዜ ሊያልፍ ይችላል። ለምሳሌ እንጦጦ ተራራን አቋርጦ የሚሄደው መንገድ የተለየ ቴክኒክ ካልጠቀምን ጊዜ ሊወስድብን እንደሚችል እሙን ነው፡
በሌላ በኩል የሌሎች መንገዶችም ስናይ የነበረውን ትራፊክ ማስተናገድ ላይ አሁን ካለንበት ደረጃ አቅማቸው ያነሰ ነበር፤ በተጨማሪም ከግንባታ ቆይታቸው አንፃር ያረጁ ነበሩ፤ እነሱንም መልሶ የመገንባት ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት። አሁን ወደ 80 ኪሎ ሜትር አካባቢ የሚጠጋ መንገድ ከፊሉ እየተሠራ ነው ያለው። ለምሳሌ ከኖክ 18 እስከ ኬላ ወይም ታጠቅ አካባቢ መልካኖኖ ክፍለከተማ እስከ ኬላ ድረስ ወደ 16 ነጥብ 5 የሚሆን ኪሎ ሜትር እየተገነባ ነው ያለው። በተጨማሪም ወደ 50 ሜትር ስፋት ያለው መንገድ እየተገነባ ነው። እንዲሁም እስከ ሰበታ የሚደርሰው መንገድ ኮንትራት ተሰጥቶ ሥራው የመጀመር ሂደት ውስጥ ነው ያለው።
በተጨማሪም ከኬላ እስከ ሱሉልታ፤ ከአዲስ አበባ ድንበር ጣፎ የሚሄዱ መንገዶች ፕላን ተሠርቶ አልቋል። በአጠቃላይ መሰረተ ልማቶቹ ለከተማ አስፈላጊ ስለሆኑ ወደ መሬት የማውረድ፤ ውስጥ ለውስጥ ደግሞ ገባርና ብሎክን ከብሎክ ወይም መንደርን ከመንደር የሚያገናኝ መንገዶችን በተለያዩ ግብዓቶች የሚሠራ ወደ 380 ኪሎ ሜትር ግንባታ በአብዛኛው ተጠናቋል።
እንደ አጠቃላይ አስቀድሜ ባነሳሁት ሶስት ነገሮች ላይ ሰውን፤ አስተዳደሩን የከተሜነት ባህሪ እንዲላበስ ከማድረግ አንፃር የተለያዩ ሥራዎች በስፋት ታቅደው እየተሠሩበት ነው ያለው። የዘጠኝ ወር ግምገማችን ይህንን ማዕከል ያደረገ ነበር። ዘንድሮ ልንሠራቸው ካቀድናቸው ውስጥ በተለይ በመሰረተ ልማት አቅርቦት አንፃር የተጀመሩ ሥራዎች ጥሩ እንደሆኑ ነው ያየነው። የሚጎሉን ነገሮች በቀሪ ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሠራበት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አኳያ ታዲያ እየተሠራ ያለው ሥራ ሸገር ከተማን አዲስ አበባ ካለው ልማትና እድገት ጋር ምን ያህል ተመጋጋቢና ተመጣጣኝ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ጉግሳ፡- በከተማዋ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል በዋነኝነት የፕላን ማጣጣም ሥራ ነው። በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የሸገር ከተማ አስተዳደርን ለማጣጣም ሞክረናል። የአዲስ አበባ ቀድሞ ስለተሠራ እንደመነሻ በመውሰድ ለማጣጣም ሙከራ ተደርጓል። የምንሠራቸው የልማት ሥራዎች ቀጣይነትና ተያያዥነት ያላቸው እንዲሆኑ ነው የሚደረገው። አሁንም የምንሠራቸው የልማት ሥራዎች እርስ በርስ የመደጋገፍና ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚለማበት ሁኔታዎች አሉ።
በተለይ የኮሪዶር ልማት ሁለቱም ከተሞችም ተመጋጋቢ በሆነ መንገድ ነው እየሠሩ ያሉት። ለምሳሌ ከጎሮ ወደ ኮዬና ቱሉ ዲምቱ በሚወስደው መንገድ በአንድ በኩል የአዲስ አበባ አስተዳደር በሌላኛው ደግሞ የሸገር ከተማ በተናበበ መልኩ የኮሪዶር ልማት ሥራ እየሠሩ ነው ያሉት። በፉሪ በኩልም ጎን ለጎን የሚሠሩ ሥራዎች አሉ። በአጠቃላይ በአቅም ጉዳይ ሆኖ ሁሉንም ቦታ መድረስ ባንችልም አሁን ላይ የተናበበና የተመጣጠነ ሥራ ለመሥራት ጥረት እያደረግን ነው። ይሁንና በሁለቱ ከተሞች መካከል ግን በሥራ ተናቦ የመሥራት ሥራ እንጂ በፋይናንስ የምንደጋገፍበት ሁኔታ የለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሸገር ከተማ የወደፊት ስማርት ሲቲ እንደመሆንዋ ሁሉንም ሕብረተሰብ በሚያማክልና ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ የልማት ሥራዎችን ከመተግበር አኳያ እየተደረጉ ስላሉ ጥረቶች ቢያስረዱን?
አቶ ጉግሳ፡- እንደተባለው ሸገር የወደፊት ስማርት ከተማ እንደመሆንዋ በአጠቃላይ ዘላቂነትን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። እንደ ሀገር ሲታይ የከተሜነት ደረጃችን 22 በመቶ ነው ያለው፤ ይህም ሲባል 78 በመቶ የሚሆነው ማሕበረሰብ በገጠር የሚኖርበት ሁኔታ ነው ያለው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ስናይ በአሜሪካ ከተሜነት 81 በመቶ፣ አውሮፓ 78 በመቶ፣ ኤዤያ ሀገሮች ደግሞ 76 በመቶ የደረሰ ሲሆን አፍሪካ በአማካኝ 43 በመቶ አካባቢ ነው። ከአፍሪካ ውስጥም ከሰሃራ በታች ያሉት 22 በመቶ ላይ ናቸው። ይህም በመሆኑ አብዛኛው ማኅበረሰብ የከተማ አገልግሎት ተጠቃሚ አይደለም።
ከኢኮኖሚ አንፃር ስናይ የዓለም ምርት 80 በመቶ የሚሆነው ከተማ ውስጥ ነው የሚመረተው። እንደ ሀገር ደግሞ ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ ጂዲፒ ደግሞ ከ50 እስከ 60 በመቶ አዲስ አበባ ውስጥ ነው የሚመረተው። ይህም የሚያሳየው ከተማ ማለት የኢኮኖሚ ማዕከል መሆኑን ነው። ስለዚህ ከተሜነትን ሳናመጣ ሀገርን መቀየር፤ የኢኮኖሚ ለውጥን፤ እንደማንችል ያመላክታል።
እንዳነሳሽው ከተማ አካታች መሆን መቻል አለበት፤ ሁሉም ማኅበረሰብ እንደ አቅሙ፤ እንደየሁኔታው የሚገፋ ሳይሆን የሚያካትት መሆን መቻል አለበት። ሁለተኛ ከተሜ ማለት በማስተር ፕላን የሚመራ መሆን መቻል አለበት፤ የመሬት አጠቃቀሙ ሕግን የተከተለ፤ ሥርዓትን የተከተለ ሊሆን ይገባል። የመሬት ዋጋን ሊጨምር የሚችል ወይም የመሬት አጠቃቀም ብቃትን ሊፈፅም የሚችል፤ በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ መሥራት የሚያስችል አቅም መገንባት ይገባል። ከከባቢ አየር ጋር ተስማሚ መሆንና የአፈር መሸርሸርን የሚቀንስ መሆን መቻል አለበት። በመሆኑም ይህንን ለማድረግ አጠቃላይ ከተማ ታስቦበት የሚቋቋም፤ የሚመራ መሆን ይጠበቅበታል።
ከዚህ ሃሳብ ተነስተን ወደ እኛ ስንመጣ ከተሜነት ልምዳችን ሲታይ ኢትዮጵያ ከሶስት ሺ ዓመት በፊት የከተማ ልምድ እንደነበራት የተለያዩ አስረጂ ፅሁፎች ያነሳሉ። ለምሳሌ አክሱማዊነትን እንደምሳሌ መውሰድ እንችላለን። በዚያን ጊዜ የከተሜነት ባህሪ ነበረው። ከተማ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይቆረቆር እንደነበረ ታሪክ ያስረዳል። እንደታሪክ የረጅም ጊዜ ተሞክሮ አለን፤ ይሁንና ከተማ ተብለው የተቆረቆሩት ታስቦበት አካታች በሆነ፤ ለሁሉም በሚመችና ሁሉንም ማቀፍ በሚችል መልኩ የተመሰረተ አይደለም። የከተሞቻችንን ታሪክ ስናይ ግማሹ ካምፕ ነበረ፤ በሂደት ወደ ከተማነት የመጣ ነው። በሌላ በኩል ሰው የሚበዛበት ቦታ ትናንሽ ንግዶች የተጀመሩበት፤ ሰው እየጨመረ ሲመጣ በሂደት ወደ ከተማ የመጣ ነው፡፡
ይህም ሲባል ፕላን ኖሮት፣ ታቅዶበት፣ መንገድ በየት በኩል ነው የሚወጣው? መኖሪያ ቤቶች የት መሆን አለባቸው? ፋብሪካዎች የት ነው የሚገነቡት የሚለውን ነገር ታሳቢ ተደርጎ የተመሰረቱ ከተሞች የሉንም። ከዚህ አንፃር ሲታይ አሁን የሚሠራው የኮሪዶር ሥራ መልሶ የማልማት ሥራ ነው። ከተሞች ማሟላት የነበራቸውን ነገሮች አሟልተው ስላልተመሰረቱ ለኑሮም፤ ለሥራም አመቺ ባለመሆናቸው የከተማ ስታንዳርድን በሚመጥን መልኩ መልሶ የመገንባት ሥራዎች ናቸው እየተከናወኑ ያሉት ። ይህ የሆነበት ምክንያት ከመጀመሪያውኑ እነኚህን ነገሮች አካቶ፤ በውስጡ ይዞ ስላልተቋቋመ ነው። አሁን እየገነባን ያለነው ከተማ ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን የልማት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገና ቀጣዩን ትውልድ ጭምር ታሳቢ ያደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከመሰረተ ልማት ግንባታው ባሻገር አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?
አቶ ጉግሳ፡– በነገራችን ላይ ስማርት ሲቲ ወይም የወደፊቱ ስልጡን ከተማ ለመሆን ገዘፍ ያሉ መስፈርቶች አሉት። ለምሳሌ ስማርት ኢኮኖሚ፣ አካባቢን፣ አስተዳደር፣ ማኅበራዊ አገልግሎትን ይፈልጋል። ከስድስትና ከዚያ በላይ የሚሆኑ መስፈርቶች አሉት። ከዚያ ውስጥ አንዱ ከተደራሽነት፤ ከጥራት አንፃር ሁሉም ማኅበረሰብ ሊያዳርስ በሚችል እሳቤና የሚሰጡ አገልግሎቶችም ጥራት የጠበቁ መሆን አለበት። ከዚህ አንፃር ከተማው ከተመሰረተ ጀምሮ እየሠራን ያለነው አገልግሎትን የማሻሻል ሥራ ነው። አገልግሎት ሲባል ደግሞ ቢሮ ውስጥ ብቻ የሚሰጥ አገልግሎት አይደለም። እንደሚታወቀው አገልግሎት አሳጣጣችን ችግር አለበት፤ ፈጣን አይደለም፤ ወጪ ቆጣቢ አይደለም፤ ፍትሓዊነትና ግልፀኝነት የሚጎለው ነው።
አገልግሎቱን ለማሻሻል በዋናነት ሶስት ነገሮችን ማዕከል ባደረገ መልኩ መሥራት አለብን ብለን እየሠራን ነው። አንደኛ አገልግሎትን በሚመለከት ሰራተኛን ማዕከል ያደረገ ሥራ መሥራት ያስፈልገናል። ምክንያቱም አገልግሎቱን የሚሰጠው የሰው ኃይሉ በመሆኑ ነው። የሰው ኃይሉን ሳንቀይር የተቀላጠፈ አገልግሎት ማቅረብ አንችልም፤ ብቃት ያለው አገልግሎት መስጠት አንችልም። ስለዚህ በተለይ አቅም ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚሠሩ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። በአሁኑ ወቅት በስልጠና የማብቃትና ክህሎትን የማሳደግ ሥራዎች ናቸው እየተሠሩ ያሉት፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ሠራተኛው ራሱን እንዲቀይር የመደገፍ ሥራዎች ናቸው እየተሠሩ ያሉት። በተለይም ጥረት የሚያደርገውንና ብቃቱን ያሳደገውን ደግሞ ሙያን ማዕከል በማድረግ ለእሱ የሚመጥን ቦታ የመስጠት ሁኔታ አለ። ይህም ሥራና ሥራን የሚያገናኝ፤ ሙያና ሙያተኛን የሚያገናኝ ነው። ጥንቃቄ አድርገን እየሠራን ያለነው ሰው ሙያው ላይ እንዲሠራ ማድረግን ነው። ከዚህ አንፃር ብዙ ስልጠናዎች ሰጥተናል። ምደባ ስናካሂድም እያንዳንዱን ፈፃሚ አወዳድረን ነው ያስቀመጥነው። ከምደባ በኋላ ደግሞ ሠራተኛው ብቃቱን እንዲያሻሽልና የከተሜነት ባህሪ እንዲላበስ ከማድረግ አንፃርም ሥንሠራ ቆይተናል። በተለይም የአገልጋይነት መንፈስን ለማላበስ የተለያዩ ስልጠናዎችን ከተለያየ አካላት ጋር ተቀናጅተን እየሰጠን ነው።
በተጨማሪም አገልግሎቱን ወደ ኤሌክትሮኒክስ መንገድ (ኢ-ሰርቪስ) የመቀየር ሥራ በማከናወን ላይ እንገኛለን። ይህንንም የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ለማስጀመር ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ፣ ከኢንሳና ከኢትዮቴሌኮም ጋር ተቀናጅተን እየሠራን ነው። አሁን ላይ ወደ ሥርዓት መግባት የጀመሩ ብቻ ሳይሆን ውጤትም ያመጡ ዘርፎች አሉ።
ለምሳሌ መሬት አገልግሎት ውስጥ የካዳስተር ሥራ እየተከናወነ ያለው በዚሁ መንገድ ነው። በሌላ በኩል የኢንቨስትመንት ጥያቄ የሚስተናገድበትን ሥርዓት በኦንላይን እንዲሆን ተደርጓል። ከዚህ ቀደም ግን የኢንቨስትመንት ጥያቄ ለማቅረብ ኢንቨስትመንት ቢሮ ሰው ተሰልፎ ገበያ ይመስል ነበር። አሁን ግን አንድ ሰው አይገኝም። ምክንያቱም የትም ቦታ ሆኖ በቀላሉ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ማመልከት የሚችል በመሆኑ ነው። ማመልከት ብቻ አይደለም፤ መስፈርቶች አሉ፤ ካሟላ ይቀበለዋል። ካላሟላ ደግሞ አላሟላም ብሎ መልስ ይሰጠዋል። ካለፈ በኋላ ወደ ቀጣይ ደረጃ ያልፋል። ስለዚህ በዚህ ላይ ጥሩ ውጤቶች እያመጣን ነው። ግን ማስፋትና ማሻሻል ይፈልጋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ዲጂታል አገልግሎት ለመስጠት የመሰረተ ልማት ችግሮች አሉ፤ ለዚያ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች ብቃታቸው፣ ጥራታቸው፣ አቅማቸው ላይ ችግሮች አሉ። እሱን ከሚመለከተው አካል ጋር እየተነጋገርን፤ እያሻሻልን ነው ያለነው። ከዚህ ቀደም ግን አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ችግር ሆኖብን ሕዝብም የሚወቅሰን መታወቂያ አሰጣጥ ላይ ነበር። አድሎ ያለበት የሚል ቅሬታ ይነሳ ነበር። አሁን ወደ ዲጂታል ቀይረናል። አሁን ላይ ተጠቃሚው የሚጠበቅበትን አሟልቶ ካመለከተ ባለበት ቦታ በአካል ሳይገኝ ሂደቱን ጨርሶ መጨረሻ ላይ እንዲወስድ የሚደረግበት ጅምር ሂደቶች አሉ። ይሁንና ያለቀለት፤ ችግሮችን የጨረሰ፤ የሕዝብን እርካታ አምጥቷል፤ ቅሬታዎች የሉም ማለት አይደለም። እነዚህን ጅምሮች የማስፋትና የማስተካከል ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ ኦሮሚያ ክልል አመራሩ በሳምንት ሶስት ቀን የተገልጋዩን ቅሬታ እንዲሰማ የተደረገበት አሠራር ተዘርግቶ እያለ፤ ሸገር ላይ አሁንም ችግሮች እንዳልተቀረፉ ይነሳል፤ ይህ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ጉግሳ፡- እንዳነሳሽው እንደ ከተማ አስተዳደርም፤ እንደ ክልሉ መንግሥትም በሳምንት ሶስት ቀናት ኃላፊዎች ቢሮ ቁጭ ብለው ባለጉዳዩን ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል። ሆኖም ሁሉም ቀናት የአገልግሎት ቀናት ናቸው፤ ፈፃሚው ሳምንቱን ሙሉ አገልግሎት መስጠት ይገባል። እንደ ሸገር ከተማ አስተዳደርም እነኚህ ነገሮች ተግባራዊ እየሆኑ ነው ያሉት። ነገር ግን ሰው ቢሮ ስለተቀመጠ ባለጉዳይን ያረካል ማለት አይቻልም፤ ቢሮ ቆልፎ ተቀምጦ ባለጉዳይን ሊያስተጓጉል ይችላል፡፡
በአግባቡ ባለጉዳዩን ጥያቄ አድምጦና ተረድቶ መስጠት ያለበትን አገልግሎት በብቃት፤ በጥራትና በጊዜው ሁሉም ሰው ይሰጣል ማለት አይቻልም። ነገር ግን እንደተነሳው ሰኞ፣ ረቡዕና አርብ የአገልግሎት ቀናት ናቸው።
እነዚህ ቀናቶች ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር ማገልገል ስለሚጠበቅባቸው እንደ ከተማ አስተዳደርም ተጨማሪ ሥራ አንሰጣቸውም፤ በተቻለ መጠን ተደራራቢ ነገሮች ካልመጡ፤ አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ ነው ያለው። የቢሮ መቀመጥ ሳይሆን ቢሮም ሆኖ በሚያረካ መልኩ አገልግሎት መስጠቱ ላይ ዋናው ቁም ነገሩ ነው። እኛም ባለጉዳይን ማርካት ላይ ጉድለቶች እንዳሉብን ገምግመናል። በእርግጥ የተሻሻሉና ውጤቶች የመጡባቸው አሠራሮች አሉ። ነገር ግን ሁሉም ዘርፍ ላይ አይደለም። እነዚያን ማስፋት ያስፈልጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትም፤ የሕግ የበላይነት ማስከበር የግድ ይላል።
አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ ነዋሪ ከሆኑ በዋናነትም ኮዬ ፈጬ መኖሪያ ቤት ነዋሪ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለስድስት ዓመታት በተደጋጋሚ የሚያነሷቸው የንፁሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፤ የኃይል፤ የመንገድ፤ ጤና ጣቢያና ትምህርት ቤቶች ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች ለዓመታት መመለስ ያልተቻለበት ምክንያት ምንድነው? መቼስ ነው የሚፈታው?
አቶ ጉግሳ፡- ያነሳሽው ነገር እውነት ነው፤ ከመሰረተ ልማት አቅርቦት አንፃር ጉድለቶች አሉ። እነኚህ ጉድለቶች ሸገር ከመቋቋሙ በፊት ለረጅም ጊዜ ተደራርበው የመጡ ናቸው። ለምሳሌ ከመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነት አኳያ ሲታይ አጠቃላይ ሽፋናችን አነስተኛ የሚባል ነው። አሁን ባለው ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ ሽፋናችን ከሶስት በመቶ በታች ነው። ምንአልባት አሁን እየሠራን ያለነው ሥራ የበለጠ መሻሻል ያመጣል ብለን እናምናለን።
የውሃ አቅርቦታችንም እንደዚሁ ችግር አለበት። የመብራት አገልግሎት ከሌላው አንፃር ቢሻልም በሚፈለገው ደረጃ አይደለም። እነዚህ ችግሮች እንዳሉ እናውቃለን፤ ከዚያ በመነሳት ነው መሰረተ ልማት ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ያለነው። ከዚህ አንፃር የኮዬ ችግር ስናይ እንደሚታወቀው የጋራ መኖሪያ ቤቶች እንደመሆናቸው ሁሉም መሰረተ ልማቶች በፕሮጀክት ነው የሚሠሩት፡፡
በዚህ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያሠራው በመሆኑ ኮንትራት ተሰጥተው እንዲከናወኑ ቢደረግም አፈፃፀሙ በተፈለገው መንገድ አልተሳካም። የተበላሹ ኮንትራቶች አሉ፤ እነዚያን የተበላሹ ኮንትራቶችን ለማሻሻል ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር አብረን እየሠራን ነው ያለነው። ቀደም ብሎም ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ኮርፖሬሽን በኩል ስለተሰጠ ውሉም ከእነሱ ጋር ስለሆነ በእኛ በኩል የወሰን ማስከበር ሥራ ጋር በተያያዘ ነው እገዛ የምናደርገው።
ቤቶቹ ሲያልቁ መሰረተ ልማቶቹ አብረው ማለቅ አልቻሉም። ለምሳሌ አሁን ላይ የተጀመሩ የመንገድ ሥራዎች አሉ፤ የውሃ መስመር ዝርጋታ ተጀምሮ የውስጥ ጥገና ሥራ የሚቀሩ አሉ፤ የፍሳሽ ማስወገጃም በተመሳሳይ በሚፈለገው መልክ ያልተሠሩ አሉ። ስለዚህ እነኚህ ችግሮች በሚመለከት ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር ተነጋግረናል፤ በመሰረቱ በየጊዜው የሚቀርቡ ቅሬታዎች ስለሆኑና ከእውነት የሚነሱና መሰረት ያላቸው በመሆናቸው እንዲፈታ ጥረት እያደረግን ነው።
በአሁኑ ወቅት የተበላሹ ኮንትራቶችን አቋርጦ ለአዲስ ኮንትራክተር እንዲሰጥ ተደርጓል። ግማሹ ደግሞ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው እንዲቀጥል የተደረገበት ሁኔታ አለ። ይህም ሆኖ ግን በሚፈለገው ደረጃና በችግሩ ልክ አብሮ እየሄዱ አይደሉም። ስለዚህ አሁንም አስተዳደራዊ ርምጃዎች እየተወሰዱ አገልግሎትን ለማሻሻል የሚደረጉ ጥረቶች ይቀጥላሉ።
ከትምህርት ቤትና ከጤና ተቋም ጋር ተያይዞ የተነሳው ጥያቄ በተወሰነ መልኩ አግባብነት አለው። ሆኖም ሸገር ከተቋቋመ ወዲህ እንኳን ሶስት ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፤ ማስፋፊያም የተሠራላቸው አሉ። በተጨማሪም አምስት መዋለ ሕፃናት ተገንብተዋል። አንደኛ የጋራ መኖሪያ ቤት አካባቢ እንደመሆኑ፤ ከሕዝቡ ብዛት አኳያ ያሉ መሰረተ ልማቶች ጋር ያለመጣጣም ችግሮች አሉ። ሁለተኛ ባለውም መሰረተ ልማት ላይም ቢሆን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር እንዳለ እናውቃለን። ለምሳሌ ጤና ጣቢያ ላይ በሚፈለገው መልኩና ጥራት አገልግሎት ማቅረብ ላይ ውስንነት ይስተዋላል። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ለመቅረፍ አንደኛ መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ሥራዎች እየሠራን ነው ያለነው። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይቀረፋል የሚል እምነት አለኝ። በተጨማሪም የተሠሩትን ራሱ ውስጣቸውን የማሻሻል ሥራ ሊከናወን ይገባል። አገልግሎት አሰጣጥን የማሻሻል፣ የማደራጀት ሥራዎች፤ እዚያ ውስጥ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችንና ሎጅስቲክሶችን የማሟላት ሥራዎች በቀጣይ ይከናወናሉ።
ሌላ ክፍለ ከተማ ላይም እንደዚህ አይነት ችግሮች አሉ፤ በአንድ በኩል ያሉት መሰረተ ልማቶች የጥራት ጉድለት፣ የብቃት ክፍተት ይታይባቸዋል። በተጨማሪም ከተደራሽነት አንፃር የሚስተዋሉ ችግሮች አሉ። እንደመልካም አስተዳደር ችግርም፤ እንደአገልግሎት ጉድለትም ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች በመሆናቸው እንደከተማ አስተዳደሩ ከሁሉም በፊት እነኚህ ችግሮች ትኩረት ሰጥተን የምንሠራቸው ናቸው። እነኚህን ችግሮች ለማሻሻል አስቀድሜ እንዳነሳሁት ሰው ኃይሉ ላይ መሥራት፤ አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ ደግፎ በተቻለ መጠን የተሻለ አገልግሎት ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
በዋናነትም አገልግሎቶችን ወደ አንድ ማዕከል ለማምጣት ጥናቶችን አካሂደናል፤ አገልግሎቶችን አደራጅተናል። አሁን ላይ ለአገልግሎቶቹ የሚያስፈልጉትን ቦታዎች እያዘጋጀን ነው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጀመራል። ምንአልባት ወደ አንድ ማዕከል ከመጡ እነዚህ ችግሮች ይቀረፋሉ የሚል እምነት አለን። አንዳንድ ጊዜ አገልግሎት መስጫ ተቋማቶቻችን ተበታትነው ያሉ በመሆናቸው ወደ አንድ ማዕከል ስናመጣ ሁሉም አገልግሎቶች አንድ ላይ ስለሚመጡ ችግሮቹ ይፈታሉ የሚል እምነት አለን። በጥቅሉ ችግሮች እንዳሉ እናምናለን፤ ነገር ግን ደግሞ በተቻለ መጠን እየተሠራበት ነው ለማለት እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ቤቶቹ ለተጠቃሚ ከተላለፈ ስድስት ዓመታት ተቆጥረው ሳለ እስከ አሁን ለችግሩ መፈጠር ምክንያት የሆኑ አካላትን (የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ) በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ለምን አልተቻለም?
አቶ ጉግሳ፡– ከዚህ ጋር ተያይዞ እንዳነሳሽው ተጠያቂነት ለማስፈን ጥረት እየተደረገ ነው፤ አስተዳደሩ በውላቸው መሰረት ያልሠሩ ኮንትራክተሮች ላይ ርምጃ ወስዷል፤ ውል አቋርጧል፤ በሂደት ወደ ሕግ የሚቀርቡ ኮንትራክተሮች አሉ። እዚህ ጋር ግን በዋናነት ኮንትራክተሮቹ የሚያነሱት በፊት የነበረው የኮንትራት ዋጋ እና አሁን ያለው በዋጋ ንረት ምክንያት ሥራ ለመሥራት መቸገራቸው ነው።
ስለዚህ በፊት በገቡት ውል መሰረት ሥራውን በጊዜ የማጠናቀቅ ችግሮች አሉ። በወቅቱ ደግሞ ተከታትሎ እንዲጨርሱ የማድረግ ሂደት ላይ የተለያዩ ችግሮች አሉ። እኛ ስንረከብ ከነበሩት ችግሮች አንዱ የወሰን ማስከበር ችግሮች ናቸው። በአጠቃላይ በቀጣይ ጊዜ ውስጥ የተነሱት ችግሮች ይቀረፋሉ የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በጤና ተቋም ረገድ አሁን ላይ በኮዬ አንድ ላይ ያለው ጤና ጣቢያ አይደለም ለክፍለ ከተማው ነዋሪ በሙሉ ቀርቶ ቀድሞ ታሳቢ ተደርጎ ለተሠራለት የኮዬ 1 ነዋሪ እንኳን አይበቃም፤ ያም ቢሆን በቂና አቅም ያለው ባለሙያ የለም፤ ችግሩ አሁን ላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደመሆኑ ከዚህ አኳያ ምን ታስቧል?
አቶ ጉግሳ፡- እውነት ነው፤ አንቺም እንዳነሳሽው ከነዋሪው ቁጥር ጋር የሚመጣጠን የጤና ተቋም የለም። ከአገልግሎት ጥራትና ደረጃ አንፃርም ቢሆን አይጣጣምም። በቀጣይ ግን የሚሠሩ ፕሮጀክቶች አሉ። ለዚያ ሕዝብ የሚመጥን ሆስፒታል ያስፈልጋል። በተጨማሪም ያሉትን ጤና ጣቢያዎች ደረጃ የማሻሻል ሥራዎች ይሠራሉ። በነገራችን ላይ ኮዬ ላይ ብቻ ሳይሆን ቱሉዲምቱ ላይም ሌላ አንድ ጤና ጣቢያ አለ። ያም ቢሆን ካለው ሰው ብዛት አንፃር በቂ አይደለም። አገልግሎት አሰጣጥና በውስጡ ያሉ መሰረተ ልማቶችን ማዘመን ላይ ብዙ ሊሠራ የሚገባ ጉዳይ አለ። እያሻሻልን መሄድ ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- በሌላ በኩል እርሶ ያነሱት የተወሰኑ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም ለግሉ ባለሃብት በትምህርት ዘርፍ ላይ እንዲሠማራ ምቹ ሁኔታ ያልተፈጠረበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ጉግሳ፡– ለግሉ ባለሃብት በትምህርትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ ሕብረተሰቡ አማራጭ አገልግሎት እንዲያገኝ ያልሆነበት ዋነኛው ምክንያት የከተማዋ ማስተር ፕላን እስከሚሻሻል ድረስ ነው። እስከ አሁን የኢንቨስትመንት ፍቃድ አልሰጠንም፤ ይሁንና አሁን ላይ ፕላኑ በመጠናቀቁ ኢንቨስት ለሚያደርግ ሁሉ በሩ ክፍት ሆኗል።
በተለይ እንደ ጤና እና ትምህርት መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ሕዝባዊ አገልግሎት ለሚሰጡ አካላት ቅድሚያ ሰጥተን የምንቀበል ነው የሚሆነው። ስታንዳርድ አለ፤ መስፈርቱን ካሟላ እኛ ጋር ብዙ ችግር ይኖራል ብዬ አላስብም። እንዲህ አይነቱን መሰረተ ልማት ወደ አካባቢው መምጣቱን ደግሞ እንፈልገዋለን፤ እያስተናገድንም ነው ያለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የመልሶ ማልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ጎን ለጎን የቤትና የመሬት አቅርቦት ለነዋሪው ማመቻቸት ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ጉግሳ፡- አቅርቦቶቹ አሉ፤ ነገር ግን ፍላጎትን በአንድ ጊዜ ማሟላት ላይ ውስንነቶች አሉ። ለምሳሌ ባሰባሰብነው ዳታ መሰረት የቤት ፈላጊው ቁጥር ከ80 ሺ በላይ መሆኑን ለማወቅ ችለናል። ግን ደግሞ ለእነዚህ ሁሉ በአንድ ጊዜ ማቅረብ ለአስተዳደሩ ከባድ ነው። በነገራችን ላይ መሬትና ቤትን ለብቻ የሚታይ ነገር አይደለም፤ ቤት ከቀረበ መሰረተ ልማቶች ያስፈልጉታል። ውሃ፣ መብራት፣ መንገድና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች ተያይዞ መሥራት ይጠይቃል። ያም ቢሆን አቅርቦቱ ዜሮ የሚባል አይደለም፤ ነገር ግን ደግሞ ከፍላጎቱ ጋር አይጣጣምም። እንደ አጠቃላይ ለከተማዋ ምስረታም አንዱ ምክንያት የሆነው የመሬት ወረራዎች ናቸው፤ ሕገወጥ ግንባታዎች በተለየ መልኩ ተስፋፍተው ነበር።
እነኚህ የመሬት ወረራዎች የሚካሄዱት ደግሞ የቤትን ችግር በሚቀርፍ መልኩ ሳይሆን እድሉ ያለው ሰው ብዙ መሬትና ቤት የሚይዝበት ሁኔታ ነበር። ስለዚህ መጀመሪያ ላይ ሥንሠራ የነበረው በዚህ መልኩ ከቀጠልን እንደ ሀገርም ስጋት ስለሚሆን ሕገወጥነትን የማስቀረት ሥራ ቅድሚያ ሰጥተነዋል። አብዛኛው ከጥቅሙ ተገፍቶ ዳር ቆሞ፤ የተወሰኑ ተዋናዮች መሬቱን ይዘው ወረው የግል የሚያደርጉበት ሁኔታ ማስቀረት፤ እንዲሁም ሕጋዊ ሥርዓት በመዘርጋት አብዛኛው ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ነው ጥረት ሲደረግ የነበረው። ስለዚህ ሕግ የማስከበር ሥራዎች ሲሠሩ ነበር።
በነገራችን ላይ ከመጀመሪያው ጀምሮ ጉዳዩን አውቀው ስለነበር ርምጃዎችን ስንወሰድ በአካልም ያየሁት፤ አብዛኛው ከመሬት ትርፍ ለማግኘት የሚጥሩ ሰዎች መሆናቸውን አውቃለሁ። ባለሃብቱ ቀጥታ ባልሆነ መንገድ የሚሳተፍበት ሁኔታ አለ። ደግሞም 400 ሺ እና 500 ሺ ብር መሬት ገዝቶ ጨረቃ የሚሠራ አካል ደሃ ነው ሊባል አይችልም። በሌላ በኩል ትክክለኛው ደሃ ማኅበረሰብ የእነሱን ቤቶች ጠባቂ ሆኖ የሚኖርበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች መጀመሪያ ማስተካከል ስለሚያስፈልግ ነው። ማስተር ፕላን አስቀድሜ እንደገለፅኩት ለከተማ ወሳኝነት አለው። አሁን ያንን የማንከተል ከሆነ የሚመጣው ትውልድ እያፈረሰ የሚገነባው ከተማ ነው የሚሆነው።
በመሆኑም እነዚያ ነገሮች እንዳይደገሙ የመሬት አጠቃቀማችን ሥርዓት እንዲኖረውና ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። ራዕዩን በሚመጥን መልኩ ማስተር ፕላኑን ስናዘጋጅ ነው የቆየነው፤ በተጨማሪም ከእሱ የሚሄዱ ስታንዳርዶችን አዘጋጅተን ጨርሰናል። በሶስተኛ ደረጃ ቤቶች ሲቀርቡ የነበረው በአንድ አይነት ሞዳሊቲ ነው። እንደሚታወሰው የነበረው የቤት ሞዳሊቲ በማኅበር አደራጅቶ መሬት መስጠት ነበር፤ በዚህ መሰረት ወደ 27 ሺ ሰው መሬት መውሰዱን አጣርተናል። ይሁንና 27 ሺውም ሰው ቤት አልሰራም። ግማሹ ሸጧል፤ ሌላው ከሰባት ዓመት በፊት እንደወሰደው ቁጭ አድርጎታል፤ እነዚህን እንዲሠሩበት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቿል።
በሌላ በኩል ደግሞ የቤት ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው፤ ለምን እንዳልሠሩ ጥናቶች ስናካሄድ አንዳንዱ በቂ ፋይናንስ ያለመኖር ሁኔታ አይተናል። ስለዚህ ፋይናንስ አቅርቦት ሳይመቻች መሬት ብቻ መስጠቱ ትክክል ባለመሆኑ ይህንን ማሻሻል አለብን የሚል እርምጃ ነው የወሰድነው። በመሆኑም የፋይናንስ አቅርቦቶችን ማመቻቸት ያስፈልጋል። ከቻለ ግለሰቡ ራሱ የሚሠራበት፤ አቅሙ ከሌለው ደግሞ ተበድሮ መሥራት የሚችልበትን ሁኔታዎችን ለመፍጠር ነው ጥረት ስናደርግ ነው የቆየነው። በዚህ መሰረት ከፋይናንስ ተቋማት ጋር መሥራት መቻል ያስፈልገናል። መሬት ከማቅረብ በዘለለ ሰው የተወሰነ ቆጥቦ፤ ቀሪውን ከፋይናንስ ተቋማት ተበድሮ የቤት ባለቤት የሚሆንበት ሁኔታ ለመፍጠር ነው የታሰበው፡፡
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም መሬት ይቅረብ እንጂ መሰረተ ልማቶች አልተዘረጉም ነበር። ያለመንገድ፣ ያለውሃ፣ ያለመብራት ቤት ብቻውን ቤት ሊባል አይችልም። ስለዚህ መሰረተ ልማት ዝርጋታውም አብሮ መታሰብ አለበት። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ኃላፊነትን ማከፋፋል ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የከተማ አስተዳደሩ መሬት የማቅረብ፣ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ኃላፊነት አለበት። ፋይናንስ የሚያቀርብ ተቋማት ጋር ስምምነት ላይ መድረስ አለብን። ቤት ፈላጊውም ቢሆን የተወሰነ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻል አለበት። እነኚህን ነገሮች የሕግ ሥርዓት ልናበጅላቸው ይገባል ብለን የቤት ልማትና አስተዳደር ሕግ አውጥተን የተለያዩ አማራጮችን ባካተተ መልኩ እየሠራን ነው። በተለይም የፋይናንስም ፣ የመሰረተ ልማትና የቦታ አቅርቦትም የሚያካትቱ ሕጎችን አውጥተናል፡፡
በሌላ በኩል አማራጮቹ ጠባብ ነበሩ፤ ሰው ቤት መሥራት ባይችልም እንኳን በኪራይ የማግኘት እድል ሊኖረው ይገባል። ስለዚህ ይህንን ለማድረግ የግድ መሬት ብቻ አቅርበን የቤት ችግርን እንቀርፋለን ማለት አይቻልም። ስለዚህ አማራጮችን ማስፋት ስላለብን መንግሥት አልምቶ ማቅረብ የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል። ሁለተኛ ለግል ባለሃብቱም ክፍት መደረግ መቻል አለበት።
ስለዚህ እነኚህን ነገሮች በሕግ መደገፍ ስላለብን ወደ ዘጠኝ የሚሆኑ ሞዳሊቲዎችን ለይተናል፤ በሕግ አፅድቀናል። የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። በሂደት እነኚህን ጥያቄዎችን እየመለስን እንሄዳለን። ሕዝቡ የሚያነሳቸው ቅሬታዎች እንዳሉ እናውቃለን፤ አሁንም እነዚህን ችግሮች እንዳይቀጥሉ አማራጮችን ለማስፋት እየሠራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከስምንት ዓመት በፊት ሊዝ ከፍለው መሬት ያልተረከቡ አሉ፤ እነዚህስ በዚሁ ሥርዓት ተጠቃሚ የሚሆንበት እድል አለ?
አቶ ጉግሳ፡- እንግዲህ አሁን በምትይው መንገድ በወቅቱ ሊዝ ከፍለው መሬት ያልወሰዱ ስለመኖራቸው መረጃው የለኝም፤ ያልወሰዱበትንም ምክንያት አላውቅም። ነገር ግን ከስድስት ዓመት በፊት በማኅበር ተደራጅተው ክፍያ ከፍለው መሬት ያላገኙ ካሉ በዚህ ማሕቀፍ ውስጥ እናስተናግዳቸዋለን። ምንአልባት የሊዙም በዚሁ መንገድ የሚፈታ ይሆናል። እኔ ባለኝ መረጃ ለኢንቨስትመንት ሊዝ ከፍለው ውል ከተዋዋሉ በኋላ መሬት ያላገኙ ኢንቨስተሮች መኖራቸውን ነው። አሁን ላይ እነሱንም እያስተናግድን ነው ያለነው።
አዲስ ዘመን፡- የከተማ አስተዳደሩ ኮዬ ፈጬ ላይ የተሠሩ ቤቶችን ለአንድ አንድ አመራሮች እያስተላለፈ ያለበት መንገድ ምን ያህል ፍትሓዊ ነው ብለው ያምናሉ? በሌላ በኩል በዚያው ክፍለከተማ ከሱማሌ ክልል ለተፈናቀሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሠሩ ቤቶችን ከተሠራበት ዓላማ ውጪ ለሌሎች ግለሰቦች መተላለፉ አግባብነት አለው ብለው ያምናሉ?
አቶ ጉግሳ፡– በመጀመሪያ ደረጃ የመረጃ ስህተት ያለ ይመስለኛል፤ አንደኛ ሸገር ከተመሰረተ ጀምሮ ቤት እየሰጠን ያለነው ለድሃ ነው። ለምሳሌ ፉሪ ክፍለ ከተማ ላይ 12 ቤቶችን አነስተኛ ደሞዝተኛ የሆኑ የመንግሥት ሰራተኞች እጣ አውጥተን ነው የሰጠነው። ለኃላፊዎችም ወይም ለነጋዴ አልሰጠንም። በተጨማሪም በማኅበረሰቡ ተሳትፎ አምና ብቻ 500 የሚሆኑ በዝቅተኛ ወጪ ቤት አሰርተን በየክፍለ ከተማው አነስተኛ ገቢ ላላቸው፤ ለአካል ጉዳተኞች፤ ከውትድርና ለተመለሱ ሰዎች ነው የተሰጠው። በመሰረታዊነት በዚያ በኩል ችግር አለ ብዬ አላስብም። አቅርቦቱ እጥረት አለበት የሚለውን ግን እቀበላለሁ።
ከዚህ ባሻገር የኮዬ የጋራ መኖሪያ ቤትን በሚመለከት እንደተነሳው ቤቶችን ያሰራው የአዲስ አበባ አስተዳደር ነው። አሁን ላይ ቤቶቹ በባንክ እዳ ነው ተይዘው ያሉት። ባዶ ቤቶች ላይ ሰው እየሰበረ የሚገባበትና የፀጥታ ችግር የሚሆንበት ሁኔታዎች አሉ። በመሆኑም አስተዳደሩ የቤቶቹ ሁኔታ ውሳኔ እስከሚያገኝ ድረስ ባዶ ከሚቀመጥ ሰው በኪራይ ቢገባበት የሚል ሃሳብ ለክልሉ ካቢኔ ቀርቦ ውሳኔ ተላልፎበት አነስተኛ ደመወዝ ያለው የመንግሥት ሰራተኛ በአነስተኛ ኪራይ ቤት እንዲወስድ ነው የተደረገው። ይህ መደረጉ እነሱን ከመጥቀም በዘለለ ቤቱም እንዲጠበቅ ያደርጋል።
በኪራይ ከገቡበት መካከል ደግሞ መምህራኖችም ይገኙበታል። ስለዚህ እዚያ ውስጥ የሚታዩ አድሎዎች የሉም። የአሠራር ክፍተቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ሰውን ለመጥቀም ሆነ ለመጉዳት ሕግና ደንብ አውጥተን የተሠሩ ነገሮች የሉም። በነገራችን ላይ በኮታ ነው የሰጠናቸው፤ ለሕክምና ባለሙያ፤ ለመምህራን፤ ለፖሊስና ለመከላከያ አባላት፤ ለወረዳ ሰራተኞችም ሆነ ሌላው የመንግሥት ሰራተኛ የተሰጠው በኮታቸው ሆኖ ለሁሉም ማዳረስ ስለማይቻል በእጣ ነው የተላለፈላቸው። በእጣ ያጡ ሰዎች ደግሞ በቀጣይ ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ የሚታሰብበት ሁኔታ ነው ያለው።
በሌላ በኩል እንዳነሳሽው አዲስ አበባ አስተዳደር ከሱማሌ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች ኮዬ ፈጬ ላይ የሰራቸው ቤቶችን በሚመለከት ያለኝ መረጃ በመጀመሪያ ርክክብ ሳይደረግ የማይመለከታቸው አካላት ቤቱን ገብተውበታል። ተፈናቃይ ያልሆኑ ግለሰቦቹ ቤት የወሰዱበት ሁኔታ አለ። በተጨማሪም ወንጀል የሚፈፀምባቸው ሁኔታዎች አሉ። አሁን ላይ ከ100 በላይ የሚሆኑ ቤቶች በፍርድ ቤት ክርክር እየተደረገባቸው ነው። ውስጡ የነበሩ ሰዎች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወጥተው በፖሊስ ቤቶቹ እንዲታሸጉ ተደርጓል። በጥቅሉ እነዚህን ቤቶች በሚመለከት በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ በመሆኑ ዝርዝር ነገር ማንሳት አልችልም። ነገር ግን ቤቱ የተሠራው ለተፈናቃዮች ሆኖ ስለ መምህራንም ሆነ ለሌላ አካል መስጠት ተገቢ አይመስለኝም።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ አስተዳደር ያሠራቸውና አሁን ሕጋዊ ባለቤት የሌላቸው እነዚህ የኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ፈንታ ምንድን ነው የሚሆነው?
አቶ ጉግሳ፡- እንደሚታወቀው ቤቶቹን ያሠራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው፤ ያን ጊዜ ደግሞ የድንበር ውዝግቦች ነበሩ። በወቅቱ የነበረው የልዩ ዞንና የከተማ አስተዳደሩ ውዝግቡን እንዲፈታ ተደርጓል። ቤቶቹን በኪራይ ያስተላለፍነው ከባንክ ጋር የተያያዘ ችግር በመኖሩ ነው። ይህ ችግር እስኪፈታ በኪራይ ይቀመጡና ችግሩ ሲፈታ ደግሞ ምንአልባት በከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ ቤት ውስጥ በኪራይ እየኖረ ያለው ሰው እዳውን ከፍሎ የቤቱ ባለቤት ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። አልያም ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ በራሱ ከፍሎ በኪራይ ለነዋሪዎች የሚያስተላለፍበት ሁኔታ ይፈጠራል።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ለመምህራን የቤት ባለቤት እንዲሆኑ የተዘረጋ ሥርዓት ቢኖርም ሸገር ላይ ይህ ተግባራዊ ያልሆነበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ጉግሳ፡- በመሰረቱ ቤት ለመምህራን ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ሁሉ መሰረታዊ ፍላጎት ነው። መምህራን ቤት ማግኘት የለባቸውም፤ መሬት አናቀርብም አላልንም። አስቀድሜ እንዳነሳሁት መረጃ የማደራጀት ሥራ አስቀድሞ ለመሥራት፣ አማራጮችን ለማመቻቸት ነው ጥረት ሲደረግ የቆየው። በነገራችን ላይ አሁን ላይ በሸገር ከተማ ባዶ የተቀመጠ መሬት የለም፤ ለመምህራንም ሆነ ለሌላ አካል መሬት እንስጥ ብለን ስንነሳ አርሶአደሩንም ሊጎዳ እንደሚችል ታሳቢ ማድረግ ይገባል።
በአንድ በኩል ብቻ ማየት የለብንም። ለእኔ ቤት ለመስጠት ሌላውን ማፈናቀል ፍትሓዊ አይሆንም። እኛ የቤት ችግር እንዳለ እናውቃለን፤ ለዚህም ነው አስተዳደሩ በቂ ነው ባይባልም በካቢኔ ወስኖ ለመምህራን የቤት ኪራይ እየከፈለ ያለው። በጥቅሉ ጉዳዩ አይመለከተንም አላንም፤ ደግሞም ዝም ተብሎ የታለፈ ነገር አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ሸገር ከተማ ትላልቅና ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሚሠሩበት እንደመሆኑ በዚህ ልማት ውስጥ የሚነሱ አርሶአደሮችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ሥራ ለመሥራት ምን ታስቧል?
አቶ ጉግሳ፡- ከአርሶአአደሩ ጋር ተያይዞ ሸገር እንዲቋቋም ትልቅ መሰረት ያደረገው የአርሶአደሩ ጉዳይ ነው። በሸገርና አዲስ አበባ ላይ ብቻ ሳይሆኑ በሌሎችም አካባቢዎች ከተማ በተስፋፋ ቁጥር አርሶአደሩ ወደ ኋላ ይገፋል። አርሶአደሩን ታሳቢ ያላደረገ ከተማ ልማት ቀጣይነት አይኖረውም። ለግጭቶች መንስኤ ሊሆን ይችላል። አዲስ አበባ ላይም ይቀርብ የነበረውም ቅሬታ ከተማው ሲያድግ እና ሲስፋፋ አርሶአደሩን አላቀፈም የሚል ነው። ስለዚህ ይህንን ላለመድገም ነው ጥረት የተደረገው። ለምሳሌ በሸገር ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ አርሶአደሩን ልዩ ተጠቃሚ ያደርጋል። ይህም አርሶአደሩ ፈቃደኛ እስካልሆነ ድረስ በልማት ምክንያት እንዳማይነሳ በሕግ ተደንግጓል።
ለምሳሌ ፋብሪካ በሚገነባበት ቦታ ላይ አርሶአደሩ መሬቱን ትቶ የሚሄድበት ሳይሆን ማካካሻ ፤ የአክሲዮን ድርሻ አግኝተው የድርጅቱ ባለቤት መሆን እንዳለባቸው ሕጉ ላይ ያስቀምጣል። የቤት መሥሪያ ቦታዎች ላይም አርሶአደሩ ቤት ሰርቶ ማከራየት ማስተዳደር እንዲችል ሕጉ ያስቀምጥለታል። በተቻለ መጠን መገፋፋቱ እንዳይኖር የሕግ ማሕቀፍ ተዘጋጅቶለታል። ነገር ግን የአርሶአደሩ አሰፋፈር የተራራቀ በመሆኑ መሰረተ ልማት ለማቅረብ አስቸጋሪ ይሆናል፤ በተጨማሪም ከተማ ላይ የከተማ መሬትን በአግባቡ ለመጠቀም ያዳግታል። ስለዚህ ማስተር ፕላናችን ላይ እንደተቀመጠው በየቦታው የአርሶአደር መንደሮች አሉ፤ እነሱን ባገለለ መልኩ ሳይሆን ባሕላዊ ይዘቱን እንደጠበቀ የተለየ ደረጃ ተሰጥቶት በሁሉም ክፍለከተማ ላይ እንዲኖሩ ይደረጋል። ለምሳሌ ኮዬ ላይ ወደ አራትና አምስት ቦታዎች ላይ ለመሥራት ታቅዷል።
በነገራችን ላይ ልዩ ተጠቃሚ እንዲሆን በሕግ ደረጃ እንዲደነገግ ያደረግነው ከሌላው ማኅበረሰብ ለማግለል ሳይሆን አርሶአደሩ የራሱ የአኗኗር ዘይቤ ስላለው፤ ማኅበራዊ ትስስሩንም ጭምር ጠብቆ እንዲሄድ ለማድረግ ነው።
በተጨማሪም እንደዚህ አይነት መንደሮች እየተስፋፉ ሲሄዱ የቱሪዝም ምንጭ ሊሆኑ ሲለሚችልም ይህም ተጨማሪ ገቢ የመፍጠሪያ ሁኔታ ነው የሚኖረው። በሌላ በኩል ነባር የአርሶአደር ይዞታዎች ውጭ በሕገወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶች አሉ፤ ሕገወጥ ቢሆንም በአዋጅ እንዲፀድቅላቸው መንግሥት ከ2005 ጥር ወር በፊት የተሠሩ ቤቶች ወደ ሕጋዊነት እንዲመጣ ደንግጓል። እስከአሁን ሕጋዊ የማድረጉ ሥራ አልተጀመረም፤ ወደፊት ግን በሕግ አግባብ የሚስተናገዱበት ሁኔታ ይኖራል።
አዲስ ዘመን፡- ከጣራና ግድግዳ ክፍያ ከአዲስ አበባ ከተማም ሆነ ከሌሎች ዋና ከተሞች በተለየ ሸገር ላይ ከፍ እንዲል በመደረጉ በርካታ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ቅሬታ ያሰማሉ፤ በሌላ በኩል ከግብሩ ጎን ለጎን በመንግሥት ራሱ በሚሰበስበው ግብር ሊሠራቸው የሚገባቸውን የልማት ሥራዎችና ክፍያዎችን በሌላ ደረሰኝ ተጨማሪ ሕብረተሰቡ እንዲከፍል ይደረጋል፤ ለምሳሌ የሚሊሻና የቦሳ ጎኖፋ እንዲከፍል መደረጉ ምን ያህል አግባብነት አለው?
አቶ ጉግሳ፡– በሸገር ከተማ የጣራና ግድግዳ ግብር ከሌላው አካባቢ የበዛ ነው የሚል ግምገማ የለንም። የክልሉ መንግሥት ተመኑን ያስቀመጠው የተለያዩ ክልሎችን ተሞክሮ በመቀመርና ጥናት በማጥናት ነው። በምክር ቤት ፀድቆ የወጣ ተመን ነው። ምንአልባት ሰው ከዚህ ቀደም ከሚከፍለው አንፃር በዝቷል ሊል ይችላል። ሆኖም እውነታው እንደዛ አይደለም ፡፡
ቅሬታው በተደጋጋሚ ይነሳ ስለነበርም የምክር ቤት አባላትም መላልሰው ተወያይተውበታል። በጥቅሉ ከሌሎች አንፃር ስናየው የእኛ የበለጠ ሆኖ አላገኘነውም። ከነዋሪው ገቢ አንፃርም ተመጣጣኝ እንደሆነ ገምግመናል። ግን ደግሞ የግብር አከፋፈል ልምዳችን ጥሩ የሚባል አይደለም፤ ግብርን እንደግዴታ ሳይሆን እንደ እዳ ነው የምናየው።
ዞሮ ዞሮ የሚሰበሰበው ገቢ መልሶ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚውል መሆኑም ግልፅ ነው። ለምሳሌ ትልቁ የቀለበት መንገድ የሚሠራው የከተማ አስተደደሩ ከሚሰበስበው ግብር ነው። እሱ ብቻ አይደለም ዘንድሮ ብቻ ወደ 16 ቢሊዮን የካፒታል በጀት መድበን ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት። የልማት ፍላጎታችን ትልቅ ስለሆነ ያንን ለማሟላት ግብር መሰብሰብ አለብን ።
በሌላ በኩል ማኅበረሰቡ የልማት ሥራዎች ላይ ካልተሳተፈ ካሉብን እዳዎች አንፃር የምንፈልገውን እድገት ማምጣት አንችልም። በመንግሥት በጀት ብቻ የሕዝብን ፍላጎት ማሟላት አይቻልም። ስለዚህ ማኅበረሰቡ በአቅሙ መሳተፍ አለበት። ሆኖም የተከፈለው ክፍያ ምን ላይ እንደዋለ ግልፅ ማድረግ ይገባል። ይህንንም ሕዝቡ እንዲቆጣጠር ማድረግ ይገባል።
በነገራችን ላይ ዘንድሮ ብቻ በከተማ አስተዳደራችን አምስት ሺ ሼዶችን ሰርተናል፤ እነዚህም ዶሮ፣ ላም የሚረባበት፣ ከብቶች የሚደልቡበት ከ300 ሺ በላይ ለሚሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሥራ እድል ፈጥረናል። ስለዚህ ይህንን ማከናወንና የሥራ እድል መፍጠር የቻልነው ማኅበረሰቡ ከኪሲ ባወጣው ገንዘብ ነው። መንግሥት በራሱ በጀት ብቻ ይሥራ ቢባል ኖሮ ይህንን ማድረግ አንችልም ነበር። ስለዚህ በማኅበረሰብ አስተዋፅኦ የሚሰሩ በርካታ ሥራዎች አሉ። መንገድ ልማት አንፃር ኮብልስቶን 24 ኪሎ ሜትር በማኅበረሰቡ አስተዋፅኦ ነው የተሠራው። ስድስት ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ በሁለት ክፍለ ከተማ ላይ የአካባቢው ማኅበረሰብ አዋጥቶ ሰርቷል።
ስለዚህ ይህ መደረጉ እንደጉድለት አላየውም፤ ነገር ግን ማኅበረሰቡ የሚያወጣው ገንዘብ አንደኛ አሰባሰቡ ላይ ግልፀኝነት መፈጠር አለበት። የሚሰበሰበው በሕግ ሥልጣን የተሰጠው ሊሆን ይገባል፤ የሚሰበስበት ዓላማና በተጨባጭ ሥራ ላይ ስለመዋሉ ሕብረተሰቡ ሊያውቅ ይገባል። ራሱም ኮሚቴ ሆኖ ውስጡ መሳተፍ መቻል አለበት። ብክነቶችን መቀነስ መቻል አለብን፤ እኛም ጋር ጉድለቶች እንዳሉ አይተናል፤ ተጨባጭ ማስረጃ ያገኝንበት ቦታ ላይ ተጠየቂነት የማስፈን ሥራ ይሠራል፡፡
በነገራችን ላይ የቦሳ ጎኖፋ ዋና ዓላማ እኛ ራሳችንን መርዳት የምንችልበትን ሁኔታ መፍጠር እንጂ ሌላ ዓላማ የለውም። ሰው እስከሆንን ድረስ በኑሯችን ውስጥ ደስታም ሆነ ችግር አለ፤ ያ ብቻ ሳይሆን ጎረቤቶቻችንም ሊቸገሩ ይችላሉ። እነዚያን ችግሮች ለማለፍ ሌላ ሀገር ሄደን እርዳታ ከምንጠይቅ ሲኖረን አውጥተን እናስቀምጥ፤ ስንቸገር ከዚያ እያወጣን የሚቸገረውን አካል የመርዳት ዓላማ ነው ያለው። በመሰረቱ ቦሳ ጎኖፋ ከአባላት የሚሰባሰብ መዋጮ ነው። ለመክፈል በመጀመሪያ አባል መሆን አለበት ዓላማውን ማወቅ አለበት፤ ክፍያውም በዓመት አንዴ ነው መከፈል ያለበት። ማኅበረሰቡም ሲከፍል መክፈል ብቻ ሳይሆን ደረሰኝ መጠየቅ መቻል አለበት።
ከሚሊሻ ጋር ተያይዞ ያነሳሽው ነገር በመሰረታዊነት ፀጥታችንን ለማስከበር ፤ የአካባቢው ማረጋጋት ላይ የሚሊሻ አባላት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። በነገራችን ላይ ደመወዝ ሳይከፈላቸው ነው ቀን ከሌሊት የሚሰሩት። አምነውበት ሕብረተሰቡን ለማገልገል ነው የሚሠሩት፤ ሆኖም ጥሩ የሚሠራ እንዳለ ሆኖ አንዳንድ ዋልጌም አይጠፋም። ደግሞም የጥሩዎቹን ስም የሚያጠፋ አይኖርም ማለት አይደለም፤ ከሕብረተሰቡ በምናገኘው መረጃ አንዳንድ እርምጃዎች ወስደናል። አሁን ላይ በአብዛኛው ተስተካክሏል። ያነሳሽው ነገር ትክክል ነው፤ ኮዬ ላይም እንዲህ አይነት ነገር ተፈጥሮ እርምጃ ተወስዷል። የሚስተዋሉ የሥነ-ምግባር ችግሮችና የሙስና ተግባራትን እየቀረፍን መሄድ ይጠበቅብናል። ለዚህ መሳካት ደግሞ የሕዝቡ ድጋፍ ያሻናል።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ በከተማዋ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ አካላት የሚያቀርቡት ጥሪ ካለ እድሉን ልስጥዎትና ውይይታችንን እናብቃ?
አቶ ጉግሳ፡- የሸገር ከተማ አስተዳደር አንደኛ ከሚገኝበት አካባቢ አንፃር በመጀመሪያ ደረጃ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ አቅራቢያ የሚገኝ ነው፤ ትላልቅ መሰረተ ልማቶችም በውስጡ የሚያልፉ ናቸው። ለምሳሌ ወደ ጎረቤት ሀገራት ጋር የምናካሄደው የንግድ መስመር፤ የባቡር መስመር፤ ሌሎችም መንገዶች ከተማዋን አልፈው የሚሄዱ ናቸው። በሌላ በኩል ሰፊ የሕብረተሰብ ክፍል ያለበት እንደመሆኑ ትልቅ የገበያ እድል ያለበት ነው። ሶስተኛ ምቹ የአየር ሁኔታ ነው ያለው። በተጨማሪም ሰፊና ለልማት ምቹ የሆነ መሬት ያለበት አካባቢ ነው።
በመሆኑም በከተማችን በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ መሰማራት የሚፈልግ ማንኛውም ባለሃብት ወደ ከተማችን እንዲመጣ ጥሪ እናቀርባለን። አሠራሮችን በማዘመንና በማሻሻል፤ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር እነሱን የምናስተናገድ መሆኑንም ለመግለፅ እወዳለሁ። ራሱንም ጠቅሞ ሌላውን መለወጥ ይችላል። በተለይ በማኑፋክቸሪንግና ንግድ ሥራዎች ላይ ቢሠማሩ የበለጠ ተጠቃሚ ስለሚሆኑ ወደ ከተማችን እንዲመጡ እጋብዛቸዋለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ጊዜ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ጉግሳ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
በማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም