የሰው ወርቅ አያደምቅ

በአብዛኛው በከተማ አከባቢ የሚኖሩ፣ የራሳቸውን ቤተሰብ የመሰረቱ ባለትዳሮች ኑሯቸውን ለማሸነፍ ፣ ለልጆቻቸው የተሻለ ሕይወትን ለመስጠት ሲሉ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራሉ። ታዲያ እናት እና አባት ሥራ፤ ልጆች ደግሞ ትምህርት ቤት ውለው የሚገናኙት ማታ ወደ ቤት በሚገቡበት ሰዓት ነው።

በጊዜ ሒደት እየተቀየረ በመጣው ባሕላችን እናቶች ቤት ውስጥ ከሚኖራቸው ኃላፊነት ባለፈ ወጥተው ባላቸው አቅም እና እውቀት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ይሠማራሉ። አንዳንድ እናቶች የልጆች እናት ከሆኑ በኋላ ልጆቻቸውን በቤት ውስጥ ለማሳደግ ወስነው ሥራቸውን ሙለ ሙሉ አቁመው በቤት ውስጥ ይቀመጣሉ። ምክንያቱም ልጅን በሚፈለገው እና ትክክለኛ በሆነው መንገድ ቀርጾ ለማሳደግ የሕጻናት እስከ አምስት ዓመት ያለው እድሜ ትልቁን ሚና ይጫወታል።

ነገር ግን ሥራን ሙሉ በሙሉ ትቶ ልጅን በቤት ውስጥ ለማሳደግ መወሰን ሁሉም ሰው ሊያደርገው የማይችል እና ባለትዳሮች ያላቸው የገቢ ዝግጁነት ላይ እርግጠኛ መሆንን ይጠይቃል።

ታዲያ በውጭ ሥራቸውን የሚሠሩ ሴቶች ደግሞም በቤታቸው የልጆች እናት የሆኑ እንስቶች ምንም እንኳን ልጆቻቸውን ቤት ትተው መሄድ እረፍት የማይሰጣቸው ጉዳይ ቢሆንም ሥራ እና ሕይወት ነውና በአስተማማኝ እጅ ላይ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ይፈልጋሉ። የታደሉ ወላጆች በቅርባቸው የሚያግዟቸው የቤተሰብ አባላት ሲኖሩ ልጆቻቸውን እነርሱ ጋር ጥለው ይሄዳሉ። ሌሎች ደግሞ ዘመኑ በፈጠረው የሥራ ሀሳብ የሕጻናት ማቆያዎች ላይ በማድረግ ልጆቻቸው ትምህርትቤት እስከሚገቡ ድረስ በዚያ እንዲቆዩ ያደርጋሉ።

ነገር ግን ይህም ካልሆነ ባለትዳሮች እንደ አንድ የቤተሰባቸው አካል በማድረግ የቤት ሠራተኛ አልያም አጋዥ በመቅጠር ልጆቻቸው እቤታቸውን ትተው ይሄዳሉ። የቤት ውስጥ አጋዥ የሚኖራት የሥራ ኃላፊነት እንደምትሠራበት ቤት፣ የቤተሰብ አባላት ቁጥር የሚወሰን ሲሆን አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ብቻ የምትይዝላቸው አጋዥም ይቀጥራሉ።

ታዲያ ሰዎች በብዙ መንገድ ጉርብትናን ወዳጅነትና ቤተሰባዊነትን የሚፈጥሩ ሲሆን የቤት ውስጥ አጋዥም በምትሠራበት ቤት ውስጥ ከምትከተላቸው ሕጎች ባሻገር የቤተሰቡ አንድ አካል ትሆናለች። መልካም ጸባይ እና ሥነ-ምግባር ያላቸው ከሰዎች ጋር በቀላሉ ተግባብተው እና ተዋደው መኖር የሚችሉ ሲሆኑ ለቤተሰቡ እረፍት የሚሰጡም ናቸው።

እነዚህ የቤት ውስጥ አጋዦች ሥራቸውን ሲለቁ ወላጆች በእጅጉ ይቸገራሉ። በተለይ ደግሞ ከልጆቻቸው ጋር ጥሩ ቅርርብ የነበራቸው ከሆኑ እንደገና በሌላ ሰው መተካት ከባድ ይሆናል። የቤት ሰራተኛ አልያም አጋዥ ማግኘት አንዳንዶች በሰው በሰው በሚያውቋቸው ሰዎች አማካኝነት የሚያደርጉት ሲሆን በቀጥታ በድለላ አማካኝነትም ሰራተኞችን የሚቀጥሩ ብዙዎች ናቸው። ይህ ሲሆን ደግሞ የሥራ ውል፣ ማስረጃ እንዲሁም አጋዧን የሚያውቅ ተያዥ በማድረግ ሰዎች ለቤታቸው አጋዥን ይቀጥራሉ።

ብዙ የተመሰገኑ አጋዦች፣ ለሚሠሩበት ቤት ቤተሰብ የሚሆኑ አሠሪዎችም እንዲሁ የሚገባቸውን ክብር ሰጥተው እንደ እህት፣ እንደ አንዱ የቤተሰብ አካል የሚያዩ እንዳሉ ሁሉ ሠራተኞችን ደሞዝ የሚከለክሉ፣ ጥቃት የሚያደርሱ አሉ። እንዲሁም በአንጻሩ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ያለመወጣት ይኖራል። የዛሬው የዶሴ ገጻችን ያልተገባ ጥቅምን ለማግኘት በመፈለግ እና አጋዥ በመምሰል ሰዎች ቤት ውስጥ በመግባት የተፈጸመ ምዝበራ ሲሆን፤ ፖሊስ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ውሳኔ እንዲሰጥበት አድርጓል።

ወጣቷ ቤዛዊት በቀለ በአዲስ አበባ ከተማ መኖር ከጀመረችበት ግዜ አንስቶ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ በመሰማራት የሠራች ሲሆን በቤት ውስጥ አጋዥነት ረጅም ዓመታትን አገልግላለች። ነገር ግን ይህ ነው የሚባል አድራሻ አልያም በገባችባቸው ቤቶች ውስጥ ቢበዛ ስድስት ወር በላይ ሰርታ እንኳን አታውቅም። በምትሠራባቸው ቤቶች ውስጥ ለመግባት በእርሷ እና በሚቀጥራት አካል መካከል የሥራ ቅጥር ውል ቢኖርም ነገር ግን የምትጠቀመው ስምም ሆነ አድራሻ ግን የተለያየ ነው።

ማንነት ሲገለጥ

አቶ ዳንኤል እንዲሁም ባለቤታቸው ሁለተኛ ልጃቸውን ከወለዱ በኋላ ባለቤታቸው አራስነት ጊዜዋን አጠናቃ ወደ ሥራ ለመመለስ በምታስብበት ወቅት ተጨማሪ አጋዥ ቤቷ በመቅጠር ወደ ሥራዋ ትመለሳለች። ታዲያ የሥራ ቦታዎ እና የመኖርያ ስፍራዋ ያን ያህል ሩቅ የማይባል በመሆኑ በቀን ውስጥ የተወሰነ ሰዓቷን ወደ ቤት ተመልሳ ልጇን የማየት እድል ነበራት።

ታዲያ ይህች አጋዣቸው ወደቤተሰቦቿ ቤት ለበዓል እረፍት ብላ ከሄደች በኋላ ተመልሳ ባለመምጣቷ ወይዘሮ ዓለም የተወሰኑ ቀናትን በቤት ውስጥ ለማሳለፍ ተገዳለች። በምትሠራበት አካባቢ ልጇን በቅርበት ልትከታተልበት የምትችለው ማቆያም ሆነ ለሕጻናት የሚሆን ምቹ ስፍራ ባለመኖሩ ሌላ የቤት ውስጥ አጋዥ መቅጠር ነበረባቸው፡፡

ለዚህም የሚየውቁትን ደላላ በመጠየቅ ቤዛዊትን ወደ ቤታቸው ያስገቧታል። ቤዛዊት ከዚህ ቀደም በተለያዩ የድለላ ሥራዎች ልምድ እንዳላት በደረሳት መረጃ መሰረት በቤቷ ውስጥ የሚሠራውን ነገር ከነገረቻት እና ዋናው ሥራዋ ግን 2 ዓመት ሊሞላት ጥቂት ጊዜ የቀራትን ልጅ መንከባከብ እንደሆነ በማስረዳት ከቀናት እረፍት በኋላ ወደሥራዋ ተመለሰች።

ቤዘዊትም የተሰጣትን ሥራ በአግባቡ መረዳቷን በማረጋገጥ ለቀናት ይህንን ስትተገብር ቆይታለች። ወይዘሮ ዓለምም በቀን ውስጥ በሚኖራት ትርፍ ሰዓት በተቻላት መጠን ወደቤት በመሄድ ልጇን የምታይ ሲሆን አልፎ አልፎም እንዲሁ ወደቤት ሳትሄድበት የምታሳልፍበት ጊዜ ይኖራል።

ታዲያ በአንዱ ቀን ወይዘሮ ዓለምም ሆኑ ባለቤታቸው አቶ ዳንኤል ወደ ሥራ ከሄዱ ከአንድ ሰዓት በኋላ አንድ በቤታቸው ያለን ሰነድ ለመውሰድ አቶ ዳንኤል ተመልሰው ወደ ቤት ይመጣሉ። ነገር ግን በቤት ውስጥ ያልጠበቁት ነገር ይከሰታል። የሁለት ዓመት ልጃቸውም ሆነ በቅርቡ የቀጠሯት አጋዣቸው በቤት ውስጥ የሉም። በጉዳዩ ግራ የተጋቡት አባት ለባለቤታቸው ደውለው ለማጣራት ቢሞክሩም ነገሩ ግን ለባለቤታቸውም አስደንጋጭ ነበር። ወይዘሮ ዓለም ወደቤት ተመልሰው በአካባቢው ለማፈላለግ ቢሞክሩም የሰላም መሆኑ የቸገራቸው ወላጆች መፍትሄ ለማግኘት በአቅራቢቸው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በማምራት አቤት ይላሉ።

ቀስ በቀስ

ፖሊስ መረጃው ከደረሰው ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩን ለማጣራት እና ወንጀለኛውን ለመፈለግ የራሱን ተከታታይ ማጣራት ያደረገ ሲሆን፤ ተከሳሽን ለጊዜው ካልተያዘው አባሪዋ ጋር በመሆን ለአካለ መጠን ያልደረሰችን ልጅ በመጥለፍ ገንዘብ ለመቀበል በማሰብ መጋቢት ሰባት 2015 ዓ.ም በግምት ከቀኑ አምስት ሰዓት ከ30 ላይ በን/ስ/ ላ/ክ/ከ ወረዳ 09 ልዩ ቦታው ሳሪስ አዲስ ሰፈር ኤልቤቴል በሚባል አካባቢ ከአባራዊ ጋር በሰራተኝነት በመቀጠርና ልጅ በመስረቅ ገንዘብ ለመጠየቅ ተስማምተው በአቶ ዳንኤል ሙሉ መኖርያ ጠልፋ ወስዳለች። ፖሊስ ባደረገው ክትትል ከአምስት ተከታታይ ቀናት ፍለጋ በኋላ መጋቢት 12 2015 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ሱሉልታ ከተማ ሕጻኗን እንደያዘች እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር የዋለች በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸመችው ወጆ ለመቀበል ለአካለ መጠን ያልደረሰች ልጅን በመጥለፍ ወንጀል ተከሳለች።

ነገር ግን በተከሳሽ ቤዛዊት በቀለ ላይ ባደረገው ተከታታይ ማጣራት ተከሳሿ በፈጸመችው የሕጻን ልጅ የመጥለፍ ወንጀል በቁጥጥር ስር ከመዋሏ በፊት በተለያዩ ቤቶች ውስጥ በቤት ሰራተኝነት በመግባት በከባድ የውንብድና ወንጀል ተደጋጋሚ ክስ የቀረባባት እና የተለያዩ ስሞችን እንዲሁ እንደምትጠቀም ደረሰበት። በዚህም አቃቤ ሕግ የሕጻን ልጅ መጥለፍ ወንጀልን ጨምሮ በሌሎች ሰባት ክሶች ሊያቀርብባት ችሏል።

2ተኛ ክስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 669(2) መ ላይ የተመለከተውን ተከሳሽ የማይገባትን ብልጽግና ለማግኘት በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ በምትሠራበት ቤት ን/ስ/ላ/ክ/ከ ወረዳ 09 ልዩ ቦታው ሳሪስ አዲስ ሰፈር ኤልቤቴል ግምቱ 14 ሺህ ብር የሚሆን ሳምሰንግ ኤ6 ሞባይል፣ ሳምሰንግ አልፋ ሞባይል ግምት አራት ሺህ 800 ብር፣ ሶስት የአንገት መስቀል ነጭ ወርቅ ማጫወቻ ሁለት ግራም 10ሺህ ብር፣ ሶስት ብረት ድስት የዋጋ ግምቱ አንድ ሺህ 500 ብር በጠቅላላው 32 ሺህ 100 ብር የሚያወጣ እቃዎን በመስረቅ በፈጸመችው ከባድ ስርቆት ወንጀል ተከሳለች።

3ተኛ ክስ በ28/042015 ዓ.ም በኮ/ቀ/ክ/ከ ወረዳ 07 ልዩ ቦታው አንፎ ድልድይ አከባቢ የግል ተበዳይ ተሾመ ታደሰ መኖርያ ቤት በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ በምትሰራበት ቤት ውስጥ 53ሺህ ብር የሚያወጣ ሌኖቮ ላፕቶፕ፣ ሶስት ኪሎ ግራም የተነጠረ ቂቤ አንድ ሺህ 200 ብር፣ የተለያዩ የቤት እቃዎች በአጠቃላይ 55 ሺህ 400 ብር በከባድ የውንብድና ወንጀል ተከሳለች።

4ተኛ ክስ በሁለተኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበ ሲሆን በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 682(1) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ የተሰረቀ 53 ሺህ ብር የሚያወጣ መሆኑን እያወቀ በ16 ሺህ ብር በመግዛት ተከሷል።

በተጨማሪ አንደኛ ተከሳሽ ተቀጥራ በምትሰራባቸው ቤቶች ከባድ የስርቆት ወንጀል በመፈጸም በሌሎች ሶስት ክሶች የቀረቡባት ሲሆን 5ተኛ ክስ ተከሳሽ በ27/05/2015 ዓ.ም ከግል ተበዳይ ሰላማዊት ዳምጠው መኖርያ ቤት በቦሌ ክ/ከ ወረዳ 03 ልዩ ቦታው ጣና አፓርትመንት 35ሺህ ብር የሚያወጣ ላፕቶፕ አይፎን 13 ፕሮማክስ 100ሺህ ብር የሚያወጣ የአንገት ወርቅ 18 ካራት 5 ግራም 25 ሺህ ብር የሚያወጣ እንዲሁም 24 ካራት ዘጠኝ ነጥብ ሶስት ግራም የዋጋ ግምቱ 52 ሺህ ብር በጠቅላላ 212 ሺህ ከአንድ መኖርያ ቤት በመስረቅ በከባድ የውንብድና ወንጀል ተከሳለች።

በ6ተኛ ክስ በ16/03/2015 በን/ስ/ላ.ክ/ከ ወረዳ 15 ልዩ ቦታው 72 ካሬ የማኅበር ቤት አካባቢ የግል ተበዳይ መንበረ ተስፋዬ መኖርያ ቤት በሰራተኝነት በምትሠራበት ቤት ወቅት የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያ እቃዎች በድምሩ 162 ሺህ ብር፣ በሰባተኛ ክስ በተከሰሰሰችበት ወንጀል በተመሳሳይ 132ሺህ ብር የሚያወጡ የቤት ውስጥ እቃዎች እና በስምንተኛ ክስ በምትሠራበት መኖሪያ ቤት ውስጥ ተቀምጦ የነበረ ጥሬ ብር 262 ሺህ ብር በመስረቅ በከባድ የውንብድና ወንጀሎች ተከሳለች።

ማስረጃዎች

ዓቃቤ ሕግ ተከሳሽን በቁጥጥር ስር ካዋለበት ቀን ጀምሮ በሚደርገው ምርመራ እና ክትትል ተከሳሽ በተለያየ ጊዜ የፈጻመቻቸውን ወንጀሎች የሚያስረዳ ግል ተበዳይ ቃል በመቀበል እንዲሁም ምስክሮች በማቅረብ 30 የተለያዩ የሰው ምስክሮች ያቀረበ ሲሆን ተከሳሽ የሰጠችውን ቃል፣ እና በተለያዩ መኖርያ ቤቶች ውስጥ ተቀጥራ የሠራችበትን ቅጥር ውል በሰነድ ማስረጃነት አያይዞ አቅርቧል።

ዓቃቤ ሕግ አንደኛ ተከሳሽ ተከሳ ፍርድቤት በቀረችበት የውንብድና ወንጀል የሰረቀችውን ገንዘብ እና እቃ በኤግዚቢትነት በመያዝ፣ እንዲሁም በገላጭ ማስረጃው አንደኛ ተከሳሽ ቃል ስትሰጥ የሚያሳይ ሲዲ፣ ልጅ በመጥለፍ ወንጀል በተከሰሰችበት ወቅት በቁጥጥር ስር ስትውል የሚያሳይ ቪዲዮ፣ በከሳሽ እርሷ መሆኗን ለማረጋገጥ ስትመረጥ የሚያሳዩ ሰባት ፎቶግራፎች ፣ በስድስተኛ ክስ ላይ ወንጀሉን ስተፈጽም የሚያሳይ ቪዲዮ አያይዞ በማስረጃነት አቅርቧል።

ውሳኔ

በከሳሽ ፌደራል ዓቃቤ ሕግ እና በተከሳሽ 1ኛ ተከሳሽ ቤዛዊት በቀለ ሀይሌ ቤተልሄም ረታ/ሰላም ግዛቸው እና 2ተኛ ተከሳሽ ኃይለየሱስ ኮርጆ በሹ መካከል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ችሎት በነበረው ክርክር በ 25/10/2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት 1ኛ ተከሳሽ የሆነችው ቤዛዊት በቀለ/ቤተልሄም ረታ ሃይሌ / ሰላም ግዛቸው በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንድትቀጣ ፣ 2ተኛ ተከሳሽ ሀይለየሱስ ኮርጆ በሌለበት ስምንት ወር ቀላል እስራት እንዲቀጣ በኤግዚቢትነት የተያዙ ንብረቶችንም ለግል ተበዳዮች እንዲመለሱ ውሳኔ የተሰጠ በመሆኑ በሌለበት ቅጣት የተወሰነበት 2ተኛ ተከሳሽ በማፈላለግ የእስራት ቅጣቱ እንዲፈጸም እንዲደረግ አዟል።

በሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You