በማህበራዊ ድረገፆች ጥላቻን የሚዘሩ ንግግሮች በመሰራጨታቸው አገር እንዳትረጋጋ እያደረጉ ነው። ጉዳዩ ያሳሰባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ማህበራዊ ድረገፆች የአጠቃቀም ገደብ ይበጅላቸው ይላሉ። ጉዳዩን አጥንቶ መፍትሄ የሚሰጥ አካል እንደሚያስፈልግም ይገልጻሉ።
ዶክተር ደምመላሽ መንግስቱ በጅማ ዩኒቨርስቲ ፐብሊክ ሪሌሽን ኤንድ ኮሙኒኬሽን ኢን ዘካልቸራል ኮሙኒኬሽን ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው። የጥላቻ ንግግሮች መንስኤ የቋንቋና ተግባቦት ተጣጥመው ያለመገኘታቸው ውጤት ነው። በተለይ ቋንቋ ከሚሰጠው ተግባር አኳያ በተለያየ መንገድ መተርጎም መቻሉ የጥላቻ መልክ ይዘው የሚወጡ ንግግሮች እንዲበዙ እያደረጉ ነው። ይህ አካሄድ ደግሞ ለአገር ህልውና እጅግ ከባድ መሆኑን ይናገራሉ።
ማህበረሰቡ ንግግሮቹን የሚፈታው ባለው አቅም ልክ ስለሆነ ግለሰብ የሚፈልገውና የራሱ የሆነውን ስሜት ሲጽፍ ቡድናዊ ይሆናል። በተሳሳተ መንገድ የተረዳቸውን ሀሳቦች ማጋራቶችና መውደዶች ይበዙና ጥላቻ እንዲስፋፋ እድል ይፈጠራል። ከፖለቲካው ትኩሳት የተላቀቁ መገናኛ ብዙሃን ባለመኖራቸው የጥላቻ ንግግሮች በማህበራዊ ድረገጾች የሚራገቡበትን እድል እንደፈጠረ ይናገራሉ።
በባህርዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ጥናት መምህሩ አቶ እምቢአለ በየነ፤ ማህበራዊ ድረገጾች ማህበረሰቡ የቡድንም ሆነ የግል አመለካከቶችን የሚያንጸባርቅባቸው አማራጮቹ ናቸው። አሁን ባለው ሁኔታ በቡድን የሚዘሩ የጥላቻ ንግግሮች በርካታ የመሆናቸውም ምስጢርም ይኸው ነው ይላሉ። በተለይ የብሔር ጥላቻን የፈጠሩ ማህበራዊ ድረገፆች ያለገደብ በነጻነት ስለሚሰራባቸው እንደሆነም ያብራራሉ።
ማህበራዊ ድረገፆች አገር እንዳትረጋጋ፣ ሰዎች እንዲፈናቀሉና እርስ በእርስ እንዲገዳደሉ ብሎም ብሔር በብሔር ላይ እንዲዘምትና የመግባባት እድሎች እንዲጠቡ ያደረጉት ዋናው ምክንያት በአግባቡ የመጠቀም ልምድ አናሳ በመሆኑ ነው። በተጨማሪም የማህበራዊ ድረገፆች የአጠቃቀም ህግ አለመኖሩና ብዙ ሰው በሚታወቅበት ስሙና ፎቶው ባለመጠቀሙ የጥላቻ ንግግሮች እንዲበራከት በር ከፍቷል። ተጠቃሚዎች ተጠያቂነት ባለው መልኩ ማህበራዊ ድረገፆችን እንዲገለገሉበት ባለመደረጉ ችግሩን እንዳገዘፈው ያስረዳሉ።
‹‹የጥላቻ ንግግር ከዚህ በተለየ መልኩ መታየት አለበት» ይላሉ። ባልሆነ ወይም ባልተሰራ ነገር ላይ መናገር፣ በቡድን የሚከፋፈሉና ብሔር ተኮር የሆኑ ንግግሮችን መጻፍና መለጠፍ የጥላቻ ንግግሮች መገለጫ ናቸውና ጥላቻን ከትክክለኛው ንግግር ለመለየት ማስቸገሩ በአገር ላይ ትልቅ አደጋ እየጣለ የመጣ ጉዳይ መሆኑንም ያነሳሉ።
እንደ አቶ እምቢአለ ማብራሪያ፤ በህጋዊ መንገድ ተቋቁመው የሚሰሩት መገናኛ ብዙኃን ከማህበራዊው ሚዲያ ቀድመው መረጃዎችን ማስተላለፍ አለመቻላቸው ለጥላቻ ንግግሮች መስፋት ምክንያት ሆነዋል። መደበኛው የመገናኛ ብዙሃን የማህበራዊ ድረገጾች ሲያራግቡት የቆዩትን መረጃ እንደ አዲስ ደግመው ይሰሩታል። ይህ ደግሞ ተአማኒነትን ያሳጣል። በዚህም ታማኝ ምንጮች ማህበራዊ ድረገጾች ይሆኑና የተሳሳቱና ጥላቻን የሚዘሩ ንግግሮች እንዲስፋፉና ተመራጭ እንዲሆኑ ምክንያት ይሆናል።
በኮተቤ ሜትሮፖሊታል ዩኒቨርሲቲ የህግ አገልግሎት ዳይሬክተርና የፕሬዚዳንቱ ልዩ አማካሪ ዶክተር ተስፋዬ ባዬ በበኩላቸው፤ በማህበራዊ ድረገጾች የሚለቀቁ የጥላቻ ንግግሮች ምንጫቸው የተጠና ባይሆንም በተማረው ኃይል ላይ በስፋት እንደሚስተዋሉ ታዝበዋል። ይህ ደግሞ ወደ አልተማረው የህብረተሰብ ክፍል ይተላለፍና የተሳሳተ አመለካከትን እያራገበ የብሄር ግጭትን ያስፋፋዋል። የመረጃ ምንጮቻቸው ታማኝ እንደሆኑ በማሰብም የአገሪቱን ህዝቦች የመግባባትና የመስማማት እድላቸውን ያጠበዋል ይላሉ።
«የፍራቻ፣ የጥላቻና መሰል ጉዳዮች ግፊት የጥላቻ ንግግር መገለጫ ናቸው» የሚሉት ዶክተር ተስፋዬ፤ ፖለቲካው በወለደው ችግር ምክንያት በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መስማማት እንዳትችል እያደረጋት ነው። እውነትና ውሸቱን በሚገባ ለይቶ መገንዘብ የሚችል ማህበረሰብ ገና አልተገነባም። በመሆኑም ትንሽ እውነታ ይዞ ግነት የታከለበት ውሸትም እያናወጣት ነው።
እንደ ዶክተር ተስፋዬ ገለጻ፤ አሁን በማህበራዊ ድረገፆች ላይ የጥላቻ ንግግሮች ውድድር ውስጥ ገብተዋል። ማሸነፍና መሸነፍ የማይታይበት ነውና ማህበረሰቡ የማይወጣው ችግር ውስጥ እየገባ እንዲሄድ አድርጎታል። ሌላ አገር ላይ የተከሰተን ጉዳይ ሳይቀር በፎቶ እያቀናበሩ ማቅረብ ተጀምሯል። ይህ ደግሞ አገር በሰብአዊነት ጭምር እንድትፈተንና የበለጠ ግጭት ውስጥ እንድትገባ እያደረጋት ይገኛል።
በተለይ በዩኒቨርስቲዎች ደረጃ የጥላቻ ንግግሮች ገነው ስለሚወጡ አንድ ዩኒቨርስቲ ምንም ችግር ሳይፈጠር ሌላው ጋር «የእገሌ ብሔር ተወላጅ ተገደለ» በሚል እርስ በእርስ እንዲጋጩ እየተደረገ ነው። ይህ አካሄድ አገሪቱ ውስጥ ተማሪዎች ተረጋግተው መማር እንዳይችሉ አድርጓል።
አገሪቱ በሁሉም ነገር ገና በማደግ ላይ ያለች ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ቴክኖሎጂ በአግባቡ የመጠቀም ችግሮች ይስተዋላሉ። በመሆኑም መፍትሄው ህግ አውጥቶ ተጠያቂነት የሚሰፍንበትን አሰራር በመፍጠር እንደሆነ ዶክተር ደምመላሽ ይናገራሉ። በዚህ ሀሳብ የሚስማሙት ዶክተር ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ማህበራዊ ሚዲያው ከመደበኛው ኢንተርኔት ውጪ ተዘግተው ለተወሰነ ጊዜ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባር ቢከናወን የጥላቻ ንግግሩም ሆነ በአገር ላይ እየተፈጠረ ያለው ችግር መፍትሄ ያገኛል ይላሉ። በተመሳሳይ መምህር እምቢአለም መደበኛውና ተጠያቂነት ያለበት መገናኛ ብዙሃን ከማህበራዊ ሚዲያዎች ቀድሞ መረጃ የሚያደርሰበትን አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ ይናገራሉ።
በቅርብ ጊዜ የወጣ መረጃ እንደሚያመላክተው በሀገራችን16ነጥብ4 ሚሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ይገኛሉ። 3ነጥብ6ሚሊየን የሚሆኑት የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ናቸው። በማይናማር፣ በኬኒያ፣ በደቡብ አፍሪካና በደቡብ ሱዳን በነበሩት ቀውሶች በማህበራዊ ሚዲያው የተቀነባበሩ እንደነበሩም መረጃዎች ያመላክታሉ።
የጥላቻ ንግግሮቹ ገደብ ካልተበጀላቸውና በዚህ ከቀጠሉ ሰብዓዊ መብት ማክበር አይኖርም፤ ብሔር ከብሔር ጋር የመጋጨቱ ሁኔታ ይሰፋል፤ በአገሪቱ ላይ ሰላምና መረጋጋት ይጠፋል።በአጠቃላይ አገሪቱ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ትገባለች።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው