በ1900 ዓ.ም የመጀመሪያውን የአማርኛ ቋንቋ ልብ ወለድ መጽሐፍ ያሳተሙት ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ሕይወታቸው ያለፈው ከዛሬ 73 ዓመት በፊት በዚህ ሳምንት መስከረም 15 ቀን 1939 ዓ.ም ነበር።
ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ በ1860 ዓ.ም ጎንደር ውስጥ ዘጌ በተባለ ቦታ ተወለዱ። በልጅነት ዕድሜያቸው እትብታቸው የተቀበረበትን ቀዬ ለቀው ወደ አዲስ አበባ መጥተው እድገታቸውን በከተማ አደረጉ። አፈወርቅ 20 ዓመት ሲሞላቸው አጼ ምኒልክ ወደ አውሮፓ ተጉዘው ዘመናዊ ትምህርት እንዲቀስሙ ከመረጧቸው ወጣቶች አንዱ መሆን ቻሉ። በ1881 ዓ.ም ከሌሎች ወጣቶች ጋር ለትምህርት ወደ ስዊዘርላንድ ካቀኑ በኋላ ከስዊዘርላንድ ጠፍተው ወደ ጣሊያን አገር በመሄድ ቱሪን በሚገኘው የሥነጥበብ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱም ከዘመኑ አስተዳደር ጋር ባለመግባባታቸው ተመልሰው ወደ ጣሊያን አገር በማምራት ትምህርታቸውን ቀጥለዋል። በኋላም ናፖሊ በሚገኘው የምሥራቅ ጥናት ኢንስቲትዩት ውስጥ በአማርኛ ቋንቋ መምህርነት ለአስር ዓመታት አገልግለው የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል።
እንደገና ወደ ሀገራቸው ቢመለሱም የሥጋ ዘመዳቸው ከሆኑት እቴጌ ጣይቱ ጋር በነበራቸው አለመግባባት ምክንያት በአስመራ ከተማ በንግድ ሥራ ሲተዳደሩ ቆይተው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ወደ ሥልጣን ሲመጡ በነጋድራስነት ሹመት የድሬዳዋ ጉምሩክ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል። ቀጥሎም በኢጣሊያ የኢትዮጵያ ቆንስላ ኃላፊ በመሆን ሠርተዋል።
አፈወርቅ በጣሊያን አገር እያሉ በ1900 ዓ.ም የጻፉት “ጦቢያ (ልብወለድ ድርሰት)” የተባለው መጽሐፋቸው ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ የመጀመሪያው የፈጠራ ጽሑፍ ነው የሚሉ የሥነጽሑፍ ጠበብቶች አሉ። አፈወርቅ ከጦቢያ በተጨማሪ በ1901 ዓ.ም “ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ታሪክ” በሚል ርእስ አጼ ምኒልክንና አስተዳደራቸውን የሚያወድስ የታሪክ መጽሐፍ ጽፈዋል። የሥነጽሑፍ ሰዎች ይህ መጽሐፍ ከታሪክ ሰነድነቱ ይልቅ ሥነጽሑፋዊ ውበቱ እጅጉን የጎላና በዘመኑ አማርኛ ለሥነጽሑፍ ቋንቋነት ማገልገል እንደሚችል ያስመሰከረ ነው ይላሉ።
አፈወርቅ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችባቸው አምስት ዓመታት “የቄሣር መንግሥት መልዕክተኛ” የተባለው የጣሊያን መንግሥት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን የወራሪው መንግሥት አገልጋይ ሆነው አገራቸውን ከድተዋል። ለዚህ አገልግሎታቸው የጣሊያን መንግሥት ከፍተኛ የሆነውን የአፈ ቄሣርነት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል። ለጠላት በመወገናቸው ምክንያት ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ሲለቁ በዙፋን ችሎት ሞት የተፈረደባቸው ቢሆንም ፍርዱ ወደ እድሜ ልክ እስራት ተቀይሮላቸው ጅማ ውስጥ በእስር ላይ እያሉ መስከረም 15 ቀን 1939 ዓ.ም በ79 ዓመታቸው አርፈዋል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 14 / 2012
የትናየት ፈሩ