‹‹የምትኖርለት ዓላማ ከሌለህ እየኖርክ አይደለም›› የሚል ዝነኛ አባባል አለ። የሚኖርለት ዓላማ የሌለው ሰው እየኖረ አይደለም፤ የሚኖርለት ዓላማ ለሌለው ሰው በመኖር እና ባለመኖር መካከል ያለው ልዩነት ምንም ነው እንደማለት ነው። ‹‹የምትሞትለት ነገር ከሌለህ የምትኖርለት ነገር የለህም›› የሚሉም አሉ። ይሄኛው የዓላማ ጽናትን ለመግለጽ ነው። ላመኑበት ነገር ሕይወትን አሳልፎ እስከመስጠት ነው።
የሚኖሩለት ዓላማ የሌላቸው ሰዎች ተስፋቢስ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በውሃ ቀጠነ ምክንያት ሁሉ ከሰው ይጣላሉ። በጣም ሲከፋ ደግሞ ራሳቸውን ያጠፋሉ። መደብ መጥቀሱ ይቅርብንና በትንሽ ትልቁ ከሰው የሚጣሉ ምን አይነት ሰዎች እንደሆኑ ግን ልብ እንበል። የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች ናቸው። ከሰው በታች ነን ብለው የሚያስቡ ሰዎች ቁጣ ቁጣ ይላቸዋል። በነገራችን ላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ይፈራሉ (ጠብቆ ይነበባል)። እንዲያውም ይባስ ብሎ ድህነታቸውን እንደ መልካም አጋጣሚ ይጠቀሙታል። እኔ ድሃ ነኝና ልትፈሩኝ ይገባል ብለው ያስባሉ። ሰዎችም ይፈሯቸዋል። ባደኩበት አካባቢ ከማስተውለው በተጨማሪ የሀገር ቤት የቃል ግጥሞች ምስክር ይሆኑኛል።
ላም እሳት ወልዳ
እንዳትልሰው ፈጃት
እንዳተወው ቆጫት
የማይረባ ኑሮ ያደርጋል እመጫት!
ላም እንደወለደች ጥጃዋን ትልሳለች። የግጥም አንዱ ውበት ከተጠይቃዊ ሐቅ ማፈንገጥ ነውና ላም እሳት ወለደች።
ዋናው መልዕክት ያለው ‹‹የማይረባ ኑሮ ያደርጋል እመጫት›› የሚለው ላይ ነው። ሰውየውም ልክ እንደ ላሚቷ ነው የሆነው። ወይ ኑሮው የተደላደለ አይደለም፤ ወይም ፍጹም ድሃ ሆኖ እንደልቡ ገዳይና አስፈራሪ አልሆነም። ሰውየው ፍጹም ድሃ መሆንን እየተመኘ ነው ማለት ነው። ፍጹም ድሃ ሆነ ማለት ‹‹ቤቴ፣ ልጆቼ…›› የሚለው ስለሌለ ቀና ብሎ ያየውን ሁሉ በጥይት ሊቆላ ነው። ምክንያቱም የሚኖርለት ዓላማ የለውም። ሕግንም ሰውንም አይፈራም፤ ቢታሰርም ቢገደልም ጉዳዩ አይደለም።
የሚገርመው ነገር እርስበርስ እንኳን ሲጣሉ መመኪያቸው ድህነታቸው ነው። ‹‹ድሃ ነኝና ልትፈራኝ ይገባል›› የሚል መልዕክት ያለው ዛቻ ነው የሚለዋወጡት። ‹‹ልጆቼ ቤቴ የምለው የለኝምና እገልሃለሁ›› ነው ነገሩ። በአንጻሩ ልጅና ቤት ያለው ሰው ደግሞ ለልጆቹና ለቤቱ ሲል የውስጡን ወኔ አምቆ ለመፍራት ይገደዳል፤ የሚኖርለት ዓላማ አለዋ! ያኛው ግን ቢሞትም አይጨንቀውም። ዓላማ ያለው ሰው ግን ሞትን የሚፈራው ለራሱ ሳይሆን ለሚኖርላቸው ልጆቹ ነው። አንድ የቃል ግጥም ልጨምር።
አትንኳት ጎጆዬን በአንድ እግሯ ቆማለች
ትልቁን አዳራሽ ይዛው ትጓዛለች!
እንዲህ የሚለው በኑሮ ሆድ የባሰው አንጎራጓሪ ነው። ድሃ ነኝና አትንኩኝ እያለ ነው። ከነካችሁኝ ትልቅ ቤት ያላችሁ ሁሉ አለቀላችሁ እያለ ነው። የኔ ቤት ቢፈርስም አይቆጭም፣ የእናንተ ቤት ግን ቢፈርስ ይቆጫችኋልና እኔን ፈርታችሁ ኑሩ ነው ነገሩ። ሲጣሉ ‹‹እስኪ እንግዲህ ከእኔና ከአንተ ቤት!›› እየተባባሉ ነው የሚዛዛቱት። ከእኔና ከአንተ መፍራት ያለበት መባባላቸው ነው።
የትምህርት ቤት ሕይወት እናስታውስ። ፈርቶ እና ሥነ ምግባር አክብሮ ሲኖር የምናየው ጎበዝ ተማሪ ነው። ጎበዝ ተማሪ ሲሰድቡት እንኳን ቻል አድርጎ ነው። አስተማሪ ውጣ ሲለው ሹልክ ብሎ ይወጣል፤ ክፉ ነገር አይናገርም። ምክንያቱም የሚኖርለት ዓላማ አለዋ! ያንን ዓላማውን ሳያሳካ ምንም ነገር መሆን አይፈልግም። እባረራለሁ ብሎ ይፈራል።
በአንጻሩ ሰነፍ ተማሪ ደግሞ የዚህ ሁሉ ተቃራኒ ነው። መምህር ይገላምጣል፣ አርፍዶ ይገባል፣ አጠገቡ ካለው ተማሪ ጋር ሁሉ ይጣላል። ይሄ ተማሪ እባረራለሁ የሚል ስጋት የለበትም። ቢባረር ደስታው ነው እንጂ አይጨንቀውም። ሰነፍ ተማሪዎች ጎበዝ ተማሪዎችን ሲያስፈራሩ ‹‹እንዳላስባርርህ!›› እያሉ ነው። ምክንያቱም ጎበዙ ተማሪ መባረርን እንደሚፈራ ያውቃሉ። የሚኖርለት ዓላማ ያለው ሰው እንዲህ ነው።
ከላይ ያየናቸው የትምህርት ቤት ሕይወትም ሆነ የሀገር ቤት ሰዎች ድርጊት ፍርሃት የማሰብ ምልክት መሆኑን ይነግሩናል። አንድ ሰው የሚፈራው ከሞተ ወይም ከገደለ በኋላ የሚመጣውን ነገር በማሰብ ነው። ቢገድል በሰማይም በምድርም ይጠየቃል፤ የሰው ነፍስ ለማጥፋት ሕሊናው አይፈቅድም። የደረሰበት በደል ሕሊናውን የሚፈታተን ቢሆንም ሕግን ወይም ፈጣሪውን ይፈራል። ራሱ እንዳይሞት ደግሞ ያ የሚኖርለት ዓላማ እንደሚሰናከል ያውቃል። ልጆችና ቤት ካለው የሚደርስባቸውን እንግልት ያስባል። ስለዚህ አሳቢ (አስተዋይ) ሰው ይፈራል።
ለዘመናት የተሰጠው የጀግንነት ትርጉም ተጋዳይነት ነው። በዘመነ ኢሕአዴግ ‹‹ጀግንነት ድህነትን ማሸነፍ ነው›› የሚል ፕሮፖጋንዳ ነበር። ትክክል ነው፤ ድህነትን ማሸነፍ ጀግንነት ነው። ሆኖም ግን የየጀግንነት ትርጉም ሰው ከመግደል አላለፈም።
በነገራችን ላይ ብጥብጥ የሚፈልጉ ተስፋ ቆራጮች መሆናቸውን የሚገልጹ የቃል ግጥሞች የመኖራቸውን ያህል የጀግናን ምልክት የሚያሳዩ ግጥሞችም አሉ።
ቆራጥ ጎበዝ እና ነብር አንድ ናቸው
ደርሰው አይናኩም ካልደረሱባቸው!
እንደሚታወቀው አንበሳ እና ነብር የጀግና ምልክት ተደርገው ይወሰዳሉ። ነብር ካልተንቀሳቀሱና ሊመቱት ካልቃጡ አይነካም የሚባል እንስሳ ነው። በረሃ ውስጥ ከብት የሚጠብቁ እረኞች በዘዴ አብረውት ይኖራሉ። ማታ ማታ ማደሪያቸው እየመጣ እሳት ይሞቃል። ዋሽንት መጫወት የሚችል ሰው ካለ ዋሽንት ይነፋለታል። ካልነኩት አይነካም። ጎበዝ ጀግና ከዚህ ነብር ጋር ይመሳሰላል።
ጀግና ካገኘው ጋር ሁሉ አይጣላም። ልኩን ያውቃል። ፀብ ይንቃል። ከደረሱበት ግን ልካቸውን ያሳያል እንደማለት ነው።
በአንዳንድ አጋጣሚዎች የግጭት ችግሮች ሲፈጠሩ እንኳን ልብ በሉ። ልጅና ቤት ያላቸው ሰዎች ይመክራሉ፣ ወጣቶችና ከየመንገዱ የመጡት ደግሞ ማንን እንደሆነ ባይታወቅም ፀያፍ የስድብ ቃላት እየተጠቀሙ ‹‹መጥረግ ነበር! መፍጨት ነበር፣ ማንደድ ነበር….›› ይላሉ። አንዳንዱ ደግሞ ‹‹ጦርነት ቢነሳና ይሄ መንግሥት ቢወድቅ›› ይላል፤ ቀጥሎ ምን እንደሚመጣ ግን አያውቅም። ለሰካራምነቱ ሁሉ ጦርነት ቢነሳ መፍትሔ ይመስለዋል። ቀጥታ የፖለቲካ ተልዕኮ ካላቸው በተጨማሪ ምኑንም የማያውቁትም የግጭት አቀጣጣዮች ናቸው። የእነዚህኞቹ ገፊ ምክንያት የሚኖሩለት ዓላማ ማጣት ነው።
ፍርሐት የማሰብ ምልክት ነው! ሕፃናት እሳት የማይፈሩት ለምንድነው? ስለማያስቡ ነው። ነፍስ ካወቁ በኋላ የሚፈሩት ለምንድነው? ማሰብ ስለጀመሩ ነው። ከብቶች ገደል እና ገዳይ መርዛማ ነገሮችን የማይፈሩት ለምንድነው? በደመ ነፍስ ስለሚኖሩ ነው! ሰው ሞትን የሚፈራ ለምንድነው? አሳቢ ፍጡር ስለሆነ ነው። ፍርሐት የማሰብ ምልክት ነው፤ አለማሰብ ደግሞ እንስሳትነት ነው!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም