ሰዎች! ሰላም ነው? እንዴት ነን? መቼም በዚህ ጊዜ ከተወለድንበት አገር፣ ከአገርም ከተማ፣ ከከተማ ሰፈር፣ ከሰፈር ግቢ ቆጥረው፤ ጠብበው ጠብበው፤ «ሰዎች!» ሲባሉ ድንግጥ የሚሉ «አካላት» እያየን ነው። «እንዴ! እኛ ሰዎች አይደለንም…» ሊሉ ይቃጣቸዋል። «እኮ ምንድን ናችሁ?» ሲባል ብሔራቸውን መጥራት፤ አልገጠሟችሁም? አካሄዱ ወደዛ እየመሰለ ነዋ!
እዚህ ላይ «እነርሱ» የሚለውን ተውላጠ ስም መጠቀሜንና «እኛ» እያልኩ አለመግለጼን ከትህትና ጥሰት የመነጨ ተግባር አድርጋችሁ አትቁጠሩብኝ። በበኩሌ «ምንድን ነሽ?» ስባል ወይም ብባል መልሴ እንደጠያቂው ሁኔታ ይሆንና ግን ከሁለት አያልፍም። አንደኛው መልሴ «ሰው ነኝ» ሲሆን ሁለተኛው «ኢትዮጵያዊት ነኝ» የሚል ነው። ዋሸሁ እንዴ? ያው ምን ዓይነት ሰውና ምን ዓይነት ኢትዮጵያዊት ተብሎ አይጠየቅም እንጂ!
መግቢያዬን አንዛዛሁት! አፉ በሉኝ። ነገሬ ወዲህ ስለመቶው ቀናት ነው። መቼም ወደ ሌሎች መጠቆም ይቀናናል! ይቀናናል ራሱ አይገልጸውም፤ ይመቸናል! «እንዲህ ያደረገው እገሌ ነው፤ እነ እገሌ ምን አደረጉ? እነ እገሊት እንዲህ ባያደርጉ ኖሮ!» በቃ! ወደሌሎች ስንጠቁም እኛ የለንም፤ ወይ ከቅዱሳን ተርታ ተሰልፈናል ወይም በታዛቢነት የሰየሙን ይመስል ፈቃድ እንዳለን ይሰማናል። ብቻ መጠቆም ነው!
እናማ! በዚህ ሌሎችን የመቃኘት አባዜ-አችን የተነሳ «የሚኒስትሮቹ መቶ ቀናት፤ የመሥሪያ ቤቶቹ መቶ ቀናት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መቶ ቀናት፣ የካቢኔው መቶ ቀናት…» ወዘተ እየተባለ ስም እየተሰጠ በሕጋዊ መንገድ ተቋማት ስማቸው ይነሳል። እዚህ ላይ ግን! እንደው ሰዎች በተለይ ሴቶች በቡና ሰበብ ሰብሰብ ብለው ሰው ያማሉ ይባላል እንጂ፤ በሕጋዊ ፈቃድ በአዋጅ አስነግረው፣ በሕግ እየተጠበቁ የሚያሙ አሉ አይደለ? እነ መገናኛ ብዙኃን።
አይ! ነገሩንስ ለጨዋታችን ድምቀት ነው እንጂ የብዙኃን መገናኛ ጥቅምን አጥቼው አይደለም። እንደው እግረ መንገዴን ቡና እየጠጡ ሰው ማማት እንጂ ቡና እየጠጡ ፖለቲካን እና የፖለቲካ ስርዓትን ማማት ስላልተከለከለ፤ ማኅበረሰባችን እየዘነጋ ያለውንና ሰብሰብ ብሎ የመወያየትን ነገር፤ በቡና ሰበብም ቢሆን እንዲመለስበት ቅስቀሳ ቢደረግ የሚል ሃሳብ ለማቀበል ነው።
ብቻ ግን የእነዛን ሁሉ ተቋማት መቶ ቀናትን እያራገፉ አደባባይ የሚያሰጡቱ ስለራሳቸው መቶ ቀናት ገልጸው አያውቁም፤ ጠያቂም የላቸው። አሃ! የእነርሱስ መቶ ቀናት? አራት ኪሎ ያለው ትልቁ ቤት እንዳለው ዓይነት ለውጥ ሁሉም ጋር ያለ እየመሰለን፤ ታችኛውን ትተን የላይኛውን መቶ ቀናት ነው የምናጠናው? ለውጡን ያራምዳል ተብሎ በየተቋሙ ወንበር የተሰጠው አመራርስ?
መቼ እለት በአንድ ተለቅ ያለ የመንግሥት ተቋም ከሚሠራ የቅርብ ቤተሰብ ጋር ጨዋታ ይዘን ስለአዳዲስ የተቋማቸው አመራር አነሳልኝ። «ሥራውን ለቅቄ ልወጣ ነው፤ ካለፈው የተሻሉ ኃላፊዎች መጡ ስል ያለእኛ አዋቂ የለም የሚሉ ሆነውብኛል» አለኝ። «እኛም ጋር እንደዛው ነው!» ልለው ነበር፤ ግን የሱን ብሶት መስማቱን መርጬ ነው መሰለኝ ያሰብኩትን ሳልለው ቀረሁ።
ቀጠለ፤ «ግርም የሚለኝ፤ እነርሱ ምክንያታዊ ሳይሆኑ እኛ ግን በምክንያት እንድንንቀሳቀስ ይጠይቃሉ። ለምሳሌ፤ ‘ቦርድ ላይ የሚለጠፍ የውስጥ ማስታወቂያ ይቅር፤ ምክንያቱም ስገባ ስወጣ አየዋለሁና ምንም ለዓይኔ ደስ አላለኝም።’ ይላሉ አለቅየው። የውሳኔ ሰው በመሆናቸው ቦርዱ በፍጥነት ይነሳል። ‘ኧረ አስፈላጊ ነው’ የሚሉ ሰዎችን ታድያ ‘አሳማኝ ምክንያት አቅርቡና ከዛ ቦርዱ ዳግም ወደሥራው ይገባል’ ይሏቸዋል።»
እርፍ!
እመኑኝ! በየተቋማቱ ከለውጡ ጋር ይራመዳሉ ተብለው ወንበር የያዙትም መቶ ቀናት ቢፈተሽ እንደምንጠብቀው አስደሳች ዜና ላይገኝ ይችላል። በእርግጥ በመቶ ቀናት ጀንበር ሁሉም አይስተካከልም። እኛም አስቸጋሪ ነን! መሪው አንድ ሆኖ እኛ አስር ሺህ፤ ከዛ ፍላጎታችን ደግሞ ከእኛም በእጥፍ አድጎ ሃያ ሺህ ነው። የምንፈልግለውን ራሱ በትክክል የምናውቅ አይመስለኝም።
እንዴ እንዴ! ኧረ እንደው የእኛ /የሰፊው ሕዝብ/ መቶ ቀናትስ? ጥሩ! እንደ ሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰው «የእኛ መቶ ቀናት ከመቼ ይጀምራሉ?» የሚለውን ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን። የእኛ መቶ ቀናትን ቀመር ማግኘት ከባድ ቢሆንም፤ «ለውጥ መጣ፤ ጭላንጭሉን አየነው» በሚል ደስ ከተሰኘንበት ጊዜ አንስተን እንመልከት፡-
በዛ መሰረት፤ ግማሹን በ«ለውጥ መጣ» ደስታና ሆታ ስናሳልፍ፤ የተወሰነውን በአዳዲስ አመራር አቀባበልና የቀድሞውን ብሶት በማራገፍ ስንገፋ፤ ከዛ «ወይ ዝርፊያ!» ብለን አገራችን በተዘረፈችው ውስጥ የነበራትን ሀብት ስንስል፤ ለጥቆ ያልተናነሰውን «አይ ጭካኔ!» እያልን ስናዝን፤ በሚቀጥለው ስብሰባ፣ ስልጠና፣ ግምገማ፣ ኤዲቶሪያል፣ የሻይ ሰዓት፣ የትራንስፖርት ሰልፍ ወዘተ ቦታ ቦታቸውን ይዘው፤ የቀረው እንኳ መቶ ቀን ቢሆን፤ የእኛ መቶ ቀናት እንዴት ነበሩ?
በመቶው ቀናት ከሃሜት በዘለለ ምን ሠራን? ባንሠራስ ዝም ማለት ተስኖን ምን አወራን? «አይ! የሚሆን አይመስለኝም» እያልን አይደለ? እንደው የታመመ ዘመዳችሁ ምን ከባድ ሁኔታ ውስጥ ቢገባ፤ «እንግዲህስ ተስፋ የለህም! ቤት የመቀበሪያህን ቀን እየጠበቅን ስንዴና ሽንብራ እያዘጋጀን ነው። በል የምትናዘዘው ካለ ተናዘዝ» እንላለን? ያው በከንፈር መጠጣችንና በዓይናችን ይህ ነገር ቢገለጥ እንኳ፤ አንደበታችን ግን ለዛ ሰው ተስፋ መስጠቱን አይተውም።
እናስ! ምን አወራን? በገጻችን ላይ ምን ተነበበ…ምን «ፖስት» አደረግን? የቱን ሃሳብ ተጋራን? የቱን ተግባር አከናወንን? ማንን አጽናንተን ማንን ተስፋ አስቆረጥን? ስንት በመቶ ወድደን ስንት በመቶ ጠላን? አደባባይ ተሰጥቶ ቢታይ ልባችን ምን መሰለ? ምን ሠራን ምን አሴርን? በመግለጫ እንደሚቀርብ እንደተመረጠ ሃሳብ ስንቱን ስብዕናችንን ገልጠን ስንቱን ሸፈንን? አቋማችን እንዴት ሆነ? ሲጠቃለል፤ የእኛ መቶ ቀናት እንዴት ነበሩ?
ይህ የሦስቱ ጣቶች ጥያቄ ነው። ሁሉም እንደሚያውቀው ብሂላችን፤ ሌባ ጣት ወደሌላው ስታመለክት ሦስቱ እንደየስማቸው ወደ ጠቋሚው ሰው አይደለ የሚዞሩት? እንጂ ለውጡ ይሄ አይደለም! የኖረ አመላችን በመቶ ቀናትም ይሁን በየወሩ እየታጠበ ካልጸዳ፤ ተጠራቅሞ የሌላ ሰላሳ ዓመት እዳ መሆኑ አይቀርም። ለሁላችንም ነው፤ በያለንበት ኃላፊነት አለብና! ዘነጋን እንዴ? ሌላው ስልጣንና ኃላፊነት ቢረሳ እንኳ «ሁላችሁም ከንቲባ ናችሁ» መባላችን ይዘነጋል?
ክቡራትና ክቡራን፤ እውነቴን ነው! በጠቅላዩ ተሰይሞ ቦታ መያዝና መታመን ብቻውን በቂ አይደለም። ተሽሎ መገኘት በተግባር መገለጥ አለበታ! እንዴ! በእናንተ ጊዜ እንኳ እስቲ ከ«ተቻችሎ» መኖር ወደ፤ ተዋዶና ተከባብሮ መኖር እንሻገር! እኛም /ሰፊው ሕዝብ እንደየ ድርሻችን/ መለስ ብለን ያለፉትን ቀናት ሻንጣ በርበር አድርገን ሰዎች እንዲሆኑ የምንፈልገውን ሰው እኛው በመሆን እንጀምር።
ላብቃ! ፀሐፊ መሆን ጥቅሙ ይህ ነው፤ በትህትና ስትናገር «እኛ» ብለህ ከአመራሩም ከሰፊው ሕዝብም መካከል መሆን ትችላለህ። ብቻ ዋናው ነጥብ፤ መቶው ቀናት የሁላችንም ናቸው ነው። መቶው ቀናት፤ እንደላይኛው ቤት ሁሉ ለታችኛው፤ «የእገሌ መቶ ቀናት» እያለ ለሚገመግመው፤ የእነ እገሌን መቶ ቀናት ግምገማ ቁጭ ብሎ የሚመለከተውንም ይመለከታል ለማለት ነው። አሁን ይህቺን ለማለት ነው ያንን ሁሉ ያልኩት? ውጋት ሆንኩባችሁ አይደለ? ተውት…እገመገማታለሁ! ሰላም።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2011
ሊድያ ተስፋዬ