በብዙ ሀገራት የሚሾሙ ፕሬዚዳንቶች ወይንም ጠቅላይ ሚኒስትሮች ምን ሰሩ? ምንስ አልሰሩም? ተብለው በሕዝባቸውና በዓለም አቀፍ ተቋማትም ጭምር መገምገም የሚጀምሩት ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ እስከ መቶ ቀናት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ነው። የእኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድም (ዶ/ር) በመቶ የሹመት ቀናቸው ምን አከናወኑ በምንስ ጉዳዮች ላይ ደከሙ የሚሉ ግምገማዎችን ከአንድ ዓመት በፊት ማስተናገዳቸው አይዘነጋም። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም ለምን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ? “የሚኒስትሮቻችን 100 ቀናትስ?” በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ በአንድ የግል ጋዜጣ ላይ ማስነበቡ ይታወሳል።
በተለይም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር አፅንኦት ሰጥተው ተስፋ ከገቡባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሕዝቡን እየናጠ ለነበረው ከፍተኛ የሰላም እጦት “የዘንባባ ቀንበጥ በአፏ የያዘች የሰላም ርግብ በኢትዮጵያ ምድር ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ እየበረረች ሰላምን እንድታውጅ መንገዷን አሳምርላታለሁ” የሚል እንደነበር እናስታውሳለን። ሃሳቡን እንጂ የገለጸው ምናባዊና ሥነ ጽሑፋዊ ቅባት የጸሐፊው መሆኑን ልብ ይሏል።
ጠቅላዩ በገቡት ተስፋ መሠረት እውነትም ውለው ሳያድሩ በሰላም ርግቧ መልዕክተኛነት የሀገሪቱን የወህኒ ፍርግርጎች በመነቃቀል ብዙ ሺህ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞችን ነፃ ለቀቁ። ተገንዘው ያሸለቡ የጸሐፍት ብዕሮች መግነዛቸው ተፈቶላቸው እስትንፋስ እንዲዘሩ አርነት አወጧቸው። የተቃዋሚና የተቀናቃኝ የፖለቲካ ቡድኖች ደቀመዛሙርት ከበረሃም ሆነ ከዲሲ፣ ከአስመራም ሆነ ከኒዮርክ ሻንጣቸውን ሸክፈው፣ ጠብመንጃቸውን ወርውረው ሲገቡ አርሂቡ ብለው ተቀበሏቸው። ምላስ አደር አክቲቪስቶችም በሩ ወለል ተደርጎ ተከፈተላቸው። አልፎም ተርፎ በየሀገራቱ በሰንሰለት የታሰሩ ምንዱባንን እያስፈቱ በራሳቸው “ኤር ፎርስ ዋን ጄት” ምነው ባደረገልን! በአንድ ወንበር ላይ እየተጋፉና እየተጨዋወቱ ለሀገራቸው አፈር አበቋቸው። በሀገራቸው ዳር እስከ ዳር እየዞሩ፣ በወዳጅነትና በጠላትነት ወደ ተፈረጁ ሀገራት እየዘመቱ የሰላም ርግብ ተምሳሌትነታቸውን አስመሰከሩ። “ከቢሮ እስከ ሀገር” የዛጉትን ጉዳዮችና ቅጥረ ግቢያቸውን እያፀዱ ሰላምን በሚወክል “ነጭ ቀለም!” የሕዝባቸውንም የቢሮ ግድግዳቸውንም ለማጽዳት ብዙ ደከሙ፣ ላይ ታች እያሉም ታተሩ።
በርግጥም የተስፋ ብርሃን ያንጸባረቀው አብለጭላጩ የጠቅላዩ የመደመር ሰይፍ (ሰላም፣ ይቅርታ፣ ፍቅር) የተንሰራፋውን የውርስ ኃጢያት እየመተረ በመላ ሀገሪቱ ተምዘገዘገ። የሰላም ርግቧም “ብረሪ፣ ብረሪ” እየተባለች ከአፅናፍ አፅናፍ ተበረታታች። አዲሱ ዘመን ሊጠባና ወገግታው ለመድመቅ እያቅላላ ሳለ ግን የነገሮች መልክ መለዋወጥ ጀመሩ።
ለመሆኑ ምን ነካን? ማስተዋላችንንስ ምን ነጠቀው?
እ.ኤ.አ በ1948 ዓ.ም ፓሪስ ላይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሰላም ጉባዔ ላይ ስፓኛዊው ፓውሎ ፒካሶ የሰላም ተምሳሌት አድርጎ ያበረከተልን የዘንባባ ዝንጣፊ በአፏ የያዘችው ርግብ በሀገራችን በምክንያት የለሽ ሀገራዊ ጠብ አጫሪ ቡድኖችና ጥቅማቸው በነጠፈባቸው ተጠቃሚዎች ወንጭፍ እየተመታችና እየቆሰለች ደሟን ስታዘራ ደጋግመን አስተዋልን። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከአንድ ዓመት በፊት በተካሄደ ሀገራዊ የሰላም ጉባዔ ላይ ባቀረበው የጥናት ጽሑፍ ውስጥ ያቺን እብሪትና ትዕቢት፣ ግትርነትና እብለት ያቆሰላትን የሰላም ርግብ በሚከተሉት አራት ስንኞች እንደሚከተለው ለመግለጽ ሞክሮ ነበር፤
“ዘንባባዋን ጥላ የት ሄደች ለምን ግብር፣
የሰላምን ብስራት አብሳሪዋ ርግብ፣
እያልኩኝ ስጠይቅ የእኔም ተስፋ ወድቆ፣
ከደሟ ነጠብጣብ ጣለኝ እግሬ ወስዶ።”
የሰላም ርግቧን ያቆሰሉ ብዙ ሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከአሁን ቀደም ባስነበብኳቸው በርካታ ጽሑፎቼ ውስጥ ለመነካካት ስለሞከርኩ በዚህኛው ጽሑፌ ብዙ ላለማለት ተቆጥቤያለሁ። በግሌ እንደ ሀገሬ ለዘመናት በየሥርዓተ መንግሥታቱ የሰላም ርሃብተኛ ሆኖ የኖረ ሌላ ሕዝብ ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም። ያውም የምድር በረከት ሳይጎልብንና ሳይነጥፍብን፣ ተደጋግፈን፣ ተከባብረን፣ ተቃቅፈንና ተካፍለን መኖር ስለማናውቅበት ብቻ፣ አሮጌ የታሪክ ስልቻዎችን እየጎተትንና የተቀበሩ ክስተቶችን አፅም ከመቃብር እየፈነቀልን በማውጣት ስንገዳደልና ስንረባበሽ፣ ባለመስራታችን ተፈጥሮ ስትቀጣንና ስንራብ መኖራችን ለእኛም ሆነ ለዓለም ማኅበረሰብ እንቆቅልሽ/ህ ሆኖ ዛሬም ድረስ እየተሸጋገረ አብሮን አለ። ጣጣው አለቅ ብሎንም እነሆ የቆሰለችውን የሰላም ርግባችንን ማከምና ለራሳችንም መፈወስ አቅቶን እንደተሸመደመድን ዘመን እንገፋለን።
ለመሆኑ ከሰላም ርግብ ጋር ጠበኛ ለመሆን የተረገምነው ለምን ይሆን? ከወደ ኋላ 100 ዓመታትን አፈግፍገን በግርድፉና በወፍ በረር ቅኝት አንዳንድ ታሪካዊ ጉዳዮችን ለማስታወስ ልሞክር። ያለፉት መቶ ዓመታቶቻችንን በአንጓ እየከፋፈልኩ ከሰላም አኳያ ምን ይመስሉ ነበር? ለመቃኘት ሞክሬያለሁ። መነሻዬ 1911 ዓ.ም ሲሆን መድረሻዬ ደግሞ ፋይሉን የዘጋነው 2011 ዓ.ም ነው። 2012 ዓ.ም ከጠባ ገና ድክ ድክ እያለ ስለሆነ አዲሱን ዓመት አላስቸግረውም።
ከ1911 – 1928 ዓ.ም
ሰላም ብርቅ የነበረባቸው፣ ሀገርና ሕዝብ የተጨነቁባቸው ዓመታት ነበሩ። በምኒልክ እረፍት ማግሥት አልጋው ተነቃንቆ የዋለለበት፤ “የህዳር በሽታ” እየተባለ በሀገራችን የሚታወቀው “የስፓንሽ ፍሉ” በአጭር ቀናት ቆይታው በሺህዎች የሚቆጠር ሕዝባችንን የፈጀበት፣ ራስ ተፈሪ መኮንንም ሳይቀሩ በበሽታው ምክንያት ሞቱ ሲባል በተዓምር የተረፉበት፣ በተዓምርነት የሚነገርለት ከፍተኛ የእሳት ዝናብ ከየት መጣ ሳይባል የአዲስ አበባን ጎጆዎች ያጋየበት፤ ቤተ መንግሥቱም ሳይቀር በወላፈኑ የተደፈረበት ዓመታት ነበሩ።
ልጅ እያሱና ወደረኞቻቸው እስከ 1913 ዓ.ም ድረስ ለ55 ወራት ያህል ለመጠፋፋት የተፈላለጉበት፣ የ53 ዕድሜ ባለጠጋዋ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና የ20ዎቹ ዓመታት ጉብል ራስ ተፈሪ መኮንን ለሥልጣን የተሻኮቱበት፣ በቤተ መንግሥቱ ዙሪያ ይገኝ የነበረው የመሃል ሰፋሪ ጦር በሰበብ ባስባቡ “እኔ ነኝ ያለ!” እያለ የሚጎፈላበት አስጨናቂ ዓመታት ነበሩ።
የ1923 ዓ.ም ሕገ መንግሥት ሲረቀቅ በአፍቃሬ ፊውዳል አቋማቸው በግትርነት የቆሙት ራስ ካሣ ኃይሉና በለውጥ ፈላጊነት በተፈረጁት በበጅሮንድ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም መካከል ፕሮግሬሲቭ የሆነ ሕገ መንግሥታዊ መሻሻል ይደረግ አይደረግ በሚለው ክርክር ፖለቲካው ግራ ተጋብቶ የጦዘበት፣ “ስለ ባሮች አስተዳደርና ነፃነት የቆመው ደንብ” ተግባራዊ መሆን ሲጀመር “የባሮች አስተዳዳሪ ፊውዳሎችና” ነፃ ልቀቁን ባይ ንፁሃን ምስኪኖች የተፋጠጡበትና ጡዘቱ የከረረበት ወቅትም ነበር።
እርግጥ ነው በዚህ ሁሉ ትርምስ መሃከል ሀገሪቱ የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል ለመሆን የበቃችበት፣ ዘመናዊ የሀገር አስተዳደርና የትምህርት መስፋፋት የጀመረበት፣ ጥቂት የሚይባሉ ወጣቶች ለትምህርት ውጭ ሀገራት መላክ የተጀመረባቸውና አንዳንድ መነቃቃቶች የታዩባቸው ዓመታትም ነበሩ። ከብዙ ጥቂቱ ለአብነት ይበቃል።
ከ1928 – 1933 ዓ.ም
በአጭሩ በፋሽስት ወረራ ምክንያት መንግሥትና ሀገር የፈረሰበት፣ ሀገራዊ ክብርና ሉዓላዊነት የተናደበት፣ ከወራሪው ሠራዊት ጋር የመጡ ክፉ ማኅበራዊ ቀውሶች የተስፋፉበት፣ ሞትና ለሀገር መሰዋት ብርቅ ያልሆነበት፣ የዜግነት ኩራትና ባንዳነት ፊት ለፊት የተፋለሙበት፣ ሰማዕትነት እንደተራ ሕይወት የተቆጠረበት፤ ዝርዝሩ ብዙ ቢሆንም ለዘመኑ ማሳያነት የሚያንስ አይመስለኝም።
ከ1933 – 1953 ዓ.ም
በወራሪው ፋሽስት የፈራረሰው አስተዳደር፣ ኢኮኖሚውና ማኅበራዊ ሕይወቱ ለማንሰራራት እጅግ ከፍተኛ ጥረትና ሙከራ የተደረገበት። አርበኞችና የአርበኞች ልጆች በአንድ ጎራ፣ የውስጥ አርበኞች ነበርን የሚሉ ወገኖች በሌላ ወገን፣ ከስደት ተመላሾች ነን ባዮች በሌላ ምድብ እየተቧደኑ ለሽልማት፣ ለሹመትና ለእውቅና ቅድሚያው የእኛ ነው በማለት እስከ ፍልሚያ የጨከኑበትና “ለነፃነቱ መገኘት የእኔ ሀገራዊ ድርሻ ከሁሉም የላቀ ነው” የሚሉ ድምፆች ገነው የተደመጡበት ዓመታት ነበሩ።
ጎንደሬው ታከለ ወልደሐዋርያት በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራዎችን በማቀነባበር የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በማድረግ ያሴሩበት፣ የ1953 ዓ.ም የጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ብዙ ነፍሶችን ጭዳ አድርጎ የከሸፈበት፣ በዚሁም ሰበብ የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት በታላላቅ ሹማምንት ደም የጨቀየበትና በኋለኛው ዘመን ለነውጠኛው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቤተ መንግሥቱ ለትምህርት ተቋምነት የተሰጠበት ወቅት ነበር።
እንደዚያም ቢሆን ግን ንጉሠ ነገሥቱ እጅግ በረቀቀ ጥበብ ተቀናቃኞቻቸውን እያስወገዱ ሥልጣናቸውን በማደላደል ትልልቅ ሀገራዊ ተግባራት ተከናውነው ሀገሪቱ ወደ ተሻለ ከፍታ ማቅናት የጀመረችባቸው ዓመታት ነበሩ። የንጉሡና የሀገሪቱ ዓለምአቀፋዊ ተቀባይነት ከፍ ብሎ “አንቱታ” የበዛባቸው ዓመታትም ነበሩ።
ከ1953 – 1967 ዓ.ም
ይህ ወቅት በአብዛኛው የወጣቱ የነውጥ ባህርይ ገንፍሎ የወጣበት፣ በተለይም የወቅቱ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲና የሀገሪቱ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለፊውዳል ሥርዓቱ የጎን ውጋት በመሆን ወጥረው አላፈናፍን ያሉበት ዓመታት ነበሩ። የድርቅ ሰደድ በሀገሪቱ የተስፋፋበት፣ የወታደሩና የተለያዩ ባለሙያዎች መንበረ ሥልጣኑን በጥያቄዎች ያዋከቡበት የለውጥና የነውጥ ዓመታት ነበሩ።
አዳዲስ የአይዲኦሎጂ ፍልስፍናዎች የገነኑበትና “ግራና ቀኝ” ዘመም እየተባባሉ ወጣቶቻችን በአርጀንቲናዊው ቼ ጉቬራ፣ በቪዬትናሙ ሆችሚኒ፣ በቻይናው ማኦ ዜዱንግ፣ በጀርመናዊው ማርክስ፣ በሶቪዬት ኅብረቶቹ ሌኒንና ስታሊን ፍልስፍናዎች ያበዱበትና ሰላማዊ ሰልፍ እንደ ዕለት እንጀራ በትጋት የተፈለገባቸው ዓመታት ነበሩ። ዕድሜ የተጫናቸው ንጉሥ ግራ ተጋብተውና መያዣ መጨበጫ አጥተው የሀገሪቱ መልህቅ ተፈትቶ ኢትዮጵያ በለውጥ አውሎ ነፋስ የተላጋችበት ዓመታት ነበሩ ብሎ መጠቅለሉ ይበጃል።
ከ1967 – 1983 ዓ.ም
ይህ ዘመነ ደርግ በንፁሃን ዜጎች ደም ምድሪቱ የጨቀየችበት፣ እንደ ተራ ጨዋታ የጦርነት ፍልሚያ የዕለት ወሬ የነበረበት ነበር ቢባል ያስማማል። በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች የተቧደኑ ኃይሎች በውስጥና በውጭ፣ በግልጽና በህቡዕ የተፋለሙበትና እንደ እሳት እራት ያለ ሁነኛ ዓላማ እርስ በእርስ ተጠፋፍተውና እንደ አሜባ ተበላልተው ታሪኩ የተዘጋበት ዓመታትም ነበሩ። ሃይማኖት፣ ባህልና ቅርስ የተናቁበትና በባህል አብዮት እርምጃ ስም በይፋ እንዲጠፉ የተፈረደባቸው ዓመታት ነበሩ። የሀገሪቱን አየር የሞላው የእናቶች እንባ፣ ነጋ ጠባ የሚወራው የውርስ አዋጅ፣ የሞት ዜናና ውድመት ነበር ብሎ ሰፊውን ሃሳብ መሰብሰብ ይቻላል።
ከ1983 – 2010 ዓ.ም
ስለ ዘመነ ኢህአዴግ መግለጽ ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል። በአጭሩ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በእብደት ያኮላሸው ሲስተሙን በሙሉ ነበር ብሎ ማለፉ ይበጃል። የተኮላሸው ግለሰባዊ ክብርና መብት፣ ማኅበራዊ ትሥሥርና የዜጎችም ህሊና ጭምር ነበር። የትምህርት ሥርዓቱ ከሽፏል፣ ኢኮኖሚው ወደ አንድ ቡድን ተጠቅልሏል፣ ዜጎች በቋንቋና በብሔራቸው ክብር ስም እየተሸነገሉ ለመቃቃርና ለመገዳደል እንዲጀግኑ በበቂ ሁኔታ ተሰርቷል፤ ዕቅዱም በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ እነሆ ፍሬውን እየገመጥን ነው።
በእነዚህ መቶ ዓመታት ውስጥ የሀገሬ የሰላም ርግብ ስትቆስልና ደሟን ስታዘራ የኖረችው በእነዚህ መሰል ግርድፍ ታሪካዊ መንስዔዎች አማካይነት ነበር። ምናልባትም የሰላም ርግባችንን ማከምና ቁስሏን መጠገን ይቻል እንደሆን ተብሎም የሰላም ሚኒስቴር መ/ቤትና የሰላም ኮሚሽን ተቋቁሞልናል። የሰላም ርግብ ግን ዛሬም ከአፏ የወደቀውን ዘንባባ አንስታ በሃሴት ለመዘመር አቅም አላገኘችም።
መጪዎቹ 100 ዓመታትም እንዲሁ እንዳይቀጥሉ ስጋት ገብቶኛል። የሰላምን ርግብ እያሳደዱ ለማቁሰልና ለመግደል የሚሞክሩ ባለ ሙት ህሊና ዜጎችና “እኛ ብቻ” ባዮች መቶ ዓመታትን ወደፊት እያዩ የጥፋታቸውን ፈረስ እንዲገቱ መልዕክቴ ይድረሳቸው እላለሁ። ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለሕዝቧ! ሰላም ለተፈጥሮ! ሰላም! ሰላም! ሰላም! በሁከትና በማወክ ለሰለጠነ አእምሮ። አሜን ሰላም ይሁን።
(በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)