የዘንድሮው መስከረም ወር ታላላቅ በዓላትን የሚያስተናግድ ነው። መስከረም 17 የመስቀል በዓል፣ መስከረም 24 ቀን ደግሞ ከ150 ዓመታት በኋላ የእሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበርበት ነው። በዓላቱ በዩኔስኮ የተመዘገቡና የቱሪዝም መስህብ ሲሆኑ፤ የዓለም የቱሪዝም ቀን እንዲሁ መስከረም 17 ቀን 2012 የሚከበር መሆኑ በዓላቱን ድርብ ድርብርብ ያደርጋቸዋል።
የመስቀል በዓል ታሪካዊ አመጣጥ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ህሙማንን በመፈወሱ ምክንያት በርካታ አሕዛብ ክርስቲያን እንዲሆኑ አስችሏል። በተአምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑና ይህን የተመለከቱ አይሁዶች ቅዱስ መስቀሉን በአንድ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ እንዲቀበር አደረጉ። የአካባቢው ነዋሪዎች በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚጥሉበት ቦታው ወደ ተራራነት ተቀየረ። ምንም እንኳን መስቀሉን ለማውጣት ባይችሉም በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን ያውቁት ነበር። በሰባ ዓመተ ምሕረት በጥጦስ ወረራ ኢየሩሳሌም ስለጠፋች በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ተሰደዱ። የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቅ ባለመገኘቱ መስቀሉ ከ300 ዓመታት በላይ ተዳፍኖ (ተቀብሮ) ኖረ።
በ326 ዓ.ም. የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ቅዱስ መስቀሉን ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ አደረገች። እዚያም ደርሳ ጉብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍር መስቀሉ ያለበትን ቦታ ማግኘት አልቻለችም፤ ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅ አልተገኘም። በመጨረሻም የመስቀሉ መገኘት የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበርና አንድ ይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ አግኝታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትንና የተጣለበትን አካባቢ ያውቅ ዘንድ ጠየቀችው። ሽማግሌውም “አንቺም በከንቱ አትድከሚ ሰውንም አታድክሚ እንጨት አሰብስበሽ ዕጣን አፍሽበት በእሳትም አያይዢው የዕጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው በዚህ ምልክት ታገኚዋለሽ” አላት። እርሷም ያላትን ሁሉ አደረገች። እንጨት ደምራ በዚያ ላይም ዕጣን ጨምራ በእሳት ለኮሰችው፤ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያህል አመለከተ። ንግሥት ዕሌኒም ጢሱ ያረፈበት ቦታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበት እንደሆነ አመነች። ይህ ይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ በኋላ በክርስቶስ አምኖ ተጠምቋል፤ ስሙም ኪርያኮስ ተብሏል።
በዚህም መሠረት ከመስከረም 17 ቀን አስጀምራ እስከ መጋቢት 10 ቀን ሌሊትና ቀን ለሰባት ወራት ያህል የጉድፍን ኮረብታ ቆፍረው ቆሻሻውንም ካስወገዱ በኋላ ሦስት መስቀሎች ተገኙ። የጌታም መስቀል ሙት በማስነሣቱ ተለይቶ ታውቋል። መስቀሉ የተገኘው መጋቢት 10 ቀን 326 ዓ. ም ነበር። ቅድስት ዕሌኒ ይህን ተአምር በማየቷ እጅግ ደስ አላት። ሕዝቡም ሁሉ መስቀሉን እየዳሰሱ ኪርያላይሶ እያሉም በመዘመር ደስታና ሐሴት አደረጉ። ቀኑ መሽቶ ጨለማ በሆነ ጊዜም የኢየሩሳሌም ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስና ንግሥት ዕሌኒ፣ ሠራዊቱና ሕዝቡ በሰልፍ በችቦ መብራት መዝሙር እየዘመሩ ቅዱስ መስቀሉን ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደው በአንድ የጸሎት ቤት አኖሩት። በኋላም በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዕብነ መሠረት ወይም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ለመስቀሉ መታሰቢያ ቤተክርስቲያን ተሠርቶ (ቅዳሴ ቤቱ) ተመርቆ የገባው መስከረም 17 ቀን 327 ዓ.ም ነው። በቤተ ክርስቲያን ሁለቱም ዕለታት ይከበራሉ፤ በደማቅ ሁኔታና በመጀመሪያ ደረጃ የሚከበረው ግን መስከረም 17 ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት መጋቢት 10 ቀን ሁልጊዜም በዐቢይ ጾም ወቅት የሚውል መሆኑና ለመስቀሉ የተሠራው ቤተ መቅደስ የገባው መስከረም 17 በመሆኑ ነው።
ይህ ዕለት ከ300 ዓመታት በላይ ጠፍቶ የነበረውን ቅዱስ መስቀል በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት መገኘቱን የምንዘክርበት በዚህም ደስ የምንሰኝበት ዕለት ነው። ይህን መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ደመራ በመደመር የመስቀል በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል።
የደመራ ትርጉም
ደመራ የሚለው ቃል – ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን፤ መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትን እና ኅብረትን ያመለክታል። ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው ዘጠኙ የጌታችን ንዑሳን በዓላት አንዱ በዓል ነው። መስቀል የሰላማችንና የደኅንነታችን የመቀደሳችን ዓርማ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን፥ የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት መስዋዕትነት የከፈለበት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት መንበር ሲሆን፤ አምላካችንን የምንመለከትበት መስታወት ነው።
በሀገራችን በኢትዮጵያ የመስቀልን በዓል ደመራ በመደመርና ችቦ በማብራት፥ ቅዳሴ በመቀደስና ማኅሌት በመቆም የምናከብረው ለዚህ ነው። በዚሁም ላይ ይህን ታላቅ ዕፀ መስቀል በወቅቱ የነበሩ ታላላቅ ነገሥታት የሚያደርጓቸውን ተዓምራት በማየት ለእያንዳንዳቸው ይደርሳቸው ዘንድ ከአራት ክፍል ሲከፍሉት ከአራቱ አንዱ የቀኝ እጁ ያረፈበት ግማድ (ክፋይ) ብቻ በደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም ሲገኝ ሌሎች ሦስቱ ግን የት እንደደረሱ አይታወቅም።
የኢሬቻ ክብረበዓል
አዲስ አበባ መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም የኢሬቻ በዓልን ታስተናግዳለች። “ሆራ ፊንፊኔ” የኢሬቻ በዓልን በአዲስ አበባ ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ሰሞኑን የኦሮሚያ አባ ገዳዎች ህብረትና የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ማስታወቃቸውም የሚዘነጋ አይደለም።
የመጀመሪያው የክረምት መውጣትን ተከትሎ በውሃማ አካባቢዎች የሚከበር ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በበልግ ወቅት በተራራማ አካባቢዎች ይከበራል።
ጥቂት ሐሳብ ስለኢሬቻ በዓል
የኢትዮጵያ 13 ወራት መባቻ መስከረምን ከሚያደምቁ በዓላት አንዱ ኢሬቻ ነው። በዚህ ወቅት የሚከበሩ ኢሬቻና ሌሎችም በዓላት ጭጋጋማውን ክረምት አልፎ ወደ በጋ መሸጋገርን መነሻ ያደረጉ ናቸው። ከዘመን ዘመን መሸጋገርን፣ ብርሃን ማየትን፣ ልምላሜን ያሞግሳሉ። በበዓላቱ አዲስ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የብልጽግና እንዲሆን ምኞቶች ይስተጋባሉ። ለፈጣሪም ምስጋና ይደርሳል። ከበዓላቱ አንዱ የሆነው ኢሬቻም ተመሳሳይ ድባብ አለው።
ኢሬቻ ከክረምት ወደ ብራ መውጣትን ምክንያት በማድረግ የሚቀርብ ምስጋና ነው። የሚሞገሰው ልምላሜ ነውና ለምለም ቄጠማና አደይ አበባ የበዓሉ ልዩ መገለጫ ናቸው። የበዓሉ ታዳሚዎች ከኦሮሞ ባህላዊ አልባሳቶቻቸው በተጨማሪ ቄጠማና አደይ አበባ ይዘው ይታያሉ። ፈጣሪን እያወደሱ መልካሙን ሁሉ ይመኛሉ። በየዓመቱ በወርሐ መስከረም በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ (ሐይቅ) ዳርቻ የሚከበረው ኢሬቻ በእንስቶች ‹‹መሬ ሆ…›› ዜማ ማልዶ ይጀመራል።
ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለበዓሉ በቢሾፍቱ የከተሙ ሰዎች በባህላዊ ዜማ ታጅበው ወደ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ ይተምማሉ። የአባ ገዳና የዕድሜ ባለፀጎች ምርቃት በማኅረሰቡ ዘንድ ልዩ ቦታ ይሰጠዋል። የተወለዱ እንዲያድጉ፣ የተዘራ እንዲበቅል፣ አገር ሰላም እንዲሆን ሲመርቁ ታዳሚዎች በኦሮምኛ ‹‹ያታኡ›› ማለትም ይሁን ይላሉ።
ከማለዳ አንስቶ ረፋድ ድረስ ልዩ ልዩ ኅብረ ዝማሬዎች በሐይቁ ዙሪያ ይስተጋባሉ። በኢሬቻ ከአባ ገዳዎች ምርቃት በመቀበል የሚጀመር ትዳር መልካም እንደሚሆን ስለሚታመን ጥንዶችም በቦታው ይገኛሉ። የኦሮሞን ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች ገበያ እንዲሁም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የታሪክ መጻሕፍት ሽያጭም የበዓሉ ገጽታ ናቸው።
ከጥንት ሲወርድ ሲወራረድ የመጣው ኢሬቻ ከማኅበረሰቡ ክብረ በዓሎች አንዱ ነው። ኢሬቻ እርጥብ ሣር፣ ቅጠል፣ ቄጠማ፣ አበባ ማለት እንደሆነ አባ ገዳዎች ይናገራሉ። ‹‹13ቱን ወር በሰላም ያስጨረስከን ፈጣሪ፣ ለመጪው ዓመት በሰላም አድርሰን። ለሰው ልጅና ለሁሉም ፍጥረት ብለህ አጥርተህ የፈጠርከው ሐይቅ ላይ ምሥጋና እናቀርባለን። ውሃ ንፁህ ነውና፤›› ይባላል።
በኢሬቻ ሣሩን አበባውን ያበቀለ ፈጣሪ ለሰው ልጆች ዘርና ፍሬ በመስጠቱም ይመሰገናል። በክረምት መልካው፣ ወንዙ ሞልቶ ዘመድ ከዘመዱ፣ ወዳጅ ከጓደኛው ሳያጠያይቅ ከርሞ በበጋ ውሃው ጎድሎ በመገናኘቱም ውዳሴ ይቀርባል። በኢሬቻ በዓል ምርቃት የሚሰጥበት ቦታ ‹‹ድሬ›› ይባላል። የተስተካከለ ቦታ እንደማለት ሲሆን፣ በቦታው ምርቃት ካልተከናወነ ወደ ሐይቁ አይሄድም።
ወደ መልካው ሲኬድ ዳለቻ ኮርማ ታርዶ፣ ‹‹እንኳን በሰላም ከክረምቱ ወደ ብርሃኑ አመጣኸን። ዘመኑን የሰላም አድርግልን። ሕዝቡና አገሪቱን ይባርክልን፤›› ይባላል። የበዓሉ አክባሪዎች የያዙትን ለምለም ቅጠል፣ ቄጠማ፣ ርጥብ ሣርና አደይ አበባ ሐይቁ ውስጥ እየነከሩ ይረጫሉ፤ ሰውነታቸውን ያስነካሉ፤ በሐይቁ ዳርቻም ያስቀምጡታል። በሥርዓቱ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞችና የዋቄ ፈታ ተከታዮችም ይካፈላሉ። ዝማሬ፣ ምርቃትና ሌሎችም ሥርዓቶች በዋርካው ‹‹ኦዳ›› ሥር ይከናወናሉ።
ኢሬቻ እርቅ ማለት ስለሆነና የሰላምና ፍቅር ዐውደ ዓመት በመሆኑም በማኅበረሰቡ መካከል ያለመከፋፈል ይከበራል። መስከረም ከጠባ በኋላ በዓይነ ሥጋ ለመተያየት የበቁ ወዳጅ ዘመዶች ‹‹እኛ ደርሰናል፤ እናንተ ደረሳችሁ?›› ይባባላሉ። በበዓሉ የተጣሉ ይታረቃሉ። የበደሉም ይቅርታ ይጠይቃሉ። የተለያየ ሃይማኖት የሚከተሉ የማኅበረሰቡ ተወላጆች በዓሉን በጋራ የሚያከብሩትም ለዚሁ ነው።
“የኢሬቻ በአል ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው ነው”
ኢሬቻ ማለት ማምለክ እና ማመስገን ማለት ነው። ይሄን ስላደረግህልኝ፣ ከክረምት ወደ በጋ (ብራ) ስላሸጋገርከኝ አመሠግናለሁ እየተባለ ፈጣሪ የሚመሰገንበት ነው። ኢሬቻ ሠፊ አገልግሎቶች አሉት። መነሻውም በጣም የራቀ ነው። ሰው ማምለክ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የመጣ ነው። መጀመሪያ እንደውም አምልኮ የተጀመረው በኢሬቻ ነው። በተለይ የኦሮሞን ብሔር ጨምሮ በኩሽቲክ የቋንቋ ክፍል ውስጥ የሚጠቃለሉ ብሔሮች ሃይማኖቶች ከመምጣታቸው በፊት ኢሬቻ (እርጥብ ሣር) ይዘው ነው ፈጣሪያቸውን የሚለማመኑት። ኢሬቻ በእርጥብ ሣር ይወከላል።
ለጋብቻ ጥያቄ በራሱ (ኢሬቻ) እርጥብ ሣር አገልግል ውስጥ ተጨምሮ ነው የሚላከው። እንግዲህ እነዚህን ነገሮች በምናይበት ጊዜ ኢሬቻ ሃይማኖታዊ ዳራ ያለው መሆኑን እንገነዘባለን። ድሮ ሰዎች መልዕክተኛ ሲልኩ እርጥብ ሣር ቆርጠው በመስጠት፣ “አደራህን በፈጣሪ ስም ይህን መልዕክት አድርስልኝ” ብለው ይልኩታል። እንግዲህ ቃል በቃል ሲገለፅ፤ ኢሬቻ ሣር ወይም የተመረጡ ዛፎች ቅጠል ማለት ነው።
ኢሬቻ በዓመት ሁለት ጊዜ ነው የሚደረገው የመጀመሪያው ከነሐሴ መጨረሻ ጀምሮ እስከ ጥቅምት መጨረሻ ይካሄዳል፤ ሁለተኛው ደግሞ በበልግ ወራቶች ግንቦትና ሰኔ ውስጥ የሚደረግ ነው። ሁለተኛው ግን አሁን እየተረሣና እየተዳከመ ነው ያለው። ሰዎች መገንዘብ ያለባቸው ኢሬቻ ሃይማኖት አይደለም፤ ነገር ግን ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው። ለምሣሌ መስቀል ሃይማኖታዊ በዓል ነው እንጂ ሃይማኖት አይደለም። ኢሬቻም እንዲሁ ነው።
እምነቱ ምንድን ነው?
የሃይማኖቱ ስም ዋቄፈና ነው። የእምነቱ ተከታይ ዋቄፈታ ነው የሚባለው። ከዋቄፈና ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ ኢሬቻ ነው፤ ሌሎችም ብዙ በአላት አሉ። ሌላው ከዚህ ሃይማኖታዊ በዓል ጋር በልማድ አብሮ ተቀላቅሎ የሚከወን ነገር አለ። ለምሣሌ ቡና ማፍላት፣ ዛፍ ቅቤ መቀባት፣ ስለት ማግባት፣ ሽቶ ውሃ ውስጥ መወርወር የመሣሰሉ አሉ። እነዚህ ሁሉ ልማዶች ናቸው እንጂ የሃይማኖቱ መርሆች የሚያዛቸው አይደሉም። ቅቤ መቀባት ግን “ሙዳ” ከሚባለው ሥርዓት ጋር ይያያዛል። አንድ ንጉሥ ሣይቀባ እንደማይነግሥ ሁሉ አንድ የማምለኪያ ቦታም ተቀብቶ እውቅና ሊያገኝ ይገባዋል። ነገር ግን አሁን እየተደረገ እንዳለው በየጊዜው ሣይሆን አንድ ጊዜ ብቻ ነው ይህ ሥርዓት ተፈፃሚ የሚሆነው። አንድ ንጉሥ በየጊዜው እንደማይቀባ ሁሉ አንድ የተመረጠ የማምለኪያ ስፍራም በየጊዜው ሊቀባ አይገባም። ቀቢውም ማንኛውም ሰው ሣይሆን የተመረጠ መሆን አለበት።
እንደማጠቃለያ
የኢትዮጵያው የመስቀል ክብረ በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ኅዳር 25 ቀን 2006 ይፋ ሆነ። በተመሳሳይ ሁኔታ የገዳ ሥርዓት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ግዙፍነት በሌላቸው ባህላዊ ቅርሶች ወካይ መዝገብ (ሪፕረዘንታቲቭ ሊስት ኦፍ ዘ ኢንታንጀብል ካልቸር ኦፍ ሂውማኒቲ) መስፈሩ ይፋ የተደረገው ኅዳር 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር። በገዳ ሥርዓት ውስጥ የሚካተቱት እንደ ኢሬቻ፣ ጉዲፈቻ፣ ዋቄፈና ሲንቄ የሚባሉት ሥርዓቶች መሆናቸው ይታወቃል።
የመስቀል በዓል እና የኢሬቻ በዓል ታላላቅ ሕዝባዊ በዓላት ናቸው። በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ከማንም በላይ ሕዝቡ ሲቀጥል መንግሥት ኃላፊነት አለባቸው።(ማጣቀሻዎች፡- አዲስ ዘመን፣ አዲስ አድማስ፣ ሪፖርተር ጋዜጦች፣ አምደተዋህዶ ድረ ገጽ…. ናቸው)
(ፍሬው አበበ)