አዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ.ም ይዞት የወጣው ዜና በርካቶችን አስገርሟል። ዜናው ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በየወሩ ሳይቆራረጥ ከእጃቸው የሚገባ አስራ ስምንት ሺ ብር የቤት ኪራይ አበል እንዲከፈላቸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መወሰኑን ይገልፃል። ከነሐሴ አንድ ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደተደረገ የተገለፀው መመሪያ ሚኒስትር፣ ሚኒስትር ዴኤታ ፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ኮሚሽነርና ምክትል ኮሚሽነር፣ ዋና ዳይሬክተር እና ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤና ምክትል አፈ ጉባኤ እንዲሁም በእነዚህ ደረጃ የተሾሙ የበላይ ኃላፊዎች በጥቅማ ጥቅሙ ይካተታሉ ይላል።
በበኩሌ ጥቅማ ጥቅሙ እነማንን እንደሚመለከት የሚዘረዝረው የመመሪያው ክፍል ውስን የሥልጣን እርከኖችን ከጠቀሰ በኋላ “በእነዚህ ደረጃ የተሾሙ የበላይ ኃላፊዎች” በሚል ሐረግ መቋጨቱ አልጣመኝም። እንዲህ ያለ ድፍን አገላለጽ አስፈፃሚው አካል በፖለቲካዊ ውሳኔ የአገርን ሀብት ላሻው ወገን እንዲያድል በር ይከፍታል። ውሳኔው ሲተላለፍ የሚመለከታቸው አካላት በቀጥታ መጠቀስ ነበረባቸው። በእርግጥ የብሔር ተዋጽኦን ለመጠበቅና የተሻለ ደመዎዝና ጥቅማ ጥቅም ለመስጠት ሲባል በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ፣ በሚንስትር ማዕረግ፣ በሚንስትር ዲኤታ ማዕረግ ብሎም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ እየተባለ ለአማካሪና ለቢሮ ኃላፊ ሹመት በሚሰጥባት አገር የጥቅማ ጥቅሙን ተቋዳሾች ቁጥር በውል ማወቅ አስቸጋሪ ነው።
ወላጆች ይህን ዜና ካደመጡ በኋላ ህጻናት ልጆቻቸው የወደፊት ምኞታቸውን እንዲቀይሩ የሚጫኗቸው ይመስለኛል። በዚህ ምክንያት ልጆች “ወደፊት ምን መሆን ትፈልጋላችሁ?” ተብለው ሲጠየቁ በዶክተርና በፓይለት ምትክ “ባለሥልጣን” ማለት መጀመራቸው አይቀሬ ነው።
ጥቅማጥቅሙ ከሌሎች አፍሪካ አገራት አንፃር አነስተኛ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። የመንግሥት ባለሥልጣናት ደመዎዝና ጥቅማጥቅም መነፃፀር ያለበት ከአገሪቱ ምጣኔ ሀብትና ከህዝቡ አኗኗር ጋር ነው። በስመ አፍሪካ ኬኒያን፣ ናይጄሪያንና ደቡብ አፍሪካን ከመሰሉ ከኢትዮጵያ የተሻለ ኢኮኖሚ ካላቸው አገራት ጋር መወዳደር የለበትም። መንግሥት እንደ አገሩ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም።
አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ የሚያገኘው ወርሐዊ ደመዎዝ ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የቤት ኪራይ አበል የተመደበውን ገንዘብ ዕሩብ ነው። ውሳኔውን ከመቀበል ውጭ ምን ምርጫ አለን ?
ባለሥልጣናቱ በ18 ሺ ብር የሚከራዩትን ቤት በዕዝነ ልቦናዬ ስስለው መጠነኛ አዳራሽ የሚኖረው ይመስለኛል። አዳራሹን በሥራቸው ካሉ ሠራተኞች ጋር ለመሰብሰብና የሚመሯቸውን ኮሚቴዎች የሥራ እንቅስቃሴ ለመገምገም ይገለገሉበታል። ድራጎን የሚያስጋልበው ሳሎን ደግሞ በቀይ ምንጣፍ ተውቦ ባለሥልጣናቱ የውጭ አገራት ዲፕሎማቶችን፣ ኢንቨስተሮችንና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች አመራሮችን ተቀብለው በቤታቸው ውስጥ እንዲነጋገሩ የሚያስችል ነው። ይህም ወደ ቢሮ በመመላለስ የሚባክነውን ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ በማዋል ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። መጠነኛ የመዋኛ ገንዳ ያለው በአረንጓዴ ዕጽዋት የተዋበ ግቢም ምክንያት እየፈለጉ ከአገር በመውጣት በሚያገኙት የውሎ አበል ዘና ፈታ የሚሉትን ባለሥልጣናት አንቆ በመያዝ አገሪቱ በገፍ የምታወጣውን የውሎ አበል ይታደጋል።
መንግሥት ለባለሥልጣናት ከሚያቀ ርበው ቤት ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ ለሐሜት ተዳርጓል። ከዓመታት በፊት ጡረታ ለሚወጡ ስድስት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለእያንዳንዳቸው በ25 ሚሊየን ብር ወጪ ቅንጡ ቤቶች እየተገነቡላቸው መሆኑን መነገሩ ከፍ ያለ አቧራ አስነስቶ ነበር። ለቀድሞው ፕሬዚዳንት የመኖሪያ ቤት ኪራይ በየወሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር ፈሰስ ይደረጋል እየተባለም ብዙ ጉርምርምታዎች ይሰሙ ነበር። አሁን ደግሞ በተወረሱና በኪራይ ህንጻዎች አገልግሎት በሚሰጡ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ለሚሠሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት 18 ሺ ብር ወርሐዊ የቤት ኪራይ አበል መመደቡ ያስተዛዝባል። በ “4 ሺ 600 ብር” ደመዎዝ ብቻ 21 ዓመት ሙሉ አገር ያስተዳደሩት “ታላቁ መሪ” ለአፍታ ቀና ብለው ይህን ጉድ ቢመለከቱ እንደ ከዚህ ቀደሙ ባልሆነ ድምፀት “ራዕዬስ ? … ሌጋሲዬስ ?” ብለው የሚጠይቁ ይመስለኛል።
ለ 80 የፌደራል ተቋማት ቢሮ ኪራይ በዓመት አንድ ቢሊየን ብር ገደማ ወጪ በማድረግ አብዛኛዎቹን ሥራዎቹን በኪራይ ቤት የሚያከናውን መንግሥት ለተቋማቱ ህንጻ በመገንባት ፈንታ ለከፍተኛ ባለሥልጣናት መኖሪያ ቤት ይህን ያህል በጀት መመደቡ ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ ያሰኛል። ዶክተር ምህረት ደበበ በአንድ መድረክ “ችግር ሲያስቸግረን ነው መፍትሄ የምንፈጥረው ከተመቸን ግን አብረነው እንከርማለን” እንዳሉት፣ ችግሩ እስካሁን ድረስ የዘለቀው ለአንዳንዶች ስለተመቸ ነው። ችግሩን ተጠቅመው ህንጻ ከሚያከራዩ ባለሀብቶች ጋር ያልተገባ ግንኙነት ፈጥረው ባቋራጭ ከሀብት ጋር የተገናኙ ብዙዎች ናቸው።
የቀድሞ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በቢሮ ጥበት ምክንያት ተጨማሪ ህንጻ ተከራይቶ በዓመት ዘጠኝ ሚሊየን ብር ይከፍል ነበር። በየተቋሙ መሰል ወጪ ከሚወጣ የመንግሥት ሠራተኞችም እንደ ፋብሪካ ሠራተኞች በሽፍት ቢሠሩ ይሻላል፤ ሲጨልም የሚጨልምባት አገርም ህይወት ትዘራለች። ይህን ሐሳቤን እንዳትንቁት ! በቅርቡ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊው የከባድ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት እንዲሆን የተወሰነበት አንዱ አብይ ምክንያት ከተማዋ በሌሊትም እስትንፋስ እንዲኖራት ተፈልጎ ነው ማለታቸው ልብ ይባልልኝ።
እርግጥ ነው የመንግሥት ሥራን ሌሊት መሥራት ማለት በብርሃን መቆጣጠር ላልቻልነው ሌብነት የይለፍ ካርድ መስጠት ነው። ነገር ግን ለሌብነት ተጋላጭ በሆኑ የሥራ መደቦች ላይ የሚሠሩ ሠራተኞችን ዘጠኝ ገቢና አዳሪ ከመመደብ ይልቅ ጀነራል ሽፍት ማድረግ ፍቱን መፍትሄ ይሆናል። ምን ይላል ይሄ … አትበሉኝ … ዋናው ችግር ቸል ተብሎ ለከፍተኛ ባለሥልጣናቱ የቤት ኪራይ አበል ትኩረት መሰጠቱ ቢያማርረኝ መላ መምታቴ ነው።
አሊያም ደግሞ በተለምዶ የአርከበ የሚባሉት ሱቆች ስድስትና ሰባት ሺ ብር በሚከራዩበት ዘመን የከተማው እንብርት ላይ የሚገኙ ግዙፍ ህንጻዎችን በንጉሡ ዘመን ዋጋ የሚያከራየው የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚያስተዳድራቸው ህንጻዎች የግለሰቦች መበልፀጊያ ከሚሆኑ ለመንግሥት ተቋማት አገልግሎት መስጫነት ቢውሉ ችግሩን ያቃልላሉ። ይህን ስል እንደ አንገብጋቢነቱ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠውም እንጂ ጉዳዩ ጨርሶ መንግሥትን አያሳስበውም ማለቴ አይደለም። ከረፈደም ቢሆን አንዳንድ የፌዴራል ተቋማት የራሳቸው ህንጻ እንዲኖራቸው ታስቦ ግንባታ መጀመሩ መልካም ነው።
የትናየት ፈሩ