አንድ አባት ዓውደ ምህረት ላይ ቆመው እያስተማሩ ናቸው። የትምህርቱ ርዕስ ስለ አስራት ነው። ክርስቲያን ሁሉ አስራት ማውጣት አለባችሁ እያሉ ያስተምራሉ። አንድ ክርስቲያን አስራት የሚያወጣው ከገቢው ላይ ከአስር አንድ ነው። አስራቱን ማውጣት ያለበት በገንዘብ ብቻ አይደለም፤የጊዜም አስራት አለ። የኪዳን ሰዓት፣ የቅዳሴ ሰዓት፣ ሰንበት… የስጋ ሰዓት አይደለም፤ ይሄ ሰዓት ለነፍስ ስራ የምናውለው መሆን አለበት እያሉ በሰፊው ያስተምራሉ።
በዚህ አላበቁም‹‹የነፍስንም ሆነ የስጋን ተግባር ለመፈፀም የሚቻለው የእግዚአብሄርን ለእግዚአብሄር የቄሳርን ለቄሳር ማድረግ ሲቻል ነው›› አሉ። ለመንግስትም አስራት(ግብር) ይከፈላል ሲሉ ቀጠሉ። እያንዳንዱ ሰው ከገቢው ላይ ለመንግስት ግብር/ታክስ መክፈል አለበት። መንግስትም በራሱ ህግና ደንብ መሰረት ከእያንዳንዱ ሰው እና ድርጅት የገቢ ግብር ይሰበስባል። ከነጋዴው፣ ከመንግስት ሰራተኛው፣ ከግል ድርጅቶች፣ ከቤት አከራይ… ብቻ ከሚያገኘው ገቢ ባስቀመጠው ህግ መሰረት ያንን ግብር ገቢ ያደርጋል። ይሄ ደግሞ የስጋችን ነው።ለሀገር ልማት ይውላል። ስለዚህ ሁላችንም የሚጠበቅብንን ግብር በወቅቱ መክፈል አለብን።በመንፈሳዊም በአለማዊም ይሄንን በትክክል ስንከፍል ነው ሀቀኛ የምንሆነው። የእኛ ያልሆነን ገንዘብ ገንዘባችን ብለን ልንጠቀምበት አይገባም፤መጽሀፉም ‹‹…የቄሳርን ለቄሳር›› ይላል አሉ።
እውነት ነው። ግብር መክፈል የውዴታ ግዴታ ነው። ግዴታውን ተወጥቶ መብቱን የሚጠይቅ ማህበረሰብ መፍጠር ያስፈልጋል። ሆኖም ግን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በሀቀኝነት በትክክል ግብር እየከፈለ ያለው የመንግስት ሰራተኛ ብቻ ነው ለማለት ያስደፍራል። የመንግስት ሰራተኛው የሚያገኘው ገቢ ይታወቃል፤ ገቢውም በእጁ ከመግባቱ በፊት ተቀንሶ ወደ መንግስት ካዝና ገቢ ስለሚደረግ የግብር ስወራም ሆነ ማጭበርበር አይኖርም።
ከመንግስት ሰራተኛው ውጪ ያለውን ግብር ከፋይ ግን ሙሉ ለሙሉ ብሎ ለመድፈር በሚያስችል መልኩ ግብርና ታክስ የመክፈል ግዴታውን እየተወጣ አይደለም።ይሄም በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ካቀደችውም በላይ በጀቷን ከብድር ለመሸፈን ተገድዳለች።
ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2007 ዓ.ም የግብር ገቢ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ዓመታዊ ምርት 13ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ ነበረው። በ2012 ደግሞ ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ ለማሳደግ ነው ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ያለው።ይሁን እንጂ አሁን ባለው ሁኔታ ይሄንን ዕቅድ ማሳካት ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።ምክንያቱም እያንዳንዱ ግብር ከፋይ ያለበትን የሚጠበቅበትን የግብር ገቢ በትክክልና በወቅቱ እየከፈለ አይደለም። ለምሳሌ ያህል በ2010 በጀት ዓመት 230 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታስቦ የተሰበሰበው ግን 176 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው።በ2009 በጀት አመት ሳይሰበሰብ ከቀረው ጋር ተደምሮ በአጠቃላይ 70 ቢሊዮን ብር አልተሰበሰበም።ይሄ ገንዘብ ተሰብስቦ ቢሆን ኖሮ እንደ ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉ 10 ፓርኮችን መገንባት ያስችል ነበር።
እንዲሁም በ2011 በጀት አመት ከአገር ውስጥ ገቢ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚሰበሰብ የታሰበው ገቢ 28.8 ቢሊዮን ብር ሲሆን የተሰበሰበው 25.62 ቢሊዮን ብር ነው። በሦስት ወራት ያልተሰበሰበው 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ግብር፣ ከጉምሩክና ተያያዥ አገልግሎቶች ደግሞ ከ6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡በአጠቃላይ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ በሩብ አመቱ አልተሰበሰበም።
ይሄ የሚያሳየው መሰብሰብ ያለበት እኛም መክፈል የሚገባን ገንዘብ በግለሰቦች ኪስ ማድለቢያ እየሆነ መሆኑን ነው። ይሄ አንድም የግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት ስራውን በአግባቡ አለመወጣቱን የሚያሳይ ሲሆን ግብርን በወቅቱ በሀቅ አለመክፈል፣ ማጭበርበር፣ የተደራጀ ሌብነት እና ገቢን መሰወር ደግሞ በግብር ከፋዩ በኩል የነበረ ድክመት መሆኑን መናገር ይቻላል።ስለዚህ የቄሳርን ለቄሳር ነውና ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡
ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ታክስ 17 ነጥብ 2 በመቶ ማድረስ ቢቻል ሀገሪቱ የሚኖራት የበጀት ጉድለት ሶስት በመቶ እና የብድር ፍላጎት 93 ቢሊዮን ብር ብቻ ይሆናል። ነገር ግን አሁንም ባለበት መልኩ የሚቀጥል ከሆነ ግን የበጀት ጉድለታችን እና የብድር ፍላጎታችን ከተቀመጠው በላይ ይሆናል።ይሄም ደግሞ አገሪቱን በ2025 ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ለማስገባት የተያዘውን ዕቅድም ለማሳካት አዳጋች ይሆናል። በመሆኑን እያንዳንዱ ግብር ከፋይ የሚጠበቅበትን ግብር በታማኝነት በመክፈል የዜግነት ግዴታውን መወጣት ይጠበቅበታል። ግዴታን ተወጥቶ መብትን መጠየቅ ደግሞ የስልጣኔ አንዱ መገለጫ ነው።ይሄንን በመረዳት ጭምር በመፅሀፉም እንደሰፈረው የቄሳርን ለቄሳር ማድረግ ይገባል።
አደስ ዘመን ታህሳስ 13/2011