የምርምርና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና አጠባበቅ በቴክኖሎጂ የተጋዘ አለመሆን እንዲሁም ዘመናዊ የግብርና አሠራር በፍጥነት አለመተግበር ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ማረጋገጥ እንዳትችል ፈተና ሆኖባታል፡፡
የግብርና ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አበራ ዴሬሳ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት ፈተና የበዛበት እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በያዘችው አካሄድ በመጓዛቸው በርካታ አገራት ችግር ውስጥ ገብተው እንደነበር የሚገልፁት ዶክተር አበራ፤ አሁን የሚስተዋለው የአየር ንብረት ለውጥ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ መፍጠሩን ያስረዳሉ፡፡
የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም አለመዘመን፣ የተፈጥሮ ሀብትን ከሚገባ በላይ መጠቀምና እንክብካቤ ማጣት ለአብነት የሃሮማያ ሃይቅ መጥፋት፣ የአብጃታና ሌሎች ሃይቆች መመናመንን ዓይነት ችግር ስለሚያስከትል ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ አዳጋች መሆኑን ዶክተር አበራ ያብራራሉ፡፡
«ባለሙያዎች በአርሶ አደሩ መንደር ምርምር የሚያካሂዱበት፣ ምርታማነት የሚጎለብትበትና የተፈጥሮ ሀብት የሚጠበቅበት ሥራ አልተሰራም፡፡ መንግሥት፣ ግብረሰናይ ድርጅቶችና ተመራማሪዎችም የተፈጥሮን ልገሳ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚጠበቅባቸውን ሰርተዋል የሚል እምነትም የለኝም» ሲሉ ዶክተር አበራ ይገልፃሉ፡፡
የአፈር በአሲዳማነትና ጨዋማነት መጎዳት የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ መጠቀም አለመቻል፣ አፈሩ ውስጥ ያለውን የአሲዳማነት መጠን ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት በቂ አለመሆን፣ ችግሩን ለማቃለልም የምርምር ሥራዎች በአግባቡ ተግባራዊ ያለመሆናቸው ምርታማ የመሆን ፈተና እንደሆነ ዶክተር አበራ ያስረዳሉ፡፡
እንደ ዶክተር አበራ ገለፃ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ያለመጠቀም፣ የደን መመናመንና የምርታማነት መቀነስ ችግሩ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለምን ከፍተኛ ስጋት ላይ የጣለ ሆኗል፡፡ የህዝብ ቁጥር መብዛት፣ የተፈጥሮ ሃብት አለመመጣጠና ሰፊ የእርሻ መሬት የመፈለጉ ሁኔታ ለአገሪቱ ተግዳሮት፤ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም አዳጋች ነው፡፡
የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠቀም አኳያ በአግባቡ ባለማስኬዳቸው ከፍተኛ ፈተና ውስጥ የገቡ አገራት ፊንላንድ ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ብራዚልና ህንድ በአፈር አሲዳማነት ተቸግረው እንደነበር ይናገራሉ። አሁን የተፈጥሮ ሀብትን መልሶ በማዳንና አፈሩን በማከም ከችግር ማምለጣቸውን ይጠቅሳሉ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ፈታኝ በመሆኑ በዚህ መንገድ የሚቀጥል ከሆነ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ችግር ውስጥ እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡
የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢስሞ በበኩላቸው፤ አገሪቱ ውስጥ በቀጣይ ድርቅ የሚከሰትባቸው አጋጣሚዎች በርካታ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡ የአፈር አሲዳማነትን ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት አለመደረጉና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም አለመዘመኑ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተሰጠው ምርታማነት መቶ በመቶ ሊቀንስ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡
«ሰፊ መሬት በነበረን ወቅት የእርሻ መሬት እንዳይጎዳ እስኪያገግም ድረስ ሌላ መሬት ይታረስ ነበር፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር በመኖሩ፤ በቀድሞው ሁኔታ ማስኬድ ከባድ ሆኗል፡፡ በየዓመቱ በአሲዳማነት የሚጠቃው መሬት ምርትን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ ሲሆን፤ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ከባድ ያደርገዋል» ይላሉ ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የግብርና ውጤቶችን ወደ ውጭ በመላክ የሚገኘው ዓመታዊ ገቢ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ እነዚህ ምርቶች ወደ ውጭ ቢላኩም ከፍተኛ መጠን ያለው የግብርና ውጤቶች ከውጭ በከፍተኛ ምንዛሪ ይሸመታሉ፡፡ ለአብነትም ዘይት፣ ሩዝ፤ ስንዴና ሌሎችንም የግብርና ውጤቶች ኢትዮጵያ በሰፊው ከውጭ ትገዛለች፡፡ ይሁንና የግብርና ውጤቶችን ሸጦ የግብርና ውጤቶች መግዛት ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
የአገሪቱ መልክዓምድር ከውጭ ለሚገዙት ምርቶች የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በመኖራቸው በአገር ውስጥ ምርት መተካት እንደሚያስፈልግ፣ ይህ ካልሆነ ግን በተፈለገው ጊዜ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደማይቻል ያስረዳሉ፡፡
እንደ ዶክተር ማንደፍሮ ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው የአየር ንብረት ለውጥ በምርምር ተደግፎ መፍትሄ ካልተበጀለት አስቸጋሪ ስለሚሆን ድርቅን የሚቋቋሙና ምርት የሚሰጡትን መጠቀም ለነገ የማይተው ጉዳይ ነው፡፡
ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከኢትዮጵያ 11 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በጨዋማነት የተጠቃ ሲሆን፤ በዚህም በዓመት ከ60 እስከ 80 ሚሊዮን ብር ታጣለች፡፡ በአፈር አሲዳማነት ደግሞ በዓመት 18 ቢሊዮን ብር ታጣለች፡፡
ምሁራኑ እንደሚሉት፤ አርሶ አደሮችን በሰፊው በማሳተፍ የጋራ ሥራና የጋራ አጠቃቀም ሊዘረጋ ይገባል፡፡ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ማልማት፣ መጠበቅና መጠቀም ከችግሮች የማምለጫ አንዱ መንገድ ነው፡፡ ሰዎች ሳይጠቀሙ የተፈጥሮ ሀብትን ማልማት ስለማይቻል ህዝብ እያለማ እየተጠቀመም ተፈጥሮ የሚለማበት አካሄድ ካልተዘረጋ የምግብ ዋስትና አይረጋግጥም፡፡ አገሪቱ ስታካሂዳቸው የነበሩ ምርምሮች ትክክለኛ አቅጣጫ የያዙና ውጤታማ ባለመሆናቸው ከተፈጥሮ ሀብት ጋር ተዛምደው የሚሰሩ ሥራዎች ውጤታማ አልነበሩም፡፡
የዘርፉ ባለሙያዎች ቴክኖሎጂን አላምደው ምርታማነትን ካላጎለበቱ፣ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ በከፍተኛ ደረጃ ካልተሻሻለና ጥበቃ ካልተደረገለት፣ አገሪቱ በአየር መዛባት ፣ መሬቷ በጨዋማነትና በአሲዳማነት በመጎዳት ምርታማነት ያሽቆለቁላል፤ የምግብ እጥረትም ተባብሶ ህዝቧ ለከፋ ረሃብ ሊዳረግ ይችላል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር