አዲስ አበባ:- የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ንግድ ዘርፍ ማህበር በአዲስ መልክ ለሦስተኛ ዙር ያሳተመውን የሆቴልና ከተማ መመሪያ ይፋ አደረገ።
መመሪያው በአዲስ አበባ ከተማ የቱሪስት ፍሰትን ለመጨመር እንዲሁም የማህበረሰቡንና የሀገርን ገቢ ከፍ ለማድረግ የሚጠቅም መሆኑ ተገለጸ።
የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ብስራት ማህበሩ ያሳተመውን የሆቴልና ከተማ መመሪያ አስመልክተው ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣መምሪያው 120 ባህላዊና ዓለም አቀፍ ሆቴሎችን ጨምሮ በአዲስ አበባና አካባቢዋ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከነስማቸው በዝርዝር የያዘና ስለሚሰጡት አገልግሎት የተሟላ መረጃ ያለው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ እንዳብራሩት፤ይህ ሦስተኛው የአዲስ አበባ ከተማና ሆቴሎች ቱሪስት መመሪያ ባለፉት ጊዜያቶች ካዘጋጇቸው በብዙ መልኩ የተሻሉና የቱሪስት ፍሰቱንም የሚጨምር ሲሆን፣ ጎብኚዎች በከተማዋ የሚኖራቸው ቆይታ እንዲጨምር ያስችላል፡፡በተጨማሪም በከተማዋ የኮንፈረንስ ቱሪዝም እንዲያድግ የተለያዩ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚሆኑ ሀብቶች በማስተዋወቅ ትልቅ ሚና ይጫወታል።መመሪያው በድረ-ገጽ ለሁሉም ተደራሽና ከዚህ ቀደም ከነበረው በአጠቃቀም የተለየ መሆኑም በመግለጫው ተመልክቷል፡፡
የከተማ መመሪያ በየዓመቱ እንደሚዘጋጅና ከዓመት ዓመት ደረጃውን በጠበቀና ጥናቶችን በማካተት እየተሻሻለ የሚቀርብ እንዲሁም የቱሪስት ፍሰቱ በሀገሪቱ እንዲጨምር አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑም ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2011
በሰሎሞን በየነ