ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማናጀሮችና ወኪሎች ስር ሆነው የተለያዩ የግል ውድድሮችን ማድረጋቸው የተለመደ ነው። ይህ አሠራር በሌላው ዓለምም የተለመደ ሲሆን፤ እንደ ኬንያ ያሉ ሀገራትም ናይኪ እና ግሎባል ስፖርትስ ኮሙዩኒኬሽን የተባሉ ትልልቅ ማኔጅመንቶች ካምፕ በመገንባት አስፈላጊው ነገር ሁሉ ተሟልቶላቸው ለውድድሮች ይዘጋጃሉ። አትሌቶቹ በግል ውድድሮቻቸው ከሚያገኙት ውጤት በገንዘብና በሌሎች የሀገራቸው ፌዴሬሽን ተጠቃሚ ነው። በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በእነዚህና በሌሎች ማኔጅመንቶች ታቅፈው ውጤታማ ቢሆኑም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሚገባው ልክ ተጠቃሚ አለመሆኑን ሲገልፅ ይስተዋላል።
የፌዴሬሽኑ የአትሌቲክስ ፋሲሊቲ ማኅበራት አገልግሎት የሥራ ሂደት መሪ አቶ አሰፋ በቀለ፤ ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጋር የሚሠሩ በተለምዶ ማናጀር የሚባሉ የአትሌት ተወካዮች እንደየጊዜው ቁጥራቸው ቢለያይም 20 እንደሚደርሱ ይናገራሉ። እንደ አቶ አሰፋ ገለፃ፣ አብዛኞቹ ማናጀሮች የውጭ ሀገር ዜጎች ሲሆኑ ኢትዮጵያውያኑ በቁጥር እጅግ ጥቂት ናቸው። እነዚህ የአትሌት ወኪሎች ከዓለም አትሌቲክስ ዕውቅና ያላቸውና በኢትዮጵያ ከፌዴሬሽኑ ጋር ውል አስረው ሲሠሩም ቆይተዋል፡፡ ከዚህ ቀደምም በፌዴሬሽኑ ተገኝተው ውል (ዕውቅና) የሚያድሱም ሲሆን፤ በዚህም ፌዴሬሽኑ በዓመት እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ገቢ ሲያገኝ ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጂ የዓለም አትሌቲክስ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የትኛውም ማናጀር መሥራት ያለበት ከየሀገራቱ ፌዴሬሽኖች ጋር ሳይሆን ከዓለም አቀፉ ተቋም ጋር መሆን እንዳለበት ማሳወቁን ተከትሎ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር የሚሠሩ ማናጀሮች ያላቸው ውል ተቋርጧል። ያም ሆኖ የትኛውም አትሌት ለውድድር የውጭ ሀገር ጉዞ በሚያደርግበት ወቅት አስፈላጊውን ሁሉ አሟልቶ ከተገኘ ፌዴሬሽኑ ድጋፍ ማድረጉን አላቋረጠም፡፡
ይህም ያለምንም ክፍያ አትሌቶችን ለመርዳት ሲባል የሚደረግ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ ከአትሌት ወኪሎች ምንም አይነት ጥቅም እያገኘ አይደለም፡፡ ማግኘት የሚገባቸው ጥቅሞች መኖር እንዳለባቸው ግን ያምናል፡፡ ጥያቄው እንዴት? ወይም በምን መልኩ የሚለው ነው፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ፌዴሬሽኑ ከአትሌት ወኪሎች የሚያገኘው ክፍያ ቢቀርም አትሌቶች ከወኪሎች ጋር በመሥራታቸው ብቻ ተጠቃሚ መሆኑን ያምናል፡፡ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አትሌት የማነ ፀጋይ እንደሚናገረው፤ ማናጀሮች ተሰጥዖ ያላቸውን አትሌቶች አፈላልገው በመመልመል፣ ቤት ተከራይተው፣ አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላትና ውድድር አፈላልገው በማሳተፍ ገቢ ያገኛሉ። ይህ የስፖርት ቢዝነስ አንዱ አካል ሲሆን፤ በየትኛውም ዓለም የተለመደ የወቅቱ አሠራር ነው፡፡ በዚህ ብቻ ፌዴሬሽኑን እየጠቀመ መሆኑን ከመረዳት ይልቅ ከማናጀሮች ክፍያና ሌሎች ጥቅሞችን መጠበቁ ተገቢ አይደለም፡፡
አትሌት የማነ ይህንን ሲያብራራም፣ የአትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን እና ጠንካራ ክለቦች በሌሉበት ሁኔታ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤታማነት ማናጀሮች በሚያመቻቹት ውድድሮችና ሥልጠናዎች ምክንያት እንደቆየ መገንዘብ ያስፈልጋል ይላል፡፡
ግዙፉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ናይኪ በራሱ ማኔጅመንት ስር የተለያዩ አትሌቶችን አቅፎ ይሠራል፡፡ የናይኪ ኢንተርናሽናል ተወካይ ከሆኑት አንዱ ዮናስ አያና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከማናጀሮች የሚያገኘው ጥቅም መኖር አለበት ብሎ ያምናል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ ረገድ እየተጠቀመ አለመሆኑ የፈጠረበት ቁጭትም ለአዲስ ሥራ ያነሳሳው ኢትዮጵያዊ ባለሙያ ነው፡፡ የናይኪ ተወካይ በመሆን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር ለዓመታት ከሠሩ ባለሙያዎች መካከል ብቸኛው ኢትዮጵያዊም ሲሆን፤ በርካታ ወጣትና ስኬታማ አትሌቶችንም ማፍራት ችሏል፡፡ ዮናስ ከወከለው የናይኪ ማናጅመንት ስር ሆነው የሚሠሩ አምስት ኢትዮጵያውያን ማናጀሮች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ አትሌቶች ጋር የሚሠሩ ማናጀሮች ግን የውጭ ሀገር ዜጎች መሆናቸውን ይናገራል።
እንደ ዮናስ ገለፃ፣ ኬንያ ውስጥ የሚሠሩ ማናጀሮች በሀገሪቱ ከሰባት ያላነሱ የአትሌቲክስ ካምፖችን ገንብተው አትሌቶችን በመመልመልና በማዘጋጀት በውድድሮች ላይ ያሳትፋሉ፡፡ በአንጻሩ ከ20 ዓመታት በላይ በሠሩባት ኢትዮጵያ ለስፖርቱ አንድም አስተዋፅዖ ሲያደርጉ አይታይም፡፡ አትሌቶችንም አይደግፉም፡፡ እንዲያውም ውጤታማ የሆኑ አትሌቶችን ከየስፍራው ተሻምተው በመያዝ ነው ውድድሮች ላይ የሚያሳትፉት፡፡ ይህ ሁኔታ በፈጠረበት ቁጭትም ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ማጠናቀቅ የሚችሉ አትሌቶች ማፍራትን ዓላማው ያደረገና የራሱ የአትሌቲክስ ካምፕ ያለው ፕሮጀክት በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍቶ አትሌቶችን በመመልመል ለሌሎች አርዓያ የሚሆን እርምጃ ወስዷል፡፡ ሌሎችም ማናጀሮች በሀገሪቱ አትሌቶች እስከተጠቀሙ ድረስ ፌዴሬሽኑን የሚጠቅሙበት መንገድ ሊኖር ይገባል የሚል አቋም አለው፡፡
ከማናጀሮች መጠቀም አለብኝ የሚለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በዮናስ ሀሳብ ይስማማል። ማናጀሮች በሌሎች ሀገራት የማሠልጠኛ ማዕከላትን የሚገነቡ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን በተግባር የታየ ነገር አለመኖሩን ነው ፌዴሬሽኑ የሚጠቁመው፡፡ በዚህም ምክንያት የአትሌት ባለቤት ከሆኑት ክለቦች ከፍተኛ ቅሬታ በተደጋጋሚ እንደሚቀርብም አቶ አሰፋ ያስረዳሉ። ይህንን ሲያብራሩም አትሌቶችን የሚያሳድጉት፣ ትጥቅ የሚሰጡትና ደመወዝ የሚከፍሉት ክለቦች ሆነው ሳሉ ማናጀሮች ከስር ጀምረው ታዳጊዎችን ከማፍራት ይልቅ ብቁና ዝግጁ የሆኑ አትሌቶችን ከክለቦች በመንጠቅ ያልተገባ ጥቅም እያገኙባቸው ይገኛሉ ባይ ናቸው፡፡
በተወዳዳሪነት ዘመኑ በማናጀሮች ስር ሲሠራ የቆየው አትሌት የማነ በበኩሉ በአቶ አሰፋ ሀሳብና በፌዴሬሽኑ አቋም አይስማማም፡፡ ፌዴሬሽኑ መጠቀም ካለበትም ሌሎች ማናጀሮችን የሚስብ አሠራር ከኬንያ ተሞክሮ በመውሰድ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ነው የሚሞግተው። ለዚህም የአትሌቲክስ ካምፖች መገንቢያ የመሬት አቅርቦትም ሆነ ሌሎች ሁኔታዎችን ማመቻቸት ማናጀሮች በሌሎች ሀገራት የሚሠሩትን በኢትዮጵያም ለመሥራት ፍላጎት ያሳድርባቸዋል ይላል፡፡ ይህን ለማድረግም ማናጀሮች ፍላጎት አላቸው የሚል እምነት አለው፡፡
ያም ሆኖ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሠራር ለዚህ ክፍት አይደለም ሲል ይወቅሳል፡፡ ከዚህ ይልቅ ፌዴሬሽኑ ማናጀሮችን በአስር ሺዎች የሚቆጠር ዶላር እንዲከፍሉ በመጠየቅ ተስፋ አስቆራጭ መንገድ ለመከተል እንደሚሞክር የሚጠቁመው አትሌት የማነ፣ ከዚህ ቀደም ይህ ገንዘብም በሚገኝበት ጊዜ ለአትሌቲክሱ በሚጠቅም ጉዳይ ላይ ውሏል የሚል እምነት እንደሌለው ያስረዳል። ‹‹ክለቦችም ቢሆኑ ለአትሌቱ ውድድር በማመቻቸት ምን ያህል እየሠሩ ነው›› ሲልም ይጠይቃል፡፡
አዲሱ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚም በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት በመስጠትና አሠራሩን በማስተካከል ማናጀሮቹን መመለስ እንዲቻል መሥራት እንዳለበት የሚጠቁመው አትሌት የማነ፣ ክለቦችም ቅሬታ እንዳያድርባቸው ከማናጀሮች ጋር በማቀራረብ አብረው እንዲሠሩ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ይጠቁማል፡፡
ማናጀሮች የኢትዮጵያ ሃብት በሆኑት አትሌቶች ተጠቃሚ ይሁኑ እንጂ ፌዴሬሽኑም ሆነ ሀገሪቷ ከእነሱ የሚጠቀሙት ነገር እንዳይኖር እንቅፋት የሆኑ ችግሮች መቀረፍ እንዳለባቸው አቶ አሰፋ ይናገራሉ፡፡ ይህንን ወደ መስመር ሊያመጣ የሚችል አሠራር በማዘጋጀትና ለዓለም አትሌቲክስ በማሳወቅ ስፖርቱ የሚያድግበት ሁኔታ መመቻት ይገባልም ይላሉ፡፡ ለወደፊትም ይህንን ሊያስታርቅ የሚችልና ሀገሪቷንም የሚጠቅም መመሪያ ማዘጋጀት አስፈላጊ እንደሚሆንም አመላክተዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም