ከአዲሱ የአትሌቲክስ አመራር ብዙ እንጠብቃለን!

የኢትዮጵያ የኩራት ምንጭ የሆነው የአትሌቲክስ ስፖርት ዛሬም የሀገርና የሕዝብ ኩራት ነው:: ያም ሆኖ ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት በአግባቡ ባለመመራቱ አስተዳደራዊ ስንክሳሮች በየጊዜው በስፖርቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ትልቅ እንቅፋት እየሆነ ይታያል:: በዚህም ምክንያት በየጊዜው በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አመራሮች ላይ የተለያዩ ቅሬታዎች ይሰነዘራሉ::

እነዚህ ቅሬታዎች በየጊዜው እያሽቆለቆለ ከመጣው የአትሌቲክስ ውጤት ጋር ተያይዞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሕዝብን ያስቆጡ ጭምር ናቸው:: በዚህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አፍቃሪዎችና የስፖርቱ ተቆርቆሪዎች ስፖርቱን ወደዘመናዊው የአስተዳደር ደረጃ ሊያሻግሩ የሚችሉ የአመራር ብቃቱ ያላቸው ሰዎችን ለማየት ይፈልጋል:: ይሁን እንጂ በሚጠበቀው ልክ የስፖርቱን እድገት ዕውን ሊያደርጉ የሚችሉ አመራሮችን ለማየት ሳይቻል ቆይቷል::

አልፎ አልፎ የመሥራት አቅሙና ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎች ብቅ ሲሉም በስፖርቱ ዙሪያ ባለው የመጠላለፍ ፖለቲካ፣ ለግል ጥቅም እና ፍላጎታቸው ብቻ በሚጨነቁ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ሴራ በፍጥነት ከአካባቢው ገለል እንዲሉ ይደረጋል::

በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አመራር ዙሪያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የታዩት የአስተዳደር ግድፈቶች ከምንግዜውም የከፉ ነበሩ:: ምክንያቱ የአስተዳደር ዕውቀት እና አቅም ማነስም ይሁን የግል ስሜት እና ፍላጎቶችን መከተል በፌዴሬሽኑ አመራር ዙሪያ ደካማ የውሳኔ አሰጣጦች፣ አቅዶ የመተግበር ችግር፣ እና ግልፅ ያለመሆን እንዲሁም አትሌቶቻችን እና አጠቃላይ ስፖርቱን የሚመለከቱ ችግሮችን አግባብ ባለው መንገድ መፍታት ያለመቻል ችግሮች በተደጋጋሚ ታይተዋል።

እነዚህ ከአስተዳደር ብቃት እና ቁርጠኝነት ማነስ ጋር የተያያዙ ችግሮች የፈጠሯቸው ክፍተቶችም የኢትዮጵያን አትሌቲክስ እድገት ከማደናቀፍ በዘለለ ከጊዜ ወደጊዜ በፌዴሬሽኑ፣ በአትሌቶች፣ በአሰልጣኞች እና በስፖርቱ እውነተኛ ደጋፊዎች ዘንድ መተማመን እንዲጠፋ ሲያደርጉ ታዝበናል::

በፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅት እና በውድድሩ ወቅት እንዲሁም ከዛም በፊት በነበሩት ጊዜያት በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አመራር ዙሪያ አስተዳደራዊ ድክመቶች በስፋት ተስተውለዋል:: ከድክመቶቹ አብዛኞቹ በቀደሙት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መሪዎች ጊዜም የነበሩ እና ባሉበት ሲንከባለሉ እዚህ የደረሱ ናቸው:: ነገር ግን በጊዜው በነበረው አመራር አንዳንዶቹ ችግሮች እጅግ መስመራቸውን ሲስቱ እንደታዩም ማስተባበል አይቻልም::

ለረጅም ዓመታት ባለበት የቆመው የሀገር ውስጥ ውድድሮች የጥራት ደረጃ፣ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ የመጣው የልምምድ እና የውድድር ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እጥረት፣ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች በተቃረቡ ቁጥር ከአትሌቶች ምርጫ ጋር በተያያዘ የሚታየው ውዝግብ፣ የአትሌቲክስ ስፖርትን ለሚያስተዳድር ተቋም የጀርባ አጥንት ከሚባሉ ነገሮች መካከል አንዱ የሆነው የመረጃ ቋት አደረጃጀት ዙሪያ በአግባቡ መሥራት ያስፈልጋል።

የሚወጡ የመተዳደሪያ ሕግ እና ደንቦችን ለስፖርቱ ባለድርሻ አካላት እና ለሕዝብ በይፋ አለማስተዋወቅ እና በአግባቡ አለመተግበር፣ እንዲሁም ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ጉዳዮች ለይቶ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ ለመተግበር አለመሥራት በዋናነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት ችግሮች መካከል ናቸው::

በተዘረዘሩት ችግሮች እንደተከበበ 28ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ታኅሣሥ 12 እና 13 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ያካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የፕሬዚዳንት እና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ አድርጎ አዳዲስ አመራሮች ወደፊት መጥተዋል::

አዳዲሶቹ የአትሌቲክስ አመራሮች አብዛኞቹ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከዚህ ቀደም በአትሌክስ ፌዴሬሽኑ ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው እንደመሆኑ አዲስ ለማለት ቢከብድም ከስፖርቱ ጋር ቅርበት ያላቸው ናቸው:: ይህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከምንጊዜውም በከፋ የአስተዳደር ችግር ውስጥ ባለበት በዚህ ወቅት ትልቅ ኃላፊነት ተሰምቷቸው ቢያንስ እየገዘፉ የመጡትን ችግሮች ሊቀንሱ እንደሚችሉ ተስፋ ተጥሎባቸዋል::

አዳዲሶቹ አመራሮች በምርጫው ወቅት ራሳቸውን ሲያስተዋውቁ አብዛኞቹ የፌዴሬሽኑን ችግሮች ጠንቅቀው እንደሚያውቋቸው ታዝበናል:: ይህም ‹‹ችግሩን ማወቅ የመፍትሔው ግማሽ አካል ነው›› እንደሚባለው የስፖርቱን ችግሮች ማወቃቸው ተስፋ እንድንጥልባቸውና ብዙ እንደምንጠብቅባቸው ያደርገናል::

ምክንያቱም ከተመረጡ በኋላ ችግሩ ምንድነው ብለው ለማጣራት የሚያጠፉት ጊዜ ሳይኖር በቀጥታ የሚያውቋቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ወደሚያስችለው የመፍትሔ ሃሳብ እና ትግበራ እንዲገቡ ያግዛቸዋል::

ያም ሆኖ እነዚህ አዳዲስ አመራሮች ተጠባቂ ፈተናዎች እንደሚጠብቀቸው ግልፅ ነው:: ኮስተር ያለ የአመራር ብቃታቸውን ለማሳየትም ቁርጠኛ መሆን አለባቸው::

አዲሱ አመራር ውጤታማ ሥራን ለማከናወን የአጭር ጊዜ እና የረዥም ጊዜ ስትራቴጂክ ዕቅዶችን ማዘጋጀት ያስፈልገዋል:: እነዚህን ዕቅዶች ለማዘጋጀትም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑን ወቅታዊ ሁኔታ በጥልቀት በመፈተሽ ቁልፍ ጥንካሬዎችን፣ ድክመቶችን፣ እድሎችን እና ሥጋቶችን መለየት አለበት።

የአጭር ጊዜ እቅዱ ፈጣን ማሻሻያዎችና የቅድሚያ ትኩረት በሚያስፈልጋቸው በጊዜያዊ የልምምድ እና ውድድር ማዘውተሪያ ችግሮች መፍቻ፣ መቀየር ያለባቸው የአሠራር ሂደቶች፣ የአሰልጣኝነት ሥልጠና መርሃ ግብሮችን ማሳደግ፣ ስፖንሰርሺፕን ማጠናከር፣ በቅርቡ ለሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች እና ሌሎችም መካተት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ሊያተኩር ይችላልና በነዚህ ጉዳዮች ላይ የስፖርት ቤተሰቡ ለውጥ ማየት ይሻል::

የረዥም ጊዜ ስትራቴጂው ደግሞ የውድድሮች ጥራትን እና የውድድር ማዘውተሪያዎችን ማስፋፋት እና ማዘመን፣ የሥልጠና ተቋማትን ማሳደግ፣ በሁሉም ዘርፎች ለአትሌቶች እድገት ቅድሚያ መስጠት፣ ዘላቂ ዓለም አቀፍ አጋርነትን መፍጠር እና ሌሎችም መካተት የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ላይ ሊያተኩር ይችላል።

በሁለቱም ዕቅዶች ውስጥ የሚካተቱት ነገሮች ግልጽ፣ ሊለኩ የሚችሉ ግቦች ያሏቸው እና በጊዜ ሰሌዳዎች የተደገፉ መሆን አለባቸው:: መደበኛ የአፈፃፀም ግምገማ ማድረጊያ ጊዜ ሊኖሯቸውም ይገባል። አፈፃፀሞቹን የሚቆጣጠር ኮሚቴ በማቋቋም የአፈጻጸም መለኪያ ዳታዎችን እና ትንታኔዎችን በመጠቀም የሩብ ዓመት ግምገማን ማድረግ፤ ትግበራውን ለማሳካትም እንደ አስፈላጊነቱ ስልቶችን መቀየር ይቻላል።

ከባለድርሻ አካላት ጋር በተለያዩ መንገዶች አዘውትሮ በመገናኘት እና ግልጽ የሆነ ሪፖርትን በማቅረብም ተጠያቂነትን እና እያደገ ካለው የዓለም የአትሌቲክስ ገጽታ ጋር መጣጣምን የበለጠ ለማረጋገጥ መትጋት ያስፈልጋል።

የጽሕፈት ቤት አሠራርን መፈተሽ እና ማዘመን ሌላው የቤት ሥራ ይሆናል:: የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዓለም አትሌቲክስ መስፈርቶችን ተከትሎ እንዲራመድ የጽሕፈት ቤቱን አጠቃላይ አሠራር መገምገም እና ማዘመን ግድ ይላል። ይህም ማሻሻያ ማድረግ የሚቻልባቸውን የአስተዳደር፣ የቴክኒክ ወይም የውድድር ዝግጅት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን ጠንካራ እና ደካማ ጎን መለስ ብሎ መመልከትን ይጠይቃል።

ከቢሮው አስተዳደራዊ እና ድርጅታዊ መዋቅር ጋር በተያያዘ በሀገር ውስጥ በቢሮው ውሳኔ ማግኘት ለሚገባቸው ጉዳዮች የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውጤታማነት እንዲሁም በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ላይ ለሚደረጉ ለውጦች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በቂ አቅም ያለ መሆኑም መታየት አለበት::

በተለይ ለአትሌቶች የሚሰጡ አገልግሎቶች ቅልጥፍና፣ የውድድር ውጤቶችን በአግባቡ መሰነድ እና ለሚፈልጉት ሁሉ በቀላሉ የሚገኙ እንዲሆኑ ማድረግ፣ አጠቃላይ የዓለም አትሌቲክስም ሆነ የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች መተዳደሪያ ሕጎች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች እንዲሁም የውድድር ሕጎች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሊያውቋቸው የሚገቡ ለውጦች ሲኖሩ ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ማሳወቅ ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል::

እንዳደጉት ሀገራት የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት የሥራ ነፃነት ከተጠያቂነት ጋር ተሰጥቶ በዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይም ዋና ዳይሬክተር እንዲመራ ቢደረግም ጥሩ ነው:: የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞችን የአፈፃፀም አቅም ለማጎልበት እና በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ዙሪያ ከሚደረጉ ለውጦች ጋር እኩል እንዲራመዱ ለማስቻልም የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች በቋሚነት ቢሰጡ ስፖርቱን ከዘመኑ ጋር እንዲራመድ ወሳኝ ነው::

የሀገር ውስጥ ውድድሮችን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ማካሄድ ለነገ የሚባል የቤት ሥራ አይደለም:: የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርትን ወደኋላ እየጎተቱት ይገኛሉ ተብሎ ከሚታሰቡ ነገሮች መካከል በዋናነት ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሠራበት የሚያስፈልገው የሀገር ውስጥ ውድድሮችን በዓለም አትሌቲክስ ደረጃ ማካሄድ ነው::

በሀገር ውስጥ የሚካሄዱ ውድድሮች በዓለም አትሌቲክስ ደረጃ አለመካሄድ የኢትዮጵያውያን አትሌቶችን በሙሉ በተለይም የአጭር ርቀት እና የሜዳ ላይ ተግባራት ተወዳዳሪዎች ልፋት ተገቢውን እውቅና እንዳያገኝ እያደረገ የሚገኝ ችግር ነው:: ስለዚህ ቢያንስ በዓለም ደረጃ(ወርልድ ራንኪንግ) ነጥብ ለማስመዝገብ የሚረዱ ዋና ዋናዎቹን የሀገር ውስጥ ውድድሮች ውጤት በኤሌክትሮኒክስ የሰዓት መቆጣጠሪያ የሚደገፍ ለማድረግ መሥራት እጅግ አስፈላጊ ነው::

የውድድሮችን ውጤቶች በዘመናዊ እና ዓለም አቀፉን መለኪያ በሚያሟላ መልኩ አለመያዝ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ ለተሳትፎ የሚያበቁ ውጤቶችን (የዓለም ደረጃዎች ነጥብ) በማስመዝገቡ ረገድ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን እዚህ ጋር ማስታወስ ተገቢ ይሆናል::

የዓለም አትሌቲክስ እ.አ.አ. በዲሴምበር 2022 ዓ.ም. ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በላከው መልእክት የትኛውም ዓይነት ውድድሮች በዓለም አትሌቲክስ የውድድር ካላንደር ላይ እንዲመዘገቡ እስካልተደረጉ እና ውጤታቸው በአወዳዳሪው አካል እስካተላከለት ድረስ ውጤቶቹ በድረ ገፁ ላይ እንደማይሰፍሩ እና ለማንኛውም የስታትስቲክስ ዓላማው (የመግቢያ ደረጃዎች፣ የዓለም ደረጃዎች፣ ከፍተኛ ዝርዝሮች፣ ሪከርዶች፣ ወዘተ) እንደማይጠቀማቸው አሳውቋል።

መልዕክቱ ከተላከ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል ለዓለም አትሌቲክስ የተላከ ብቸኛ የውድድር ውጤት እ.አ.አ. ከጁላይ 02 እስከ 06/2024 የተካሄደው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና ውጤት ነው::

ስለዚህ ፌዴሬሽኑ በዓመቱ ውስጥ የሚያደርጋቸውን ውድድሮች በዓለም አትሌቲክስ የውድድር ካላንደር ላይ እንዲመዘገብ በማድረግ እና ውጤቶችን በሰዓቱ በመላክ የአትሌቶቹ ልፋት ዓለም አቀፍ ዕውቅናን እንዲያገኝ የመሥራት ኃላፊነትም እንዳለበት መዘንጋት የለበትም::

የመረጃ ቋት የማደራጀት ጉዳይ የሁሉም የስፖርት ፌዴሬሽኖች ችግር ነው:: የመረጃ ቋት የአትሌቲክስ የጀርባ አጥንት ነው:: በአግባቡ የተደራጀ እና ወጥነት ያለው የመረጃ ቋት ያለመኖር ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አንዱ ድክመት ነው:: የአትሌቶችን ምዝገባ፣ ፕሮፋይሎችን እና የሀገር ውስጥ የውድድር ውጤቶችን የሚያጠቃልል የተማከለ ዲጂታል የመረጃ ቋት ማዘጋጀት ለአንድ ሀገር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው።

ለአሰልጣኞች እና የፌዴሬሽን ባለሥልጣናት የአትሌቶችን አፈፃፀም፣ እድገት እና ተሳትፎን በመከታተል በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ እንዲወስኑ ጠቃሚ መረጃዎችን ይሰጣል። በደንብ የተደራጀ የመረጃ ቋት ግልፅነትን ያሳድጋል፣ የውድድር ውጤቶችን ወጥ በሆነ መልኩ ያሳያል፣ ሪኮዶችን በአግባቡ ለመለየት፣ የአትሌቶችን ጥንካሬ እና ድክመት እንዲሁም ወቅታዊ ሁኔታዎችን ለመገምገም፣ የእድሜ ማጭበርበርን ለመቆጣጠር፣ እና የረጅም ጊዜ የአትሌቶችን እድገት ሂደት ለማወቅም ይረዳል።

ከሁሉም በላይ በስፖርቱ ውስጥ የላቀ ተጠያቂነትን፣ ፍትሃዊነትን እና የአሠራር ቅልጥፍናን ያጎለብታል:: ይህን ክፍተት ለማስተካከል ፌዴሬሽኑ የሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት ክፍሉን የድረ ገፅ ማልማት እና ማዘመን እንዲሁም የአትሌቲክስ መረጃዎቹን በአግባቡ ማዘጋጀት በሚችሉ ባለሙያዎች ጥምረት ማጠናከር ይኖርበታል::

የአትሌቶች ምርጫ አዲሱ አመራር ለውጥ ሊያመጣበት የሚገባ ዋናው ጉዳይ ነው:: በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያሰለቸ ነገር ቢኖር ለዓለም አቀፍ ውድድሮች የአትሌቶች ምርጫ በሚደረግ ጊዜ የሚታየው ውዝግብ ነው::

ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ ፌዴሬሽኑ ግልጽ የሆነ የመምረጫ መስፈርት በማስቀመጥ አስቀድሞ ለባለድርሻ አካላት እና ለሕዝብ ወቅቱን በጠበቀ መልኩ በይፋ የማሳወቅ ሥራውን ችላ ስለሚለው ነው:: አንዳንዴ መስፈርት ቢወጣም መስፈርቱ በይፋ ሳይገለጽ ከጀርባ የግል ፍላጎቶች እየተጫኑት ችግሩን ሲያባብሰው ይታያል::

ይህን ችግር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መቅረፍ የሚቻለው ሁሉንም የስፖርቱን ባለድርሻ ባሳተፈ ምክክር ወጥ እና ግልፅ የመምረጫ መስፈርት ሲወጣ ነው:: ሁሉንም ገዢ የሆነ የምርጫ መስፈርቶች ከወጡ በኋላም በፌዴሬሽኑ ድረ-ገጽ፣ የማህበራዊ ግንኙነት ገፆች እና በተለያዩ ሚዲያዎች አትሌቶች ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመመረጥ ዝግጅት ከመጀመራቸው በፊት በደንብ መተዋወቅ አለባቸው።

ሁሉም አትሌቶች እና አሰልጣኞች ሙሉ በሙሉ እንዲረዷቸው ለማድረግም መስፈርቶቹ በብዙ ቋንቋዎች ተደራሽ መሆናቸውን ማረጋገጥም በጣም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም የምርጫ ሂደቱ ለይግባኝ ሂደቶች ክፍት መሆን አለበት። መስፈርቶቹን ቀድሞ ማሳወቅ አትሌቶች የሚጠበቅባቸውን እንዲያውቁ ስለሚያደርግ ያለመግባባቶችን እምቅ አቅም ይቀንሳል:: በአትሌቲክስ ማህበረሰቡ ውስጥም መተማመንን ያሳድጋል።

አዳዲሶቹ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መሪዎች እነዚህን የቤት ሥራዎች በትክክል በመምራት ስፖርቱ በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ግንባር ቀደም ደረጃውን ጠብቆ እንዲጎለብት የማድረግ አቅም አላቸውና የስፖርት ቤተሰቡ ከእነሱ ብዙ እንደሚጠብቅ አውቀው በትጋት ሊሠሩ ይገባል::

በስፖርቱ ዙሪያ ያሉትን ችግሮች በሚቻለው መንገድ ለመቅረፍ ከመሞከር ባሻገር የጠቅላላ ጉባኤው አደረጃጀት ላይ፣ አዎንታዊ እና አሉታዊ ሚናዎቹም ላይ ውይይት የሚደረግበት መድረክ ቢፈጠር መልካም ነውና አዲሱ አመራር ጊዜ ወስዶ እንዲያስብበት ተስፋ እናደርጋለን::

ልዑል ከካምቦሎጆ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You