እግር ኳስ ቲያትር ነው፣ ለዚያም ነው የዓለም ሕዝብ ተወዳጁ መዝናኛ የሆነው። እግር ኳስ ቲያትር ነው የሚባለው በምክንያት ነው። ያልተጠበቁና ፈፅሞ ይሆናሉ ያልተባሉ ተዓምራት የሚፈፀሙበት መድረክ ነውና። እግር ኳስ በጥሩ ደራሲ የተፃፈ ቲያትር ተደርጎ የሚቆጠረው አዝናኝ፣ አስቂኝ፣ አስከፊና አስቆጪ የማይረሱ ታሪኮችን በዘጠና ደቂቃ ፍልሚያ ማስኮምኮም በመቻሉም ነው ቀዳሚው ተመራጭ ስፖርት የሆነው።
ፊፋ ተጫዋቾች ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ማልያቸውን አውልቀው ደስታቸውን እንዳይገልፁ ከ2004 ጀምሮ መከልከሉ ይታወቃል። ይህን የፈፀሙ ተጫዋቾች ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቢጫ ካርድ ሲመለከቱ ኖረዋል። ፊፋ ይህን ሕግ ሲያወጣ ማልያ አውልቆ ደስታን መግለፅ የስፖርት ሥነምግባር አይደለም ብሎ በማሰብ ሲሆን በዋናነት ተጫዋቾች ማልያቸውን አውልቀው ደስታቸውን ሲገልፁ በጨዋታ የሚባክን ሰዓትን ለመቀነስ በማሰብ ነው።
በደስታ የሰከሩና ስሜታቸውን ለመግለፅ የተቸገሩ በርካታ ተጫዋቾች ይህን ሕግ ጥሰው ማልያ አውልቀው ደስታቸውን በመግለፅ የቢጫ ካርድ ሰለባ ሲሆኑ ማየት የተለመደ ነው፡፡ እግር ኳስ ፈገግ ካለባቸው አጋጣሚዎች አንዱ የሆነው ክስተትም የተፈጠረው ከዚሁ ሕግ ጋር በተያያዘ ነው።
ጊዜው ሩቅ አይደለም እኤአ 2013 ነው፣ ተጋጣሚዎቹ የጣሊያኑ ክለብ ዩቬንቱስና ፔስካራ ናቸው። አሮጊቶቹ ሴሪ ኤውን በመምራት የስኩዴቶው ሻምፒዮን ለመሆን ይህ ጨዋታ የመጨረሻቸው ነው። ተጋጣሚያቸው ፔስካራ በበኩሉ ከሊጉ ላለመውረድ ቱሪን ላይ የመጨረሻውን ትግል የሚያደርግበት ወሳኝ ጨዋታ ነው። ጉሴፔ ሪዞ በሠራው ጥፋት 72ኛ ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ሲወገድ ዩቬ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝቶ አማካኙ ሚርኮ ቩሲኒች አስቆጥሮ መምራት ቻለ። ይህ ሞንቴኔግሯዊ ተጫዋች ፍፁም ቅጣት ምቱን አስቆጥሮ ማልያውን አውልቆ ደስታውን በመግለፁ ቢጫ ካርድ ተመለከተ። ብዙ ሳይቆይም ቩሲኒች ለክለቡም ለራሱም ሁለተኛ ግብ ከመረብ ማሳረፍ ቻለ። አሁን ግን ከደቂቃዎች በፊት እንዳደረገው ማልያውን አውልቆ ደስታውን ለመግለፅ አልቻለም። ምክንያቱም በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግዶ ቡድኑን በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ዋጋ ሊያስከፍል ነው።
ልብስ እያውለበለበ ካልሆነ በቀር ደስታውን የገለፀ የማይመስለው አማካኝ ግን ዳግም ቢጫ ካርድ የማይመለከትበትን አንድ መላ ወዲያው ዘየደ። ከላይ ከለበሰው ማልያ (ቲሸርት) ይልቅ ቁምጣውን አውልቆ በእጁ በማወዛወዝ ሜዳውን በሩጫ እያካለለ ደስታውን ገለፀ።
የጨዋታው ዳኛ ማልያውን አውልቆ ደስታውን ለገለፀ ተጫዋች ቢጫ ካርዳቸውን መምዘዝ የለመዱትና ቀላሉ ሥራቸው ነው። ቁምጣውን ላወለቀ ተጫዋች ቢጫ ካርድ መምዘዝ ግን ሕጉ ላይ አልተቀመጠምና ያላቸው አማራጭ እንደማንኛውም ተመልካች በድርጊቱ ፈገግ ማለት ነበር። የተጫዋቹ ድርጊት ብዙዎችን ዘናና ፈገግ ከማድረጉ ባሻገር በዚያች ግብ ባስቆጠረባት ቅፅበት የሕግ ክፍተቱን በፍጥነት ማሰቡ አስገርሟቸዋል። የወቅቱ የዩቬ አሠልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ግን “ይህ እብድ ሌላ ጣጣ ሳያመጣብኝ” ያሉ ይመስላሉ፣ የተጫዋቹን ድርጊት እንደተመለከቱ ወዲያው ቀይረው ከሜዳ አስወጥተውታል። የተጫዋቹ ድርጊት ሊያስቀጣ ይገባል አይገባም በሚል በወቅቱ ብዙዎችን አከራክሯል፡፡ ያም ሆነ ያ አጋጣሚና የተጫዋቹ ድርጊት ግን ሁሌም ፈገግ ከሚያደርጉ የእግር ኳሱ ታሪኮች አንዱ ሆኖ ይታወሳል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም