‹‹ጥላሁን ለምን ለምን ሞተ?››

ፕሮፌሰር እንድሪያስ እ ሸቴ ነገሩን እንደሚያስታውሱት፤ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሲጀመር ንጉሡ ብዙ አልተቆጡም ነበር:: እንዲያውም የግጥም ምሽቶች ላይ እየተገኙ ሥርዓተ መንግሥታቸው ሲወቀስና ሲሰደብ ያዳምጡ ነበር:: ‹‹ቁጭ ብዬ ስሰደብ አልሰማም›› ብለው የግጥም ምሽቱን መታደሙን አቆሙ:: ፕሮፌሰር እንድሪያስ እንደሚሉት፤ ንጉሡ ተማሪዎችን ልጆች ናቸው ይመለሳሉ የሚል ምኞት የነበራቸው ይመስላል::

እየቆየ ሲሄድ ግን ነገሩ ጠነከረ:: እንደነዋለልኝ መኮንን እና ጥላሁን ግዛው ያሉ አብዮተኞች አብዮቱን አቀጣጠሉት:: የጥላሁን መሞትም የበለጠ አብዮቱን አጋጋለው:: በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን የጥላሁን ግዛውን አሟሟትና ‹‹ጥላሁን ለምን ለምን ሞተ?›› በሚል መገደሉን ተከትሎ የመጡ ነገሮችን እናስታውሳለን::

ይህ ድምጽ በተለምዶ ‹‹የ60ዎቹ ትውልድ›› እየተባለ የሚጠራው የዚያ ትውልድ ተማሪዎች ድምጽ ነበር:: ‹‹ጥላሁን ለምን ለምን ሞተ!›› የጥላሁን ግዛውን አገዳደል ፍትሕ የሚጠይቅ የተማሪዎች መፈክር ነበር:: ጥላሁን ግዛው የተገደለው ከ55 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 19 ቀን 1962 ዓ.ም ነበር:: ለመሆኑ ጥላሁን ግዛው ማነው? ለምን ተገደለ? በማን ተገደለ? የሚሉ ጥያቄዎችን የታሪክ ሰነዶችን ዋቢ አድርገን በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን እናስታውሰዋለን:: ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የዚህ ሳምንት የታሪክ አጋጣሚዎችን እናስታውስ::

ከ37 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 17 ቀን 1980 ዓ.ም ኢትዮጵያ የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ዋንጫ (ሴካፋ) ለመጀመሪያ ጊዜ አሸነፈች:: ኢትዮጵያ ባስተናገደችውና ስምንት ሀገራት (ኢትዮጵያ፣ ዚምባብዌ፣ ዛንዚባር፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ማላዊ) በተካፈሉበት 15ኛው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ዋንጫ (ሴካፋ) ለፍፃሜ የቀረቡት አስተናጋጇ ኢትዮጵያ እና ዚምባብዌ ነበሩ:: የወቅቱ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም እና ሮበርት ሙጋቤ ነበሩ:: ይህ ጨዋታ በዝነኛው የስፖርት ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ‹‹…ወይኔ! ወይኔ ዳኙ! ዳኙ አገባ!…›› በሚለው አይረሴ ድምጽ ይታወሳል:: የዚህን ታሪክ ዝርዝር ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም የታተመ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሳምንቱ በታሪክ ዓምድ ላይ ማግኘት ይቻላል::

ከ33 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ዴሴምበር 26 ቀን 1991 (በኢትዮጵያ ታኅሣሥ 17 ቀን 1984 ዓ.ም) የሶቪየት ሕብረት መበታተን በይፋ ታወጀ:: እነሆ አሁን ሩሲያ (ራሽያ) በሚለው ስሟ ትጠራለች:: በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊ ከነበሩት ሀገራት አንዷ በመሆን ከአራቱ የዓለም ልዕለ ኃያላን ሀገራት (አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ሶቪየት ሕብረት) አንዷ የነበረችው ሶቪየት ሕብረት በኋላ ከአሜሪካ ጋር ‹‹ቀዝቃዛው ጦርነት›› የሚባለው ጦርነት ውስጥ ገባች:: አሜሪካ የምዕራቡን ዓለም፣ ሶቪየት ሕብረት የምሥራቁን ዓለም አጋር እያደረጉ ጎራ ፈጠሩ:: እንዲህ እንዲህ እያለ የቀጠለው የሶቪየት ሕብረት ጉዳይ በ1984 ዓ.ም በይፋ ፈረሰ:: እነሆ የሶቪየት ሕብረት መፍረስ በብዙ ፖለቲከኞችና የታሪክ ባለሙያዎች በየአጋጣሚው ሲጠቀስ እንሰማለን::

ከ117 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 20 ቀን 1900 ዓ.ም በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የመጀመሪያዋ መኪና ወደ አዲስ አበባ ገባች:: እነሆ የመጀመሪያዋ መኪና እየተባለችም በታሪክ ትጠቀሳለች::

በዕለቱ በዝርዝር የምናየው የሳምንቱ ታሪክ በንጉሣዊ ሥርዓቱ ጊዜ የግራ ዘመም አራማጅ የነበረውን የጥላሁን ግዛው መገደል እና የነበረውን የተማሪዎች እንቅስቃሴ እናስታውሳለን::

ጥላሁን ግዛው የተገደለው ከ55 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 19 ቀን 1962 ዓ.ም ነበር:: የጥላሁን መገደል ሲሰማ ‹‹ጥላሁን ለምን ተገደለ?›› በሚል በተማሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር:: ‹‹ኅብር ሕይወቴ›› በሚል ከዓመት በፊት የታተመው የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የግል የሕይወት ታሪካቸው መጽሐፍ ያንን ክስተት ያስታውሳል:: የታኅሣሥ ግርግርን በዓይናቸው አይተው እንደነበረው ሁሉ በጥላሁን ግዛው መገደል የተፈጠረውን የአባታቸውን ጭንቀት እና የነበረውን ሁነት አስታውሰዋል:: በነበረው ግርግር በአዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ ነበር፤ ከ9 ዓመታት በኋላ የተከሰተ ሌላኛው የታኅሣሥ ግርግር መሆኑ ነው:: በርግጥ ለተማሪዎች አብዮት መቀጣጠል እርሾ የሆነውም ያው የ1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው::

ወደ ታሪኩ ስንመለስ፤ በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የግራ ዘመም ፖለቲከኞች ስብስብ ተጠናክሮ አዞዎች (ክሮኮዳይልስ) የተሰኘ ቡድንን በመፍጠር 1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ተማሪዎች የትግል መርህ ‹‹መሬት ላራሹ›› መሆኑ ይፋ ተደረገ:: መጋቢት 4 ቀን 1957 ዓ.ም ‹‹መሬት ላራሹን የምትሹ፤ ተዋጉለት አትሽሹ›› እያሉ ተማሪዎች በአደባባይ ሰልፍ በወጡበት ወቅት የ11ኛ ክፍል ተማሪ የነበረው ጥላሁን በሰልፉ ተሳትፏል።

ጥላሁን ግዛው የ«አዞዎቹ» ዓላማ አራማጅና በኋላም ለመሪነት ለመታጨት የበቃ ወጣት ነበር። በ1961 ዓ.ም በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በመኮንን ቢሻው ቢሸነፍም በቀጣዩ ዓመት ኅዳር 1962 ዓ.ም በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በከፍተኛ ድምጽ ብልጫ አሸንፏል። ጥላሁን የፕሬዚዳንትነት ዘመኑ ቀዳሚ ሥራው የተማሪውን የመናገር፣ የመጻፍና የመደራጀት ነጻነት ይበልጥ ማጠናከር ነበር። ለሁለት ወር ብቻ በፕሬዚዳንትነት የቆየው ጥላሁን የተለያዩ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ በማበረታታት የሚታወቅ ታጋይ ነበር ይባልለታል።

ታኅሣሥ 19 ቀን 1962 ዓ.ም ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ ከታናሽ ወንድሙ መኮንን ሲሳይ ጋር በመሆን ከስድስት ኪሎ በስተጀርባ አፍንጮ በር በሚባለው አካባቢ ፍቅረኛውን ዮዲት ታዬን ለመሸኘት ወጥተው ታርጋ በሌለው መኪና በተተኮሰ ጥይት ተገደለ።

ሱልጣን አባዋሪ የተባሉ ሰው ‹‹የተማሪው ትግልና የአብዮቱ ደመና›› በሚል ርዕስ አንታዛ መጽሔት ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ የጠቀሷቸው ሌተናል ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ ስለአሟሟቱ ሲገልጹ፤ ‹‹ስለ ጥላሁን ግድያ የተለያዩ ነገሮች ቢወሩም … ሐቁ ግን ግድያው የተፈፀመው በንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ፣ የንጉሱ የቅርብ አጃቢ ወይም አንጋች ክፍል ምክትል አዛዥ በነበሩት በኮሎኔል ጣሰው ሞጃ ትዕዛዝና ከብሔራዊ ጦር ተዛውረው እኔው ራሴ ደብረ ብርሃን ካሰለጠንኳቸው በኋላ የአንጋች ክፍል ባልደረባ በሆኑት ሁለት ወታደሮች ነበር። ለዚሁ ድርጊታቸውም ሁለቱም የምክትል መቶ እልቅና ማዕረግ የተሰጣቸው መሆኑን የድርጊቱ ፈፃሚዎች ነግረውኛል›› ብለዋል።

በግድያው የተቆጡ ተማሪዎች የጥላሁንን አስከሬን ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (ስድስት ኪሎ) ቅጥር ግቢ በመውሰድ ከአዲስ አበባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከመጡ ተማሪዎች ጋር የሀዘኑ ተካፋይ ሆኑ። የጥላሁን ታሪክና የትግል ዓላማ በግጥምና በስድ ንባብ እየተሰማ የሀዘን መግለጫው ዝግጅት ተካሄደ።

ቀጥሎም በተማሪዎች ሰልፍ ታጅቦ በክብርና በጀግንነት በሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ይፈጸም ዘንድ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ያደረጉት ጥረት በንጉሡ ጸጥታ ኃይሎች ርምጃ የተጨማሪ ተማሪዎችን ሕይወት ቀጥፎ አስከሬኑ ከተማሪዎቹ ተወሰደ።

የጥላሁን ግዛው አስከሬን ከተማሪዎቹ በኃይል ርምጃ ከተወሰደ በኋላ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ታኅሣሥ 22 ቀን 1962 ዓ.ም መላው ዘመድ አዝማድ በተገኙበት በአካባቢው ተማሪዎች ሰልፍ አጃቢነት በወቅቱ ትግራይ ጠቅላይ ግዛት በማይጨው ሕዝባ ማርያም ቤተክርስቲያን ተፈጸመ።

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄም የጥላሁንን መገደል አስመልክቶ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አወጥቶ ነበር:: የመግለጫው ጥቅል መልዕክት፤ በጥላሁን መገደልና መገደሉን ተከትሎም በተከሰተው ተጨማሪ ጥፋት ሁሉ የወቅቱን ገዥ መንግሥት (የንጉሡን ሥርዓት) ተጠያቂ የሚያደርግ ነበር::

የተማሪዎች እንቅስቃሴም የበለጠ ተቀጣጠለ:: ‹‹የጥላሁን ገዳዮች እኛንም ግደሉን! ጨርሱን! ተኩስ! እስቲ በል ተኩስ! ፋሽስት!›› የሚሉ መፈክሮችና ቁጣዎች ተጠናክረው ተቀጣጠሉ:: ይህ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ቀጥሎ ከሦስት ዓመት በኋላ ደግሞ ኅዳር 29 ቀን 1965 ዓ.ም የጥላሁን ግዛው የትግል አጋር የነበረው ዋለልኝ መኮንንና ፍቅረኛው ማርታ ተገደሉ:: አሁንም ተቃውሞውና መፈክሩ ቀጠሉ::

ጥላሁን ለምን ለምን ሞተ?

ዋለልኝ ለምን ለምን ሞተ?

ማርታ ለምን ለምን ሞተች?

በኃይል በትግል ነው

ነፃነት የሚገኘው!

እያለ ያ ትውልድ ለቀጣይ ትግል ቅስቀሳ ጀመረ:: ዝማሬዎች የየሰልፉ ማድመቂያና መቀስቀሻ ሆኑ። ማንነቱን ለሕዝብ መብትና ነፃነት አሳልፎ ሊሰጥ የተዘጋጀ ትውልድ መሆኑን ደጋግሞ ተናገረ። ወደ ጥላሁን ግዛው እንመለስ::

ጥላሁን ግዛው በአሁኑ አወቃቀር ከደቡብ ትግራዩ የራያና አዘቦ አውራጃ ተወላጅ አባቱና እንዲሁም ደግሞ ከሰሜን ወሎዋ የራያ ቆቦ አውራጃ ተወላጇ እናቱ አብራክ የተወለደ የሁለት ራያ ልጅ መሆኑን ዋልታ ላይ የተሰነደ ታሪክ ያሳያል:: ጥላሁን የተወለደውና እንዲሁም ሲሞት የተቀበረው አባትዬው አቶ ግዛው አበራ ተድላ ይኖሩበት በነበረው የራያና ዓዘቦ አውራጃ ዋና ከተማ ማይጨው ውስጥ እንደሆነ ወንድሙ ጭምር አረጋግጠዋል:: በማይጨው ከተማ የማይጨው ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በጥላሁን ግዛው ስም መሰየሙንም የታሪክ ሰነዶች ያሳያሉ::

የጥላሁን ወላጆች ትዳር ሳይሰምር ቀርቶ በፍቺ ለመለያየት እንደተገደዱና እርሱም ገና ከልጅነት ዘመን ዕድሜው ጀምሮ ከእናቱ ጋር ወደ ራያ ቆቦ የሄደበት ሁኔታ ስለመፈጠሩም ታናሽ ወንድሙ ተናግረው እንደነበር ከዓመታት በፊት የተሠራ የዋልታ ዘገባ ያሳያል::

ስለጥላሁን የተጻፉ ሰነዶች እንደሚያሳዩት፤ ጥላሁን ግዛው ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ዓለም አቀፋዊ የስርነቀል ለውጥ ፍለጋ ንቅናቄ መሪ ተዋንያን የተለየ የሚያደርገው መሠረታዊ ምክንያት፤ በአባቱ ወገን ከትግራይ ታላላቅ መሳፍንቶች መካከል አንዱ ከነበሩትና በተለይም የራያ ዓዘቦ አውራጃ ዋና ከተማ የሆነቺውን ማይጨውን እንደቆረቆሯት ከሚነገርላቸው ከደጃዝማች ተድላ ገብረ ዋህድ ቤተሰብ የተገኘ ሆኖ ሳለ፤ የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን ዘውዳዊ አገዛዝ ታግሎ ስለማስወገድ አስፈላጊነት በመገንዘብ የስርነቀል ለውጥ አቀንቃኝ መሆኑ ነው::

የአሁኑ ትውልድ ምናልባትም ከዚህ ሊማረው የሚገባው ነገር፤ የጋብቻ መተሳሰር፣ የብሔርና የሃይማኖት ወገንተኝነት፣ የራሴ ወገን ነው… የሚሉ ነገሮች የጋራ ዓላማ እንዳይኖር የሚያደርጉ መሆኑን ነው:: ለድጋፍም ይሁን ለተቃውሞ የጋራ ዓላማ እንጂ የግል እና የቡድን ፍላጎት የጋራ ሀገር አይገነባም::

ሌላው ልብ መባል ያለበት ነገር፤ በተለምዶ ‹‹የ60ዎቹ ትውልድ›› የሚባሉ የለውጥ አቀንቃኞች ትግላቸው ምን ነበር? እነማን ምን አደረጉ የሚሉትን በወቅቱ ከነበሩ ሰዎች፣ ወይም በወቅቱ የነበረውን ሁነት ጽፈው ያስቀመጡ ሰዎችን ሰነዶች ማየት ያስፈልጋል:: ያ ባለመሆኑ ይመስላል በተለይም የእነ ጥላሁን ግዛው እና ዋለልኝ መኮንን ጉዳይ በተለያዩ አወዛጋቢ (ወጥ ባልሆነ) መንገድ ሲከራከሩባቸው ይሰማል:: በመሆኑም በዘመኑ የነበሩ ሰዎች የነበረውን ሁነት ሊጽፉልን ይገባል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You