ፋልሴቶ- ነጩ የሙዚቃ ድልድይ

“የነጭና የሰይጣን መልካም የለውም:: በእጅ ከሰጠህ የጭንቅላትህን ሊነጥቅህ ፈልጓል ማለት ነው” ያለኝን ወዳጄን አልዘነጋውም:: በዚህ አስተሳሰብ የሚስማሙ አይጠፉም። ይህን ስል የነጭ ጥላቻ አለብን ማለት ሳይሆን ለሀገራችን ካለን ፍቅርና አሳቢነት የመነጨ ጥርጣሬን ከግምት በማስገባት ነው:: በርግጥ በነጭ የሆነው እንጂ ያልሆነው ምን አለና እንዲያ ቢታሰብ አይፈረድም። ይሁንና ልክ እንደዛሬው ዝነኞችን ዓይነቱ ቅንም አለና “ከስንዴ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” ብለን በጅምላ መፈረጅ አያስችለንም::

መጥፎ መጥፎ አርቅ፤

ደግ ደጉን አምጣልን፤

ሚነጅሰን ሳይሆን፤

የሚመጅነንን::

ማለት ለዚህ ሰው ነው:: ይህም ሰው ፍራንሲስ ፋልሴቶ ነው:: ሐበሻ ሳይሆን ፈረንጅ ነው:: ኢትዮጵያዊ ሳይሆን እልም ያለ ፈረንሳዊ ነው:: ከሙዚቃ ጨረቃ ጋር ብዙ ዓለማትን ዞሯል:: ጥንቅቅ ያለ የሙዚቃ ሊቅ ነው:: ሙዚቃን በጆሮው አሽትቶ፣ በልቡ ማጣጣም የሚችል ነው:: ከቀመሰውና ካጣጣመው ሁሉ ግን እንደ ኢትዮጵያ ሙዚቃ አንጀቱን ያራሰው የለም:: ለዚህም ነው ሀገራትን እያቆራረጠ መዝመቱ:: እየሰማው አድጎ እየሰማው ላለውና ለሚያውቀው የሀገሩ ሙዚቃ ያልሆነውን፣ ምን ጆሮው ቢቆረጥ ትርጉሙን ለማያውቀው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ልቡን ከፍቶ በፍቅር ከነፈበት:: የወደቁትን የትናንትናዎቹን አበቦች አንስቶ ለዛሬ ፍሬዎች አደረጋቸው:: ድንገት ጆሮው የገባች አንዲት ሙዚቃ መላ ሰውነቱን አንዝራ፣ በፍቅር አነሆለለችው::

ለዚህ ሁሉ መነሻ ከሆነው የነጩ ሰው ፍራንሲስ ፋልሴቶ አጋጣሚ ስንጀምር፣ ከሆነው ነገር በፊት የሆነው ታሪኩ እንዲህ ነው…ዘመን ሲወሳ መቼም ያቺ ዘመን ከሁላችንም የትውስታ ማህደር ውስጥ ተሰንቅራ ዛሬም አለች:: ወርቃማው የሙዚቃና የኪነ ጥበብ ዘመን ጭምር ናትና:: እሷም በ1960ዎቹና 70ዎቹ አጋማሽ መካከል ተንፈላሳ እናገኛታለን።

የቁጥሯ ነገር በትክክልም ተሰልቶና ተቆጥሮ ባይሰፍርም የወርቃማዋ ዘመን ወርቆችን ጭና፣ በ70ዎቹ ድንበር አልፋ አጋማሹ ላይ የደረሰችው መርከብ ውጥንቅጧን ያወጣው እክል ገጥሟት ነበር:: በውጥንቅጡ መሃል የተፈጠሩ መልካም ነገሮች እንደነበሩ ባይካድም ወርቃማውን ለጫነች መርከብ ግን በመሃል የዘመን ቤርሙዳ እንዲፈጠር ሆኗል:: በሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም የተዋከበው ፖለቲካና ሌሎችም ውስጣዊና ውጫዊ ማዕበሎች እየተንቀሳቀሱ መርከቧን ከኤርትራም፣ ከሙት ባህርም አንኮታኩተዋታል:: አባላቱ ሁሉ የወርቃማውን ዘመን የመጨረሻ ወርቃማ ጽዋ ከተጎነጩ በኋላ ገሚሱ በስደት፣ ገሚሱም በሞትና በድብርት ከሆነው ሁሉ ቀሪውም ቤርሙዳውን ተሻግሮ ለማስታወሻነት ታየ::

ይሄን ሁሉ ያነሳነው ነጩን ፋልሴቶ ዘንግተን አይደለም፤ ይልቁንስ ይህ ክስተት ከእርሱ መነሻ ጋር የሚገጣጠም ነገር ስላለው ነው:: የወርቃማው ዘመን መጨረሻና የእርሱ መጀመሪያ ሳይተዋወቁ የተላለፉ ናቸው ለማለት አይቻልም:: በአንድም ሆነ በሌላ ያ ታሪክ የርሱም ታሪክ ሊሆን ነው:: እንዴት? ካስባለን… የ1970ዎቹ አጋማሽ ብርጭቆ አንስተው እንኳን “ቺርስ ለሶሻሊዝም” የሚባባሉበት ጊዜ ነበር:: እያንዳንዱ ሰው፣ ሁሉም በየሙያው መስክ አንድ አዲስ ነገር ይዞ ለመምጣትና ለመሥራት ተጣምሮ ወደተባለበት ሁሉ የሚሯሯጥበት እንጂ ቁጭ ብሎ ስለቀድሞ ትዝታው ለማሰብም ሆነ ለማስቀጠል የሚችልበት አልነበረም:: ሁሉም ነገር አዲስ፣ ብዙ ነገርም የማፍረስና የመገንባት አብዮት ነበር::

ይህ እጣፈንታ ለኪነ ጥበብም ደረሰና ለመርከቧ ተንሳፎ መቅረት ምክንያት ሆነ:: እኚያን የሙዚቃ ሸክላዎች እያፈራረቁ ማጫወቱ ከአሸሼ ገዳሜ እንዳይቆጠርበት የፈራም ብዙ ነው:: ቀድሞ ሲደመጡ የነበሩ ሙዚቃዎች ሁሉ በገጠር ከተማው ድር ያደራባቸው ጀመረ:: … እያሉም ጉዟቸው ወደመጥፋት ነበር:: ለእንስፍስፏ የጥበብ አንጀት፣ አትሙቺ ያላት ሙዚቃ ነብስ የጣለው ደጉ ሰው፣ ነጩ ፈረንጅ ፋልሴቶን አንከላውሶ ከፈረንሳይ አስነስቶ አዲስ አበባ ምድር ላይ ጣለው:: ያቺ “መላ መላ” ናት ለዚህ ያበቃችው:: አሁንም ዕድሜ ለርሷ! ዕድሜ ለማህሙድ አህመድ!…

ጊዜው በ1970ዎቹ መጀመሪያ ነው። ነጩ ሰው ፈረንሳዊው ፋልሴቶ አዲስ አበባን ሳይረግጥ በፊት በሀገሩ ውስጥ “ፖይተርስ” በሚሏት ትንሽ ከተማ ውስጥ እየኖረ በአንድ ለትርፍ ባልተቋቋመ ድርጅት ውስጥ ይሠራ ነበር:: የሚኖርባት ፖይተርስ ከፓሪስ አንጻር ስትታይ ምንም እንኳን ትንሽና ጥቂት ሕዝብ የነበራት ብትሆንም የዋዛ ግን አልነበረችም:: በአዲስ አበባ መነጽር ቢመለከቷት ውቤ በረሃን ማለት ናት:: በከተማዋ ውስጥ የሚደገሰው የሙዚቃ ድግስ ሽታው ፓሪስ ላይ ያውዳል:: የዚህ ድግስ አዘጋጆች ደግሞ ፍራንሲስ ፋልሴቶና ሌሎች ወዳጆቹ ናቸው::

ፖይተርስም በነፋልሴቶ ሙዚቃዎች ቀውጢ ነበረች:: ታዲያ ግብዣው እዚያው ለዚያው የሆነ አልነበረም:: በአውሮፓ ቢሉ በአሜሪካ በጊዜው አሉ የተባሉ ሙዚቀኞች ሁሉ የሚሳተፉበት ነው:: ከእኚህ ትልልቅ የሙዚቃ ፈርጦች ጋር ሲቀራረብና ሲጋብዛቸው የፋልሴቶ ትልቁ ዓላማው ታዳሚዎቹን ለማስደሰት በማሰብ ብቻ አልነበረም:: ይልቁንስ በሌላ ሀገራት ውስጥ ያለውን የሙዚቃ ጥበብ ለማወቅና ምርምሮችንም ስለማድረግ እያሰላሰለ ነበር::

የነጩን ሰው የሙዚቃ እጅና እግር ያበቀለች፣ ያቺ የሸክላ ሙዚቃ አጋጣሚ የተፈጠረችው እንዲህ ነበር:-

እንደሌላ ጊዜው ሁሉ ከውጭ የተጋበዙ እውቅ አቀንቃኞች ለዝግጅት ተሰናድተዋል:: ሁሉም ቦታ ቦታውን እየያዘ ቀውጢው የፖይተርስ ከተማ ጨረቃ ቁልቁል ማዘቅዘቅ ጀምራለች:: ገና ከጅምሩ መዓዛው የተለየ ድግስ መደገሱን የሚያሳብቅ ነበር:: በድግሱ ለመገኘት ትኬት ቆርጦም፣ ተገፋፍቶም ለመግባት የሚተናነቀው ብዙ ነው:: ወደዚያ የድግስ ስፍራ ከመጡ ሰዎች ሁሉ የተለየው ሰው ግን አንድ ነገር ይዞ መጣ:: ሲያዩት እንደነገሩ የሚመስል ግን ደግሞ ውስጡ ሌላ ተአምር የያዘ ሸክላ ነበር:: ያ ሰው ሸክላዋን በእጁ እንደያዘ፣ በሰው መሃል አልፎ፣ ፋልሴቶና ሌሎች እንግዶች ሰብሰብ ብለው ወዳሉበት አመራ:: ወደ ፋልሴቶ ጠጋ ብሎም “እንካ ይቺን ነገር ስማት” ሲል እንደ ልዩ መልእክት አቀበለው:: ፋልሴቶ ምንም ጊዜ ለማባከን አልፈለገም:: እየተጣደፈ ሄዶ የሸክላውን ሲዲ ማጫወቻው ላይ አኖረው:: ጠቅ! አደረገና እያጠነጠን ድምጽን እስኪያሰማ አፍታ ጠበቀው:: ማጫወቻው ቴፕ ድምጽ አወጣ…

“ኧረ መላ መላ፤

መላ መላ

“ኧረ መላ መላ…”

ገና በመጀመሪያው መግቢያ የሰማውን ለማመን አቃተው:: የማያውቀውን ሰምቶ ለዘመናት ሲፈልገው የኖረውን ነገር እንዳገኘ ያህል ልቡ በሀሴት ሲመታ ታወቀው:: ሲከንፍ ተመልሶ መጣና አብረውት ለነበሩት ወዳጆቹና የሙዚቃ ባለሙያዎች አስደመጣቸው:: እነርሱም ሙዚቃ እንጂ ስለምን እንደሆን ባያውቁም አጃኢብ ነው! አሉ:: አሁንም ጊዜ ሳያጠፋ፣ ሸክላውን ሬዲዮ ጣቢያ ለሚሠራ ለአንድ ጋዜጠኛ ላከው:: በአይቤክስ ባንድ ተሠርቶ የነበረው የማህሙድ አህመድ “ኧረ መላ መላ” የሬዲዮ ሞገዱን ሳይቀር አነዘረው:: የሰማ ሁሉ “ኧረ ከወዴት አመጣችሁት?” ነበር ጥያቄው::

እንዴት እንደመጣ እንጂ፣ ከወዴት እንደመጣ ፍራንሲስ ፋልሴቶም አያውቀውምና ምላሹ እርሱም ጋር አልነበረም:: ግን ሰማይ ቧጦም ቢሆን የዚህን መነሻ ምንጭ ማግኘት ግዴታው ነበር:: አንድም ጊዜ የመርገጥ አጋጣሚውን አላገኘምና አፍሪካን የሚያውቀው በስም ብቻ ነው:: ስለአፍሪካ ሙዚቃም ጫፍ ጫፉን ያውቃል:: “ኢትዮጵያ” ስለምትባል ሀገር ግን ከዚያ ቀደም በካርታ ላይ ስለመኖሯ እንኳን የሚያውቀው የለም:: የማያውቃት ሀገር፣ በማያውቀው ቋንቋ ልቡን ያስፈነደቀችውን ሀገር ሳያይ ነግቶ ቢመሽ ሞት ነውና ሻንጣውን ብድግ አድርጎ ሊነሳ ሲል ግን ሌላ አንድ ነገር ገጠመው:: ኢትዮጵያ አርማዋን ቀይራ በሶሻሊስትነት ተጠምቃ ነበርና ከኢምፔሪያሊስት ሀገር ዘሎ እንዲሁ መግባቱ የማይታሰብ ነበር:: ዋጋ ከፍሎም ቢሆን ሊኖሩት የሚችሉትን አማራጮች ሁሉ ለመጠቀም ሲያስብ ራሺያን አማላጅ አድርጎ በርሷ በኩል ለመምጣት ወሰነ:: ከፈረንሳይ ራሺያ፣ ከራሺያም ወደ ናፈቃት ሀገር ኢትዮጵያ ገባ::

ፋልሴቶና አዲስ አበባ። ከአዲስ አበባ ሰማይ ላይ፣ ከቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ከወረድክበት ሰዓት አንስቶ የነበረው ነገር እንደምን ነበር? ብላችሁ ብትጠይቁት፤ “እሱንስ አታንሱት፣ ብቻ አይነገር…” ብሎ ዝም ባላችሁ ነበር:: ለዚህ ምክንያቱ እንግዳ ሰው ሲገጥሙት የነበሩት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ናቸው:: ለወትሮ እንግዳ በእቅፏ የምትቀበለው እናት ሀገር ኢትዮጵያ፣ በጊዜው የነበረው የፖለቲካ አየር አውሎ ንፋሱ የበረታበት ነበር:: ከአየር ማረፊያው ብቅ ካለበት ቅጽበት አንስቶ በየፌርማታው፣ መንገዱ ላይ ያለው የፍተሻ አጀብ ውስጡን ሳይቀር ተፈታትኖታል:: ይዞ የሚንቀሳቀሰው ካሜራና መቅረጸ ድምጽ የተከለከሉ በመሆናቸው ሌላ ጣጣ ሆነበት::

አመጣጡና ዋነኛ ግቡ “መላ መላ” ሲል በሙዚቃው ልቡን ያሸፈተውን ማህሙድ አህሙድን ማግኘት ነበርና የማህሙድ ያለህ ማለቱን ጀመረ:: ከዚህም ከዚያም ፈልጎ አስፈልጎ በመጨረሻም አገኘው:: ሁለቱም ከአንድ ጠረጴዛ ፊት ተቀምጠው አወጉ:: ፋልሴቶም የፖይተርስን ግብዣ ለማህሙድ አቀረበለት:: እንኳንስ ለእንዲህ ዓይነቱ ለሚጠቀምበት ዕድል ቀርቶና ለሌላ ለማያገኝበት ነገርም ቢሆን እምቢታን የማያውቀው ትሁቱ ማህሙድም በእሺታ ተቀበለው:: የዓለም ክዋክብት በደመቁባት የፈረንሳይዋ ፖይተርስ መድረክ ላይ ፍንትው ለማለት ተመካክረው ጨረሱ:: በአንድ ወቅት ላይ ጋዜጠኛዋ ብሌኔ “ያንን አጋጣሚ፣ በዚያን ሰዓት ይሰማህ የነበረውን ስሜት ታስታውሰዋለህ?” ስትል በእንግሊዝኛ አፍ ጠየቀችው:: ፋልሴቶ ቃል ከማውጣቱ አስቀድሞ፣ በትዝታ ቅጽበት ሄድ መለስ ካለ በኋላ ነበር “እንዴታ! አሁን ድረስ ዓይኔ ላይ ነው:: አሁንም ድረስ ከውስጤ እንዳለ አለ” ሲል መለሰላትና አሁንም በአፍታ ትዝታ ደፍቆ ወጣ::

ፋልሴቶ የመጣበትን የመጀመሪያ ጉዳዩን ከማህሙድ ዘንድ አሳክቷል:: ግን እቅዱ ማህሙድንና የማህሙድን ሥራዎች ማግኘት ብቻ አልነበረም:: ረዘም ባለ ቆይታ ውስጥ በሁሉም የኢትዮጵያ መንደሮች ውስጥ እየዞረ፣ ሁሉንም የኢትዮጵያን ባሕልና ሙዚቃ ማጥናት ነበር እቅዱ:: ሆኖም ግን ከመጀመሪያው አንስቶ ምቾት የነሳው የፖለቲካው አቀበት አሁንም አልሆንልህ አለው:: ወደ ባለሥልጣናቱ ተመላልሶ እቅዱን ቢተርክላቸውም በጄ! ሳይሉት ቀሩ:: ይህን ለማድረግ እንደማይችል ደጋግመው ነገሩት::

ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላም እቃውን ሸካክፎ፣ ከአስቸጋሪው ሁኔታ ውስጥ እንኳን ይባስ ከመጀመሪያው ፍቅሩ የጠነከረበትን የኢትዮጵያን ባሕልና ሙዚቃ ዞሮ በናፍቆት እየተመለከተ ወደ ሀገሩ ፈረንሳይ ተመለሰ:: ቅሉ እንዲህ ቢሆንም ሲሄድ ግን ባዶ እጁን አልነበረም:: በተቻለው ሁሉ እያነፈነፈ፣ ከያሉበት ያደናቸውንና አሁን እንድናወራለት ያደረጉትን የተወሰኑትን የሙዚቃ ሸክላዎች ይዞ ነበር የተመለሰው::

በእጁ የገቡት የሙዚቃ ሸክላዎች ቀላል የሚባሉ አልነበሩም:: የምርምር ሥራውን ለመጀመርም በትንሹም ቢሆን በቂ ነበሩ:: ቀጣይ ለመሥራት ላሰበው ሥራም ለጅምር የሚሆኑት ያህል ናቸው:: ነገር ግን ፋልሴቶ ስለሙዚቃና ሙዚቀኛ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነው:: አገኘሁ ብሎ ያለፈቃድ፣ በሌሎች ልፋት እንዳሻው ለማድረግ እንደማይችል ያውቀዋል:: በጣም ተጨንቆበትም ነበር:: ሸክላዎቹ ግን አንድ መላውን ሹክ ብለው፣ ወደ አንድ ሰው አመለከቱት::

በአብዛኛዎቹ ውስጥ አሳታሚ ሆኖ ስሙ ወደሰፈረው አምሀ እሸቴ ዘንድ ነበር:: ሲያጠያይቅ አምሀ የሚገኘው አሜሪካን ውስጥ መሆኑ ተነገረው:: ልፋቱ ሳይታየው ይበልጥ ደስ አለው:: ጊዜ ሳያባክን ተነስቶ፣ አምሀን ፍለጋ አሜሪካ ገባ:: እምብዛም ሳይንከራተት ዲሲ ውስጥ አገኘውና ያሰበውን ነገር አዋየው:: አምሀ ግን ሥራው የበርካታ ሙዚቀኞች እንደመሆኑ ብቻውን ለመወሰን እንደማይችልና ይህን ቢያደርግ እንደሚያስወቅሰው ገለጸለት:: ሆኖም ምንም ለማድረግ አልችልም ብሎ ሳይተወው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ከሌሎች ጋር አብሮ እንደሚመክርና የደረሱበትን እንደሚያስታውቀው ነግሮት ተለያዩ::

“ጊዜ ለኩሉ” ይለዋል የሀገሬ ሰው:: ለሁሉም ጊዜ አለውና የሚሆነውም በጊዜው ነው:: ፖለቲካ ፖለቲካን፣ ጊዜም ጊዜን ገርስሶ ከሀገሬው ሰማይ ጥላ ስር ሁሉም ነገር ተለዋወጠ:: የደርግ መንግሥት ዙፋኑ በኢህአዴግ ተነጥቆ 1983ዓ.ም የሚነፍሰው ነፋስ ሌላ ነበር:: ቀደም ሲል ከመርከቧ ተጓዦች የነበረው አምሀ እሸቴም ከ19 ዓመታት በኋላ ተመልሶ ሀገሩ ለመግባት በቃ:: ይህን የሰማ ፋልሴቶም ተከትሎ ከፈረንሳይ ከተፍ አለ::

ዲሲ ላይ መክረው እስቲ ጊዜ እስኪፈታው ተባብለው የነበሩትን ነገር ለመጀመርም መልካሙን የጊዜ አጋጣሚና ሁኔታ ፈጠረላቸው:: የተገናኙት ከምንጩ ላይ ነውና የሥራዎቹን ባለቤት ለማግኘትም ዳገት የሚሆን ምንም ነገር አልነበረም:: ከዳግም ምክክር በኋላም አምሀን የቀኝ እጁ አድርጎ አንድ ሲል ፋልሴቶ ሥራውን ጀመረ::

በ1989ዓ.ም መባቻ ላይ አስቀድሞ በነበሩት የማህሙድ ሥራዎች ቀሪዎቹንም በማከል፣ ከሙላቱ አስታጥቄና ሙሉቀን መለሰ እንዲሁም የሌሎችንም ሰብሰብ አድርጎ “ኢትዮጲክስ” የተሰኘውን ማህደረ ሙዚቃ ለዓለም ገለጠው:: በዓለም ዙሪያ ባሉ ሚዲያዎች ሁሉ እኚህን የኢትዮጵያን ሙዚቃዎች ተቀባበሉት:: ከሙዚቃ ተንታኞች ዘንድ ሊገጥመኝ ይችላል ሲል የፈራው ትችትም ሳይሆን ቀረና በምትኩ አድናቆትና ዝነኝነት ጎረፈ:: በሰሟቸው የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች ልባቸው መለከፉን የሚናገሩ አድማጮችም በዙ:: በጊዜው አሉ ከተባሉት ዓለም አቀፍ ፈርጦች መካከል አንዱ የሆነው፣ ሙዚቀኛው ኤልቪስ ካስቴሎ ሳይቀር ይሄስ የጉድ ነው! ሲል መደነቁን ከፍ አድርጎ ተናገረው:: ለፋልሴቶም ሆነ ለኢትዮጵያ ሙዚቀኞችም ትልቁን የዓለም በር የከፈተ አጋጣሚ ሆነ::

ከዚህ በኋላም ያለምንም እረፍት በየስርቻው ሁሉ እየገባና እያነፈነፈ ሙዚቀኛው ሳይቀር የዘነጋውን ሙዚቃ ማደኑን ተያያዘው:: ለማግኘት አዳጋች ከሆነው የደቡብ ክፍል ድረስ እየወረደ ከወደ ኮንሶ መንደር ሁሉ አልቀረም:: የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችም እየተከታተሉና እየተግተለተሉ ወደ ዓለም ጆሮ መትመማቸውን ቀጠሉ:: “Abyssinia swing” ሲልም በመጽሐፍ ሰድሮታል::

ፋልሴቶ በትውልዱ ፈረንሳዊ፣ በማንነቱ ነጭ ነው:: ይሁንና በሥራው ግን ኢትዮጵያዊ ልንለው ግድ ሆኗል:: ምናልባትም ንፍገት ብናበዛበት እንኳን አንድ ኢትዮጵያዊ የጥበብ ሰው ለእናት ሀገሩ አበርክቶ፣ ውለታን ውሎላታል ብለን በትንሹ ልንነግርለት ከምንችለው ጋር በሚነጻጸር መልኩ ሠርቷልና:: ዛሬ ላይ የምናደምጣቸውን አብዛኛዎቹን የወርቃማ ዘመን ወርቆችን ስናጣጥም “እድሜ ለፋልሴቶ! እድሜ ለነጩ ሰው!” እያልን:: ማንም ይሁን ምን… ነጩ ሰው ፍራንሲስ ፋልሴቶ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ድልድይ ሆኖ ከዓለም አድማጮች ጋር እንዲደርስ መልካሙን ሠርቶልናልና እናመሠግናለን!! ረዥም ዕድሜና ጤና ለሰማንያ ዓመቱ አዛውንቱ ፍራንሲስ ፋልሴቶ!!

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You