አዲስ አበባ፡- የሸገር ከተማን መሠረተ ልማቶችን እና የአገልግሎት ተቋማትን በማሟላት ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።፡
በሸገር ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ጉዮ ገልገሎ እንደገለጹት፤ ሸገር ከተማን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የመንገድ ሥራ፣ የጤና ተቋማት ግንባታ፣ የትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ ዘመናዊ ግብርና ሼዶችንን መሰል የግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
ከባለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በርካታ የልማት ሥራዎች ሲሠሩ ነበር ያሉት አቶ ጉዮ፤ ከእነዚህ መካከልም በኮዬ ፈጬ እየተገነባ ያለው የሸገር ከተማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል አንዱ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ባለፈው በጀት ዓመትም ስምንት ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ስለመገንባታቸውም አውስተው፤ ከተማ አስተዳደሩ በተያዘው በጀት ዓመትም ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ደረጃቸውን የጠበቁ 100 ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ላይ እንዳለ ገልፀዋል፡፡
በሰበታ እና በቡራዩ ክፍለ ከተሞች ሁለት ሆስፒታሎች እየተገነቡ መሆኑን የገለጹት አቶ ጉዮ፤ እነዚህ ሆስፒታሎች ተጠናቀው ሥራ ሲጀምሩ ነዋሪዎች ርቀው ሳይሄዱ የጤና አገልግሎትን በስፋትና በጥራት እንዲያገኙ ያስችላሉ ብለዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ አጠናክሮ እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመው፤ በተያዘው ሁለተኛ ሩብ ዓመት ከ120 ሺህ በላይ የሥራ ዕድሎች መፈጠራቸውን አስታውሰዋል፡፡ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ የሥራ ዕድሉን 300ሺህ ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡
ከ475 ሚሊዮን ብር በላይ ለብድር አቅርቦት እንዲሁም ተጨማሪ 10 ሚሊዮን ብር የፋይናንስ ዘርፉን ለመደገፍ በጀት መያዙንም አመልክተዋል፡፡
የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንጻር የከተማ ግብርና መርሐ-ግብሮችን ተግባራዊ በማድረግ ከተማዋን ልምድ የሚቀሰምባት ማዕከል ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ ለዶሮ እርባታ፣ ለከብት እርባታና ለንብ ማንባት ሥራ የሚያገለግሉ ከአምስት ሺህ በላይ የግብርና ሼዶች መገንባታቸውንም፤ ሁለት ሺህ ሙያተኞች በ65ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የጎጆ ኢንዱስትሪ እያለሙ መሆኑንም አቶ ጉዮ አብራርተዋል፡፡
ነፃነት ዓለሙ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም