ቤተሰቦቻቸው ንብረታቸውን ቀምተው ከቤት በመባረራቸው ምክንያት ወደ ጎዳና እንደወጡ የሚናገሩት አቶ ገብረሚካኤል ገ/ብርሃን፤ ይኖሩበት የነበረው ክፍለ ከተማ ለመቄዶንያ ባደረሰው ጥቆማ መሠረት ወደ ማዕከሉ እንደመጡ ያስታውሳሉ፡፡ እኝህ አባት ወደ ማዕከሉ ገብተው መጦር ከጀመሩ ስምንት ዓመት ሆኗቸዋል፡፡
የተለያዩ የጤና እክሎች እንዳሉባቸው የሚገልፁት አቶ ገ/ሚካኤል፤ ማዕከሉ ባይቀበለኝ ኖሮ ጎዳና ወድቄ ተበላሽቼ እቀር ነበር፡፡ አሁን ማዕከሉ ግን እያበላ፣ እያጠጣ፣ እያከመና እየተንከባከበ በወጉ ይዞኛል፡፡ አሁን ላይ በተለያየ መንገድ ማዕከሉን እያገዙ መሆኑን ይገልፃሉ።
በቅርቡም አረጋውያኑን በመወከል አዲግራት ድረስ በአውሮፕላን የሄዱበትና የማዕከሉን በከተማው የሚገኝ ቅርንጫፍ ጉዳይ ያስፈፀሙበት አጋጣሚ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ቅርንጫፉ የተከፈተው አንዲት የውጭ ዜጋ ባበረከተችላቸው ቤት እንደነበርና የእሱን ካርታ ለመጨረስ እየሠሩ ባሉበት ወቅት የከተማ አስተዳደሩም የሕንፃ መሥሪያ ቦታ እንዳበረከተላቸው ይገልፃሉ፡፡
ከዚህ ባሻገር በተለያዩ ጊዜያት አረጋውያኑን በመወከል ከማዕከሉ መሥራች አቶ ቢኒያም በለጠ ጋር በመሆን በማዕከሉ ድጋፍ ዙሪያ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ የገለፁት አቶ ገ/ሚካኤል፤ በእነዛ አጋጣሚዎች ቤታቸውን ሳይቀር ለማዕከሉ የሰጡ በጎ አድራጊዎች እንደነበሩ ያነሳሉ፡፡
መቄዶንያ ገመናችንን ሸፍኖልናል የሚሉት አቶ ገ/ሚካኤል፤ በመቄዶንያ ማዕከላት ከሚገኙት ከስምንት ሺህ በላይ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን የቅርብ ክትትል የሚሹ ናቸው፡፡ ቀለብና ሕክምናም ሌላኛው ወጪ መሆኑን ገልፀው፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ አይለየን የሚል ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ፡፡
የማዕከሉ መሥራች የሆኑት አቶ ቢንያም በለጠ በበኩላቸው የጎዳና ኑሮ ከመታረዝና ከመራብ ባሻገር ብዙ መከራዎች እንዳሉት ይገልፃሉ፡፡ ተገዶ መደፈርና ሕይወትን ማጣት የመሳሰሉ ጉዳቶችን እንደሚያስከትል ገልጸው፤ በቅርቡም አራት ወይም አምስት ሴቶች ተደፍረው ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ የተደረገበት አጋጣሚ እንደነበር ይገልፃሉ፡፡
በተለይ በክረምት ወቅት በብርድ ምክንያት ጎዳና ላይ እንደሚሞቱ አንስተው፤ መቄዶንያ ከጎዳና አንስቶ በሰው ድጋፍና ሸክም ያስገባቸው ሰዎች ከሕመማቸው ድነው ድርጅቱን በተለያየ ሥራ እያገዙ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
ወገኖቻችንን ከእንዲህ ያሉ ችግሮች መታደግ ከፈጣሪም ትልቅ ዋጋ ስላለው ሁሉም ሰው ባለው አቅም እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበው፤ እገዛችሁ አልጋ ላይ የቀረውን ሰው እንዲሄድ የሚያደርግ፣ ምንም አያደርግም የተባለ ሰው የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት የሚለውጥ ነውና ድጋፋችሁ አይለየን ይላሉ፡፡
ቋሚ ገቢ በሌለበት ሁኔታ የማዕከሉ የቀን ወጪ ሁለት ሚሊዮን ብር መድረሱን የገለጹት አቶ ቢኒያም፤ የግለሰቦችና የተቋማት እገዛ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ፡፡ በተለይም የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ለሚጀመረው የማዕከሉ ባለ15 ወለል ሕንፃ ማጠናቀቂያ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ላይ ሁሉም አካላት ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ያቀርባሉ፡፡
የሆስፒታሉን ግንባታ ለማጠናቀቅ አራት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ገልፀው፤ የካቲት
1 በሰይፉ ኦንላይና ኢቢኤስ ሾው ዩትዩብ ቻናል የቀጥታ ስርጭት ገቢ ማሰባሰቢያው እንደሚጀመር ይገልፃሉ። ለዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብርም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከወዲሁ ሁለት ሚሊዮን ብር ገቢ ማድረጉን አስታውሰው፤ ኮተቤ ዩኒቨርሲቲና ሌሎችም ተቋማት በስማቸው ድጋፍ ማድረግ መጀመራቸውን አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንደሚጎበኟቸው ገልጸው፤ ለዚህም ምስጋናቸውን በመግለፅ አሁንም የግለሰቦች እንዲሁም የተቋማት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕመምተኞች መርጃ ማዕከል ከተጨናነቁ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች አንስቶ እስከ 44 ከተሞች ድረስ ጎዳና የወደቁ ወገኖችን በማንሳት ሕይወታቸው መልሶ እንዲያገግም ዕድል እንደሚሰጥ ከማዕከሉ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በቀጣይም በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ለመሥራት እና የቅርጫፉን ቁጥር 240 ለማድረስ እንቅስቃሴ መጀመሩን መረጃው ይገልፃል። ባሉት ማዕከላትም አልጋ ቁራኛ የሆኑ እንዲሁም የአዕምሮ ሕሙማንን ጨምሮ ከ8ሺህ በላይ ሰዎችን እየረዳ ይገኛል፡፡
ነፃነት ዓለሙ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም