አዳማ፡- ባንኩ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአነስተኛ ሥራ ለተሠማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ምቹ የብድር አገልግሎት ሥርዓትን በመዘርጋት ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ማበደሩን የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ገለጸ፡፡
የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በተቋም ደረጃ ለ6ኛ ጊዜ የኅብረት ሥራ ቀንን ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ባከበረበት ወቅት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደርቤ አስፋው በሰጡት ማብራሪያ፤ ባንኩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተዘጋጀው ምቹ የብድር አገልግሎት ሥርዓት ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ አበድሯል፡፡
አብዛኛዎቹ የብድሩ ተጠቃሚዎች ወጣቶች እንደሆኑና ከእነዚህም ውስጥ የሴቶች ቁጥር 65 በመቶ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የብድር አገልግሎቱን ከክልሉ ውጭ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ጭምር ሲጠቀሙበት እንደነበር አስታውሰው፤ በአጠቃላይ ከ700 በላይ የሚሆኑ ዜጎች መበደራቸውን አብራርተዋል፡፡
ባንኩ ሲመሠረት የግብርና ሥራን መሠረት አድርጎ እንደነበር ጠቅሰው፤ በአሁኑ ጊዜ የፋይናንስ እጥረት ላለባቸውና በተለያየ ሥራ ለተሠማሩ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የብድር አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡ የምቹ ብድር አገልግሎት ሥርዓት ተበዳሪዎች ቴክኖሎጂን በመጠቀም ባሉበት ቦታ ሆነው የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መተግበሪያ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት በሌለባቸው ገጠራማ አካባቢዎች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግም በፀሐይ ብርሃን ኃይል በማመንጨት ኅብረተሰቡ ኢንተርኔት አግኝቶ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ስለመደረጉም ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም 70 የሚሆኑ የኢንተርኔት አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ተዘጋጅተው ጥቅም እየሰጡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ምቹ የብድር አገልግሎት፤ አርሶ አደሩ የራሱን የባንክ ደብተር (አካውንት) እንዲያወጣና ከባንክ ጋር እንዲለማመድ ያደረገ፤ የፋይናንስ እጥረት ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ያስቻለ፤ የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች በብድር ሥራ ጀምረው ከተደራጁ በኋላ ፈቃድ አውጥተው እንዲሠሩ ያደረገ መሆኑን አቶ ደርቤ ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የእርሻ እና የማኅበራት ክፍል ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ዮሐንስ ሀምቢሳ በበኩላቸው ፤ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የዛሬ 20 ዓመት የተቋቋመ እንደሆነ እና 60 በመቶ የሚሆነው የባንኩ ድርሻ የማኅበራት እና የአርሶ አደሮች ሀብት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ማኅበራቱ ቀደም ሲል ከነበሩበት ደረጃ አሁን ትልቅ ሃብት ወደ ማፍራት እንደተሸጋገሩም ገልጸዋል፡፡
የግብርናው ዘርፍ የፋይናንስ ችግር አለበት ያሉት አቶ ዮሐንስ፤ ለዚህም አንዱ ችግር ባንኮች ለዘርፉ ብድር የመስጠት ፍላጎት ማጣት እንደሆነ ተናግረዋል። የግብርና ሥራ ለተፈጥሮ አደጋ የተጋለጠ መሆኑ እና አርሶ አደሮች አነስተኛ መሬት ይዘውና ተበታትነው ያሉ መሆናቸው ባንኮች ባላቸው የፋይናንስ አሠራር መሠረት እንዳያስተናግዷቸው ምክንያት ነበሩ ብለዋል።
የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ትኩረቱን አርሶ አደሩ ላይ አድርጎ ምቹ የብድር አገልግሎትን በመዘርጋት በነባሩ የብድር አገልግሎት መበደር ለማይችሉ ዜጎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
በዚህም የሙከራ ጊዜውን ጨምሮ በሁለት ዓመት ውስጥ በርካቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡ የምቹ ብድር አገልግሎት ተጠቃሚዎች ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን (ሞባይላቸውን) በመጠቀም ብቻ፣ ምን አይነት ነገር ሳያሲዙ ብድር የሚያገኙበት አሠራር እንደሆነም አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል፡፡
በመርሐ-ግብሩ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱላዚዝ ዳውድ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራሁ ሽጉጤ፣ የፌደራልና የክልል ሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን እሁድ ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም