የጋምቤላ ብሔራዊ ክልል ሊጎበኙ በሚችሉ ሀብቶቹ በእጅጉ ይታወቃል፤ ወደ ክልሉ ዋና ከተማ ጋምቤላ በየብስ ወይም በአውሮፕላን በመጓዝ እነዚህን የተፈጥሮ፣ ሰው ሠራሽና ባሕላዊ የቱሪዝም ሀብቶች መጎብኘት ይቻላል::
ክልሉ በተለይ በተፈጥሮ ሀብቶቹ በእጅጉ ይታወቃል:: ለጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ጥበቃና ልማት ለማድረግ መንግሥት፣ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣንና በአፍሪካ 12 ሀገሮች 23 ፓርኮችን በማስተዳደርና በማልማት ሥራ ላይ ከተሰማራው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በቅርቡ ስምምነት በተፈጸመበት እለት እንደተጠቆመው፤ የጋምቤላ ክልል ለቱሪዝም አገልግሎት ሊውሉ በሚችሉ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች የበለጸገ ነው::
ከእነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል የሚጠቀሰው አብዛኞቹን የተፈጥሮ ሀብቶችን አካቶ የያዘው ይሄው የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ነው:: ፓርኩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዱር እንስሳትና አእዋፋት እንዲሁም በርካታ ወንዞች፣ ሐይቆች፣ ኩሬዎችና ፏፏቴዎች ይገኙበታል::
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርእሰ መስተዳደር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ከጋዜጠኞች ለቀሩባላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ከሌሎች የሀገሪቱ ፓርኮች ጋር ሲነጻጸር የጋምቤላ ክልል ሙሉ ለሙሉ ፓርክ ነው ሊባል እንደሚችል ገልጸዋል:: ሌላ አንድ የክልሉ ባለሥልጣን ሰሞኑን ከገለጹት መረዳት እንደቻልነውም፤ በክልሉ አንድ ዞን ያለው የደን ሀብት ሲታስብ ዞኑን ሙሉውን ፓርክ ሊያሰኘው ይችላል::
የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ከደቡብ ሱዳን ሁለት ፓርኮች ጋር የሚዋሰንና የዱር እንስሳቱም ወቅቶችም መሠረት ባደረገ መልኩ አንዴ በኢትዮጵያ ሌላ ጊዜ በደቡብ ሱዳን እንደሚገኙ ከክልሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል:: ይህ ሁኔታም የዱር እንስሳት ድንበር የላቸውም ለሚለው እንድ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል::
በጋምቤላ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም መዳረሻና ጥናት ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ደርባቸው ሸዋለም እንደሚሉት፤ ክልሉ ለቱሪዝም መዳረሻነት ሊያገልግሉ የሚችል የተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽና የባሕል ሀብቶች ባለጸጋ ነው::
የጋምቤላ ቱሪዝም ሲነሳ በዋናነት የሚጠቀሰው የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ መሆኑን ጠቅሰው.፣ ፓርኩ የሀገሪቱ ግዙፉ ፓርክ መሆኑን ተናግረዋል:: ይህ ፓርክ በውስጡ አያሌ የዱር እንስሳትና አእዋፋትን አቅፎ ይዟል:: በያዛቸው በርካታ የእንስሳት እና የአሳ ዝርያዎችም በእጅጉ ይታወቃል ሲሉም አብራርተዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ የዱር እንስሳቱ ክረምት ላይ ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ሱዳኑ ቦማ ብሔራዊ ፓርክ ይሰደዳሉ፤ ወደ ደቡብ ሱዳን ከሚገቡት እንስሳት መካከል የአንቴሎፕ ዝርያዎች ይገኙበታል፤ ሌላው ብርቅዬ የሚባለው የአጋዘን ዝርያ ነው:: እንስሳት በበጋ ወቅት፣ ውሃ ሲጎድል ወደ ጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ይመለሳሉ::
ሌላው የክልሉ የተፈጥሮ ቱሪዝም መዳረሻ በመጀንግ ብሔረሰብ ዞን ሜንጊሽ ወረዳ የሚገኘው ቡሬ ሀይቅ ይጠቀሳል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ አምስት በዩኔስኮ ከተመዘገቡ አያሌ ብዝሀ ሕይወቶች /ባዮስፌሮች / ከሚገኙባቸው ባየስፌሮች መካከል የጋምቤላው የመጀንግ ባዮስፔር አንዱ ነው:: ባዮስፌሩ በርካታ የዱር እንስሳት፣ አእዋፋት፣ ወንዞችና ፏፏቴዎች ይገኙበታል::
አቶ ደርባቸው እንዳብራሩት፤ ክልሉ ባሮ፣ አኮቦ፣ ጊሎና አልዌሮ የተሰኙ ክረምት ከበጋ የሚፈሱ አራት ትልልቅ ወንዞች ባለቤት ነው፤ በርካታ ኩሬዎችና ረግራጋማ ቦታዎች መገኛም ነው፤ በኢታንግ ወረዳም ሀይቅ በርካታ የአሳ ዝርያ የሚገኘበት ትልቅ ሀይቅ አለ:: ታዬ የሚባል ሀይቅም አለ::
ሌላው የክልሉ መስህብ የታታ ሀይቅ ነው፤ ከዚህ ትልቅ ሀይቅ አቅራቢያ የጊሎ ወንዝ ይገኛል፤ የአኙዋክ ብሔረሰብ አባላት በዚህ ወንዝ በመጠቀም በባሕላዊ መንገድ አሳ ያስግራሉ:: ሀይቁ ከጋምቤላ ከተማ 119 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል::
ከፍተኛ ባለሙያው በአበቦ ወረዳ የሚገኘው የአልዌሮ ግድብ ለቱሪስት መስህብነት እየዋለ እንደሚገኝ ተናግረዋል:: ይህ ሰው ሠራሽ ሀይቅ ለመስኖ ልማት በሚል በደርግ መንግሥት በተገነባ ግድብ የተፈጠረ ሀይቅ ነው ሲሉ አመልክተው፣ ከጋምቤላ ከተማ 47 ኪሎ ሜትር ርቀት እንደሚገኝና በርካታ የአዞና የአሳ ዝርያዎች ያሉበት መሆኑንም አመልክተዋል::
ክልሉ በአሳ ሀብት ዝርያዎቹም እንደሚታወቅ ተናግረዋል፤ በክልሉ ወደ 102 ዓይነት የአሳ ዝርያዎች ይገኛሉ:: ከሀገሪቱ የአሳ ዝርያዎች 75 በመቶው በዚህ ክልል እንደሚገኙ ይናገራል:: ከእነዚህ ውስጥ ናይል ፕርች የሚባለው የአሳ ዝርያ በክልሉ ይገኛል፤ አሳው ከ100 እስከ 110 ኪሎ ይመዝናል ሲሉም አብራርተዋል::
ባሮ ወንዝ ሌላው የቱሪስት መዳረሻ ነው፤ ከተማዋን ለሁለት ከፍሎ ያልፋል፤ ድልድዩ 315 ርዝመት 15 ስፋት 12 ሜትር ጥልቀት አለው:: የአግዜር ድልድይ የሚባል ለቱሪስት መስህብ ሊሆን የሚችል ሥፍራም በክልሉ ይገኛል:: እንግሊዞች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተመባበር የገነቡት ታሪካዊ ወደብም ሌላው መስህብ ሊሆን የሚችል ሲሆን፣ በሀገሪቱ የውሃ ላይ ትራንስፖርት ታሪክ ሲነሳ የጋምቤላው የባሮ ወንዝ አብሮ ይጠቀሳል:: አሁን በእዚህ ወንዝ ላይ የጀልባ ጉዞ ይደረጋል::
ባሕላዊዎቹን ስንመለከት ደግሞ የክልሉ ነባር ብሔረሰቦች የሆኑት የአኝዋክ፣ ኑዌር፣ መዠንገር፣ ኮሞ፣ ኑዌርና አፓና ብሔረሰቦች አኗኗር፣ ባሕላዊ ቁሶች፣ ዘፈኖችና ውዝዋዜዎች እና ሌሎች ባሕላዊ ሥርዓቶች የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ ናቸው::
በጋምቤላ ከተማ የተለያዩ መካነ መቃብሮች በቅርስነት ተይዘዋል:: ከእነዚህም መካከል የኮንጎና ቤልጂየም ወታደሮች የተቀበሩት ስፍራ አንዱ ነው፤ ከ1900 እስከ 1941 ድረስ አርመኖች ግሪኮች አረቦች የተቀበሩበት ስፍራም አለ:: እነዚህም ለቱሪስት መስህብ በመሆን ያገለግላሉ::
ከክልሉ የቱሪስት መስህቦች የለማ ተብሎ የሚታሰበው የቡሬ ሀይቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሀይቁ ውብ ኢኮሎጂ እንዳለው፣ መጎብኘት ለሚፈልግም መንገድና ሎጅ የተገነባለትም መሆኑን ጠቁመዋል::
ኢታንግ ወረዳ የሚገኘው ሀይቅ መንገድ ያለውና ሊጎበኝ የሚችል መሆኑን ጠቅሰው፣ ባሮ ወንዝ ለመዝናናትም ለውሃና ስፖርትም ምቹ መሆኑን፣ የኦልዌሮ ግድብም እንዲሁ ከጋምቤላ ከተማ ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ፣ መንገድ ያለውና ሊጎበኝ የሚችል ነው::
ኮቪድ እና ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ ክልሉን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር በተለይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ፍሰት የተቀዛቀዘበት ሁኔታ እንደነበርም ጠቅሰው፤ የሀገር ቱሪስት ፍሰቱ ግን ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል:: በክልሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በብዛት ይንቀሳቀሳሉ፤ ኮንፈረንሶች በብዛት ይካሄዳሉ፤ ይህም ለሀገር ቱሪዝም ተስፋ ሰጪ መሆን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ሲሉም አስታውቀዋል::
የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ የሚያነቃቁ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል:: በቅርቡ በአንዳንድ ቴክኒካል በሆኑ ጉዳዮች ላይ እገዛ የሚያደርግ ከቱሪዝም ሚኒስቴር የመጡ ባለሙያዎች በክልሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል::
በባሮ ወንዝ ዳርቻ ላይ የመረጃ ማዕከልና ወጣቶች ተደራጅተው ወደ ሥራ የሚገቡበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሰሞኑን ውል በመፈራረም ወደ ሥራ እየተገባ መሆኑንም አመልክተው፤ በዚህም የወጣቶች መዝናኛና የቱሪስት የመረጃ ማዕከል ይገነባሉ፤ አምስቱን የክልሉን ነባር ብሔረሰቦች ታሳቢ ያደረገ ዲዛይን ተሠርቶ የሚተገበር ይሆናል ብለዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ አካባቢውን የሚመስል የአምስቱን ብሔረሰቦች ባሕል የሚያንጸባርቅ መዝናኛ ማዕከል ይገነባል፤ ወጣቶች የሥራ እድል የሚፈጠርበትም ይሆናል:: ስፓርታዊ እንቅስቃሴዎች የሚካሄድበት ሥፍራም ተያይዞ ይሠራል፤ ጋምቤላ በብስክሌትና ቮሊቦል ይታወቃል:: የሚገነባው ማዕከልም ይህን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ የወጣቶች የመዝናኛ ማዕከል ይሆናል:: በጀቱ በቱሪዝም ሚኒስቴር የሚሸፈን ይሆናል::
የዛሬ ሳምንት አካባቢ የቱሪዝም ንቅናቄ ሳምንትን ምክንያት በማድረግ የሚመለከታቸውን አካላት ያሳተፈ መድረክ ምክትል ፕሬዚዳንቱ በተገኙበት መካሄዱንም ጠቅሰዋል:: በክልሉ ለቱሪስቶች የሚሆኑ ማረፊያ ሥፍራዎች እንዳሉ ገልጸው፣ አንድ ባለኮከብ ሆቴል ብቻ እንዳለም ተናግረዋል:: ይህም ለዓለም አቀፍ ቱሪስቱ የሚሆኑ መሠረተ ልማቶች ውስንነቶች ስለመኖራቸው እንደሚያመላክት አስታውቀዋል::
የጋምቤላ ብሔራዊ ፖርክን ለመጠበቅና ለማልማት ከአፍሪካን ፓርክስ ጋር የተደረገው ስምምነት የቱሪዝም ዘርፉን ምን ያህል ይጠቅማል በሚል የተጠየቁት ከፍተኛ ባለሙያው፣ ‹‹አፍሪካን ፓርክ በአንዳንድ ጉዳዮች ሳቢያ አካባቢውን ለቆ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በፈረንጆቹ 2000 አካባቢ የተወሰነ ሥራ ሠርቷል›› ሲሉ አስታውሰዋል:: አፍሪካን ፓርክስ በአፍሪካ ፓርኮችን በማስተዳደር ልምዱ አለው ሲሉ ጠቅሰው፣ አሁን በደጋሚ መጥቶ ስምምነትም ተፈርሟል፤ አብዛኛው ሥራ ፓርኩን ማልማት ይሆናል:: ሲሉ ገልጸዋል::
በኬንያ፣ በታንዛኒያ የቱሪዝም ዘርፉ የምጣኔ ሀብታቸው የጀርባ አጥንት ከሚባሉት መካከል ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ የእኛም ፓርክ ከለማ በዚህ አይነት መልኩ ጥቅም ያስገኛል ብለዋል::
የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን ለመጠበቅና ለማልማት ከአፍሪካን ፓርክስ ጋር የተደረገው ስምምነት ለክልሉ ቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ በወቅቱ ተጠቁሟል:: የድርጅቱ የመጀመሪያ ሥራ የሚሆነው የመሠረተ ልማት ግንባታ እንደሚሆን ተጠቁሟል:: ከዚያም ወደዋናው የማልማቱ ሥራ እንደሚገባም ተመላክቷል::
የክልሉ ርእሰ መስተዳደር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ፓርኩ ከሌሎች ክልሎች ፓርኮች ጋር ሲነጻጸር ክልሉ በሙሉ በፓርክ ነው ብሎ መናገር ያስችላል ሲሉ ጠቅሰው፣ የትኛውም የክልሉ አካባቢ ብትንቀሳቀስ የዱር እንስሳት ታገኛለህ:: በተለያዩ ምክንያቶች ከእነዚህ እንስሳት አንዳንዶቹ ክክልሉ የራቁበት ሁኔታ አለ፤ እንስሳቱ ከሰዎች እንቅስቃሴዎች በሚመነጩ ድምጾች ሳቢያ ሊርቁ ስለሚችሉ የእንስሳቱን አካባቢ ከሰው እንቅስቃሴ ነፃ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል::
‹‹ፓርኩ በጣም ይጎበኛል:: የሰላም ችግር ስለነበረ ጎብኚዎች ወደ ክልሉ ለመምጣት ተቸግረዋል:: በተለይ ከታኅሣሥ ወር አንስቶ ጎብኚዎች በብዛት ወደ ክልል የሚመጡበት ሁኔታ አለ:: ማንም ሰው ቢመጣ ፓርኩን መጎብኘት ይችላል ሲሉ ጠቅሰው፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ አለመካሄዱንም ተናግረዋል:: የተወሰኑ ቦታዎች ላይ መንገዶች አሉ:: እነዚያን በመጠቀም መጎብኘት ይቻላል ሲሉም ጠቁመዋል::
ያንን ለማድረግ ክልሉ በቅድሚያ ማስተዋወቅ ላይ መሥራት እንደሚኖርበት ተናግረው፣ ጎብኚዎችን ለመሳብ በድህረ ገጾች፣ በመገናኛ ብዙሃን፣ በብሮሸሮች አማካይነት ፓርኩን ለማስተዋወቅ እየተሠራ ነው ይላሉ፤፡ መሠረተ ልማት መሥራት ከኛ አቅም በላይ ስለሆነ ነው በዚህ ላይ በትኩረት መሠራት ውስጥ የገባነው ብለዋል::
ድርጅቱ ለፓርኩ አስፈላጊ በሆኑ በአስተዳደር፣ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች በሆኑት ህንጻዎች እንዲሁም ተሽከርካሪዎችና አውሮፕላን ማረፊያዎች አተኩሮ ይሠራል::
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ አሁን በተደረሰው ስምምነት መሠረት መሠረተ ልማቱ ከተዘረጋ ማንም መጥቶ ፓርኩን መጎብኘት ይችላል፤ በክልሉ ፍሬያቸው እንደ መድኃኒትም ምግብም የሚያገለግሉ ዛፎች ሞልተዋል:: በውሃ አካላትም አሳን ጨምሮ ልዩ ልዩ ብዝሀ ሕይወቶች አሉ:: ወንዞቹ ክረምት ላይ ሲሞሉ ሜዳውን ሁሉ ያጥለቀልቃሉ፤ በጋ ሲሆን እየጎደሉ ሲሄዱ አሳ በብዛት ይመረታል:: በዚህ ወቅት ያንን አሳ ለማጥመድ ማህበረሰቡ በብዛት ወንዞች አካባቢ ይሄዳል:: ይህም ይህ ሀብት ለቱሪዝም መስህብነት ሊውል እንደሚችል ያመለክታል::
እንደ ክልል ደግሞ የጋምቤላ ከተማን የኮሪደር ልማት ለማካሄድ አቅደናል፡ አሁን ዲዛይን እየተሠራ ነው፤ በክልሉ ዋና ከተማ ጀምረን ወደ ወረዳዎች እንወርዳለን:: በዚህ ላይ ውይይት እያደረግን ነው፤ ክልሉን ወደ በኋላ የመለሰው የሰላም መናጋት ነው:: ሰላም ለማምጣት ሰፊ ጊዜ ሰርተናል፤ እንደ ሌሎች ክልሎች ልማቱን ለማስቀጠል የሚያስችል ሁኔታ እንደ ሰላሙ ሁሉ ክልሉ ከፈጠረ በኛ አቅም የሚሠሩትን እኛ እንሠራለን፤ በፌዴራል ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሠሩ ካሉ ምቹ ሁኔታ እንፈጥራለን ሲሉ አብራርተዋል::
ከክልሉ የቱሪዝም መስህቦች መካከል በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙት የዱር እንስሳት ይጠቀሳሉ፤
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን እሁድ ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም