አዲስ ሙሽራ ሠርገኛ ላይ እንደረጨው ሽቶ እኔንም የእፅዋቱ ስብስብ በራሱ ለየት ያለ ለዚያውም በቆንጆ ሽቶ ጠረን አፍንጫዬን አወደው። ሥፍራው ከተፈጥሮ ጋር ልብ ለልብ ለመግባባት የተሠራ ይመስላል። ዕጽዋቱ ውበታቸው፣ ፍካታቸው፣ ወጣ ገባ አፈጣጠራቸው፣ ጉራማይሌ ቁመታቸው በጥበቡ ለሠራቸው አምላክም፣ ወዲህ ደግሞ ለሚንከባከባቸው ሰውም ምስጋና ይግባህ ከሚል የደስታ ቃላት በዘለለ ከቶውንም ሊገልፃቸው የሚችል አንዳች ነገር ያለ አይመስልም። በፈጣሪ ጥበብ የበዙት እጽዋት በጥበብ ከሚንከባከባቸው መቶ አለቃ ባዩህ ያደሳ ጋር ለዘመናት ወዳጅነት ፈጥረው ግማሽ ክፍለ ዘመን ሊደፍኑ ጥቂት ዓመታትን እየተጠባበቁ ነው። እፅዋቱ ባዩህን፤ ባዩህም እፅዋቱን ላትተውኝ ላንተውህ ተባብለው የተማማሉ ይመስል ለ40 ዓመታት አብረው ዘልቀዋል። አይ ወዳጅነት፤ አይ ፍቅር ዓጃኢብ እኮ ነው!
የመቶ አለቃ ነገር
የተወለዱት በቱሉ ቦሎ በቾ ወረዳ ባሳ በምትባል መንደር ነው። አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ፊታውራሪ ኃይለጊዮርጊስ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደጅአዝማች ገረሱ ዱኪ ተምረዋል። ከዚያም በ1966 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተቀላቅለው የሁለት ዓመት ኮርስ አጠናቀው በ‹‹ኤር ክራፍት ቴክኒሺያን›› ሆነው ተቀጠሩ። በዚህ ሥራቸው ድሬዳዋ፣ አስመራ እና ቢሾፍቱ ተዘዋውረው ሰርተዋል። ስምንት ዓመት ከሠሩ በኋላም የመኮንንነት ማዕረግ ተቀዳጁ። በሂደት ደግሞ ማናጅመንት ፎሬን ሪሌሽን ድፕሎማቸውን አግኝተዋል። በ1981 ዓ.ም ደግሞ ወደ ራሺያ ሄደው የሰባት ወራትን ስልጠና ወሰዱ። በተለይም የወታደራዊ ሎጂስቲክስ አገልግሎት ትምህርትን በሚገባ ከቀሰሙ በኋላ ወደ እምዬ ሀገራቸው ተመልሰው የተጣለባቸውን ኃላፊነት ይወጡ ጀመር።
ከውትድርና ስንብት
በውትድርና ዓለም ከቆዩ በኋላ ሥራውን ለመልቀቅ ወሰኑ። ሻምበል የሚለውን ማዕረግ ለማግኘት በተቃረቡ ጊዜ ነበር ሥራውን ያቆሙት። በመሰረቱ ከራሺያ መልስ ኢህአዴግ ስልጣኑን ለመያዝ በተቃረበ ጊዜ እንኳን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ይወጡ ነበር። በሎጀስቲክስ ሥራቸው ለወታደር ስንቅ እያቀረቡ በርካቶችን ከውሃ ጥማት፣ ከልብስ እርዛትና ከምግብ ርሃብ ታድገዋል የወታደራዊ ሥነምግባርን ሳያጓድሉ።
ሌላው ቀርቶ ኢህአዴግ ከገባ በኋላ የደርግ ወታደር ቢበተንም እርሳቸው ለኢህአዴግ ወታደር ምግብ ሲቀርብ ሎጀስቲክሱን አቀላጥፈዋል። በእርሳቸው እምነት ስራዬ ሰብዓዊነት ያማከለ እንጂ የጠላት ጦር እያሉ ወንድምን ከወንድም መለየት አይደለም ይላሉ። በዚህ የተነሳም ከሁለቱም ወገን ያኮረፋቸውም እንደሌለ ይልቁንስ በአቋማቸው ያደነቃቸው ሰው እንደበዛ ያስታውሳሉ።
በመጨረሻ ግን ከአየር ኃይል ወጥተው በራሳቸው መንቀሳቀስ ጀመሩ። ገና በልጅነታቸው ይመስጣቸው ወደነበረው ችግኝ ማፍላትና የማስዋብ ሥራ ጠቅልሎ ለመግባትም ወሰኑ። ከዚያም ኑሯቸውን በቢሾፍቱ አድርገው ችግኝ እያፈሉ በዚያው መኖር ጀመሩ። በእርግጥ ችግኝ ማፍላቱ ቀላል ቢሆንም፤ ሽያጩ እንዳሰቡት ቀላል አልሆነም። ወደ መንገድ ዳር እየወጡም እጽዋቱን ይሸጡ ነበር ግን ብዙም የሚገዛቸው ባለመኖሩ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ብዙ ተቸግረዋል። ግን ተስፋ ሳይቆርጡ መስራታቸውን ተያያዙት።
በዚህ ሂደት ላይ ሳሉ በ1984 ዓ.ም የቃለ ሕይወት በቤተክርስቲያን በዚህ ዘርፍ ላይ ትሠራ ስለነበር ሽያጭና የማስተዋወቅ ሥራ ላይ ተቀጠሩ። በ1988 ዓ.ም ደግሞ ግሪን ፎረስት የሚባልና በአቶ ሙላት የሚመራ ድርጅት ውስጥ ማናጀር ሆነው በ600 ብር ተቀጠሩ። በወቅቱ ሂልተን እና ሸራተን ሆቴል በሚካሄዱ ስብሰባዎችንም መካፈል ጀመሩ፤ ሰዎችንም ተዋወቁ በዘርፉ ላይ የሚካሄዱ ሁነቶችን መከታተል ጀመሩ። የአበባ እግዚብሽኖችን ማዘጋጀትና መካፈልንም አዘወተሩ። በዚህም የእህል ውሃቸው ነገር እየተሳካ እያማረ ከእጽዋትም እየተቆራኘ መጣ።
በአጋጣሚ ግን በፖለቲካዊ ጫና የተነሳ አቶ ሙላት አገር ጥለው ወደ ካናዳ ተሰደዱ። መቶ አለቃ ባዩህ እርሳቸው ማናጀር ስለነበሩ የሠራተኞችን ደመወዝ ለመክፈል ተገደዱ። አበባውንም፣ እንጨቱንም ብቻ ያለውን ሃብት ሸጠው ከፈሉ። በዚህ ማግስት ግን በዘርፉ ላይ ያካበቱት ልምድ ስለነበር ዝም ብሎ መቀመጡን አልወደዱም። በ1992 ዓ.ም ‹‹ግሪን ፓራዳይዝ ጋርደን›› ብለው የራሳቸውን ሥራ ጀመሩ። በዓመታት ያካበቱት እውቀትና ልምድ ወደስኬት መራቸው- በቢሾፍቱ ከተማ
ብቸኛው መሐንዲስ
በረጅም ጊዜ ባካበቱት ልምድ በላንድስኬፕ ‹‹ብቸኛው ፈቃድ ያለኝ ሰው ነኝ›› ብለዋል መቶ አለቃ። በዚህም ደስተኛ ናቸው። መንግስትም ለዚህ ሙያቸውም ያግዝ ዘንድ በ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ከቀረጥ ነፃ የሆነና አስቸጋሪ መልክዓምድሮችን ብሎም የሳር ዝርያዎችን ለመትከል የሚያስችል ማሽን እንዲያስገቡ ፈቅዶላቸዋል። ‹‹ግሪን ላንድ ስኬፕ ጋርደን›› በሚል ስያሜ በሰፊው ወደ ሥራ ገብተዋል። በርካታ የዓለማችን ክፍል በዚህ ዘርፍ ተራቆ ተመንድጎ ለውጥ እያገኘ ሲሆን ኢትዮጵያ አንቀላፍታለች፤ ብዙ ሥራም ይቀራታል ሲሉም የዘርፉን መጓተት ይተቻሉ።
ተከሳሽ ሲሸለም
እኚህ ሰው ለዕፅዋት ያለው ፍቅር ከፍ ያለ ነው። ከእለታት በአንድ ቀን እፅዋት ውሃ እያጠጡ ሳለ የወታደራዊ ዩኒፎርማቸውን ከውስጥ ለብሰው፤ ከላይ ቱታ ደርበው ነበር። በአጋጣሚ ግን የወታደራዊ ማዕረጋቸውን ከቱታ ልብሳቸው ላይ አኑረውት ነበር። ታዲያ ይህንን ነገር የተመለከተ አንድ የሥራ ባልደረባቸው ከሰሳቸው። እንዴት ተደርጎ የወታደራዊ ማዕረጉን ከቆሻሻ ቱታ ለይ ያስቀምጠዋል፤ የውትድርና ክብርን ዝቅ አድርጓል ብሎ ከሰሳቸው። በዚህን ጊዜ አለቃቸው በነበሩት ጀነራል ዑመር ፊት ለፊት ቀረቡ። ለዚህ ፍርድ ጥልቅ ማሰብ ግድ ነበርና ጀነራል ዑመር እንዲህ አሉ።
በእውነቱ ለወታደራዊ ማዕረግ እና ፕሮቶኮል መጨነቅህ አግባብ ነው ሲሉት ከሳሹ በሃሳብ ደገፉትና መቶ አለቃ ባዩህን ገሰፁ። ወዲህ ደግሞ ለሥራ ያላቸውን ተነሳሽነት ተመልክተው መቶ አለቃ ባዩህን አደነቁ። ታዲያ ከሳሹን ሰው ጠርተውት እስኪ ነገሩን እንተወው ‹‹እንዲያው እኮ እኚህ ሰው ከወታደር አርሶ አደር ቢሆኑ ይሻል ነበር›› ብለው ነገሩን አለዝበው ከሳሽንም ተከሳሽንም አስደስተው ወደየቤታቸው መለሷቸው። መቶ አለቃም ደስ ብሏቸው ወደ ሥራ ተመለሱ። በ1974 ዓ.ም ግን ኮኮብ ሠራተኛ ሆነው ተሸለሙ። እናም ተከሳሽ ሲሸለም፤ ከሳሽ ደግሞ መቶ አለቃ ባዩህ ሽልማቱን ሲቀበሉ ቆሞ ተመለከተ። ታዲያ በዚህን ጊዜ ጀነራል ዑመር የሆነውን አስታወሰው መቶ አለቃ ባዩህ ያኔ የሆነውን አስታወስክ ጥረትህ በረከት ይዞ መጣ ብለው ጥረታቸውን አድንቀው በወታደራዊ ፈገግታ እንዳጫወታቸው ትዝ ይላቸዋል።
በአንድ ብር መባ 10 ሺ ብር
ይህን ታሪክ ዛሬ ሲያወሩት በዝምታና በመገረም ብሎም በልባዊ ምስጋና ስሜት ውስጥ ነው። በአንድ ወቅት መቶ አለቃ ባዩህ ወደቤተክርስቲያን ሲሄዱ ከልጃቸው ጋር ነበር። በኪሳቸው ሁለት ብር ነበራቸው። አንዱን ብር መባ ሰጥተው ፀሎታቸውን ይጀምራሉ። ለርጃቸው ግን እኔም፣ መባ ካልሰጠሁ ብሎ ያስቸግራቸዋል። ኪሳቸው የቀረችው አንድ ብር በግድ ይሰጡና ሙዳየ ምፅዋት ላይ አኖረ። ይሄ በአጠገባቸው የነበሩ ሰዎች ግን በልጁ አድራጎትና ቅንነት ተገረሙ።
ከኪሳቸው ያለችው ሁለት ብር መጨረሳቸው ግን ለመቶ አለቃ ሌላ ፍርሃት ደቅኗል። ከቤተ እምነቱ ወደ ቤት ሲያመሩ ልጃቸው እንደሌሎች ልጆች ከረሜላ አሊያም ደግሞ ብስኩት አምሮኛልና ይገዛልኝ ቢላቸው እንዴት ዝም እንደሚያስብሉት አያውቁም። በቁጣ አሊያም በቁንጥጫ አደብ ማስገዛት አይፈልጉም፤ የሚኖሩት ለልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ነውና።
የሚገርመው ግን ያሰቡት አልሆነም በሠላም ወደሰፈራቸው ተመለሱ። ከበራቸው ላይ ሲደርሱ ግን አንድ ነገር ማመን አልቻሉም። ከበራፋቸው ላይ ሦስት የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ተሽከርካሪዎች ቆመው ችግኝ እንደ ጉድ እየጫኑ ነው፤ አላመኑም። ለመጀመሪያ ጊዜ 10ሺ ብር እጃቸው ላይ ቆጠሩ። በአንድ ብር መባ 10ሺ ብር በረከት ይዞ መጣ ሲሉም ለፈጣሪያቸው ምስጋና አቀረቡ፤ ለአንተ የማይቻል አንዳች ነገር የለም እያሉ።
ምን ሠርተዋል?
በአገሪቱ በርካታ አካባቢዎች ያልሰራነው ሥራ የለም ሲሉ የድጅታቸውን ጥረት ይናገራሉ። የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ፣ የህንድ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጃፓን፣ ስውዲን፣ ስውዘርላንድ ኤምባሲዎችን አሳምረዋል። ሃያት ሬጀንሲ ሆቴል፣ የኢትዮጵያ መርከብ ኃይል፣ በቢሾፍቱ የሚገኘውን ሮዝመሪ ሆቴል፣ ባቦጋያና በርካታ ሆቴሎችና ሪዞርቶችን አስውበዋል። ከቱሉ ዲምቱ አዳማ ድረስ በሚዘልቀው የተሽከርካሪ መስመር በመንገድ ግራ ቀኝ እንዲሁም አካፋይ ያሉትን እጽዋትና ሣር ተክለዋል። በወቅቱም 276 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ያስታውሳሉ። ከዚህም በተጨማሪ የበርካታ ስመጥር ግለሰቦችን ቤት አሳምረዋል፤ በማሳመር ላይም ይገኛሉ። ለበርካታ ወጣቶችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
2000 የእጽዋት ዝርያ በግቢ
መቶ አለቃ ባዩህ በግቢያቸው ውስጥ 2000 እጽዋትን ሰብስበው ይዘዋል። እያንዳንዳቸውን ስያሜና ጥቅም እናት ፍትፍት አድርጋ ልጇን እንደምታጎርስ ሁሉ እርሳቸውም የእፅዋቱን ጥቅም፣ ባህሪ፣ መገኛ ሥፍራና ሌሎችንም በሚገባ ፈትፍተው ያጎርሳሉ። እንግዲህ የሰው ዘር እንደ አሳ ሲበዛ በዚያው ልክ የበዛውን እጽዋትም በዚህ ስፍራ አከማችተው ለእውቀትም፤ ለገንዘብም ለሳይንስም እየተጠቀሙበት ነው።
አምስት ሄክታር ደን ወደ ማልማት
መቶ አለቃ ባዩህ በሥራው ብዙም የረኩ አይመስልም። ታዲያ መንግስት ያግዘን ሳይሆን መንግስትን ላግዘው ሲሉም ጥያቄ አቀረቡ። አምስት ሄክታር መሬት ጠይቀው ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ መግቢያ ያለው ገልማ አባገዳ በስተቀኝ አሻግሮ ካለው ተራራ ላይ መሬት ወስደው ወደ ደን ለመቀየር እየተጉ፤ ሌሎችም ወደዚህ ሥፍራ ሄደው እንዲተክሉ እያበረታቱ፤ የተከሉትም የሚንከባከቡበትን መርሐ ግብር ቀርፀው ሥራ ለይ አውለዋል። በ2011 ዓ.ም የክረምት ወቅት ብቻ 30ሺ የተለያዩ ችግኞችን ተክለዋል። በጥቂት ዓመታት ውስጥም ሥፍራውም የዕይታና ስበት፣ የንጹህ አየር አካባቢና የጎብኚዎች ብሎም የታታሪዎች ተምሳሌትና ማስታወሻ ለማድረግ ወስነው ሥራ ጀምረዋል፤ ውጥናቸው ሙሉ ለሙሉ እውን እንደሚሆንም ተስፋ ያደርጋሉ። ለ40 ዓመታት አብሯቸው የዘለቀው የዕጽዋት መንከባከብና ማስዋብ ሥራቸው ገቢያቸውም፤ ዝናቸውም ሆኖ ቀጥሏል። በቀጣይም ይህንኑ አጠናክረው መቀጠል ይፈልጋሉ። አብሯቸውም የሚሰራ አካል ካለም አርሂቡ ብለው ለመቀበል ዝግጁ ናቸው፤ መቶ አለቃ ባዩህ።
መቶ አለቃ ባዩህ ያደሳ፤
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 10/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር