የስኳር በሽታ- ክፍል ሁለት
ማንኛውም ሰው ህመሙን ለመታከም የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ በሽታውን ማወቅ ነው። ባለፈው ጊዜ እንዳነሳነው በርካታ ሰዎች ከሰውነታቸው ውስጥ የስኳር በሽታ እያለባቸው በሽታው ያለባቸው መሆኑን ስለማያውቁ ብቻ ህክምና እያገኙ አይደሉም። ስለዚህ ተመርምረው ይህ በሽታ ያለባቸው/ የሌለባቸው መሆኑን ማወቁ በጣም አስፈላጊ ነው። ለዚህ ስኳር በሽታ መመርመር ያለባቸው ሰዎች ሲባል እድሜ እና የስኳር በሽታ ምልክቶችን መኖር ወይም አለመኖርን መሰረት የሚያደርግ ነው። በአጠቃላይ የሚከተሉት ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የበሽታው ምልክት የሌለባቸው ቢሆንም እንኳ ስኳር በሽታ መመርመር አለባቸው፡-
- ክብደታቸው የጨመረ ወይም ክብደታቸው ሲካፈል ለ(ቁመታቸው)2 (BMI) ከ25 ኪ/ግ / ሜ2 በላይ የሆነ እና ከዚህ በታች ከሚገኙት ውስጥ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ሁኔታዎች ሲኖርባቸው። ለምሳሌ ክብደቱ 85 ኪ/ግ እና ቁመቱ 1 ሜትር ከ 60 ሴ.ሜ የሆነ ሰው, BMI ስንስራለት 85 ÷ (1.6) 2= 33.2 ኪ/ግ / ሜ2 ይሆናል። ትክክል (ኖርማል) የምንለው 18.5 እስከ 25 ኪ/ግ ስሆን ነው።
- በስራቸውም ሆነ በሌላ ምክንያት የአካል እንቅስቃሴ የማያደርጉ
- የቅርብ ዘመዳቸው (እንደ እናት፣ አባት፣ ወንድማማቾች/እህትማማቾች እና የመሳሰሉት) የስኳር በሽታ አይነት ሁለት (Type II Diabetes Mellitus) ያለባቸው እንደሆነ
- የታወቀ የልብ እና የደም ስር ስርዓት ህመም ያለበት ወይም ያለባት ከሆነ
- የደም ግፊት ህመም እንዲሁም የልብ ወይም ኮሌስትሮል (Hyperchoesterolemia) ያለበት።
- እድሜያቸው 45 ዓመት የደረሱ ሰዎች ሁሉ መመርመር አለባቸው፤ ነጻ ከሆኑም በየሶስት ዓመቱ ተመልሰው መታየት አለባቸው።
- ነፍሰጡር የሆነች ሴት ነፍሰ ጡር በሆነችበት ጊዜ ተይዛ የነበረችው ከሆነ ቢያንስ በየሶስት ዓመቱ መመርመር አለባት።
- ከዚህ በፊት ተመርምረው ለስኳር በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑ ተነግሯቸው ከሆነ ቢያንስ በየዓመቱ መመርመር አለባቸው።
በስኳር በሽታ ህክምና ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ማነው?
የስኳር በሽታ ህክምና እንደ አንዳንድ በሽታዎች የጤና ባለሙያዎች ብቻ ድርሻቸውን እንዲወጡ የሚተውላቸው ሳይሆን ከፍተኛው ድርሻ የስኳር ህመምተኞች ነው። ይህም ከሐኪም ቤት ከተሰጡት መድሃኒቶች በተጨማሪ የኑሮ ሁኔታ እና ልዩ ልዩ ነገሮችን ማስተካከል ስለሚያስፈልግ እንደዚሁም ለዚህ በሽታ የሚሰጡ መድሃኒቶች ብዙውን ጊዜ ታካሚዎቹ በራሳቸው የሚወስዱ (የሚወጉ) በመሆኑ ነው። በአጠቃላይ የስኳር ህመም ህክምና የማይቋረጥ፣ የእድሜ ልክ ህክምና ነው። ይሁን እንጂ በባለፈው ጊዜ ያየናቸው የሁለቱ የስኳር በሽታ ህክምና ዘዴ የተለያየ ነው።
ስኳር በሽታ አንድ የሕክምና ዓይነት(Type I Diabetes Mellitus)
የስኳር በሽታ አንድ የሕክምና ዓይነት ከዚህ በፊት እንደገለጽነው በሰውነታቸው ውስጥ ኢንሱሊን ስለሌለ የኢንሱሊን ሆርሞን በመርፌ መልክ መስጠት ግዴታ ነው። የሚሰጠው ኢንሱሊን መጠን ወይም ክብደት እንደበሽታው አስፈላጊነት ከፍ እና ዝቅ ማለት ይችላል። ይህንን የጤና ባለሙያ አይቶ የመድሃኒት መጠን (Dose) የሚያስተካክል በመሆኑ እዚህ ላይ አናነሳም። ኢንሱሊን የሚወስድ ሰው/ ታካሚ/ በትክክል ካልተወጋ ኢንሱሊኑ በትክክል መስራት አይችልም።
ኢንሱሊን ማስቀመጥ ያለብን እንዴት ነው? መጀመሪያ ኢንሱሊኑ ለበሽተኛው እንደተሰጠ ወዲያው የተመረተበት ጊዜ ያለፈበት አለመሆኑን ለይተን ማየት አለብን። ኢንሱሊን ከፍተኛ ሙቀትም ሆነ ቀዝቃዛ እንዲሁም የፀሐይ ብርሃን ቀጥታ ቢወጣበት የመስራት ችሎታው ይደክማል። ስለዚህ ስናቀዘቅዘው (Fridge) ከቤት ያለን እንደሆነ ትንሽ የሚያቀዘቅዝ ቦታ ውስጥ እንጂ ፍፁም በረዶ የሚያደርግ (ከላይ በረዶ የሚፈጥር ቦታ) ማስቀመጥ የለብንም። መኪና ውስጥ እና በመሳሰሉት ሞቃታማ ቦታ ማስቀመጥም የመድሃኒቱን ፈዋሽነት ይጎደዋል። በመጨረሻም ልንወጋ ስንል በስሪንጅ ከመቅዳታችን ቀለሙ ያልተለወጠ መሆኑን መለየት አለብን፤ የምንወጋበትን መርፌ (Syringe) ንፁህ ቦታ ማስቀመጥ፣ ጫፉ ከቆዳችን በስተቀር ከማንኛውም ሌላ ነገር ጋር እንዳይነካካ መጠበቅ (መክደን)፣ ከሌሎች ታማሚዎች ጋር በፍፁም አለመጠቀም (መርፈውን አለመጋራት) ግዴታ ነው።
ኢንሱሊንን እንዴት መወጋት አለብን? መጀመሪያ የተነገረን የኢንሱሊን መጠን (Dose) ከእቃው ውስጥ መቅዳት ነው፤ ከዚያም የመርፌው ጫፍ ወደ ሰማይ በማዞር አንድ ወይም ሁለት ጊዜ በእጅ ጣት መምታት ነው። ይህም የምንወጋባቸውም የሰውነት ክፍሎች ከውስጡ (Arm)፣ የእግር ታፋ (Thigh)፣ መቀመጫ (Buttock) እና ሆድ ላይ (ከእምብርት ትንሽ ራቅ ተደርጎ) ነው። ስንወጋ የመርፌውን አቅጣጫ በቆዳው ላይ 45 ዲግሪ (450C) ወደ ጎን አስተኝቶ መሆን አለበት። ይህም ኢንሱሊን በቆዳ ስር እንጂ ጡንቻ ውስጥ መፍሰስ ስለሌለበት ነው።
የሁለተኛ ስኳር በሽታ አይነት ሕክምና (Type II Diabetes Mellitus)
የሁለተኛ ስኳር በሽታ አይነት ህክምና ከላይ እንደገለጽነው ብዙውን ጊዜ የሚዋጡ መድሃኒቶች (Oral hypoglycemic agent) ከሆኑ የሚሰጠው መድሃኒት መጠን (Dose) ያለውን ሁኔታ መሰረት በማድረግ የሚያክመው ባለሙያ እና ህመምተኞቹ (ታካሚዎቹ) ተወያይተው የሚወስኑት ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በመድሃኒት መቆጣጠር ሳይቻል ሲቀር ኢንሱሊን ወደ መወጋት ይኬዳል። ይህም ኢንሱሊን ከላይ በተገለፀው ሁኔታ ይወሰዳል።
የስኳር በሽታ ህመምተኞች (Diabetes Mellitus) ማድረግ የሚገባቸው ጥንቃቄ
የስኳር ህመምተኞች ለሚወስዱት መድሃኒት ላይ በተጨማሪ በኑሮዋቸው ሁኔታ ላይ አንዳንድ ጥንቃቄዎች እና ለውጦችን ማድረግ አለባቸው፤ ከእነዚህም፡-
- ጥፍር በሚቆረጡበት ጊዜ በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዳይቆርጣቸው ጥፍሩን ወደ ታች አስቀርተው መቁረጥ፣ ይህም ቢቆስል በቀላሉ ስለማይድን ነው፣
- ጫማ ካደረጉ ሰፊ ወይም ቀደም ሲል ያደርጉ በነበሩት የጫማ ቁጥር ላይ አንድ ቁጥር በመጨመር ማድረግ፣
- በሚጓዙበት ጊዜ ባዶ እግር እና እግርን የሚያሳዩ ጫማዎች ከማድረግ መጠንቀቅ፣
- እግር በሚታጠቡበት ጊዜ በቀዝቃዛ ውሃ መታጠብ፣
- በእግራቸው ላይ ቁስል ያለ ወይም የሌለ መሆኑን በየጊዜው ማየት አለባቸው፣
- በልዩ ልዩ ምክንያቶች በእግር ላይ ቁስል ከወጣ እንደ ሌሎቹ በራሱ ለመዳን ረጅም ጊዜ ስለሚወስድ ሀኪም ቤት መሄድ አለባቸው፣
- በውስጣቸው ስኳር ካላቸው እንደ ሻይ፣ ጣፋጭ የለስላሳ መጠጥ እና የመሳሰሉት መቆጠብ አለባቸው፣
- ጮማ እና ቅቤ ከበዛበት ምግብ መቆጠብ፣ ይህም ምግቡ ራሱ እንደ ልብ እና የደም ስሮች ባሉት የሰውነታችን አካል ላይ ችግር ስለሚያመጣ ይህ በሽታ ባለባቸው ሰዎች ላይ ደግሞ ስለሚበረታባቸው ነው፤
- በልዩ ልዩ ምክንያቶች (በተለይም መድሃኒት ወስደው ምግብ ሳይበሉ መቅረት) በሰውነት ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ዝቅ ካለ የማስላብ፣ የድካም፣ እየሮጠ እንዳለ ሰው የልብ ምት መጨመር እና ራስን የመሳት ምልክቶች ካያችሁ በፍጥነት ስኳር ያለበትን ነገር (እንደ ከረሜላ እና ለስላሳ) በትንሹ መውሰድ ነው። ምልክቱ እንደተስተካከለ ማቆም አለብን። በተደጋጋሚ ይህ ምልክት ቢመጣ ምናልባት እየወሰዱ ያሉት መድሃኒት መጠን (Dose)ከፍ ሊል ስለሚችል ሀኪም ቤት ሄደን ማስተካከል አለብን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 10/2012