በውትድርና ያገኙት እውቀት ነገሮችን በብዙ መልኩ እንዲገነዘቡ እንደረዳቸው ይናገራሉ። ታታሪ ብቻ ሳይሆኑ ብልህ የሥራ ሰው መሆናቸውንም በርካቶች ይመሰክራሉ። በስምጥ ሸለቆዋ የሐይቆች መናሃሪያ ቢሾፍቱ ከተማ ከአየር ኃይል ቴክኒሻንነት እስከ ዘርፈ ብዙ ፋብሪካዎች ሥራ አስኪያጅነት የዘለቀ የስራ ዘመንን አሳልፈዋል። ደርባባ ገጽታቸው በርካታ የሕይወት ውጣ ውረዶችን ስለማለፉ ያሳብቅባቸዋል።
አንዱን አንጓ የሕይወት መስመራቸውን ሲመዙት በርካታ ጥራዝ ጽሁፎችን ሊወጣው እንደሚችል የሚያውቋቸው ይናገራሉ። እኛ ግን ቦታ ይገድበናልና ሰፊው የስራ ታሪካቸውን አጠር ባለ መልኩ ልናቀርበው ተገደናል። የዛሬው የሲራራ እንግዳችን ሻለቃ አለማየሁ አምደማርያም ይባላሉ። ውልደትና እድገታቸው ከአዲስ አበባ በቅርበት በምትገኘው አዲስ ዓለም ከተማ ነው።
በአዲስ ዓለም እስከ ስምንት ዓመታቸው ሲቆዩ አባታቸው ካህን እንዲሆኑላቸው በጽኑ ይፈልጉ ነበርና የቄስ ትምህርት ልክዋቸው ነበር። ወንድሞቻቸውና ቤተዘመድ ደግሞ ዘመናዊ አስኳላ ገብተው እንዲገፉበት ስለሚፈልጉ በቅስናው ትምህርት አይስማሙም። በመሆኑም አዲስ አበባ የሚገኙት ታላቅ ወንድማቸው ዘንድ ዘመናዊ ትምህርት እንዲቀስሙ በሚል እንዲመጡ ከተደረገ በኋላ ማረፊያቸውን በኮልፌ አካባቢ አደረጉ። ወንድማቸው የእህል ነጋዴ ቢሆኑም እርሳቸው ግን ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ተነግሯቸው ዘመናዊውን አስኳላ መኮምኮም ጀመሩ።
ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታተሉ። በወቅቱ ከክፍል አንደኛ የሚወጡ ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩ ያስታውሳሉ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አዲስ አበባ መድኃኒያለም ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በወቅቱ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያን በጥሩ ውጤት በማለፋቸው በ1966 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። ወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳቱ ወደዩኒቨርሲቲም ይደርስ ነበርና በየጊዜው ፖሊሶች የዩኒቨርሲቲውን ቅጥር እያለፉ ጥያቄ የሚያነሱ ተማሪዎችን ስለሚደበድቡ ሻለቃ አለማየሁ በሁኔታው ተማረዋል።
የሁለተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያሉ እርሳቸውም እጃቸው ላይ ከባድ ጡጫ ቀምሰዋልና በወከባውና ድብደባው በመናደዳቸው ትምህርት ለማቋረጥ ፎርም ለመሙላት ጉዞ እያደረጉ ሳለ በመንገድ አንድ ማስታወቂያ ያያሉ። ማስታወቂያው ደግሞ ‹‹እንኳን ወደ አየር ኃይል በደህና መጣችሁ!›› የሚል አዳዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ያለመ ጥሪ ነበር። እናም ወጣቱ ሁሉ ተሰልፎ ሲመዘገብ እርሳቸውም ጥሩ ክፍያና ስራ አለው በመባላቸው ተሰልፈው ተመዘገቡ።
አየር ኃይል ከተመዘገቡት 3000 ሰዎች መካከል በትምህርታቸው መሰረት መዝኖ ሲመርጥም እርሳቸው አንዱ ሆነው ተመለመሉ። እናም በደብረዘይት አየር ኃይል ለሁለት ዓመታት እንዲሰለጥኑ ተደረገ።
ከደብረዘይት በኋላ ደግሞ ወደ ሩሲያ ለተጨማሪ ትምህርት ተላኩ። በሩሲያም ለስድስት ዓመታት ቆይተው የአየር ኃይል ኢንጂነርነት ቴክኒሻንነት ሙያን ቀስመው ተመለሱ። ከትምህርት መልስም ጥቂት እንደቆዩ ወደ ኤርትራ ተልከው የበረራ አገልግሎትና ጥበቃ ኦፊሰር ሆነው ሰርተዋል። ከዚያም ስኳድሮ ኮማንደር የተሰኘ ቦታን ይዘው ሙያቸውን አሻሽለዋል። ሥራ ሲገቡ የመጀመሪያ ደመወዛቸው 560 ብር እንደነበር አይዘነጉትም። በኤርትራ ተመድበው ስድስት ዓመታትን እንደሰሩ ወደ ደብረዘይት ቅያሬ ጠይቀው መኮንኖችን በማሰልጠን ሁለት ዓመት አገለገሉ።
ኢህአዴግ ወደስልጣን ሲመጣ ግን ያልነበረው ሆነ። ከአየር ኃይል ግቢ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ሲወጡ መንገድ ላይ በወታደሮች ተይዘው ቦንብ አለህ በሚል ሊገድሏችው ሲሉ እግዚአብሔርን ብለው በመማላቸው ‹‹ሶሻሊስት›› አይደሉም፤ እግዚአብሄርን ያውቃሉና አይገደሉ በሚል በተዓምር ሞትን አመለጡት። የደርግ ዘመን አየር ኃይሎችና ወታደሮች ከያሉበት ሲታፈሱ ግን እርሳቸውም ተይዘው ጦላይ እስር ቤት ወህኒ ወረዱ።
ለሰባት ወራት እንደታሰሩ ግን ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ሃሳብ ቀረበ። በወቅቱ ለምን የሰለጠነ የቀድሞው ሰራዊት ይበተናል የሚል ጥያቄ በማንሳታቸው ወደስራ እንዳይመለሱ ደባ ተሸርቦላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ያንን ሁሉ ችግር አልፈው ግን ቀድሞ ሙያቸውን የሚያውቁ ሰዎች በመገኘታቸው ድሬዳዋ አየር ኃይል አዛዥነት ሆነው አመሩ። በድሬዳዋም አየር ኃይል ግቢውን ዳግም ለማዋቀር የነበራቸውን ውጥን የበላዮቻቸው ስላልወደዱት ወደ ደብረዘይት ዳግም ተቀይረው በአየር ኃይል ዋና አዛዥ ስር ሆነው በፐርሶኔልነት እንዲመደቡ ጠየቁ።
ጥያቄያቸው ተፈቅዶ በደብረዘይት አየርኃይል ሁለት ወራት እንደቆዩ ግን ከተለያዩ የደርግ ዘመን ባልደረቦቻቸው ጋር ስማቸው በደብዳቤ የቀድሞ የአፈና አገዛዝ አካል ናቸው በሚል ከኤርትራ ሰዎች በመጣ ትዕዛዝ ከሚሰሩበት ቦታ በወታደር ታጅበው በግፍ ከሥራቸው ተሰናበቱ።
አሁን ስራ የለም። እርሳቸውን ጨምሮ ባለቤታቸው ልጆችና የእርሳቸውን እጅ የሚጠብቁ ቤተዘመዶች ያለገቢ ባዶ እጃቸውን ናቸው። በወቅቱ አገር ጥለው ለመጥፋት ቢያስቡም የቤተሰባቸው ጉዳይ ስላስጨነቃቸው አላደረጉትም። በመጨረሻ ግን የዶሮ እርባታ ሥራ ላይ ለመሰማራት ወስነው ጫጩቶችን ያፈላልጉ ጀመር።
ከቀድሞ የሥራ አጋር ጓደኛቸው መቶ አለቃ ለማ አስፋው ጋር በመሆን ጫጩት ይሸጣሉ ወደ ተባሉ ሚሲዮኖች ጋር አቀኑ። ኩሪፍቱ ሐይቅ የሚገኘው የሚሲዮኖች ግቢ በር ላይ ግን ጥበቃው አላስገባ በማለቱ ከሁለት ሰዓታት ቆይታ በኋላ ፈረንጆቹ ተገኙ።
አንድም ብር ያልነበራቸው ጓደኛማቾቹ ጫጩቶቹን በዱቤ ለመውሰድ ቢጠይቁ ግን አልተፈቀደላቸውም ነበር። ይልቁንም የተወሰነ ክፍያ ከፈጸሙ ቀሪው በዱቤ እንደሚሰጣቸው ቢነገራቸውም መነሻ ካፒታሉ ግን በእጃቸው አልነበረም። እናም ቃለሕይወት የተሰኘ ሌላ ሚሲዮን ዘንድ ሄደው ለዶሮ መግዣ የሚሆን ብድር ጠየቁ።
በወቅቱ ከብዙ ድካም በኋላ 1ሺ500 ብር ብድር ተፈቅዶላቸው አንድ ሦስተኛውን ሒሳብ ከፍለው ቀሪውን ዶሮዎችን አሳድገው ሊከፍሉ ተስማምተው በ1000 ብር እንዲወስዱ ተፈቀደላቸው። ሻለቃ አለማየሁም ከጓደኛቸው ጋር የዶሮ ቤቶችን እና መመገቢያዎችን በእጃው አዘጋጅተው ዶሮዎችን እያሳደጉ የቤተሰባቸውን ሕይወት ለመታደግ ቆርጠው ተነሱ። ጫጩቶቹ ከውጭ አገር ነበርና የሚመጡት ከአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት እንዲወስዱ ሲነገራቸው ሻለቃ አለማየሁ በሁለት ብር ተሳፍረው ከደብረዘይት ለገሃር አቀኑ። ከዚያም ከለገሃር እስከ አየር ማረፊያው ድረስ በእግር ሄዱ። አየር መንገድም በ12 ሰዓት ደረሱ።
በቦሌም ሦስት ሰዓት ገደማ ጠበቁ። ኋላም ጫጩቶቹ ደረሱ። ጫጩቶችን የያዘው መኪና ቀርቦ ሻለቃ አለማየሁ እንዲረከቡ ሲጠየቁ ግን የሚያጓጉዙበት አንድ አማራጭ ያልነበራቸው የአየር ኃይሉ ሰው በመኪናው እንዲወስዱላቸው ጠየቁ። በነገሩ ያልተስማሙት ጫጩት አቅራቢ ፈረንጆች ሲበሳጩ ግን አንድ ደብረዘይት ላይ ዶሮ የሚያረባ ሰው በአጋጣሚ ጫጩቶችን እርሱም ይረከብ ነበርና ‹‹እኔ እወስድሎታለው አብሬ ብሎ›› ነገሩን አቀለለው።
ጫጩቶቹ ተጭነው ጉዞ ሲጀመር መሽቶ ነበርና ደብረዘይት ከሌሊቱ 8 ሰዓት ደረሱ። በወቅቱ መኪናዋ የጭቃ አረንቋ ውስጥ በመግባቷ ከብዙ ልፋት በኋላ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ገደማ በመኖሪያ ቤታቸው ደርሰው ጫጩቶቹን አሳረፉ። ሻለቃ አለማየሁና ጓደኛቸው እጃቸው ላይ ከብድር የተረፈችውን 500 ብር ይዘው አምስት ኩንታል የዶሮ መኖ ገዝተው እየመገቡ ስራቸውን ጀመሩ። በአምስተኛው ቀን ግን መኖውም አለቀ። ሌላ ብድር ወደ ሚሲዮኖቹ ቤት ጎራ ብለው ስራቸው ከታየ በኋላ 3ሺ500 ብር ተፈቀደላቸው።
በብድሩ ተጨማሪ መኖ ገዝተው እየመገቡ፤ ዝናብ በሚያንጠባጥበው አሮጌ ላስቲክ ሌሊትና ቀን እየተቀያየሩ እየወጠሩ ችግርን በጥንካሬ አሳለፉ። 13 ሜትር የውሃ ጉድጓድ ቆፍረው ጫጩቶቹን እየመገቡ ካቆዩ በኋላ ጥሩ ውጤት በመገኘቱ ጫጩቶቹን ያደረሰላቸው አርቢ እነርሱንም ሊገዛቸው ጎራ አለ።
በደስታ የተቀበሉት ሻለቃ አለማየሁ በዶሮዎቹ መኖ ፍጆታ ተማረው ነበርና ገቢ ለማግኘት እያንዳንዱን ዶሮዎችን በ18 ብር ሸጠው 18ሺ ብር ገቢ አደረጉ።
ጓደኛማቾቹ ብድራቸውን ከፋፍለው የቤተሰባቸውንም ወጪ የሚሸፍኑበት ገንዘብ አግኝተዋል። በተቀረው ገቢ ደግሞ ተጨማሪ ጫጩቶችን ገዝተው ማርባቱን ተያያዙት። እንዲህ እንዲህ እያለ ከዶሮ ሽያጩም ከእንቁላል ገቢውም እያጠረቃቀሙ መንገዱን ስራዬ ብለው ያዙት። ከቀን ቀን ምርታቸው እያደገ ለአያሌዎች ይዳረስ ቀጥሏል። ከሺዎች ወደ መቶ ሺዎች እያሉ ወደ ሚሊዮን ደረጃ በመድረሳቸው ስራቸውንም ማስፋፋቱን አላቋረጡም። ገቢውም ወደ ሚሊዮኖች ደረሰ።
ከሁለት ዓመታት በኋላ አንድ ሰራተኛ ቀጥረው ማሰራት ጀምረው፤እያሉም 20 እና 30 ሰራተኛ አደረሱት። በወቅቱ ሻለቃ አለማየሁ ሆላንድ ሀገር ሄደው ስራውን የሚያስተዋውቁበት እድል አገኙ። አብሯቸው የሚሰራ ካለ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው ማስታወቂያ በትነውም ተመለሱ። በተመለሱ ስድስት ወራት ደግሞ ከሆላንድ አጋር በማግኘታቸው የኔዘርላንድ መንግስት በመደበው 500ሺ ዩሮ አማካኝነት ከጓደኛቸው ጋር 70 በመቶ ድርሻ ይዘው ፈረንጆቹ ደግሞ በ30 በመቶ ድርሻ ዘመናዊ የዶሮ መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በደብረዘይት አስመርቀው ከፈቱ።
የመኖ ማቀነባበሪያው አሁን ላይ በቀን እስከ 4000 ሺ ኩንታል ምርት ያቀነባብራል። ከመኖ ምርት በተጨማሪ እንስሳት በማርባትና የዶሮ ውጤቶችን ለተጠቃሚ በማቅረብ ስራቸውን በመላ አገሪቷ ማከፋፈሉን ቀጠሉበት። ጓደኛማቾቹም በትርፍ ላይ ትርፍ እየደራረቡ የዶሮ ቄራና የእንስሳት ማርቢያ እንዲሁም ሆቴል ከፍተው ትልቅ ሃብት ፈጥረዋል። በዶሮ ጫጩት ምርት በዓመት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ጫጩቶችን ለገበያ በማቅረብ በቀን 4000 ዶሮዎችን አርደው ለሆቴሎችና ለተለያዩ አካላት ያቀርባሉ።
ሱፐርማርኬት፣ የስጋ ማቀነባበሪያ፣ አግሮ ኬሚካል ምርትና ዘርፈ ብዙ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ላይ የተሰማራው የጓደኛማቾቹ ድርጅት ‹‹አለማ ፋርምስ›› የተሰኘው ድርጅት አሁን ላይ 880 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ሽያጭ አለው። ድርጅቱ በስሩ 900 ሰራተኞችን ይዟል።
በብድር የተጀመረው የእርባታ ስራ አሁን ላይ ለአገር የሚተርፍ ሃብትን እያመነጨ ይገኛል። ሻለቃ አለማየሁ በዚህ ደስተኛ ናቸው። ከዚህም በላይ ለመስራት እና ለመነገድ ይቻላል የሚል ዓላማ ሰንቀው በየጊዜው ማስፋፊያዎችን የማካሄድ ውጥን አላቸው።
ማንኛውም ሰው ዓላማ ይዞ በጥራት ከሠራ ውጤታማ የማይሆንበት መንገድ እንደሌለ ይናገራሉ። መጀመሪያ ገንዘብ ሳይሆን ወኔ ይቀድማል የሚል እምነት አላቸው። በወኔ ከተሰራ ደግሞ ገንዘብ ይገኛል። በመሆኑም በተለይ ወጣቱ በእቅድ በተመራ አካሄድ በዶሮና እንስሳት ልማት ላይ ቢሰማራ ትርፋማ መሆን ይችላልና ዛሬን በሥራ ስለማሳለፍ ሊያስብ ይገባል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 10/2012
ጌትነት ተስፋማርያም