ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጋር ወግና ለመዋጋት ወታደሮቿን መላኳ ተጠቆመ

ሰሜን ኮሪያ በዩክሬን ከሩሲያ ጋር ወግና ለመፋለም ወታደሮቿን መላክ መጀመሯን የደቡብ ኮሪያ የስለላ ድርጅት አስታወቀ። ይህንን የሰሜን ኮሪያ ርምጃ “ከፍተኛ የደህንነት ስጋት” ስትል ደቡብ ኮሪያ ፈርጃዋለች። ይህ የተሰማው የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ 10 ሺህ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ጦርነቱን ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ የደህንነት መረጃዎች ተገኝቷል ካሉ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ ዮል አርብ፣ ጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም በጠሩት የጸጥታ ስብሰባ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “በሁሉም መንገዶች” ምላሽ መስጠት አለበት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። እንደ የስለላ ድርጅቱ ከሆነ እስካሁን አንድ ሺህ 500 የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ወደ ሩሲያ ገብተዋል። አጠቃላይ ለሩሲያ ወግነው የሚዋጉ ወታደሮች ቁጥር ወደ 12 ሺህ ሊጠጋ እንደሚችል የደቡብ ኮሪያ ሚዲያዎች ስማቸው ያልተጠቀሱ ምንጮችን ዋቢ አድርገው ዘግበዋል።

በዩክሬን ፖልታቫ ግዛት ውስጥ ከሚሳኤል ቁርጥራጭ በተገኘ መረጃ ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ የጦር መሣሪያ ታቀርባለች የሚሉ ማስረጃዎች እየጨመሩ መጥተዋል። ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ በቅርብ ወራት ውስጥ ትብብራቸውን እያሳደጉ መጥተዋል። ለዚህም ማሳያዎች አንዱ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ልደት ዕለት ደውለውላቸው “የቅርብ ጓዴ” ሲሉ መጥራታቸው ተዘግቧል።

የደቡብ ኮሪያ የብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ክስ የመጣው የዩክሬን ወታደራዊ መረጃ ምንጮች የሩሲያ መከላከያ የሰሜን ኮሪያ ጦር ክፍል እየመሠረተ መሆኑን ከገለጹ ከቀናት በኋላ ነው። የዩክሬን የስለላ ድርጅት ኃላፊ ኪሪሎ ቡዳኖቭ በዩክሬን ለመዋጋት ወደ 11 ሺህ የሚጠጉ የሰሜን ኮሪያ እግረኛ ወታደሮች በምስራቅ ሩሲያ እየሠለጠኑ እንዳሉ በዚህ ሳምንት ተናግረዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You