ትራምፕ ለሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ፕሬዚዳንት ዘለንስኪን ተጠያቂ አደረጉ

ትራምፕ ለሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ፕሬዚዳንት ዘለንስኪን ተጠያቂ አደረጉ። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እና የ2024ቱ ምርጫ የሪፐብሊካን እጩ ዶናልድ ትራምፕ ለሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መጀመር ፕሬዚዳንት ቮለደሚር ዘለንስኪ ተጠያቂ እንደሆኑ ተናገሩ፡፡

በምርጫ ቅስቀሳ መድረኮች እና ቃለ መጠይቆች ፕሬዚዳንቱ ላይ ተደጋጋሚ ትችቶችን የሚሰነዝሩት ትራምፕ “የምድራችን ትልቁ የሽያጭ ሠራተኛ” ሲሉ ዘለንስኪን ወርፈው ነበር፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ይህን ያሉት ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ አሜሪካ እና ምዕራባውያንን በማሳመን ዘለንስኪ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ድጋፍ ማግኘታቸውን ባነሱበት ንግግር ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በዘለንስኪ ላይ ከተሰነዘሩት ትችቶች ጠንካራ እንደሆነ በተወራለት ንግግር “ምንም እንኳን ጦርነቱ ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ ቢጀመርም ዘለንስኪ ጦርነቱን ማስቆም ባለመቻሉ ብቻ ሳይሆን እንዲጀመር በመርዳት ተጠያቂ ነው” ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ትራምፕ የዩክሬኑን መሪ ከሞስኮ ጋር ሰላም መፈለግ ባለመቻላቸው ወቅሰው፤ ዩክሬን የሰላም ስምምነት ለማድረግ የተወሰነ መሬቷን ለሩሲያ አሳልፋ ልትሰጥ እንደምትችል ጠቁመዋል፡፡ ይህም የትራምፕ ንግግር በህዳር አምስቱ ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ፖሊሲያቸው ወደ ሩሲያ ሊያደላ እንደሚችል ማሳያ ነው ሲል ዘግቧል፡፡

የዘንድሮው ምርጫ ዴሞክራቶችን ከነጩ ቤት አስወጥቶ ሪፐብሊካንን የሚያስገባ ከሆነ ለዩክሬን የሚደረገው ድጋፍ በእጅጉ ሊቀንስ እንደሚችል ተነግሯል፡፡ ይህን ሃሳብ ተቀናቃኛቸው የዴሞክራት እጩ ካማላ ሃሪስም በተደጋጋሚ ሲያንጸባርቁት ከዚህ ቀደም ተስተውለዋል፡፡

“ትራምፕ አምባገነኖችን ለማወገዝ የሚግደረደር ከፑቲንም ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያለው ነው” ያሉት ሃሪስ፤ የፕሬዚዳንትነት ቦታውን የሚይዝ ከሆነ ዩክሬን ብቻዋን ልትቆም ትችላለች ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ሆኖም የሪፐብሊካኑ እጩ “ይህ ማለት በምርጫው ካሸነፍኩ ዘለንስኪን መደገፍ አቆማለሁ ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም የሀገሪቱ ዜጎች ያሳዝኑኛል ነገር መጀመርያም ቢሆን ከሩሲያ ጋር ጦርነት እንዳይጀመር ማስቆም ነበረበት” ነው ያሉት፡፡

ባሳለፍነው መስከረም ወር ዘለንስኪ “የድል እቅድ” ያሉትን በሩስያ ላይ ተጨማሪ ጫናዎች እንዲደረጉ እና ለዩክሬን የሚደረጉ የጦር መሳሪያ ድጋፎች የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን በብዛት እንዲያካትት የሚጠይቀውን እቅድ ለአሜሪካ መሪዎች ባቀረቡበት ወቅት ሁለቱንም ፕሬዚዳንታዊ እጩዎች “ጨዋዎች” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በምን አይነት መንገድ እንደሆነ ግልጽ ባያደርጉም ፕሬዚዳንት የሚሆኑ ከሆነ የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነትን በፍጥነት እንደሚያስቆሙ በተደጋጋሚ ሲናገሩ መሰማታቸውን አል ዐይን ዘግቧል፡፡

 

አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You